የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ጴጥሮስን አገኘሁት /ክፍል3/

 

ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ እግዚአብሔር ሥራውን ብቻ ሳይሆን ራሱንም እንደሠራው ለመናገር የቸኮለ ይመስላል ። እግዚአብሔር ሥራችንን እየሠራ ቀጥሎ እኛን ይሠራል ። ሌላ ጊዜም እኛን ሠርቶ ሥራችንን ይሠራል ። እግዚአብሔር ጴጥሮስን ከብኩንነትና ሁሉን ላስደስት ባይነት አውጥቶ እንደ ቃሉ ሠራው ። እርሱን ለዓለም ብርሃን ሊያደርገው ነውና ቤቱን ደግሞ ሠራለት ። ለቤቱ የማይበቃውን ከርታታ ለዓለም እንዲበቃ አደረገው ። እግዚአብሔር በማብዛት ሳይሆን በመባረክ አንዱን ሺህ አዳኝ ያደርገዋል ። ዓለም ሺህ ገዳይን ስታወድስ እኛ ደግሞ ሺህ ታዳጊዎችን እናዘክራለን ። ሌሎች ተአምራቶች ወደ እውነተኛው የነፍስ ፈውስ የሚያደርሱ ምልክቶች ናቸው ። እውነተኛው ፈውስ የነፍስ መዳን ነው ። ምልክቶችን እንደ ጅማሬ እንጂ እንደ ፍጻሜ መውሰድ እግዚአብሔር ካሰበልን አሳብ እንዳንደርስ ያደርጋል ። እርሱ ሰማይን እያየልን እኛ ምድር መቅረታችን ተገቢ አይደለም ። ሰው በማይቆይበት ዓለም በሥጋ በልጥጎ ወደሚኖርበት ዓለም ግን ባዶ እጁን ቢሄድ ምን ጥቅም አለው ? ዓለምን ከመግዛት ነፍስን ማትረፍ ይበልጣል ። ከሥጋ ፈውስ የነፍስ ድኅነት ይበልጣል ። ሰዎች ልባችንን የሚሰብሩት በሥጋ በሽታቸው ሳይሆን የነፍስ በሽታ በሆነው ክፋታቸው ነው ። 

በቤቱ ውስጥ የነበሩት ሐዋርያው ጳውሎስና ሌሎቹም ቅዱሳን ቁጭ ብሎ እንዲናገር ቆመው ሲጠይቁት 58 ዓመት ሙሉ ያለመሰልቸት የፈለገኝን ፣ 95 ዓመት ሙሉ ያለ ድካም የተሸከመኝን እግዚአብሔር ተአምራቱን ቁጭ ብዬ ልናገር አይገባኝም አለ ። ሁሉም በቃሉ ኃይል ተረቱና ዝም አሉ ። እኔ ግን በዕድሜ ሳይሆን በአሳብ ማርጀቴ ፣ ለመናገር ሳይሆን ለመስማት መታከቴ ፣ የተደረገልኝን ሳይሆን ለእግዚአብሔር ያደረግሁ የመሰለኝን መቍጠሬ ተሰማኝ ። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ንግግሩን ቀጠለ ። የሚናገረው ለብዙ ሚሊየን ሕዝብ ይመስል ነበር ። የሚናገረው ስለ እግዚአብሔር ነውና ለአንድ ሰውም ሆነ ለሺህ ሰውም ቢናገር ከሚነገርለት አምላክ የተነሣ በታላቅ አክብሮት ይናገር ነበረ ። 

“ክርስቶስ መጀመሪያ ለአማኒነት ቀጥሎ ለደቀ መዝሙርነት ፣ ከዚያም ለሐዋርያነት ጠራኝ ። ለአማኝነት የጠራኝ በነፍሴ ድኅነት አግኝቼ ፣ ሰላምን ለልቤ እንዳገኝ ፣ ምሕረትን ለወገኔ እንድሰጥ ነው ። ደቀ መዝሙርነትም አዳሪ ተማሪ ሆኜ በቃልና በተግባር ነገረ እግዚአብሔርን እንድማር ነው ። ሐዋርያነቴም ንጉሣዊ አዋጅን ይዤ እስከሚገዛበት ዳርቻ ድረስ ወንጌልን እንድሰብክ ነው ። ክርስቶስ ሥጋዬንና ነፍሴን የማረከበት ያ ጊዜ እንደ አሁን የሚታሰበኝ ነው ። አለመርካት ሕይወቴን ይወዘውዛት ጀምሯል ። ወደ ሥራዬ ብሄድም ማድረግ ስላለብኝ እንጂ በፈቃድና በአቅም አልነበረም ።  ሬሳዬ መወዛወዝ የጀመረ ይመስለኝ ነበር ። ውስጤ ሁሉን ትተህ እቤትህ ተቀመጥ ይለኛል ። ሌላኛው ማንነቴ ደግሞ ካልሠራህ ምን ልትሆን ነው ? እነ እገሌ ከዓሣ አጥማጅነት ወደ ዓሣ አቅራቢነት አድገው በኢየሩሳሌም ቤት ሠሩ ። አንተ ግን ጥብርያዶስ የተወለድህበት ቤት ልትሞት ተቃርበዋል ይለኛል ። በውስጤ አለመርካት ፣ ፍርሃት ፣ ሰዎች ሁሉ እየተሳካላቸው የእኔ መቆም ይታየኛል ። ለመቅናት ብፈልግም በሌሎች ዕድል መቅናት አልሆነልኝም ። በመኖርና ባለመኖር መካከል ለሚታገል ምስኪን የሰው ወርቅ ትዝ አይለውም ። የሚፈልገው የሕይወትን ማዕበል ጸጥ አድርጎ ሰላም የሚሰጠው ብቻ ነው ። ያን ያህል ክፉ ሰው ነኝ ብዬ ራሴን ገምቼው አላውቅም ። መልካምነት ብቻውን ያለ ክርስቶስ እንደማያሳርፍ ተረድቻለሁ ። በርግጥ ብኩን ሰው ፣ ሁሉን ላስደስት ስል ሌሊትና ቀን የምበርር ፣ የሚመለከተኝንና የማይመለከተኝን መለየት አቅቶኝ ራሴን የዓለም ዳኛ አድርጌ ያስቀመጥሁ ሰው ነኝ ። እልህ ቢያሯሩጠኝም ራሴን ሳዳምጠው መድከም ይሰማኝ ነበር ። በቤት ትዳሬን ፣ በሥራ ቦታ አብሮ አደጎቼን ለማስደሰት እጥራለሁ ። እነርሱም የማረፊያውን ወንበር ሳያሳዩኝ ማረፍ አለብህ ይሉኛል ። ያን ሰሞን ግን ልፍለፋዬ በአስጨናቂ ዝምታ ፣ ችኩልነቴ ቅዝዝ በማለት ፣ ንቃቴም በመደንዘዝ ተተክቶ ነበርና “ምን ሆነሃል?” እያሉ ከቤት እስከ ውጭ ያስጨንቁኛል ። የሆንኩትን መግለጥ ስለማልችል ጥያቄአቸው የበለጠ ያስፈራኝ ነበር ። ለካ መልስ ከሌለ ጥያቄ እንዲህ አስፈሪ ነው ያልሁት ያን ጊዜ ነው ። 

በ30 ዓ.ም. የፋሲካ በዓል መቃረቢያ ላይ ይመስለኛል ። ብሶቴ እጅግ እየጨመረ ዓይኖቼ በእንባ ይሞሉ ነበር ። ግራ መጋባትም ነፍሴን ቀስፎ ይዟታል ። ወዴት እንደምሄድ አላውቅም ። ብቻ ጥብርያዶስን በግራዬ እየተውሁ ወደ ሙት ባሕር አቅጣጫ በፍጥነት እጓዛለሁ ። ማበድ የሚባለው ነገር ስሙ ያስፈራኛል ። ዕብደትም እያሳደደኝ መስሎ ይሰማኛል ። ሰማዩን ሳየው የቀድሞ ውበቱን ነፈገኝ ። የጋለ ናስ መስሎ ታየኝ ። መስኩና ልምላሜውም በረሃ መስሎ ይታየኝ ነበር ። በጎዳና እያለሁ ከአሳብ እንቅልፌ ስነቃ ለካ እየተጓዝሁ ያለሁት ወደ ዮሐንስ መጥምቅ ወደ ዮርዳኖስ ዳርቻ ነው ። ወንድሜ እንድርያስ በዕድሜ ከእኔ ቢያንስም በንስሐ ፣ በእምነት ፣ በምስክርነት ሁልጊዜ ይቀድመኛል ። እርሱ የዮሐንስ ደቀ መዝሙር ከሆነ ሰንበት እያለ ነው ። እኔም ይህንን ጥቁር ቋጥኝ ፣ ሳላየው የተሸከምኩትን ፣ ለሰው ለማሳየት የሚከብደኝን ፣ ነገር ግን ያጎበጠኝን ቀንበር ለመጣል ወደ እግዚአብሔር አገልጋይ ገሰገስኩ ። የእግዚአብሔር አገልጋይ በቃሉ መስተዋት ራሴን ያሳየኛል ፣ ቀጥሎ አዳኜን ጌታዬ ያሳየኛል ። ያንን በረሃ አቋርጬ ጌልጌላን በቀኝ ትቼ ፣ እስራኤል ከግብጽ ሲወጡ በተሻገሩበት አቅጣጫና ቦታ የሚያጠምቀውን ዮሐንስን አገኘሁት ። እርሱም ቁመናውና መልኩ ያማረ ቢሆን ድሎትን በመናቁ ልብሱም ጸጉሩም ያስፈሩ ነበር ። ገና ከሩቅ ስመጣ ቍጣ በሚመስል ቃል ተናገረኝ ። ጌልጌላን እየው ሸለፈትህን ቁረጠው ። ዮርዳኖስን ተመልከተው መሻገርህን እመነው አለኝ ። ከላዬ ላይ የከበደኝ ጥቁር ደመና ሲነሣ ተሰማኝ ። ያ ሁሉ የከበደኝ በአንድ ጊዜ የት ሄደ ? አልኩኝ ። ወደዚያ ፍርሃት ላለመመለስ ከዮሐንስ ጋር በረሃ መቀመጥ ፈለግሁ ። ዮሐንስ ግን ፈገግ አለና፡- “ተመለስ ፣ ሥራህንም በትጋት ሥራ ። የተሰጠህን አክብረህ ስትሠራ የበለጠ ነገር ታገኛለህ ። ከእኔ የሚልቀው ወደ ጀልባህ እየተጓዘ ነው ። ለዕለት ሰላምህ ትጨነቃለህ ፣ የአዲሲቱ ዓለም የቅድስት ቤተ ክርስያን አጋፋሪ ትሆናለህ” አለኝ ። እኔም በታላቅ ችኩላ ወደ ጥብርያዶስ ለመመለስ የአቀበቱን ጉዞ ፣ ከቆላ ወደ ደጋ መጓዙን ተያያዝሁት ። ጥብርያዶስ እንደደረስሁ ታንኳዬ ላይ ተሳፈርሁ ። ሰዓቱ ዓሣ የማጠምድበት ሠርክ ነው ። ሌሊቱን በሙሉ ለማጥመድ ሞከርሁ አንድም ዓሣ አላገኘሁም ። “አይ ዮሐንስ ጽድቁ ቀርቶ በቅጡ በኰነነኝ ። እንኳን ለዓለም አጋፋሪ ለራሴም የማልበቃ ሰው ነኝ” አልኩኝ ። ቀድሞ ዓሣ ፈልጎ አለማግኘት አጋጣሚ ብዬ የምጠራው ነው ። አሁን ግን የኖርኩበትን ዘመን እንዳልኖርኩበት የምቆጥርበት ፣ ዓለም ሁሉ በእኔ ላይ እንዳደመ ፣ ሕይወት ፊቷን እንዳዞረችብኝ ፣ እግዚአብሔርም ፍጹም እንደተወኝ የማስብበት ምክንያቴ ነው ። ሆደ ባሻነቴ ጨመረ ። በእንባ እየታጠብሁ በማለዳ መረቤን አጥብ ነበር ። እጆቼ ውኃ ይዘግናሉ ፣ ትኩስ ውኃ የሆነው እንባዬ ደግሞ ከቀዝቃዛው ውኃ ጋር ይቀላቀላል ።  

ድንገት ቀና ስል ብዙ ሕዝብ የከበቡትን ፣ ቃል አምጣ እያሉ የሚያስጨንቁትን አንድ ታላቅ መምህር አየሁ ። ወደ እርሱ ሳልደርስ ወደ እኔ ደርሷል ። ከብዙ ሺህ ታንኳዎች የእኔን ታንኳ መረጠ ። እንኳን እኔን ታንኳዬንም ያውቃል ብዬ ደስ አለኝ ። ወደ ታንኳዬ ሲሄድ በርኅራኄ እያየኝ፡- “ጴጥሮስ ሆይ ፣ ዛሬ ስለ አለመሳካት ታለቅሳለህ ፣ ነገ ግን ስለ እኔ ፍቅር ታለቅሳለህ” አለኝ ። እኔም በራሴ አፈርሁ ፣ አድሮ ጥጃ ፣ ብዙ ተምሮ ጥቂት ነዋሪ ነኝ ብዬ ራሴን ወቀስሁ ። ታንኳዬን ሲሳፈርበት ደስ አለኝ ። ታንኳዬን እርሱ ስለረገጣት ከዚያ በኋላ ታሪክ ሆና ተቀመጠች እንጂ የዓሣ ገበታ አልሆነችም ። ክርስቶስን ስናገኝ በያዝነው ተግባር ላይ የበለጠ ስኬት እንጠብቃለን ፣ ከዚያ በኋላ ለዚያ ተግባራችን ላንኖር እንደምንችል ግን እንረሳለን ። ላለፈው ዘመኔ ፍጻሜ ፣ ለአዲሱ ዘመኔ ጅማሬ ሰጠ ። የምትፈልገውን ዓሣ ፣ በሚገኝበት ሰዓት ያጣኸውን በማይገኝበት ሰዓት ይኸው ውሰድ አለኝ ። መቻሉን አሳይቶ ዓለምን አስናቀኝ ። ቀድሞ በልፋቴ የማላገኘውን ሰጥቶ አስገረመኝ ። “ከዚህ በኋላ ሰው አጥማጅ ትሆናለህ” አለኝ ። አስፈራርቼና አስጨንቄ በመንጠቆ ፣ አስክሬና አደናብሬ በብርብራ ሳይሆን አክብሬ ከነሕይወቱ ዓሣ የተባለውን ሰው በወንጌል መረብ የማጠምድ መሆኔን ነገረኝ ። ዓሣ በባሕሩ ውስጥ ሕያው ሁኖ ለራሱ ይኖራል ፣ ሲወጣ ግን ሞቶ ሌላውን ያኖራል ። እኔነታቸውን ገድለው ለሌሎች ሕይወት ይሆኑ ዘንድ የምሰብካቸው ብዙ ሕዝብ እንዳሉ ነገረኝ ። እኔም የከፈትሁትን ሳልዘጋ ፣ የሰማዩን ክፍት አድርገህ ጠብቀኝ ብዬ ወደ ቤቴም ሳልመለስ ክርስቶስን ተከተልሁ ። እኔ ዘጋሁ ያልሁትም እየተከፈተ ለዓመታት ተቸግሬአለሁ ። እርሱ የሞላውን ግን ማንም አያጎድለውም ።”

ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ የተናገረውን ሁሉ ለመያዝ አልተቻለኝም ። ለትምህርቴ የሚሆነውን ግን ከራሴ ሕይወት ጋር እያዛመድሁ ሰማሁ ። እግዚአብሔር ወደ እርሱ እንድንቀርብ ሲፈልግ ነፍስን በታላቅ ጥያቄ ይሞላል ። ከእርሱ በቀርም የነፍስን ጥያቄ የሚመልስ ማንም የለም ። ስልዋኖስ የተባለው ሲላስም ውኃ በብርጭቆ አድርጎ ሰጠው ። ሐዋርያውም፡- “ጥማትህ ሁሉ በክርስቶስ ይሙላ” ብሎ መረቀው ። እኔም ሳላስበው አሜን ብዬ ተቀበልሁ ። ሐዋርያውም፡- “ደስታዬን አይቶ ጥማትህ ሁሉ በክርስቶስ ይሙላ” አለኝ ። 

ይቀጥላል 

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ረቡዕ ሚያዝያ 6 ቀን 2013 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ