የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ጴጥሮስን አገኘሁት /ክፍል 19/

 

እባካችሁ አንብቡ

በአንድ ቀን ለሦስተኛ ጊዜ ጉባዔ ሲደረግ በዚህ ቀን የመጀመሪያችን ነው ። ሐዋርያው ጴጥሮስ እያንዳንዷን ደቂቃ እየኖራት ነው ። በልባችን ጽላት ላይም የክርስቶስን ፍቅር ለመጻፍ እየተጋ ነው ። የእግዚአብሔር ቃል የሚሠራው በመንፈስ ቅዱስ ኃይል እንጂ በተናጋሪው ብርታት አይደለም ። ጦር እንደሚገድል ሁሉ የእግዚአብሔር ቃልም ማዳኑ እርግጥ ነው  ። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለሮሜ ክርስቲያኖች በጻፈው መልእክቱ በምዕራፍ አንድ ቍጥር 16 ላይ “ለሚያምኑ ሁሉ የእግዚአብሔር ኃይል ለማዳን ነው” ይላል ። በዓለም ላይ ብዙ ዓይነት ኃይል አለ ። አንዳንዱ ኃይል የሰውን ድካም የሚያቀልል ነው ። ሌላው ኃይል የሚያጠፋ ኃይል ነው ። የእግዚአብሔር ኃይል ግን ለማዳን ነው ። ብዙ የበረቱ ሰዎች ኃይላቸው ሌሎችን ለማስጨነቅ ነው ። መዝሙረኛው “ጊዜውን ስቀበል እኔ በቅን እፈርዳለሁ” ይላል ። መዝ. 74፡2 ። ብዙ ሰዎች ጊዜውን ሲቀበሉ በጠማምነት ፣ በአድልኦና በጎሠኝነት ይፈርዳሉ ። እግዚአብሔር ጊዜን ሲሰጠን ተመዝነን እናልፋለን ወይም እንወድቃለን ። አንዳንዶችም ገና ጊዜውን ሳይጨብጡ በምኞት ተመዝነው ይቀላሉ ። ይህን ባገኝ እገሌን አስሬ ፣ እገሌን አስርቤ ይላሉ ። ባልተጨበጠ ቀን የተጨበጠ ክፋት ይናገራሉ ። 

ጊዜ እግዚአብሔር እኛን የሚሠራበት ፣ በእኛ የሚሠራበት ፣ ለእኛ የሚሠራበት ትልቅ መሣሪያው ነው ። ሐዋርያው የጊዜን ክቡርነት አውቋል ። በእያንዳንዱ ደቂቃ ውስጥ ለዘመን የሚተርፍ ምክር ያስተላልፍ ነበር ። ዓመቱን በቀልድ ማሳለፍ ፣ ደቂቃውንም በቁምነገር መፈጸም ይቻላል ። ማቱሳላ ዘጠኝ መቶ ስድሳ ዘጠኝ ዓመት ቢኖርም ይህን ሠራ አልተባለለትም ። እስጢፋኖስ ግን በ17 ዓመቱ ከሐዋርያት ቀድሞ የሐዲስ ኪዳን የመጀመሪያው ሰማዕት ሆነ ። በዚህም ቀዳሜ ሰማዕት እየተባለ ይጠራል ። ሥራን ከፈጸሙ መቆየት የሠሩትን ለማበላሸት ነው ። ሞልቶ ከተረፈው ዕድሜ መድኃኔዓለም በዚህ ምድር ላይ የኖረው 33 ዓመት ከ3 ወር ነው ። ትልቅ ዕድሜ ሳይሆን ትልቅ ሥራ አስፈላጊ ነው ። የዓመታት ርዝመት ቁምነገር አያሠራም ። የልብ ቆራጥነት ካለ ዛሬን ታሪካዊ ቀን ማድረግ ይቻላል ። ዛሬን አዲስ ነገር ባንከውን ዛሬን የበደልነውን ሰው ይቅርታ በመጠየቅ ልዩ ቀን ማድረግ ይቻላል ። ቢሆንም እግዚአብሔር ኑሩ ያለንን ያህል ኖሮ ማለፍ ተገቢ ነው ። ቢታክቱም ፣ ቢሰነብቱም ሞት አይቀርም ። መቸኮልም መዘግየትም አይገባም ። እንደ ጳውሎስ መቸኮል ፣ እንደ ሕዝቅያስ መዘግየት ሁለቱም የራሱ ጉዳት አለው ። በሞታችን ላይ ሥልጣን ያለው በልደታችን ላይ ሥልጣን የነበረው እግዚአብሔር ነው ። እስረኛ ራሱን አይፈታም ፣ በዚህ ምድር ላይ ያለን እስረኞች ነን ። እስረኛን የሚፈታው ሥልጣን ያለው ነው ። ሞታችንን የሚወስንም እግዚአብሔር ነው ። የወጣቶችም መታከት ፣ የሽማግሌዎችም  ልሰንብት ማለት በእግዚአብሔር ፈቃድ መገምገም አለበት ። ተማሪ ለራሱ ደውሎ ከክፍሉ አይወጣም ። ሰዓቱ ሲደርስ ይወጣል ። በምድር ላይ ለትምህርት የተቀመጠው ፣ እስኪያረጁ ሙያን ፣ እስኪሞት እንግዳ ነገርን የሚቀስመው የሰው ልጅ በሰዓቱ ይሄዳል እንጂ ሳይጠራ አቤት ማለት የለበትም ። የጊዜ መለኪያ የሆነውን ሰዓት መግዛት ይቻላል ፣ ጊዜ ግን የእግዚአብሔር ስጦታ ነው ። 

ጀምበሩ እያዘቀዘቀ ነው ። ብርሃኑም ለዓይን ያዝ አድርጓል ። ቅዱስ ጴጥሮስ መቅረዙን ዘይት እንድትሞላ እማሆይ ፌበንን አዘዛት  ። ሲላስንም ለኵሰው አለው ። ሐዋርያው ንግግሩን ሲጀምር የጳውሎስ ቤት በወታደሮች ተከብቦ ነበር ። ልቤ በድንገት ቤተ መንግሥትንና ቤተ ክህነትን የሚደፍር ውስጡን የሚያውቀው ነው አለ ። ለክርስቶስ ይሁዳ አለበት ፣ ለጳውሎስም ዴማስ አለበት አልኩኝ ። በድሆች ምልክትነት የተገኘው የጳውሎስ ቤት ዴማስም መሪ ሁኖ መጥቶበታል ። ዴማስን በርቀት ሳየው በሱስና በመጠጥ አካሉ ሁሉ ረግፏል ። ቀድሞ ጳውሎስን በተሰሎንቄ እንደለወጠ ዛሬም ጴጥሮስን በሮሜ ሊለውጥ ጨክኗል ። ያዳቆነ ሰይጣን ሳያቀስስ አይለቅም ይባል ነበር ። የዘንድሮ ያጰጵሳል ። ወታደሮቹ ግን ወደ ውስጥ ለመዝለቅ በማይታይ ግንብ ተከልክለው ቆመዋል ። በአንድ ዓይናችን ጴጥሮስን በሌላ ዓይናችን ወታደሮችን እያየን ጉባዔው በጸሎት ተከፈተ ። ከእኛ ጋር የነበሩ እኛን ለማጥፋት የሚነሡበት ክፉ ቀን አለ ። የቅዱስ ጴጥሮስ ትምህርት ጀመረ ። ድምፁ ከቤቱ ዘልቆ ወደ ደጅ እንዲሰማ ሆን ብሎ አድርጎታል ። ካለቀ ቁጠባ ፣ ከከሱ ቅለባ ምንም አይጠቅምም ። ወታደሮቹም የእስር ወረቀት ከተቆረጠበት ሰው እየተማሩ ነው ። እኛ ተቀምጠን እነርሱ ቆመው ይማራሉ ። ሐዋርያው ጴጥሮስ ንግግሩን ቀጠለ፡-

“ልጆቼ ቤተ ክርስቲያን የምእመናን ስብስብ ናት ። ሀብትና ሕንፃ ባይኖርም ቤተ ክርስቲያን ትኖራለች ። እንደውም ብርና ወርቅ በሌላት ዘመን ፈውስን ትናኛለች ፣ ብርና ወርቅ ስትይዝ ልጆችዋን ታቆስላለች ። ቤተ ክርስቲያን በሲኖዶስ የምትመራ ተጠሪነቷ ለመንፈስ ቅዱስ የሆነ የክርስቶስ አካል ናት ። መንፈሳዊት አካል በመሆኗ ግዙፉ ዓለም ሊያሸንፋት አይችልም ። ከተለያየ ባሕልና አስተሳሰብ የመጡ ሰዎች ስብስብ ናትና ሙግትና ክርክር ይኖርባታል ። ሙግትና ክርክር ዳኛ ከሌለው መቆሚያ የለውም ። ዳኛውም ሲኖዶስ ሊሆን ይገባዋል ። ሲኖዶስም አድልኡ ለጾም እንደሚለው ለመንፈስ ቅዱስ ማድላት ፣ የጊዜ አሽከር ከመሆን መዳን አለበት ። ፍትሕ ገለልተኛ ካልሆነ ራሱ በዳይ ነው ። የሲኖዶስ ሥልጣን የተንጠለጠለውን ጣት ገጥሞ መስፋት እንጂ ቆርጦ መጣል አይደለም ። ክርስቶስ የሞተለትን ወገን በር ከፍቶ ማስገባት እንጂ በር ከፍቶ ማስወጣት የሲኖዶስ ተግባር መሆን አይገባውም ። ዓመፀኛ ቢገኝ እንኳ ለምክር በጀ ካላለ ሌሎችን እንዳይጎዳ ይገለላል ። ንስሐ ሲገባም ምሕረት ይደረግለታል ። ለማስተማር የሚሰንፍ ለውግዘት ይበረታልና እንደ ቆላ ቄስ ደርሶ አውጋዥ አትሁኑ ። ያልተማረ ቄስ ሁሉን ያረክስ ፣ የተማረ የረከሰውን ይቀድስ ነውና ልበ ሰፊ ሁኑ ። በቤተ ክርስቲያን የምእመናን ክብር ያለው በሚያስገቡት አሥራት መጠን ሳይሆን በክርስቶስ ደም በመዋጀታቸው ብቻ ነው ።” 

ሰዓቱ እየመሸ ሄደ ፣ እኩለ ሌሊቱም ገፋ ፤ ወደ ንጋት ላይ የወታደሮቹ አዛዥ መጣና በታላቅ ጩኸት ባረቀባቸው ። “አንድ ሴማዊ ፣ ሃይማኖት እንጂ ሥልጣኔ የሌለው በሮም ምድር ላይ እንዲህ ሲሰብክ ዝም ትላላችሁ ወይ ?” አላቸው ። በዚህ ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ ወደ ደጃፉ ወጣና በታላቅ ድምፅ፡-

“በምዕራብና በምሥራቅ መኖር አቅጣጫ ነው ። የሰማይ መንገድ ግን አንድ ነው ። ምንም እንኳ ቆርኔሌዎስ ሮማዊ ፣ የእናንተ መቶ አለቃ ቢሆንም ሃይማኖቴ አጥር ሆኖብኝ እንዳልንቀው ጌታ አሳሰበኝ ። እናንተ እኛን በሥልጣኔ ፣ እኛ እናንተን በሃይማኖት ሚዛን እየለካን የምንናናቀው እስከ መቼ ነው  አንዱ ባንዱ ሲስቅ ጀምበር መጥለቋ ያሳዝናል ። ጊዜን የሚያህል መክሊት እየባከነብን ነው ። ድንግል አእምሮና መሬት ይዘን ዓለም ሊያልፍ ነው ። ጥፋት ከምትሉት በላይ አይሁዳዊነቴን እንደ ትልቅ ጥፋት ትቆጥሩታላችሁ ። ለአንድ ሮማዊ በአይሁዳዊ መሰበክ ከባድ ነው ። እግዚአብሔር ግን ይህን አደረገው ። እኔ አይሁዳዊ ስሆን ለእግዚአብሔር አሳብ አቅርቤ አይደለም ። ፈቃዱን ላትለውጡ ለምን ትጣሉኛላችሁ ? ምዕራብና ምሥራቅ የምንንሰራፋበት እንጂ ሰሜንና ደቡብ እየተባባልን የምንጣላበት አይደለም ። እግዚአብሔር እስከሚያዝዝበት ድንበር ድረስ ልባችሁን አስፉት ። ጠባብ ሆናችሁ አትጨነቁ ፣ አታስጨንቁንም ። ዘረኛ ዓለሙ ይህች ብቻ ናት ። ክርስቲያን ግን የሁለት ዓለም ወራሽ ነው ። ጠባዩ ያልበደላችሁን ሰው በጎሣው እንዴት ትጠሉታላችሁ ? ሰው በሥራው እንጂ በቀለሙ መዳኘት የለበትም ። ዘረኝነት ልክ የለውምና ቀዩ በጣም ከቀላው ጋር ፣ ጠይሙም በጣም በጣም ከጠየመው ጋር ሲለያይ ይኖራል ። ዘረኝነት መቆሚያ ካልተበጀለት የሚቆመው ቆስቋሹን በመግደል ነው ። በቂ አሳብ የሌለው በቂ ጎሠኝነት አለው ። ሮማ ትቅደም እያሉ ሰላም ላይኖር ይችላል ። እግዚአብሔር ይቅደም ማለት ግን ለዓለም ሰላም ነው ። ደፋር ለመጀመሪያ ጊዜ የእኔ ወገን ትልቅ ነው ስላለ ትልቅ ይመስላል ። ቤተሰባችን ቢበዛም ምንጩ ግን አንድ ነው ። ወንዝ በምንጩ ይጠራል ። እኛ ግን በወራጁ እየተጣላን ነው ። ሰሜን ላይ አርሞንየም የሚባለው በረዶ ፣ መሐል ላይ የዮርዳኖስ ወንዝ ይባላል ። ሲፈጽም ግን ሙት ባሕር ይሉታል ። እኛም ስንፈጽም ሁላችንም ሞተ እንባላለን ። ልደት በሚል በሦስት ፊደል ጀምረን ሞተ በሚል በሁለት ፊደል እንፈጽማለን ። አጽሞችን ስትመረምሩ አውቃለሁ ። ሁሉም ግን አፈር ሆነ እንጂ ወርቅ የሆነ አጽም አላያችሁም ። ጥላቻ ሞቶ መኖር ነውና እባካችሁ ከጥላቻ ውጡ ።

ጎል ተብለው የሚጠሩት ሕዝቦች እናንተን ጥቁር ይሉአችኋል ። እንግልጣሮችም ንጹሕ ዘር እኛ ነን ይላሉ ። ጽርዓውያንም ዱር ነዋሪ የሆነውን አውሮፓ አሰለጠነው ብለው ይመጻደቃሉ ። ክርስትና ይህን ሁሉ ለማስወገድ የሚተጋ ነው ። ገዳይና ሟች የሌለባት የሰላም መንደር እንድትሆን ለዓለም የተሰጠው ክርስትና ነው ።” 

ወታደሮቹም በእያንዳንዱ ቃላት መጽናት ስላልቻሉ የመሸነፍ ምልክት የሆነውን ዱላ አነሡ ። ጴጥሮስንም ወደ ራሳቸው ስበው መሬት ላይ ጣሉት ። በዚህ ጊዜ በደጅ የቆሙት ወታደሮች ወደ ቤት ዘው ብለው ገቡ ። ለጊዜው የሚፈልጉት ጴጥሮስንና ጳውሎስን ነበርና ሌሎቻችንን ትተው ታላቅ የዱላ መዓት ያወርዱባቸው ጀመር ። ልብሳቸው በላያቸው ላይ እስኪቀደድ እንግልት አደረሱባቸው  ። እኛም ዙሪያቸውን ከብበን ብንጮህም ማዳን ግን አልቻልንም ። እየደበደቡአቸው ወደ ወኅኒ ወሰዱአቸው ። ቀኑ ሁሉ ጠፋኝ “ዛሬ ቀኑ ምንድነው ነው ?” ብዬ ብጠይቅ ሐምሌ አራት ነው አሉኝ ። አንድ ሕግ አዋቂን ጠጋ ብዬ ብጠይቅ የፊተኛው ፍርድ ስለሚጸና ዳግመኛ ችሎት አያስችሉላቸውም ። ነገ በሞት ሊቀጡ ይችላሉ አለኝ ። እኔም ልቤ ጽናትና ኀዘን እየተፈራረቀበት ቀኑን በሙሉ ከእስር ቤቱ ደጃፍ ላይ ዋልሁ ።

በረከተ ጴጥሮስ ወጳውሎስ በሁላችን ላይ ይደር።

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ሐምሌ 4 ቀን 2013 ዓ.ም.

ወድ ወገኖቻችን ለልባችሁ የቀረላችሁን እስቲ ለመጻፍ ሞክሩ ። እግዚአብሔር ከቅዱሳን በረከት ያሳትፋችሁ ።

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ