የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ጴጥሮስን አገኘሁት /ክፍል 6/

 

እንኳን ለ2013 ዓ.ም. የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል በሰላምና በጤና አደረሳችሁ !

ቅዱስ ጴጥሮስ እየመገበ ያለው ሥጋችንንም ነፍሳችንንም ነው ። ሥጋችን መቀመጥ ብቻ ያደነዝዘዋል ፣ መሮጥ ብቻም ያዝለዋል ። የተመጠነ ዕረፍትና ሩጫ ግን ሕይወት ይሆነዋል ። በጎዳናው ተላውሰን ፣ በመንገዱ ተመላልሰን ወደ ቤት ተመለስን ። ሐዋርያው ጴጥሮስም ክርስቶስ በዕድሜ በዘመኑ የሠራውን ድንቅ ነገር ለመተረክ ተነሣ ። እንደ መጨረሻ ቃሉም እያስረገጠ ሲናገር እንደ አንቀጽና እንደ ሕግ እንዲያዝለት የፈለገ ይመስላል ። እኛም በትጋትና በጥንቃቄ እንሰማ ነበር ። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም በአንክሮ ሁኖ ያዳምጥ ነበር ። የሚወራው በሰው ታሪክ ላይ ድንቅ የሚያደርገው የመለኮት ግብር ነውና በታላቅ አክብሮት ያዳምጥ ነበር ። እርሱም በማመንና በማገልገል የሚቀድመውን ጴጥሮስን ያከብር ነበር ። ብዙ መልእክት ቢጽፍም ፣ ብዙ አገር ቢያስስም ፣ ብዙ አብያተ ክርስቲያናትን ቢተክልም አሁንም ራሱን ዝቅ አድርጎ ከጴጥሮስ ለመማር ቀርቧል ። ጸጋ የበዛለት ሰው ምልክቱ የሌላውን ጸጋ የሚያከብር መሆኑ ነው ። የእኔ ጸጋ አባ ጠቅል ነው ብሎ የሌላውን ጸጋ የሚጋፋ እርሱ ጸጋ የተለየው ነው ። ጸጋ በማመን ይሰጣል ። የልጅነት ስጦታ ነው ። ጸጋ በልመናና በትሕትና ይጨመራል ። ማንም ጥበብ ቢጎድለው መጸለይ ፣ ትንቢት መናገርን ወይም መስበክን በብርቱ ቢሻ ከእግዚአብሔር ይሰጠዋል ። ሐዋርያው ጳውሎስም እስከ ዕለተ ሞት ድረስ ትምህርት አያልቅም ብሎ የሚያምን ነበር ። የማይማር ሰው ሞቶ የሚኖር ነው ። የሕያውነት ምልክቱ ትምህርትን አለማቋረጥ ነው ። የምንኖረው ለማወቅ ነውና ። አለማወቅን ማወቅ ብዙ የማወቅ ልክ ነው ። ከሌላው የምማረው አለኝ ብሎ የሚያስብ ሰው እውቀቱ ፍቅርና ትሕትና ያለበት ነው ። ፍርሃት ከጥላቻ ይመነጫል ። ሌላውን ሰው ስንወደው ያጠቃኛል ብለን መፍራት እናቆማለን ። እርሱም ጣቶቹ ምላጩ ላይ ቢሆኑም መተኮስ ግን ያቅተዋል ። ፍቅር ክፉዎችን ልምሾ ያደርጋል ። እጅግ ደንዳኖችን ግን እንደ ክርስቶስ ሰቃዮች ሰቃልያነ ጻድቃን ያደርጋቸዋል ። 

በዚህ ጊዜ እማሆይ ፌበን የሚበላና የሚጠጣ ለማቅረብ የማርታን አገልግሎት ለማከናወን ፈለገች ። የማርታ አገልገሎት የተነቀፈ አይደለም ። ጌታን ለመጋበዝ ስታስብ የጌታ ግብዣ የሆነውንም ቃሉን ብትሰማ ኖሮ አገልግሎቷ ሥሙር ይሆን ነበር ። የመጀመሪያዎቹ ሰባት ዲያቆናት የተሾሙት ማዕድ ለማሳለፍ ነው ። ለአጋፋሪነት ተሹመው ቀዳሜ ሰማዕት በመሆን እስጢፋኖስ ፣ ወንጌላዊ በመሆንና ኢትዮጵያዊውን ጃንደረባ በማጥመቅ ፊልጶስ ትልቅ ሥራ ሠርተዋል ። መንፈሳውያን አገልጋዮች የቱንም ያህል ጸጋ ቢበዛላቸው ሰው መሆናቸው መረሳት የለበትም ። እንደ ሰው ይራባሉ ፣ ይጠማሉ ። ክርስቶስ እንኳ በለበሰው ሥጋ ተራበ ፣ ተጠማ ተብሎ ተነግሮለታል ። መንፈሳውያን አገልጋዮችን በሥጋቸው መንከባከብ ይገባል ። በነፍስ ለሚመግቡንን በሥጋ መመገብ ፣ ጸጋን ለሚያካፍሉን ደመወዝን መስጠት ወግ ነው ። ደግሞም የማያልፈውን ለሰጡን የሚያልፈውን ገንዘብ መስጠት ቁምነገር የለውም ። በእግዚአብሔር ፊት ባዶ እጅ መታየትን ኦሪት ነቅፋለች ። ምእመናን ወደ ቤተ እግዚአብሔር የሚያመጡት ለአገልጋዮች መተዳደሪያ ነውና ። አገር በግብር እንደሚቆም ፣ ቤተ እግዚአብሔርም በአሥራት ይቆማል ። ግብርን አለመክፈል አገርን በመካድ ወንጀል እንደሚያስጠይቅ አሥራትን አለመስጠትም እግዚአብሔር አልሰጠኝም ብሎ መካድና በረሀብ ምክንያት የእግዚአብሔር አገልጋዮች እንዲበተኑ ማድረግ ነው ። ራሱን ደመወዝ እየከፈለ በጎች የሚጠብቅ እረኛ የለም ፣ በራሱ መሣሪያም የሚዋጋ ወታደር የለም ። እንዲሁም ድንኳን እየሰፋ ጳውሎስ ቢያገለግልም ድንኳን እንዲሰፋ ያደረጉትና ስስታም የሆኑት ምእመናን ግን ሳይጠየቁ አይቀሩም ። ድንኳን በሚሰፋበት ሰዓት ብዙዎችን ያድን ነበርና ። ድንኳን በመስፋቱ ጳውሎስን ከማድነቅ የገዛ ስስታችንን መርገም ይገባል ። ወንዶች ለእግዚአብሔር አገልጋዮች አይራሩም ፣ እህል ውኃ ያስፈልጋቸዋል ብለው አያስቡም ። ሴቶች ግን የእናትነት አንጀት ፣ ረቂቁን የማየት ጸጋ አግኝተው ለአገልጋዮች ያስባሉ ። ብዙዎች ሳሉ ኤልያስን የመገበች የሰራፕታዋ መበለት ናት ። ኤልሳዕንም ያሰበችለት የሱነም ሴት ናት ። ጌታችንንም በገንዘባቸው ያገለገሉት ሴቶች ናቸው ። ሐኪሙ ወንጌላዊው ሉቃስ እንዲህ እያለ ያነሣቸዋል፡- “አሥራ ሁለቱም ከእርሱ ጋር ነበሩ ፥ ከክፉዎች መናፍስትና ከደዌም ተፈውሰው የነበሩ አንዳንድ ሴቶች ፤ እነርሱም ሰባት አጋንንት የወጡላት መግደላዊት የምትባል ማርያም ፥ የሄሮድስ አዛዥ የኩዛ ሚስት ዮሐናም ሶስናም ብዙዎች ሌሎችም ሆነው በገንዘባቸው ያገለግሉት ነበር ።” /ሉቃ. 8፡2-3።/ 

ሴቶች በቤተ ክርስቲያን ከነበራቸው አገልግሎት አንዱ በገንዘባቸው ማገልገል ነው ። ገንዘብ ማገልገያ ነው ። መገልገያ አይደለም ። ገንዘብ ቢኖረን ቁጭ ብለን ስለመብላት እናስባለን ። ገንዘብ ግን ሌላውን የምናበላበት እንጂ የምንበላበት አይደለም ። ብዙ አገልጋዮች ድንኳኑን ሲሰፉ ሰዓቱ እየነጎደባቸው ሙሉ ዘመናቸውን ሰጥተው እግዚአብሔርን ማገልገል አልቻሉም ። ከሥራ በሩጫ ወጥተው የሚያቀርቡልን ማዕድም የችኮላ በመሆኑ አቅም አይኖረውም ። ቃለ እግዚአብሔር ጽሞናና ጸሎት ይፈልጋልና ። ጽሞናና ጸሎት እንዲኖራቸውም እኛም እንድንባረክ አገልጋዮችን በበቂ መመገብ አለብን ። አገልጋዮቿን በቂ ደመወዝ የምትከፍል ቤተ ክርስቲያን ትጉህ አገልጋዮችን ፣ ከአገልግሎት ሰዓታቸው ውጭ የማይልከሰከሱ ሠራዊቶችን ፣ ስጡ ብለው የሚያስተምሩ ብቻ ሳይሆን መስጠት የሚችሉ ቸሮችን ፣ ተገቢውን ርቀትና ክብር ጠብቀው የሚኖሩ አባቶችን ታተርፋለች ። እማሆይ ፌበንም በማዕድ ለማገልገል የማርታን አርአያነት ለመፈጸም ስትከጅል አያት ነበር ። ማርታን ጌታ እንደ ነቀፋት የሚያስቡና የሚሰብኩ ሰዎችን አውቅ ነበርና ትክክል እንዳልሆኑ ገባኝ ። ጌታ በብዙ መጨነቋን እንጂ ተግባሯን  አልነቀፈውም ።

ሐዋርያው ጴጥሮስ ፈገግ አለና፡- “አሳብሽ መልካም ነው ፣ ይህን ስፈጽም ማዕዱን ታቀርቢያለሽ” አላት ። ደግሞም፡- “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የሣራን በረከት በደስታ መታዘዝን ፣ የርብቃን በረከት ምርቃት ማክበርን ፣ የራሔልን በረከት መወደድን ይስጥሽ” አላት ። እርስዋም ብድግ ብላ ወደ መሬት ለጥ ብላ ቡራኬውን ስትቀበል ከእጅዋ የበላውን አስታውሶ አገልግሎቷን እውቅና ሰጥቶት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ለመባረክ እጆቹን አነሣ ። ሐዋርያው ጳውሎስም ቢቀሙት ቅያሜ እንደሌለበት ቅኔ ከጴጥሮስ ቀምቶ ባረካት ። መመስገን የሚገባቸውን ሳናመሰግን ጊዜ እንዳያልፍብን መጠንቀቅ አለብን የሚል ስሜት ይታይበት ነበር ። በክፉዎች እያዘንን ደጎችን መመረቅ ለምን አልቻልንም  ያለ ይመስለኛል ። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ባረካት፡- “በሃና በረከት ተባረኪ ፣ የሰጠሽን ለእርሱ መስጠት ይሁንልሽ ። በአቢግያ በረከት ተባረኪ ፣ የነደደው እሳት ይብረድልሽ ። በድንግል ማርያም በረከት ተባረኪ ፣ የምሥጢር መዝገብ ያድርግሽ” አላት ። እርስዋም ከተሰበረ ልብ የሚወጣውን ልቅሶና የሲቃ ድምፅ እያሰማች አሜን ትል ነበርና ሁላችንም አለቀስን ። በብዙ ጀምራ ብቻዋን የቀረች ፣ ብዙ ሰጥታ ጥቂት እንኳ ያልተቀበለች ፣ ለሁሉ ኖራ ለእርስዋ ግን የኖረላት ያጣች ፣ ስለ ጥሪቷ የምትወደድ ስለ እርስዋ ግን የማትፈቀር ነበረችና አሁን በበረከተ አበው ተካሰች ። የመንፈሳውያን አባቶች ቡራኬ መልካም ምኞት ሳይሆን ከመለኮት ግምጃ ቤት በነጻ የሚሰፈር የእምነት ስጦታ ነው ። ምርቃት ይዞ የወጣ አያልቅበትም ፣ ገንዘብ ይዞ የወጣ ግን ያልቅበታል ። መንፈሳውያን አገልጋዮች ያዘኑባቸውና ያለቀሱባቸው ወዮላቸው ። 

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

እሑድ ሚያዝያ 24 ቀን 2013 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ