የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ጴጥሮስን አገኘሁት /ክፍል 8/

 

ቅዱስ ጴጥሮስ ተነሣና፡- “ይህን ማዕድ ያዘጋጁ እጆች ይባረኩ ፣ ይህ ገበታ የወጣበት ጓዳ አይጕደል ፣ ይህን ሰደቃ ያለ ስስት የሰጡ ከማያልቀው ቸርነት ይጥገቡ” ብሎ መረቀ ። ሰው ይመረቃል ፣ እግዚአብሔር ይመሰገናልና ሁሉን ያዘጋጀውን እግዚአብሔር በምስጋና አከበረ ። ያዘገየውንም የጌታችንን መዋዕለ ስብከት ትረካ ቀጠለ ። በማዕበል ውስጥ ክርስቶስ ሰላም መሆኑን ለመተረክ ሲል በኃይል ተነፈሰ ። እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ እገሌ ከእኔ ጋር አልሆነም የሚል ጭንቀት እንደማይኖር የሕይወት ምስክርነቱን ሲሰጥ በዓይኖቹ እንባ አቀረረ ። 

“ያን ቀን አስታውሰዋለሁ ። ጌታችን ሌሎችን ሲናገር እኔ ጥሪዬንና ውሳኔዬን እመረምር ነበር ። ጌታችን ብዙ ሰው ሲከበው ለመናገር የሚፈልግ ፣ ብዙ ጭብጨባ ሲመጣ ግለቱን የሚጨምር ፣ እናንግሥህ ሲሉት የሚመቻች አልነበረም ። እርሱ በሰው ውስጥ ያለውን የሚያውቅ ፣ ስለ ሰውም እንዲነግሩት የማይፈልግ ነው ። ታዲያ ብዙ ሕዝብ ሲያይ ወደ ደቀ መዛሙርቱ ዘወር ይላል ። የእኛ ሕፃን ልብ ደግሞ ብዙ ሕዝብ ካስከተልን ጻፎችና ፈሪሳውያን ይፈሩናል ። ሮማውያንንም በጦር ኃይል ጥለን ታሪክ እንሠራለን የሚል ነበር ። እኛ ወደ ሕዝብ ስንሄድ ጌታ ግን ወደ አሥራ ሁለታችን ይገሰግስ ነበር ። ነገን ያየው በሕዝቡ ሳይሆን በደቀ መዛሙርቱ ነበር ። ከአሥር ሺህዎች ይልቅ በአሥራ ሁለት ደቀ መዛሙርት ተስፋ ያደርግ ነበር ። ዘር ጥቂት ፣ እርሾም ጭላጭ በመሆናቸው አይናቁም ። ታዲያ ጌታችን ሕዝቡ ሲከበው በባሕር ላይ በመሳፈር ፣ ወደ ማዶም በመሻገር ያመልጣቸው ነበር ። የሕዝብ ማዕበልን ከያዙ ሰማይና ምድርን የሚያስገብሩ የሚመስላቸው አያሌ ናቸው ። ሕዝብ ግን ሸኝቶ የሚመለስ ፣ ሞቅታ ሲበርድ የሚቀዘቅዝ ፣ ለዘላለምም የሚረሳ ነው ። ጌታችን በዚህ ሰዓት የተሻለ ኑሮን ፈልገው እርሱን መከተል ለሚፈልጉ ፣ ዳግመኛም በተከፈለ ልብ ደቀ መዛሙርቱ ለመሆን ለሚሹ መልስ ሰጠ ። ክርስቶስን ስንከተል ትርፋችንን ሳይሆን ኪሣራችንን መተመን ያስፈልገናል ። ወንጌሉ የሥጋዊ ትርፍ መገኛ ቢሆን ኖሮ ሁሉም ሰው ይቀበለው ነበር ። የተቀበለው ግን የኑሮውን ለውጥ እንጂ ሕይወቱ የሆነውን አምላክ አይደለም ። ከመንደሩም ከሰው ልብም ለመሰደድ ያልወሰኑ ደቀ መዛሙርቱ መሆን አይችሉም ። የእኔም ልብ መረቡንም ወንጌሉንም ፣ ታንኳውንም መስቀሉንም ፣ ክርስቶስንም ዓለሙንም በአንድነት ይዞ መጓዝ ይቻል ነበር ይለኝ ነበር ። ጌታ ግን፡- “ለቀበሮዎች ጉድጓድ ለሰማይም ወፎች መሳፈሪያ አላቸው፥ ለሰው ልጅ ግን ራሱን የሚያስጠጋበት የለውም አለው” ብሎ ሲናገር ከውስጤ እኔነት ተገርዞ ወደቀ ። /ማቴ. 8፡20/። አባቱን ቀብሮ ጌታን ለመከተል የጊዜ ጥያቄ ያነሣውን ሰው ተከተለኝ ሙታናቸውን እንዲቀብሩ ሙታንን ተዋቸው አለው ። ጻፊው ሲጠይቀው እንዲከተለው አልፈቀደም ። ይህን ሰው ግን ተከተለኝ አለው ። ልቡ አለመቍረጡ ፣ ከደግና ከደግ ማወዳደሩ እንጂ ክርስቶስን የጠላ አልነበረም ። ጻፊው ግን ክርስቶስን የምቾቱ አገልጋይ አድርጎት ነበር ። እርሱ ባይሄድም አባቱ ሳይቀበር አይቀርም ። እርሱ ደቀ መዝሙር ባይሆን ግን የማይሠራ ሥራ አለ ። በማያስፈልግበት ስፍራ ትርፍ ፣ በሚያስፈልግበት ደግሞ ዋና መሆኑን ነገረው ። እኔ ትዳሬን እነ ዮሐንስ አባታቸውን ትተው ሲከተሉ ክርስትና ዋጋ እንደሚያስከፍል እየነገረን ነበር ። የምድር ቤታችንን ክፍት አድርገን ወጣን የሰማዩን ክፍት አድርጎ ጠበቀን ። ከአባት ይልቅም አባት መሆኑን ነገረን ። 

ወደ ታንኳ ስወጣ የሚዋልለው ልቤ ፣ ለጥሪው የተከፈለው ዋጋ ድንገተኛ ሳይሆን ጠባዩ መሆኑን ተረድቼ ነበር ። ከሕዝቡ ሸሽተንም መሄዳችን ካገለገልን በኋላ ገለል ብለን ከሚመስሉን አገልጋዮችና ከጌታችን ጋር ማሳለፍ እንዳለብን እያስተማረን ነበር ። ከሕዝቡ ገለል ባልን ጊዜ ሁሉ ከጌታና ከደቀ መዛሙርት ገለል እንድንል አልተፈቀደልንም ። ወደ ታንኳ ቀድሞ የገባው እርሱ ነው ። እርሱ ፊታውራሪያችን ሲሆን ደስ ይለን ነበር ። እርሱ በቀደመበት ድል እንዳለ እናውቃለን ። ደግሞም እርሱ ወደ ታንኳ ቀድሞን ሲገባ ከውዳሴ ከንቱ እየሸሸን ብቻ ሳይሆን በባሕሩ ላይም አስተናጋጃችን ፣ የታንኳውም ካፒቴን ፣ የማዕበሉም አዛዥ መሆኑን ተረዳን ። የብዙ ዘመን ልምድ ፣ ጥቂት እውቀትም ፣ የኖረ ድፍረትም የማይረዳበት ጊዜ ይመጣል  ። ልምድ ሁሉ ብርክ ፣ እውቀት ሁሉ እጦት ፣ ድፍረት ሁሉ ፍርሃት የሚሆንበት ጊዜ አለ ። በታንኳ ከተሳፈርን በኋላ ታላቅ ማዕበል ገጠመን ። ከሕዝብና ከውዳሴ ከንቱ ማዕበል አምልጠን የተፈጥሮ ማዕበል ገጠመን ። የሕዝብ ማዕበል የስሜት ስካር ፣ የውዳሴ ከንቱ ማዕበል የትዕቢትን እብጠት ያመጣል ። እነዚህ ነፍስን ሲጎዱ የተፈጥሮ ማዕበል ግን የሚጎዳው ሥጋን ነው ። ማዕበሉ እጅግ አናወጠን ። ታንኳዋን ከላይ ወደ ታች እያነሣ ይጥላታል ። ለመርከብ የሚያይል ማዕበል ለታንኳ ከወለሉ የሚቀብራት ነው ። እንዴት እንደሚያደርጋት የተጨነቀ ይመስላል ። ይወዘውዛታል ፣ አቅጣጫ ያስታታል ፣ እያነሣ ያፈርጣታል ። የባሕሩን ውኃ እየሰፈረ ይሞላባታል ። ባሕሩ በራሱ ስለ ታወከ እኛን መሸከም አቃተው ። ማዕበሉም መንገድ እየዘጋ ማለፍ ከለከለን ። ለመድረስም ለመመለስም ምርጫ አሳጣን ። ድምፁ ልባችንን ሲያውክ ፣ ጉርምስናው ደግሞ ሥጋችንን ቀጠቀጠው ። ታንኳዋ በባሕር ልትጠመቅ ትንሽ ቀራት ። ልብሶቻችን ሁሉ በሰበሱ ። ጥብርያዶስን ብናውቀውም ዛሬ ግን ፈራነው ። በዚህ ሁሉ ማዕበል ውስጥ ጌታችን ተኝቶ ነበር ። በአስጨናቂ ሁከት ውስጥ ሳለን እርሱ ግን በአስደናቂ ሰላም ውስጥ ነበረ ። ልምድ እንደሚከዳ ፣ እምነት ግን እንደሚጸና ተረዳን ። 

ከአንዱ ስንሸሽ ሌላው ይገጥመናል ። ሕይወት ብዙ ዓይነት ድብብቆሽ ያለባት የጨዋታ ሜዳ ናት ። ነፍስን ለማትረፍ ስንነሣ ሥጋን የሚቀጭ ሰይፍ ይገጥመናል ። እሳቱን ስንሸሽ ነፋሱ መንገድ ይዘጋብናል ። ድንጋዮን ስንታገሥ ውኃው ይበረታብናል ። የመንቀዥቀዥ ዘመን ልጅነት ነው ተብሎ ይቅርታ ያገኛል ። ነፋስ በእሳት ተተክቶ የወጣትነት ፍም ከሁሉ ያጣላል ። እሳቱን አለፍኩት ሲባል ሁሉም ነገር ትርጉም የሚያጣበት ጎልማሳነት ይመጣል ። እርሱን ሲያልፉት የመሬት ዘመን ይመጣና ሁሉም ልርገጥህ ይላል ፣ መቃብርም ፊት ለፊት ይታያል ። መራራውን ያለ ክርስቶስ ማጣጣም ፣ ውስጣዊውን ቍጣ ያለ ኢየሱስ ማብረድ እንዴት ይቻላል  ሥጋን ላትርፍህ ሲሉት ነፍስ ይጎዳል ፣ ሚዛንን ጠብቆ ለመትረፍ መንፈሳዊ እውቀት ያስፈልጋል ። የውስጡ ፈተና ሲያበቃ የደጁ ማዕበል ይመጣል ። 

የመንገድ ላይ ማዕበል የሚገጥመው ጉዞ የጀመሩትን ነው ። ማዕበል ከገጠማችሁ ቢያንስ ጉዞ ጀምራችኋል ማለት ነው ። ማዕበል ያለው ወደቡ ላይ ሳይሆን መሐል ባሕር ላይ ነው ። ማዕበል መንገድ መጋመሱን ይነግረናል ። የውስጡ ፈተና የውጩ መከራ ፣ የውስጡ የኃጢአት ትግል ፣ የውጩ የጅራፍ ቍጥር ነው ። ከታች ወደ ላይ ያነሣን ዓለም እንደገና ከላይ ወደ ታች ያፈርጠናል ። ያከበሩን ሁሉ አዋርደው እስኪፈጽሙን ወረፋው ይረዝምብናል ። የሚመጣው መከራ በእኛ አቅም የሚቻል ሳይሆን ለትልልቆች የሚሆን ነው ። ሰይጣን ግን ታናሽነታችንን አልናቀውምና ትልቅ ፈተና ያመጣብናል ። በድህነት አቅማችን የባለጠጋ መከራ ይመጣብናል ። አበቃልኝ ስንል ህልውና እየቀጠለ ይመጣል ። ከመጨረሻው እያስጀመረ እግዚአብሔር ያኖረናል ። መወዝወዙ ያደክመናል ። በቅጡ ኀዘናችንን እንዳንወጣ አቍሳዮችና የአጽናኝ አስለቃሾች ያደክሙናል ። ለማልቀስም ጊዜ ፣ ቦታና ምቾት እናጣለን ። ማልቀስም ለካ ሲፈቀድልን ነው ። የያዝኩት ክርስትና ትክክል አይደለም ወይ ? ብለን በልባችን እስክንስት እንፈተናለን  ። የድሮውንና የአሁኑን ኑሮ እናነጻጽራለን ። ትንሽ ትልቁ አፉን ሲያላቅቅብን ፣ የስድብ መማሪያ ስንሆን ግራ እንጋባለን ። ያስተማርናቸው ከሳሾቻችን ፣ ያጎረስናቸው ሰቃዮቻችን ሆነው ይመጣሉ ። ዓለማዊነት ከመከራ የተነሣ በቤተ ክርስቲያን ይሞላል ። ያንን የሚያጠራ መንፈሳዊ ሰው እንዳይናገር ስም ይሰጠዋል ። ቢናገርም ጆሮ ዘግተው ይሰሙታል ። ወደ ዓለም ኮብልለን ትንሽ ዐርፈን ለመምጣት ብናስብም ዓለሙ በራሱ ማዕበል እየተጨነቀ ነውና መሄጃ እናጣለን ። በእግሩ እሾህ የተሰካበት የሚረግጠው መሬት ቢያገኝም መርገጥ ግን አይችልም ። ለመመለስ ቍጭቱ ፣ ለመድረስም አቅሙ እየፈተነን መሐል ባሕር ላይ እንዋትታለን ። የባሕር መንገድ ወረድ ብለው አያርፉበትም ። የዛሬው ክፉ ቀን ያለፍነውን ክፉ ቀን ያስረሳናል ። ልምድና እውቀትም በፈተና ሰዓት ይሰወራል ። ራሳችንና ዓለሙ ሲያስፈራን ፣ በጽናት ያለው ጌታ ግን የልብ ድፍረት ይሆነናል ።” 

ሐዋርያው ጴጥሮስ እየተረከና ወደ ሕይወታችን እያዛመደ ነውና ሁሉም ሰው መነካት ጀመረ ። እርሱም በዓይኑ ከበሩ አጠገብ ጀምሮ እስከ ጓዳ ድረስ ያሉትን ገርመም አድርጎ አየና ንግግሩን ቀጠለ ። 

“በዚህ ሁሉ ማዕበል ውስጥ ጌታ ተኝቶ ነበር ። ፍጹም ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ ተኝቶ ነበር ። በዚህ ጊዜ ሁላችንም ወደ እርሱ ቀርበን ጌታ ሆይ ፣ አድነን ጠፋን እያልን አስነሣነው ። እርሱ ግን ማዕበሉን ትቶ የእኛን አለማመን ገሠጸ ። ለካ ማዕበሉ እምነታችንን የምንለማመድበት አጋጣሚ ነበር ። እናንተ እምነት የጎደላችሁ አለን ። እምነት የሌላችሁ አላለንም ። መፍራታችን እምነት መጕደሉ ፣ አድነን ማለታችን እምነት መኖሩን ያመለክታል ። ጌታ ጨርሶ አይናገርም ። እምነት የጎደላችሁ በማለት አጽናናን ። ማዕበሉ እያገሣ ቢሆንም ጌታችን ግን በእርጋታ የልባችንን ማዕበል ይገሥጽ ነበር ። ከውጭው ማዕበል የውስጥ ማዕበል ይከፋልና ። ከሀሉ በላይ አለማመን ከባድ ነው ። እናንተ እምነት የጎደላችሁ ስለ ምን ትፈራላችሁ ? አለ ። የሚያስፈራው የማያስፈራን በእምነት ብቻ ስንሆን ነው ። እግዚአብሔር የሚያስፈራንን ያስፈራዋልና ። ጌታችን ነፋሱንና ባሕሩን ገሠጸ ። ነፋሱን ቁም ፣ ባሕርን ጽኚ አላቸው ። እነርሱም ጸጥ አሉ ። ጌታ ሲናገር ተፈጥሮም ያደምጠዋል ። ነፋሱንና ማዕበሉን ትልቅ አድርገን ነበርና ለካ ትልቁ ጌታችን ነው ። አሁን መደነቃችንን ለእርሱ አቀረብንለት ። የሰማነውን በልቡናችን ያሳድርብን ።”

ሐዋርያው ፈጥኖ ቁጭ አለ ። እኛም ብንደሰትም አረጋዊውን አባት ያደከምነው መስሎ ተሰማን ። የአባቶች ቆሞ ማገልገል የክርስቶስን ታላቅ መጋቢነት ማሳያ ነው ። ቆሞ እያገለገለን ያለው የማናየው ክርስቶስም ነው ። 

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

እሑድ ግንቦት 8 ቀን 2013 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ