የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ጴጥሮስን አገኘሁት /ክፍል 4/

 

ሐዋርያው ጴጥሮስ ሲናገር ሐዋርያው ጳውሎስ በታላቅ ተመሥጦ ይሰማ ነበር ። ከዚህ በፊት ሳይሰማው አይቀርምና እንዴት በእንዲህ ያለ ተመስጦ ሊሰማ ቻለ ብዬ ሳስብ አራት ነገሮች ታሰቡኝ ። የመጀመሪያው፡- እግዚአብሔር በሰው ታሪክ ውስጥ ጣልቃ እየገባ የራሱን ታሪክ ሲጽፍ የሰው ሕይወት የማይሰለች ትረካ ይወጣዋል ። ሁለተኛው፡- እንዲያደምጡት የሚፈልግ መምህር እርሱም ሌሎችን ማድመጥ ይገባዋል ። ሦስተኛው፡- ሐዋርያው ጳውሎስ ከተቃዋሚነት ወደ ክርስትና በመምጣት ወንጌል ጠላቷን ወዳጅ ፣ አፍራን ሠራተኛ አደረገች ተብሎ ሲነገር ጴጥሮስ ግን ከታላቅ ጥማት በኋላ ክርስቶስን አገኘ ። ሐዋርያው ጳውሎስም የእርሱን አመጣጥ እያሰበ ያደምጠው ነበር ። አራተኛው፡- ለደቀ መዛሙርቱ ስለ ጴጥሮስ ጥሪና አገልግሎት ይነግራቸው ነበርና ራሱ ቅዱስ ጴጥሮስ በአንደበቱ ሲያጸናለት ደስ ብሎት ያደምጥ ነበር ። ወደ ሲላስ ተመለከትኩና ማርቆስ ሲሄድ የመጣ የወንጌል ትርፍ ነው አልኩኝ ። ወደ ጢሞቴዎስ ተመለከትኩና እንደ ጳውሎስ በባዕድ አገር ቢወለድም ልቡ ግን እስራኤል ነበረ አልኩኝ ። ተመሳሳይ ቀለም ያላቸው ወፎች አብረው ይበራሉና ጳውሎስም የሚመስለውን ጢሞቴዎስን ማስከተሉ ተገቢ ነው አልኩኝ ። ሐዋርያው ጴጥሮስ ደግሞ አይሁዳዊነት የሚጫነው የደጁን ዓለም መልመድ ያልቻለ ሲሆን እርሱም የቤት ልጅና የአገር ሰው የሆነውን ማርቆስን መርጦ ወንጌሉን እንዲጽፍ አደረገው በማለት ማሰላሰል ጀመርኩ ። ማርቆስም ትላንት ሐዋርያው ጳውሎስን ወዲህ መከራ አይቶ በመሰቀቅ ፣ ወዲህ የእናቱ ናፍቆት አይሎበት ወደ ኋላ ቢልም ዛሬ ግን ሁሉን አይቶ በመምጣቱ ደስ አለኝ ። 

ያን ጊዜ ሐዋርያው ጳውሎስ ድኗል በማለት ለማርቆስ ክብር ሰጥቶት ነበርና ተቀየመው ። ሰው ተቀይሞ መቅረቱ እንጂ የሚቀየመው ዋጋ የሰጠውን ሰው ነው ። በርናባስ ግን የሥጋ ዘመድ ነበርና ልጅ ስለሆነ ነው በማለት ማርቆስን አዘነለት ። መንፈሳዊ አባት በመንፈሳዊ ሚዛን ይመዝንና በዕድሜ ለጋ የሆኑትን ወደ መንፈሳዊ ተጋድሎ ይጋብዛል ። የሥጋ ዘመድ ግን ምንም መንፈሳዊ ቢሆን የዕድሜ ለጋነቱን በማየት ገና ነው እያለ ከገድል ያዘገየዋል ። “ትንሽ ሥጋ ከመርፌ ትወጋ” እንዲሉ ። ፌበንን ሳያት በእንባ ታጥባለች ። እግዚአብሔር አይሁዳዊ ትውልድና ባሕል ያለውን ጴጥሮስን ፣ ከአይሁድ ቢወለድም ግሪካዊ ሥልጣኔን የሚያውቀውን ጳውሎስን ፣ አባቱ ግሪካዊ እናቱ አይሁዳዊት የሆነችውን ጢሞቴዎስን ፣ የኢየሩሳሌም ሰው የሆነውን በአይሁዳዊ ስሙ ሲላስ በሮማዊ ስሙ ስልዋኖስን ፣ እርስዋ ደግሞ ሙሉ ግሪካዊነት ሁና በክርስቶስ በማመን ሁሉም አንድ ሆነው መቀመጣቸው እየደነቃት ነበር ። ፌበን የግሪክ ደቡባዊ ግዛት የአካይያ አውራጃ የቆሮንቶስ ጎረቤት የክንክራኦስ ቤተ ክርስቲያን አባል ነበረች ። እስከ ሮም ድረስ በመጓዝ የሮሜ መልእክትን ያደረሰች ናት ። ይህች ሴት በሴትነት አቅሟ ይህን ያህል መንገድ ስትጓዝ ዘመንዋን ለጌታ የሰጠች አገልጋይ ወይም ዲያቆናዊት ሴት ስለነበረች ፣ ደግሞም ሀብታም ሁና ክርስቲያኖችን በገንዘብዋ የምትረዳ ነበረች ። ሐዋርያው ጳውሎስንም በብርቱ ታግዘው ነበር ። ዕድሜዋም ከስድሳ የማይበልጥ ከሃምሳ የማያንስ ይመስላል ። ከሁሉ በላይ የገረመኝ እኔ ራሴን በዚህ የቅዱሳን ማኅበር ማግኘቴ ነበር ።

የፌበንን እንባ እያየሁ የእኔም እንባ በዓይኔ ግጥም አለ ። መለስ ብዬ ጳውሎስን አየሁት ፣ ደግሜ ፌበንን አየሁ ። ሐዋርያው ጳውሎስ ለሴቶች ጥላቻ ነበረው ብለው የሚያሳድሙበትን ሰዎችና የጥናት ጽሑፍ የሚበትኑበትን አሰብኩና አንድ ሰዓት ለእግዚአብሔር መስጠት ያልቻለ ሰው ዘመኑን የሰጠውን ሐዋርያ ለማማት እንዴት ደፈረ ? ብዬ ራሴን ጠየቅሁ ። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሴቶችን የሚጠላ ቢሆን ኑሮ ፌበንን ዲያቆናዊት ሴት ወይም የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ አድርጎ አይሾማትም ነበር ። ከእርስዋ እጅም ብዙ እርዳታ እንዳገኘ ሳያፍር ለሮሜ ሰዎች አይጽፍላቸውም ነበር ። ብዙ ወንዶች ሳሉ የሮሜ መልእክትን ከግሪክ ወደ ሮም በፌበን እጅ አይልከውም ነበር ። ደግሞም የጢሞቴዎስ የሃይማኖት አባት ሳለ ለሴት አያቱና ለእናቱ ትልቅ ክብር ሰጥቶ፡- “በአንተ ያለውን ግብዝነት የሌለበትን እምነትህን አስባለሁ፤ ይህም እምነት ቀድሞ በአያትህ በሎይድ በእናትህም በኤውንቄ ነበረባቸው፥ በአንተም ደግሞ እንዳለ ተረድቼአለሁ።” አይለውም ነበር ። /2ጢሞ. 1፡5/ ጵርስቅላን የሚያደንቅ ፣ ብዙ ሴቶችን ሰላም በሉልኝ የሚል ፣ ከልዕልቶች እስከ ባሮች ያሉትን ሴቶች በመልእክቱ እኩል ስም ጠርቶ ሰላም የሚል ነው ። ደግሞም በገላትያ መልእክቱ “ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና” ያለውን ማስታወስ ተገቢ ነበር ። /ገላ . 3፡28/ እግዚአብሔር ዓለምን ለማዳን የመረጣትን ድንግል ማርያምን ሲያነሣ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡- “ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ፤” አለ ። /ገላ. 4፡4/ ሣራን ብዙ ጊዜ በእምነትዋ ሲያነሣት ፣ ራኬብን ሲያደንቃት ፣ ፌበንን ሲልካት እየሰማን ለምን እንዲህ ብለን እንከሰዋለን ? ብዬ አዘንሁ ። ሴቶች በአደባባይ ቆመው እንዳይሰብኩ መከልከሉ በዚያ ዘመን ጭቆና መሠረት ሴቶች ሳይማሩ በር ተዘግቶባቸው ቆይተው ነበርና የሚናገሩት እንዳያጡ ብሎ ክብራቸውን በማሰብም ነውና ያደረገው ውለታ ነው ። አገልግሎት ቆሞ መስበክ ብቻ አይደለምና ሴቶች ሌላ አገልግሎት እንዳላቸው አገልጋይ ተብለው እንደሚጠሩም በሮሜ. 16፡1 ላይ ስለፌበን ሲናገር ሰምተነዋል፡- “በክንክራኦስ ባለች ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ የምትሆን እኅታችንን ፌቤንን አደራ ብያችኋለሁ፤ ለቅዱሳን እንደሚገባ በጌታ ተቀበሉአት፥ እርስዋ ለብዙዎች ለእኔም ለራሴ ደጋፊ ነበረችና፥ ከእናንተም በምትፈልገው በማናቸውም ነገር እርዱአት።” በዚህ ንግግር ውስጥ ለሴቶች ክብርና ፍቅር እንጂ ምንም ጥላቻ እንደሌለው ተመልከቱ ። ሴቶች ቆመው እንዳይሰብኩ የተናገረውም በዶግማ ሳይሆን በሥነ ሥርዓት ደረጃ ነው ። በተፈጥሮና በመዳን ሴቶች ከወንድ ጋር እኩል መሆናቸውን የተናገረውን ትተው ሥነ ሥርዓትን በሚመለከት የተናገረውን እንደ ነገረ መለኮት ቆጥረው ስሙን ማጥፋታቸው ተገቢ አይደለም ብዬ አለቀስሁ ። ሐዋርያው ግን የተረጋጋ ነበርና እግዚአብሔር ምን አለ ? እንጂ ሰው ምን አለ ? ብሎ ጆሮውን የሚቀስር አልነበረም ። ይህን ሁሉ ያሳሰበኝ የፌበን እንባ ነው ። ሐዋርያው ጴጥሮስም ጉሮሮውን ሞርዶ አፉን በውኃ አርጥቦ ሊናገር ሲል ቀልቤን ከሄደበት መለስኩት ። 

 

ሐዋርያው ጴጥሮስ ስለ መጀመሪያው የአማኒነት ዘመኑ መናገር ጀመረ፡- 

“ክርስቶስን ያገኘሁት ከብዙ ጥማት በኋላ ነው ። እርሱ ለተጠማ እርካታ እንጂ ለረኩ እርካታ አይደለም ። መጠማት የሰው ድርሻ ፣ ማርካት የአምላክ ፋንታ ነው ። ያለሁበት ቦታ መጥቶ ያገኘኝ እንደ ትላንት ዮርዳኖስ በረሃ ያላገኘን ለምንድነው ? ብዬ ራሴን ስጠይቅ ለፍቅሩ ሳይሆን ለድካሜ ዋጋ እንዳልሰጥ ብሎ ነው ። ጸጋን የሚያባክንና የሚያርቅ ትምክሕት ነውና ። በመጠማት ያገኘነውን ክርስቶስ በትዕቢት ልናጣው እንችላለን ። ትዕቢት እንኳን ምድርን ሰማይን እንዳወከ ዓለመ መላእክት ምስክር ነው ። በመጀመሪያው የአማኝነት ዘመኔ ታስሮ እንደ ተፈታ እንቦሳ ሜዳው እንጂ ገደሉ አይታየኝም ነበር ። ብናገር አልጠግብም ነበር ። ሕፃን ልጅ መናገር እንደ ጀመረ መናገርን አይጠግብምና ። ደስታዬን የሚነጥቁብኝ ስለሚመስለኝ ቤተሰቤን ማሰብ አልፈልግም ነበር ። ላገኘሁት ሰው ስለ ክርስቶስ መናገር እፈልግ ነበር ። ጌታ ግን ብዙ ጊዜ ዝም በል ይለኝ ነበር ። አቅሜና የሚመጣው ፈተና ካልተመጣጠነ እንዳልወድቅ ብሎ ነው ። በመጀመሪያ የአማኝነት ዘመኔ ዓለሙን ሁሉ በዕለት አሳምኜ የማድር ይመስለኝ ነበር ። በእኔ ባካና ኑሮ መላው ዓለም ሲጨነቅ እንደ ሰነበተ አርፌአለሁ ስላቸው ሰዎች ሁሉ ወደ ክርስቶስ የሚመጡ ይመስለኝ ነበር ። ክርስቶስ ግን ባለ ማወቄ እየራራ ወደ እውቀት ይመራኝ ነበር ። በድካሜ አንድም ቀን አይፈርድብኝም ነበር ። ጥሩነቴን እያጎላ ሲናገረኝ ክፉነቴን ለመጣል እታገል ነበር ። በውሳኔዬ የምጥለውና መንፈስ ቅዱስ ደግሞ የሚያስጥለኝ ነገር እንዳለ ያውቃልና በአጭርና በረጅም ዕቅዱ ወደ መለወጥ ይመራኝ ነበር ። ከክርስቶስ ጋር የነበርሁበት እያንዳንዱ ቀን በአናጢ እጅ እንዳለ ድንጋይ እጠረብ ነበር ። ስጠረብ እያነስኩ ቢሆንም የምጠቅም ነበርሁ ፤ ቢያመኝም ውበት እያገኘሁ ነበር ። እንኳን የነፍስ ውበት የሥጋ ውበትም ሕመም አለው  ። በሥጋ የሚዋቡ ፀጉራቸውን ሲሠሩ ይጨመድዳቸዋል ፣ ሲኳሉ እንባቸው ይፈስሳል ። ጆሮአቸውን ሲበሱ በጋለ ብረት ነው ። በነፍስ ለመዋብም የሕመም ሥርዓትን ማለፍ ያስፈልጋል ። 

ሐዋርያው ንግግሩን እየቀጠለ ሳለ እንዲደግምልኝ ስለፈለግሁ በስሜት አስቆምሁት ። በዚያ መሐል መኖሬን አሁን በደንብ ልብ ያለ መሰለኝ ። በእግዚአብሔር ቤት ኗሪና እንግዳ የለምና ፣ ሁሉም የአንድ አባት ልጅ ነውና አክብሮ ሰማኝ ። እኔም ደስ አለኝ ። ራሴ ራሴን ሳላደምጠው ቅዱሱ ሰው ስላደመጠኝ ክብር ተሰማኝ ። 

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

እሑድ ሚያዝያ 10 ቀን 2013 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ