የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ጴጥሮስን አገኘሁት /ክፍል 5/

 ጴጥሮስን አገኘሁት /ክፍል 5/

ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ የጠየቅሁትን ጥያቄ ለመመለስ ሲያስብ በሞት ደጃፍ ላይ እንዳለ ሰው በፍቅርና ተተኪውን በማክበር መንፈስ አየኝ ። የሞት መድኃኒት መውለድ ነውና መምህር በደቀ መዝሙሩ በዓላማው ወራሽ ሞትን ይበቀላል ። ዓላማን ከማይወርስ የሥጋ ልጅ ሁለት መስመር ጽሑፍ ማስቀመጥ ዋጋ አላት ፣ መታሰቢያም ናት ። ወደድንም ጠላንም ፣ ተደሰትንም ተከፋንም ነገ የትውልድ እንጂ የእኛ አይደለችም ። ቅዱስ ጴጥሮስ ከዚህ በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ለመመለስ አቅሙም የዘመኑ ልክም አይፈቅድለትም ። ከኢየሩሳሌም ይልቅ ሰማይ ይቀርበዋል ። ማንኛውም አይሁዳዊ ኑሮዬ የትም ቢሆን መቃብሬን ኢየሩሳሌም ያድርግልኝ ይላል ። ጴጥሮስ ግን በኢየሩሳሌም ኖሮ በሮም ለመሞት ተዘጋጅቷል ። ሞቱን ሲያስብ የመባባት ስሜት አይታይበትም ። ሞት ለእርሱ ከሙሽራው ክርስቶስ ጋር የሚገናኝበት ነውና የናፍቆት ርእሱ ነው ። 

ሐዋርያው የመጀመሪያውን የአማኝነት ዘመኑን ጠባይ እንዲደግምልኝ ስጠይቀው የረሳውን አስታወሰ ። እንድርያስ ወንድሙ ታናሽ ቢሆንም ትልቅ ሥራ የሠራ ነው ። ከሥራ ሁሉ የሚልቀው ሥራ ትንሹን ሰው ከትልቁ ጌታ ጋር ማገናኘት ነው ። ቅዱስ ጴጥሮስ ተናገረ፡- “እንድርያስ ማለት ዘጠኝ ጊዜ አነጣጥሮ አንድ ጊዜ የሚተኩስ አስተዋይ ነው ። ብዙ ባለመናገሩም ኃይሉ አልባከነም ። ብዙ የሚናገር ሰው የተናገረውን መልሶ ሲያስብ የሚሠራበት ጊዜ ይባክንበታል ። የእናት ሆድ ዥንጉርጉር እንዲሉ እኔና እንድርያስ የተቃረነ ጠባይ ነበረን ። ጠባይ ቢለያየንም ክርስቶስ ወይም ሕይወት አንድ አደረገን ። በሥጋ ከአንድ ወላጅ ከተወለድኩት እንድርያስ ጋር እንደገና በመንፈስ ለሰማያዊ ርስት አብረን ተወለድን ። እንድርያስ በሥጋ ሲወለድ አይቻለሁ ፣ በመንፈስ ስወለድ ደግሞ እንድርያስ አየ ። እንድርያስ ሲወለድ አማምጫለሁ ፣ እኔ ለሰማይ መንግሥት ስወለድ እርሱ አማማጠ ። 

ከስመ ጥር ሰዎች ጀርባ ስመ የለሽ ሰዎች አሉ ። ከምናየው ሥራና ሰው ጀርባ የማይታይ ሠራተኛ አለ ። ከእኔ ድምቀት ጀርባ በስሱ የተጻፈ እንድርያስ የሚል ጽሑፍ አለ ። እንድርያስ እንደ እኔ ትጥቁን አራግፎ ዘመን አጋምሶ ሳይሆን በጠዋቱ ወደ መንፈሳዊ ነገር ያዘነበለ ነበር ። የዮሐንስ መጥምቅ ደቀ መዝሙር በመሆኑም የመሢሑን መምጣት ይጠባበቅ ነበር ። ባለመናገሩ የሚያውቅ አይመስለኝም ነበር ። ዝምታው የእውቀት ሳለ አለማወቅ መስሎኝ ነበር ። ብዙ ማወቁ ግን ጥቂት ለመናገር ፣ ብዙ ለመሥራት አበቃው ። እርሱን ያረጋጋው የዮሐንስ አገልግሎት ለእኔም ይጠቅም ይሆናል ብዬ ያሰብኩት ይመስለኛል ። መረጋጋት ዓለም ሁሉ የሚሰማው ትልቅ ስብከት ነው ። የቃል ስብከታችንን የሚቃወም ዓለም ሰላማችንን ግን መካድ አይችልምና በጌታ መደሰትን አጥብቀን መያዝ ይገባናል ። ሰላምና ደስታ ምስክርነቶች ናቸውና ። ሰላም የሌለው ዓለም እንዴት ሰላም አገኙ ብሎ ወደ እኛ ሲመለከት ወደ ክርስቶስ ይመጣል ። እንድርያስን ያረጋጋውን ነገር ለማግኘት ወደ ዮርዳኖስ ሸለቆ ሄጃለሁ ። እግሬ እንዳመራኝ የሄድኩ ይመስለኝ ነበር ፤ ነገር ቀድሞ በውስጤ የተቀመጠው አሳብ ለዛሬ ውጥረቴ መልስ ሆኖ ተሰማኝ ። እዚያ ጋ ሰው የሚበላውን ምግብ ባታውቀውም ለመብላት ድፍረት ታገኛለህ ። የሰው ሁሉ ችግሩ ተመሳሳይ ነውና እንድርያስን ያዳነ እኔን አይገድለኝም ብዬ በማመን ወደ ዮርዳኖስ ሄጃለሁ ። ዛሬ ሰብከን ዛሬ አያምንምና ስብከታችን በጨነቀው ጊዜ ወደ ክርስቶስ ዘወር ይል ዘንድ በልቡ አማራጭ ማስቀመጫም ነው   ። 

እንድርያስ ስሜቱን የሚገልጥና መንገደኛ ሁሉ በቀላሉ የሚያነበው ሰው አልነበረም ። እኔ ደግሞ የራሴን የግል ችግር ብሔራዊ ውጥረት አድርጌ የምናገር ፣ ዓለም ሁሉ ስሜቴን ተጋርቶ አብሮኝ ይደሰት አብሮኝ ይዘን የምል ሰው ነኝ ። ለረጋውም ለባከነውም ክርስቶስ በእኩል ያስፈልጋል ። ክርስቶስ የመጣው የአዳም ልጆችን ለማዳን እንጂ ጨዋዎችን ትቶ ብኩኖችን ለመሰብሰብ አልነበረም ። ከድፍርሱ ምንጭ ከአዳም የወጣን ድፍርስ ጅረቶች ነን ። እንድርያስ ዮሐንስን ብቻ ሳይሆን ክርስቶስንም በማግኘት ይቀድመኛል ። ማንም ሰው ለሥጋ ወንድሙ መሬት ስለማጋዛት እንጂ ክርስቶስን ስለመስጠት አያስብም ። እንድርያስ ግን ለእኔ ክርስቶስ ያስፈልገዋል ብሎ ክርስቶስን አስተዋወቀኝ ። እንድርያስ በኵረ ሐዋርያት ነው ። ከሁላችን ቀድሞ ክርስቶስን ያገኘ ነውና ልናከብረው ይገባል ። ክርስቶስን ካስተዋወቀኝ በኋላ ክርስቶስ ደግሞ ያለሁበት ድረስ በቀጣዩ ቀን መጣ ። ክርስቶስም ባገኘኝ ቀን ስሜን ለወጠልኝ ። ከአሮጌ ስሜ ጋር አሮጌው ታሪኬ የሄደ መሰለኝ ። ስምን ብቻ ሳይሆን ታሪክንም የሚለውጥ አምላክ ነው ። 

የቤተሰብ ስሜ ወልደ ዮና ነበረ ፣ የተጸውዖ ስሜ ደግሞ ስምዖን ነበረ ። አዲሱ ስሜ ግን በአራማይኩ ኬፋ በግሪኩ ጴጥሮስ ነው ። ትርጓሜውም ዓለት ማለት ነው ። ዓለትም ሁለት ዓይነት ነው ። አንደኛው የሚፍረከረክ ተሰባባሪ ሲሆን ሁለተኛው ግን የጸና ነው ። ጌታዬ የጸናውን ዓለት ስም ሰጠኝ ። ይህን ስሜን ሁለት ጊዜ አወጣልኝ ። እንድርያስ የክርስትና አባቴ ሆኖ ለአዲስ ኪዳን ስወለድ በመጀመሪያው የጥሪዬ ቀን ጴጥሮስ ተባልሁ ፤ ሁለተኛው ደግሞ ታላቅ ምስክርነትን በሰጠሁበት ቀን ቀን በፊልጶስ ቂሣርያ ጴጥሮስ ተባልሁ ። 

በዚህ ውስጥ ሁለት ነገሮች ትውስ ይሉኛል ። መጀመሪያው ተወዛዋዡ ሕይወቴና ሁለተኛው ደካማ ሰው ሳለሁ ዓለት መባሌ ነው ። ሕይወቴ እንደ ሸምበቆ ተወዛዋዥ ነበረ ። ሸምበቆ በጥቂት ነፋስ ይናወጣል ። እኔም በትንሽ ፈተና የምደነግጥ ሰው ነበር ። መውደድም መጥላትም ፣ መስጠትም መቀበልም ያስፈራኝ ነበር ። ሁሉም ነገር ፍርሃት የሆነበት ሰው ለእውነታ ሳይሆን ለይሉኝታ የምኖር ሰው ነበርሁ ። ሁሉን ላስደስት ስል ሁሉ የተከፋብኝ ፣ ጊዜ ሰጥቼ ለራሴ ምስኪንነት የማለቅስ ሰው ነበርኩኝ ። እንደ ቤተሰብ ትልቅ ልጅነቴ የወላጆቼ የወደፊት ማርጀት ያሳስበኝ ነበር ። ሳያረጁ አስረጅቼ ፣ ሳይታመሙ አልጋ ላይ አስተኝቼ ፣ ሳይሞቱ በአሳብ ገድዬ ፣ ታናናሾቼን ውጡ ግቡ ስል ይታየኝና ባልተጨበጠ ነገር እጨነቅ ለራሴም የምስኪንነት ልቅሶ አለቅስ ነበር ። ለመኖር አስፈላጊ ነው ሲሉኝ ሦስት አራት ዕቁብ የምጥል ፣ ለሞትም ያስፈልጋል ሲሉኝ ሦስትና አራት ዕድር የምገባ ሰባት ድስት ጥጄ ሁሉንም ማማሰል አቅቶኝ ሁሉም ያረረብኝ ሰው ነበርሁ ። ያለ ጊዜዬ የሸበትሁ ፣ ልቤ ስላልሞተ ብሮጥም አካሌ ግን የዛለብኝ ሰው ነበርሁ ። ስሜቴ ቶሎ ግንፍል የሚል ደስታና ሳቅ ወረፋ እያጡ አንድ መንገድ ላይ የሚገናኙብኝ ሰው ነበርሁ ። መከፋቴና መደሰቴ በፊቴ አደባባይ ቶሎ ይታይ ነበር ። ወይ ተምሬ የአይሁድ ረቢ አልሆንሁ ፣ ወይ ሠርቼ ባለጠጋ አልሆንሁ እያልሁ ሁሉ ያመለጠው ሰው ዓይነት ስሜት ይሰማኝ ነበር ። ለሁሉም ነገሮች የእኔ ድርሻ የሚጠበቅ ስለሚመስለኝ በሁሉ ጉዳይ ጣልቃ እገባና ለምን ገባሁ ብዬ መውጫው በር ሲጠፋኝ ራሴን ረግማለሁ ። ስሜቴ ሁሉን ቻይ ያደርገኝና የወደቁ ሰዎችን ሳይ እኔ ብቻዬን አነሣቸዋለሁ ብዬ እናገራለሁ ። ሙቀቴ ሲበርድ ኃይሌ ሲከዳኝ ሁሉን እርግፍ አድርጌ እንደ ሰረቀ ሰው እጠፋለሁ ። ከአሳቤ አፌ እየቀደመብኝ ምላሴን ብዙ ጊዜ ተቀይሜዋለሁ ። ይህንንማ ዕድሜ ያበርደዋል ሲሉኝ ዕድሜ አላበረደኝም ። እኔ ብቻ በማውቀው የሕይወት ውጥረት ውስጥ አልፍ ነበር ። 

እግዚአብሔር ያላሸከመኝን እየተሸከምሁ ፣ ጥሩ ሰላምታ ለሰጠኝም ሰው ዕዳ ያለብኝ እየመሰለኝ በፈቃዴ ባሪያ ካልሆንሁ እል ነበር ። ከዚህ የስሜት ስካርና መደናገር ለመውጣት ዘመናትን ያስቆጠረ ፍለጋ አድርጌ ነበር ። ያለ ባለቤቱ አይነድ እሳቱ ሁኖ ያለ ክርስቶስ የፈለግሁትን ነገር አላገኘሁም ። ሰላም ብቻዋን ሌጣ ሁና የቆመመች አይደለችም ። ሰላም አለቃ አላት ። እንደ ዝርፊያ ዕቃ መንገድ ላይ የወደቀች አይደለችም ። ክርስቶስም ሸምበቆውን ሕይወቴን ዓለት አደረገልኝ ። አሮጌው ሕይወቴ ምዕራፍ አገኘ ። ያለከልካይ ይፈስስ የነበረው እንባዬ ገደብ አገኘ ። መርገብገቤንና መቸኮሌን አይተው የተደገፉኝን መሸከም የማልችል የሸምበቆ ምርኩዝ ነበርሁ ፣ በብስጭትም የምናገረው እንደ ተሰበረ ሸምበቆ ተሰንጥሮ የሚወጋ ነበር ። ክርስቶስ ግን ታንኳውን ሳይሆን ቀዛፊውን አዳነው ። 

ገና ክርስቶስን የማስቸግር ነገር ግን ክርስቶስን ያገኘሁ ሰው ነኝ ። ጠባዬን ሳይመረምር ዓለት አለኝ ። የሆንኩትን ትቶ የምሆነውን ነገረኝ ። ጌታዬ ነገን አየልኝ ። ገና የመስቀል መንገዱን የምከለክል ፣ በአጉል አዛኝነት አትሙትብን ብዬ የዓለምን መዳን የምጋፋ ሳለሁ ፣ ገና አላውቀውም ብዬ በገረድ ፊት የምክደው ስሆን ይህን ሁሉ እያወቀ ጴጥሮስ አለኝ ። አውቆ የወደደኝ እርሱ ብቻ ነውና ክብር ምስጋና ለእርሱ ይሁን ።” 

ሐዋርያው ጴጥሮስ በታሪኩ ላይ የተጻፈውን የክርስቶስን ቀለም ሲያጎላ ሁሉም በተመሥጦ ጠፋ ። በዚህ ጊዜ ሐዋርያው ጴጥሮስ ዕረፍት እንድንወስድና የማታዋን ጀምበር እንድናደንቅ ወደ ምዕራብ አቅጣጫ ይዞን ጉዞ ጀመረ ። እኛም በደረጃችን እያወራን ጴጥሮስንና ጳውሎስን እንከተል ነበር ። “እንደ ጴጥሮስ አድርገኝ ፣ ጴጥሮስ ብለህ ስሜን ለውጥልኝ” የሚሉ ዝማሬዎችን እንዘምር ነበር ። 

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

እሑድ ሚያዝያ 17 ቀን 2013 ዓ.ም.

የዲያቆን አሸናፊ መኰንንን ትምህርቶችና ስብከቶች ለመከታተል ከስር የተቀመጡትን ማስፈንጠሪያዎች ይመልከቱ፡—

https://t.me/Nolawii

https://t.me/nolawisebketoch

https://www.facebook.com/ashenafi.mekonnen.357

YouTube player

http://ashenafimekonen.blogspot.com/

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ