የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ጴጥሮስን አገኘሁት /ክፍል 18/

 

እባካችሁ አንብቡ

የከሰዓቱ ትምህርት እስኪጀመር የጠዋቱን መልእክት በጸሎትና በማሰላሰል ከራሴ ጋር ለማዋሐድ ወደ ቫቲካን ኮረብታ ወጣሁ ። ክርስቶስ በጎች ያለን በጎች የበሉትን እንደገና ስለሚያመነዥጉ ነው ። በኦሪትም የሚበሉ እንስሳት ሰኰናቸው ክፍት የሆኑና የሚያመሰኩ ናቸው ። ሰኰናው ክፍት የሆነ ሲረግጥ ይቆነጥጣል ። እርግጠኛነትንና ጽናትን የሚያመለከት ነው ። የሚያመሰኳም ያጣራል እንጂ እንዲሁ አያሳልፍም ። ይህም ያገኘውን ትምህርት የማያግበሰብስ ነው ። ሰዓቱን አይቼ ወደ ጳውሎስ ቤት ስመለስ ራቅ ራቅ ብለው የሚሄዱ ወታደሮችን አየሁ ። እነዚህ ወታደሮች የድሆችንና የምንዱባንን ዱካ እየተከታተሉ የጳውሎስን ደጃፍ እንዳገኙት ኋላ ላይ እርግጠኛ ሆንሁ ። ሐዋርያው ጳውሎስ ድንግልናዊ ሕይወትን የመረጠው ለስንፍና ፣ ለራስ ወዳድነት ፣ ኃላፊነትን ለመሸሽ ሳይሆን የብዙዎችን ትዳር ቀና አድርጎ ለመያዝና ብዙ ልጆችን በሥጋና በነፍስ ለማሳደግ ነው ። በኢየሩሌም ድሆች ምክንያት የተጀመረው የጳውሎስ ዓለም አቀፋዊ የድሆች መርጃ እውቅና አግኝቶ ነበር ። ሁሉም ሰው በጾም ወራት ከሆነ የቁርስና የምሳውን ወጪ በማጠራቀም ለፋሲካ ያመጣል ። አንድ ድሀ እቤቱ እንደ ተቀመጠ በማሰብም የእርሱን ወጪ በየቀኑ እያስቀመጠ በዕለተ ሰንበት ቤተ ክርስቲያን ይዞ ይሄዳል ። ድሆች በየዕለቱ እንጂ በበዓል ቀን ከተረፈን የምናስባቸው አይደሉም ። ነዌ በምድር ባለጠጋ ነበረ ስላልሰጠ ግን በሰማይ ድሀና ጠብታ ውኃ የሚለምን ሆነ ። አልዓዛር ግን ድሀ ሁኖ በምድር ቢኖርም በሰማይ በአብርሃም እቅፍ ውስጥ ነበረ ። በምድር ላይ የድሆችን ጩኸት ያልሰሙ በጭንቅ ስፍራም ቢጮኹ የሚሰማቸው የለም ። ችግረኛን መስማት በችግር ቀናችን እኛም እንድንሰማ ያደርገናል ። 

የመሥዋዕትነት ሣጥን የምትባል አንዲት ሙዳይ ነበረች ። በቀን አንድ ጊዜ የማይበሉትን ለማሰብ በቀን ሁለት ጊዜ መብላቴ በቂ ነው በማለት ሦስተኛውን ወጪ በዚያች ሳጥን ይጨምሩ ነበር ። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ድሆችን ገሸሽ የሚል ክርስቲያንን እንደ አረማዊ ይቆጥር ነበር ። መስጠት እግዚአብሔር ሰጥቶኛል የሚል ምስክርነት ነው ። መስጠት ተቀባዮቹ በእኛ ምክንያት እግዚአብሔር እንዲያመሰግኑ ያደርጋልና አምልኮትን ያስፋፋል ። መስጠት ያገኘና ያጣ ሰው የሚገናኙበት መሰላል ነው ። መስጠት ያልነበረንን ዘመን የምንክስበት ፣ ለነገው ምሥጢራዊ ቀን ብድር የምናቆይበት ነው ። መስጠት ምነው በሰጠሁ ኖሮ ብሎ ከመጸጸት የሚያድን ነው ። ገንዘብ ዘር ነው ፣ ዘር ካልዘሩት ይበሰብሳል ። ገንዘብም የእግዚአብሔርን በረከት የሚያመጣው በድሆች የተቆረሰ ልብና የተከፈተ ሆድ ላይ ስንዘራው ነው ። ወደ ሰማዩ ጎተራ የምንልከው በድሆች ሆድ ነው ። ዜማ ሰምቶ ፣ ዋሽንት ሰርስሮት የሚሰጥ እውነተኛ ሰጪ አይደለም ። መስጠት ስሜት ሳይሆን ዕለታዊ ተግባር መሆን አለበት ። መስጠት እውነተኛ ወዳጆችን ያበዛል ። በምድር ላይ ለእኩያ ብንሰጥ የሰጠነውን የሚመስል ይሰጠናል ። ለድሀ ብንሰጥ ግን ራሱን ይሰጠናል ። ሬሳን የሚሸከም ፣ ስንሞት ወየው ብሎ የሚያለቅስልን ድሀ ነው ። ለድሀ መስጠት ለማይበደረው እግዚአብሔር ማበደር ነው ። እግዚአብሔር ለባለጠጎች ገንዘብን ፣ ለድሆች ደስታን ሰጥቷል ። የእኛን ስንሰጥ የእነርሱን ደስታ ይሰጡናል ። ዓይነቱ መለያየቱ እንጂ እግዚአብሔር ያልሰጠው የለም ። መለዋወጥ ግን የብልሆች ድርሻ ነው ። ገንዘብን ስንሰጥ ደስታን እናገኛለን ። በመቅደስ ደጃፍ ላይ ሁለት ሳንቲም የጣለችው ፣ አምስት ሳንቲም የማይሞላ የሰጠችው ሴትን ጌታ አመሰገናት ። እኛ ብንሆን “ምን አለሽ መልሽው ፣ እግዚአብሔር ሁሉን ያውቃል” እንላት ነበር ። እግዚአብሔር ግን የመርሕ አምላክ ነው ። “ስጡ ይሰጣችኋል” ይለናል ። 

መስጠት መጎዳት ሳይሆን ሞትን መበቀል ነው ። ስንሞትና እጃችን ሲገነዝ መስጠት አንችልምና ። መስጠት የመኖር ምስክርነት ነው ። ሐዋርያው ጳውሎስ ለድሆች ብዙ ምጽዋት ያደርግ ነበር ። ድሆችን እንደ ርግማን በሚመለከት አረማዊ አስተሳሰብ ሐዋርያው ምስኪኖችን ማቀፉ ተለይቶ እንዲታወቅ አድርጎታል ። የክርስቲያኖችን ዱካ በመከተል የጳውሎስን ቤት ማግኘት አልተቻለም ። በማለዳ የሚገሰግሱ የድሆችን ዱካ በመከተል ወታደሮቹ የጳውሎስን ቤት እንዳገኙ ለማወቅ ችያለሁ ። የክርስቲያን ቤት ምልክቱ ድሆች ሲመጡበት ነው ። ክርስቲያን ማለት ክርስቶስ በምድር ማለት ነው ። ክርስቲያን ነፍሱን ስለሰጠ ስለ ክርስቶስ እያወራ ለድሀ የማይሰጥ ከሆነ ግብዝ ነው ። ክርስቲያን ድሆችና ኃጢአተኞች የማይሸሹት ከሆነ የክርስቶስ እንደራሴ ነው ። ብዙ ክርስቲያን ነን የሚሉ ደጃፋቸው ላይ ግን ድሆች የሉምና ክርስትናቸው የቃል ብቻ እንደሆነ ምልክቱ ነው ። የአረማውያን ቤት ምልክቱ የእኩዮች ግብዣ ያለበት መሆኑ ነው ። ለባለጠጋ ሰጥቶ ከእግዚአብሔር የሚጠብቅ ፣ ለድሀ ሰጥቶም ከድሀው የሚከጅል የለም ። ስለዚህ ድሆች ከእግዚአብሔር ጋር ያገናኙናል ። ዓለም የጋራ ቤት ናትና እኛ ጋ ያለውን ድርሻቸውን በመስጠታችን ልንመካ አይገባንም ። 

ራቅ ራቅ ብለው የተቀመጡትን ወታደሮች እያልፍኩ ወደ ጳውሎስ ቤት ብጓዝም ጥማቴ ወታደሮቹን ካላስረሳኝ እውነተኛ አይደለም ብዬ በማሰብ ልቤን አበረታታሁት ። መጠጥ ቤት ደጃፍ ላይ ጠባቂ አይቆምብንም ። ወንጌል ደጃፍ ላይ ግን ብዙ ጠባቂዎች አሉ ። ስንሰክር ያልከበድናቸው ስንጸልይ እንከብዳቸዋለን ። ልቤን በእግዚአብሔር ፍቅር አበረታሁት ። ወደ ቤትም ስዘልቅ ታላቅ ደስታ ላይ እንዳሉ ተገነዘብሁ ። ዙሪያው እሳት ቢሆንም ውስጡ ግን ገነት የሆነው የክርስቲያን ዓለም ምንኛ ድንቅ ነው ። ሐዋርያው ጴጥሮስ ሐሙስ ማታ እንዳልሸሸ አሁን ግን ሙሽራዋን እንደምትጠብቅ ሙሽራይት ሰማዕትነትን እየጓጓ ነበር ። የሐሙስ ማታ ትውስታው ዘመኑን በሙሉ ያበሳጨው ነበር ። ለእግዚአብሔር ለመኖር ብቻ ሳይሆን ለመሞት ይናፍቅ ነበር ። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ጉባዔውን በጸሎት ከፈተ ። ከወትሮው ይልቅ ንቃትና ብርታት ይታይበት ነበር ። መከራ የተሰወረው ጉልበት እንዲወጣ ያደርጋል ። ሥጋ ጠባዩ ነውና ላይ ላዩን ቢታወክም ውስጡ ግን በሰላም እንደሚጠበቅ ክርስቲያን ያውቀዋል ። 

ሐዋርያው ቀጠለ፡- “በዚህ ቀን የምነግራችሁ እግዚአብሐር ማንነትን ለውጦ የክብሩ ዕቃ እንደሚያደርገን ነው ። አንዲት ገረድ ነጻነት የሌላት ፣ ከጌታዋ ንብረት እንደ አንዱ ዕቃ ተቆጥራ የምትኖር ናት ። ሰው ዕቃውን ቢሰብር ጠያቂ እንደሌለው ባሪያና ገረዱን የሚገድል አይጠየቅም ። ገረዶች የሴቶች አገልጋይ ናቸው ። ሴቶች ደግሞ የክርስቶስ ወንጌል እስኪሰበክ ድረስ እንደ ተንቀሳቃሽ ዕቃ ይታዩ ነበር ። እመቤቲቱን ብፈራ እንኳ ይሳቅብኛል ። እኔ ግን የፈራሁት የፍርሃት የልጅ ልጅ የሆነችውን ገረድ ነው ። ፈሪዋን ፈራሁ ። ፍርሃትን መዋጋት ያለብን መቆሚያ ካልሰጠነው ወሰን ስለሌለው ነው ። ፍርሃት ውሎ ሲያድር ቋሚ የአእምሮ በሽታ ይሆናል ። ሰዎች ሰይጣንን መፍራታቸው የሚገርም ነው ። ሰይጣን እንኳን ሰይጣን ሁኖ መልአክ ሳለም ኃይሉ የተወሰነ ነው ። መልአክን የሚንቁ ሰይጣንን ግን ሲፈሩ ይውላሉ ። ሰይጣን እውነተኛ ጠላታችን እንጂ እውነተኛ ፍርሃታችን አይደለም ።

በበዓለ ሃምሳ መንፈስ ቅዱስ ፈሪውን ማንነቴን የእምነት ጀግና አደረገው ። የሰከረ አይፈራም ። የሚያዩን ሰክረው ነው ይሉ ነበር ። እኛ ግን በመንፈስ ቅዱስ ሰክረን ደፈርን ። ለአንዲት ገረድ ክርስቶስን መስበክ ያልቻልሁ ፣ ሦስት ሺህ ሰዎችን ሰብኬ ማሳመኔ የመንፈስ ቅዱስን ኃይል ያመለክታል ። መንፈስ ቅዱስ አስታዋሽ ፣ ምስክር ፣ አጽናኝ ነውና አካል ያለው መለኮት ነው ። እነዚህ ሁሉ የአካል ጠባይያት ናቸው ። በዓለ ሃምሳ መንፈሴ በሥጋ ለባሽ ላይ አይኖርም ያለው እግዚአብሔር መርገምን አንሥቶ ሥጋ በለበሰ ሁሉ ላይ ከመንፈሱ ያፈሰሰበት ቀን ነው ። ትንቢት የተፈጸመበት ፣ የትንሣኤው ምስክር የሆንበት ፣ ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተችበት ዕለተ ወርቅ ነው ። በበዓለ ሃምሳ ከመላው ዓለም ለፋሲካ የመጡ አይሁድ በዓለ ጰንጠቆስጤን አክብረው በቶሎ ወደመጡበት የሚሄዱበት ነው ። በዚህ ቀን መንፈስ ቅዱስ መውረዱ ትክክለኛ ጊዜ ነው ። ስብከታችን ሰማርያ ሳይደርስ በመላው ዓለም ተሰምቶ ነበር ። 

ቀጥሎ የምነግራችሁ ስለ ሐናንያና ስለ ሰጲራ ነው ። ሉቃስ ይህን በሐዋርያት ሥራ በምዕራፍ አምስት ላይ ዘግቦላችኋል ። ሉቃስ የጳውሎስ ደቀ መዝሙር ስለነበር በጥቂቱ ስለ እኔ አገልግሎት ከጻፈ በኋላ በስፋት የጻፈው ስለ ጳውሎስ አገልግሎት ነው ። የባልና የሚስት አንድነት ለጽድቅ እንጂ ለኃጢአት መሆን የለበትም ። ሌሎች ሲያደርጉ ያያችሁትን የትሩፋት ሥራ ለመመሳሰል ብላችሁ ያለ ልባችሁ አትሥሩ ። የታዘዛችሀትን ካደረጋችሁ በኋላ ከታዘዛችሁት በላይ ወደ ማድረግ ታድጋላችሁ ። ባልና ሚስት ለእግዚአብሔር ካልሆኑ አንዳቸው ለአንዳቸውም አይሆኑም ። ከእግዚአብሔር ጋር የሚማከሩ እንጂ በእግዚአብሔር ላይ የሚማከሩ አይጸኑም ። ሐናንያና ሰጲራ ከገንዘባቸውም ከእግዚአብሔርም ሳይሆኑ ቀሩ ። ሌሎች ስላደረጉት ብቻ የሚደረግ የጉራ እንጂ የእምነት ተግባር አይደለም ። ለአገልጋዮች ያለን ንቀት ከትንሽ እውቀታችን የሚመነጭ ነው ። ከሚታዩት አገልጋዮች ጋር የማይታየው እግዚአብሔር አለ ። እኛ ደካማ ብንሆንም የላከን ግን ብርቱ አምላክ ነው ። እኔ በክህደት ፣ ጳውሎስ በማሳደድ ብንታማ ቅዱሱ እግዚአብሔር ግን ሳያፍርብን ልኮናል ። ለእግዚአብሔር አደርጋለሁ ያልነውን ነገር ማድረግ አለብን ። ይጠብቀናልና ። በቃሉ የታመነ አምላክ ቃላችንን ይፈልገዋል ። ምንም በሌለን ሰዓት ቃል የገባነውን ስናገኝ ለማረሳሳት መሞከር ትልቅ ቅስፈት ያመጣል ። የገንዘብ ፍቅር አዳምን ለሞት ያበቃ ፣ ይሁዳን ለገመድ የዳረገ ፣ ሐናንያና ሰጲራን በአደባባይ ያስቀሰፈ ነው ። የወደዱትን ገንዘብ የበሉ በዓለም ላይ የሉም ። እነ ሐናንያን ቀጥቶ ለሌሎቹ ቅዱስ ፍርሃት ያስተማረ እግዚአብሔር ነው። ቸርነት ቢያሸንፍ ኖሮ ሁለት መሐለቅ እንደ ጣለችው መበለት በተመሰገኑ ነበር ። ፍቅረ ንዋይ በማሸነፉ ግን ሞትን አተረፉ ። ይህንንም ታሪክ ተመከሩበት ። 

እግዚአብሔር በቃላችን ታምነን እሰጥሃለሁ ያልነውን ለመስጠት ያብቃን ። ገንዘብን ደብቀን ሕይወትን ከማጣት ይጠብቀን ። አሜን ።”

ሁላችንም ተነሥተን “አሜን” አልን ። ሐዋርያው ሰዓቱ እያለቀ በመሆኑ ቶሎ ቶሎ እየነገረን እንደሆነ አስተዋልን ። 

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ሐምሌ 3 ቀን 2013 ዓ.ም.

ወድ ወገኖቻችን ለልባችሁ የቀረላችሁን እስቲ ለመጻፍ ሞክሩ ። እግዚአብሔር ከቅዱሳን በረከት ያሳትፋችሁ ።

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ