የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ጴጥሮስን አገኘሁት /ክፍል 7/

 

“ነገርን ነገር ያነሣዋል አሉ” በማለት ወደ አማቱ ታሪክ ለመግባት ፈለገ ። “የዘመድ ጨዋታ ቆራጣ ቆራጣ” እንዲሉ ንግግሩ ብዙ ርእሶችን የሚያነሣው የዘመድ ጨዋታ ይመስል ነበር ። የታሪክ ባለቤት ሕዝብ ሳይሆን የታሪክ ባለቤትና መሪ እግዚአብሔር ነው ። በታሪካችን ውስጥ ያለውን የእግዚአብሔርን ሥራ ማንሣት ትልቅ ስብከት ነው ። እግዚአብሔር በውድቀታችን ትንሣኤ ፣ በስንፍናችን ምሕረት እያደረገ ለዚህ እንዳበቃን መናገር በእውነት ትልቅ ስብከት ነው ። ስብከት ብዙ ሰዎች እንደሚያስቡት መንፈሳዊ ፖለቲካ ወይም ኩሸት የሞላበት ጮሌነት ሳይሆን የእግዚአብሔርን ታላቅነት የምንናገርበት መንፈሳዊ ሰገነት ነው ። ሰባኪም አፈ ንጉሥ ፣ አፈ ክርስቶስ ነው ። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ስለ አማቱ ለመተረክ ተነሣሣ ። አማቱ ማለትም የሚስቱ እናት በዕድሜ የገፋች ፣ በጤናም ያልበረታች ፣ ተፈጥሮ እየከዳት ፣ እምነት እያጸናት የምትኖር ናት ። ብዙ ልጆች በመውለዷ ደስ ሲላት ቆይቶ አሁን ግን ሁሉም ተድረው ሲወጡ ብቸኝነት የሚያዋራት ፣ ብስጭት ጦረኛ የሚያደርጋት ባልቴት ናት ። ሀብት ቢኖራትም ዋስትና ስለማይሰማት ለማውጣትና ራስዋን ለመርዳት አትፈልግም ። ሌሎች ቢያደርጉላትም ለምን ይህን ያህል ወጪ ይወጣል እያለች ስለ መድኃኒት መግዣ እንኳ የምትቆጭ ናት ። ልጆችዋም ሠራተኛ ቀጥረውላት በቤታቸው የሚያርፉ ስለሚመስላት ሠራተኛ ታባርራለች ። አጠገብዋ ያሉትን በመውቀስ የራቁት ልጆችዋ እንዲቀርቧት ትፈልጋለች ። ከመኖር የተነሣ ከብዙ ሰው ጋር ተቀያይማለችና ስለ እገሌ መልካም ሲነገር የምታውቀውን ክፉ ነገር ታወራለች ። 

ዝቅ ብላ ለልጆች ብታዝንም በእርስዋ ዕድሜ ላሉ ግን ምንም አታዝንም  ። የተለዩአትን ሴቶች ጓደኞችዋን በማሰብ ሴትን በሙሉ የመጥላት አዝማሚያ ይታይባታል ። ዓመት ሙሉ የቆጠበችውን ለበዓል ብላ ትዘረግፈዋለች ። የእገሌ ልጆች እዚህ ደረሱ ፣ ለቤተሰባቸው ይህን ያህል ብር አፈሰሱ በማለት ልጆችዋ ከቻሉ ነግደው ፣ ካልቻሉ ከአገር ወጥተው ሀብት እንዲያመጡ መንገድ ትመራለች ። ከልጆቼ መለየት አልችልም ትልና ካላገባችሁ ብላ ደግሞ ታውካለች ። ካገቡ በኋላ ደግሞ እኔን ረሱኝ በማለት ለማፋታት ትሞክራለች ። የልጅ ልጅዋን መገኛ ትጠላና የልጅ ልጅዋን ትወዳለች ። ተለዋዋጭ ጠባይ ይታይባታል ። ወንዶች በጦር ሜዳ ወይም የሕይወትን ፈተና መቋቋም ባለመቻል ከሴቶች ቀድመው ይሞታሉና አማችይቱ ብቻዋን ትቀራለች ። ባልዋ ያለ እንደሆነ ልጆችዋ እስኪያድጉ ታግሣ ልጆቹ ካደጉ በኋላ የተዳሩ ልጆችዋ ቤት በመሄድ በስልት ትለየዋለች ። ለምን አባባ ጋ አትሄጅም የተባለች እንደሆነ እስከ ዛሬ የተቃጠልሁት ለእናንተ ብዬ ነው ትላለች ። ባልዋ የሞተ እንደሆነ እርሱ ቢሞት በልጅ እጅ ወደቅሁ ትላለች ። ብቻ ዕድሜና ፈተናው ብዙ ስለሆነ ይህች አማችይቱ ጠባይዋ ቢለዋወጥ ማንም አይፈርድባትም ። ዕድሜ እንደ ፈለገው እንዳያደርገን ክርስቶስ በፍቅሩ ያበጃጀን ! 

አማችይቱ የልጅዋን ባል የምታይበት መነጽር ብዙ ነው ። ኃይለኛ ከሆነ እኔም ችዬ የኖርሁት ይህን ነው በማለት በልብዋ በሴት ልጅዋ ላይ ትስቃለች ። ሴት ልጅዋ ኃይለኛ እንደሆነች ተመልሳ እንዳትመጣባት ጥቁሩን አንጥታ ፣ እሬቱን አጣፍጣ ቻዪ ትላታለች ። ባለመቻል እርስዋ የደረሰባትን በማሰብም ትዳር ሲፈርስ ብዙ ነገር እንደሚፈርስ በመናገር ታጸናታለች ። የልጅዋ ባል በጣም ደግ የሆነ እንደሆነ እንደ ልጅዋ ታየዋለች ። ቢያጠፋም በደሉ አይታያትም ። ሞኝ የሆነ እንደሆነ ትንቀዋለች ። ባለሥልጣን የሆነ እንደሆነ “ወፍራም ዱላ ባይመቱበት ያስፈራሩበት” ብላ ትታገሠዋለች ። ባለጠጋ የሆነ እንደሆነ “ከድሀ እከክ እንጂ ምን ይገኛል ? ምንም ቢሆን ሀብታም ይሻላል ፤ ገንዘቡ ይተርፋል” ብላ ልጅዋን ታረጋጋለች ። የልጅዋ ባል ውለታ የዋለላት እንደሆነ ክፉውን ማሰብ ትቸገርና በልጅዋ የጭንቅ ኑሮ ስሜት የለሽ ትሆናለች ። አማችይቱ የልጅዋ ባል ወታደር ከሆነ ቤቷን ለቅቃ አብራ ትቀመጣለች ። ፊት የሚነሣ ከሆነም ወይ ትርቃለች አሊያም በእልህ ዕድሜው እንዲያጥር አድርጋ በቤቱ ዕረፍት ትነሣዋለች ። ሲብስም ጠንቋይ እያማከረች ባል የሚያዘው በዚህ ነው በማለት ልጅዋን ታስታለች ። ለአንዱም ልጅ የወተት ሳታመጣ ውለዱ ትላለች ። ከዚያ ያለፈ ለመምከር እርስዋም አላገኘችምና አይጠበቅባትም ። ቢሆንም አማችም በራስዋ ቤት እንደ ጠባይዋ ብትኖር የተሻለ ነው ። በአንድ ቤት ውስጥ የሚወዱትና የሚሰጉት ካለ ከስጋቱ ይልቅ ፍቅሩ እየተጎዳ ይመጣል ። 

ባል የሆነ እንደሆነ ሚስቱን ከቤተሰቦቹ አርቆ ቢያኖር መልካም ነው ። የሚስት ቤተሰብ ጋ የሚገባ ወንድ ምርኮኛ እንጂ ባል ሊሆን አይችልም ። አማቾቹ በገዙለት ንብረት የሚሞላቀቅ ባልም የደለበ ባሪያ እንጂ ነጻ ሰው አይደለም ። ራስን መቻል ያስከብራል ። እውነተኛ ነጻነት ያለው ራስን ችሎ በመቆም ነው ። 

አማችይቱ ከበሽታ ፣ ከሥነ ልቡና ጉዳት ፣ ከከረመው ጠባይዋ ፣ ከብቸኝነት ፣ ያልተሳኩ ነገሮችን ከመቍጠር ፣ ተረስቻለሁ ከሚል ፍርሃት በመነሣት አንዳንድ ጊዜ ልጅዋ የዘነጋት ሲመስላት ትዳሩን ልታጣጥልበት ትነሣለች ፤ ትዳሩን ገሸሽ ማለት ሲጀምር ደግሞ እርስዋ ላይ መጥቶ እንዳይወድቅ በመስጋት የሚስቱ ደጋፊ ትሆናለች ። ዕድሜው ፣ የዚህ ዓለም ውጣ ውረዱ ይህን ጠባይ ሊያመጣባት ይችላል ። ሴት ልጅዋ ከሆነች የሴት ልጅዋን ባል እንደ ልጅዋ ታያለች ። እርሱም ወላጆቹን ክዶ አማቾቹን አባዬና እማዬ ስለሚል ይስማማል ። ሴት ልጅዋም ባልዋን አሳምና አሊያም ደብቃ ቤተሰቧን ትረዳለችና ስላልተረሳች አማችይቱ ዝም ትላለች ። ባል አንዳንድ ጊዜ አማቹ መጥተው ከሰነበቱበት ፣ አመመኝ እያሉ ሚስቱን ደጋግመው ከጠሩበት ፣ የሚስቱና የእናቲቱ ፍቅር ከጸናበት ማጉረምረም ይጀምራል ። አማችይቱ ልጅዋ ወንዱ ከሆነ የተጎዳ እየመሰላት ምግብ ሠርታ ትጠራዋለች ። አሊያም ሚስቱን በባል አያያዝ ትወቅሳታለች ። ሲያድግ በልቶት የማያውቀውን ምግብ እየጠቀሰች በጥሩ እንዳደገ ትነግራታለች ። ሴት ልጅ ዕቃ ፣ ወንድ ልጅ ምግብ መውደዳቸው የተለመደ ነውና እናቱ ስለ ምግብ ዓይነት ትናገራለች ። አንድን ወንድ እናትና ሚስት እኩል መውደዳቸው ሰላም እያሳጣ ይመጣል ። እርሱም ወዲህ እናቱ መገኛው ፣ ወዲህ ሚስቱ አካሉ ይሆኑበትና በመካከል ተሰንጥቆ ይኖራል ። 

ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ስለ አማቱ ለመናገር ርእስ በሰጠ ጊዜ ይህ ሁሉ ትዝ አለኝና በአሳብ ጭልጥ አልኩኝ ። ከአሳቤ ያነቃኝ፡- “ጌታዬን ክርስቶስን መከተል ከጀመርሁ በኋላ ድሮ የነበረኝ ታንኳ ፣ መረብና ቤት አሁን ባይኖረኝም ደስተኛ ነበርሁ ። ያ ሁሉ እያለኝ ያላገኘሁትን ደስታ ክርስቶስ ሰጠኝ ። የዓሣ ደንበኞቼ ፣ የሥራ ጓዶቼ ፣ የሰፈር ጎረቤቶቼ እንዳበድሁ ማውራት ጀምረዋል ። እኔ ግን አብጄ የነበርሁት ያኔ ነበር ። አብጄ እየሠራሁና እየኖርሁ መሆኑን አያውቁም ነበር ። ልክ እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ነው ። እርሱ ቤተ ክርስቲያንን ሲያሳድድ ፣ እስጢፋኖስን ሲያስገድል ፣ አማኞችን ከየቤቱ እየለቀመ ወኅኒ ሲጥል አማኝና ጤነኛ ይባል ነበረ ፤ ወንጌል መስበክና ሰዎችን ማትረፍ ሲጀምር ከሀዲና እብድ ተባለ ። ጳውሎስ የፊት ኖረውን ሲኰንን ጠላቶቹ ደግሞ የአሁን ኑሮውን ይኰንናሉ ። ሰው አላዋቂ ነው ። ብርሃኑን ብርሃን ፣ ጨለማውን ጨለማ ለማለት አልታደለም ። 

አማቼም የመንደሩን ወሬ ሰምታ ፣ የሚስቴን ግራ መጋባት ተረድታ ፣ የክርስቶስን አለመወደድ አገናዝባ ፣ የወደፊት ኑሮን ከግምት ውስጥ አስገብታ ከሚስቴ ጋር ኑሮ ጀምራለች ። እኔም ሁሉን ረስቼ ቢሆንም ክርስቶስ ግን ለቤቴ ያስብ ነበር ። አማቼም በብስጭት እንዳትሞት ፣ ሚስቴም በሰዎች ግፊትና በራስዋም ትካዜ እንዳትረበሽ ፣ በስተርጅና የመረጥሁት ምርጫም ትልቅ መሆኑን ለማሳወቅ ክርስቶስ ወደ ቤቴ አመራ ። ወደ ቤቴ የሚወስደውን መንገድ ስንይዝ ደስተኛ አልነበርሁም ። ዳግም ወደዚያ ጭንቀቴ የምመለስ መስሎኝ ነበር ። የጭንቀቴ ምክንያት የእኔ አለመርካት እንጂ ሌላ አልነበረም ። አዲሱን ደስታዬን በነፋስ ላይ እንደ ተለኮሰ ሻማ እጠነቀቅለት ነበር ። ጭንቀትን ያየ በሰላም ላይ አይቀልድም ። ጌታዬ ግን አንዱን ሲያረካ አንዱን የሚያሳዝን አይደለምና ሚስቴን ሊያረጋጋ ፣ አማቼንም ጸጥ ሊያደርግ ወደ ቤቴ አመራ ። ወደ ቤት ቀድሞ ገባ ። ቀድሞም እቤቴን የማስተዳድረው እኔ እየመሰለኝ እጨነቅ ነበር ። የቤቱ ራስ ለካ ክርስቶስ ነበረ ። እኔ ስቀድም ሁከት እየቀደመ ከትዳሬ ጋር እጋጭ ነበር ። አሁን ግን ክርስቶስ ቢቀድም ቤቴ ሰላም ሆነ ። እርሱ ቀዳሚ ሆኖ ስለገባ እርቅ ሆነ ። አማቼም በአልጋው ላይ ሁና ትንጠረጠር ነበር ። ብርቱ ንዳድም ያሰቃያት ነበር ። ወትሮም ብስጩ ነበረችና በሽታው የበለጠ ቍጠኛ አድርጓታል ። ቍጣ የሚያደክመው የተቆጣውን ሰውዬ እንጂ የተቆጡትን ሰው አይደለምና በራስዋ እሳት እየነደደች ነበር ። በሽታ ጠባይን ያመጣል ፣ ጠባይም በሽታን ይወልዳል ። ከዚህ በፊት በአካል ያላያት ፣ መታመሟንም ሰው ያልነገረው ቢሆንም ጌታዬ ግን ወደ በሽተኛይቱ አልጋ ሄደና እጁን ዘረጋላት ። በእጁ መዘርጋት ንዳዱ በረደ ፣ እሳቱ ቀዘቀዘ ፣ የልቧ ሁከትም ጸጥ አለ ። ጌታዬን አሁን ራስዋ አይታዋለችና አንተ እርሱን ተከተል እኔ ቤትህን እጠብቃለሁ ፣ ልጄንም አጸናለሁ አለችኝ ። እኔም ከደስታዬ እየሰረቀ የሚወስደኝ አሳብ ነበርና ልቤ አረፈ ። ከዚህ በኋላ ርቀን ብንሄድም የማልሰጋ ሆነ ። አማቼም የመዳን ምልክት የሆነውን ተነሥታ አገለገለችን ። አንዳንዱ በተአምራት ሌላውም በትምህርት ያምናሉ ። በተአምራት ያመኑ መማር ሲያስፈልጋቸው ፣ በትምህርት ያመኑ ግን ተአምራት ላያስፈልጋቸው ይችላል ። በርግጥ የመሸው ሌሊት ከመንጋቱ የበለጠ ተአምራት ከወዴት ይገኛል ?

ሐዋርያው ጴጥሮስ ይህን ተናግሮ ሲላስን ጠራና ከፌበን ጋር ሆናችሁ በሉ ምግቡን አቅርቡ አለ ። እነ ሲላስም ወደ ታዘዙት ነገር በቶሎ አመሩ ። እኔም ክርስቶስ ከእኛ በላይ ለቤታችን ይጨነቃል አልኩኝ ። ኋላም የጴጥሮስን ሚስት ከቅዱሳን ሴቶች ጋር እንደ ደመረ ፣ ቤተ ክርስቲያንም በየስፍራው ጴጥሮስን ስትልክ ለሚስቱም በጀትና የጉዞ እውቅና እንደ ሰጠች አሰብኩ ። ቤተ ክርስቲያን ሚስቶችን በበቂ በጀት ብትይዝ አገልጋዮች የቤታቸው ስቃይ ይቀንስ ነበር ። የትዳር ሁከት መነሻው አንዱ የገቢ ማነስ ነው ። 

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ሰኞ ግንቦት 2 ቀን 2013 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ