የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ጸሎተ እግዝእትነ ማርያም

 

“ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች፥ መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሴት ታደርጋለች፤” ሉቃ. 1 ፡ 47 ።

አባቶች የብሉይ ኪዳኗ ማርያም የንስብሖ ምስጋና ፣ ከእመቤታችን ታዐብዮ ውዳሴ ጋር ትይዩ እንደ ሆነ ያስተምራሉ ። የብሉይ ኪዳኗ ማርያም ባሕረ ኤርትራ ሲከፈል ንሴብሖ – ምስጉን ነው የተመሰገነ ብላ ከበሮ ነጥቃ ፣ ሰልፍ መርታ ፣ ከፊት ወጥታ ፣ ቀዳሚት ሁና አመስግናለች ። ዘጸ . 15፡21 ። እመቤታችንም በጌታ መፀነስ ባሕረ ሞት ሲከፈል ታዐብዮ ነፍስየ – ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች በማለት ቀዳሚት ሁና አመስግናለች  ። በማኅፀኗ አምላክ በሥጋ እንግድነት እንደመጣ ከምድራውያን ወገን የምታውቅ እርስዋ ነበረች ። ከሰማይ ቅዱስ ገብርኤል ከምድር ድንግል ማርያም የሥጋዌው ባለ ምሥጢር ሁነዋል ። በቅዱሳን መካከል ሽሽግ የለምና ኤልሳቤጥም በመንፈስ ቅዱስ ተረድታ ድንግል ማርያምን አመስግናለች ። አድንቃለች ። “አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ ፥ የማኅፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው” ብላለች ። /ሉቃ. 1፡42 ።/ ይህን ምስጋና መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል አስቀድሞ ለድንግል ማርያም አቅርቦ ነበር ። /ሉቃ. 1፡28 ።/ መልአኩንና ቅድስት ኤልሳቤጥም ያስተባበራቸው መንፈስ ቅዱስ ነው ። መንፈስ ቅዱስ የሞላበት ሰው እግዚአብሔር ያከበረውን ያከብራል ። መንፈስ ቅዱስ የክብር መንፈስ ነውና ። አንድ ሰው መንፈስ ቅዱስ እንዳደረበት ምልክቱ ለእግዚአብሔር ክብር ሲሰጥ እንደ ድንገል ማርያም ፣ እግዚአብሔር ያከበራቸውን ሲያከብር እንደ ኤልሳቤጥ ነው ። 

ቅድስት ኤልሳቤጥ፡- “የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይሆንልኛል?” በማለት ጉጉቷን ገልጣለች ። /ሉቃ. 1 ፡ 43 ።/ የእግዚአብሔር ሰዎች የሆኑትን ኤልያስና ኤልሳዕን የተቀበሉ የሰራፕታዋ መበለትና የሱነም ሴት ታላቅ በረከት እንዳገኙ የምታውቀው ኤልሳቤጥ ከሁሉ በላይ የሆነውን አምላክ በማኅፀኗ የተሸከመች ድንግል ማርያምን መቀበል ትልቅ ዕድልና በረከት መሆኑን ተገንዝባለች ። ይህን ሰላምታ ሲለዋወጡ መንገድ ጠራጊው ዮሐንስ የስድስት ወር ጽንስ ሁኖ በኤልሳቤጥ ማኅፀን ፣ የዓለሙ አዳኝ ደግሞ የዕለት ጽንስ ሁኖ በድንግል ማርያም ማኅፀን ነበሩ ። መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልና ቅድስት ኤልሳቤጥ ሳይገናኙና ሳይነጋገሩ አንድ ዓይነት አድናቆት አስተላለፉ ። የእግዚአብሔር ሰዎችን አንድ ልብና ቃል የሚያደርጋቸው የእግዚአብሔር መንፈስ ነው ። ዛሬ ቋንቋችን ሲደባለቅ ፣ የምድሩን ጨርሰን በሰማይ ያሉትን ቅዱሳን ስንሳደብ መንፈሰ እግዚአብሔር እየራቀ መሆኑን ያሳያል ። ቡራኬውም “የመንፈስ ቅዱስ ኅብረት ከሁላችን ጋር ይሁን” የሚል ነው ። 2ቆሮ. 13 ፡ 14 ። 

የእመቤታችን ምስጋና ወይም ጸሎተ ማርያም የምንለው በሉቃ. 1፡46-55 ያለው ነው ። ይህ ምስጋና ከነቢይት ሃና ምስጋና ጋር ተመሳሳይ ነው ። እመ ሳሙኤል – የሳሙኤል እናት ሃና ልጅ ባለመውለዷ ምክንያት እንደ ተረገመች ሴት ፣ ስካርና እብደት እንደ ተቀላቀለባት ወይዘሮ ተቆጥራ ሳለ እንደ ሰው በጉድለት የማይሳለቅ ፣ ጉድለት የተባለውን እንደ ችሎታው መጠን የሚሞላ እግዚአብሔር ሳሙኤልን ሰጣት ። የመሳፍንት መጨረሻ መስፍን ፣ የነቢያት መጀመሪያ ነቢይ ፣ የመጀመሪያዎቹን ሁለት ነገሥታት ሳኦልና ዳዊትን ቀብቶ ያነገሠው ሳሙኤል የሃና የጸሎትዋ መልስ ፣ የመናቅዋ ክብረት ነበረ ። ሃና ዘመኗን በሙሉ ያማጠች እንጂ አንድ ቀን ብቻ ያማጠች ሴት አልነበረችም ። የጸሎት ምጥ ሳሙኤልን ይወልዳል ። ሃናም፡- “ልቤ “በእግዚአብሔር ጸና ፥ ቀንዴ በእግዚአብሔር ከፍ ከፍ አለ አፌ በጠላቶቼ ላይ ተከፈተ በማዳንህ ደስ ብሎኛል” በማለት አመሰገነች ። 1ሳሙ. 2፡1 ። 

የእመቤታችን የድንግል ማርያም ምስጋና ወይም ጸሎተ እግዝእትነ ማርያም ከብሉይ ኪዳን ብዙ ጸሎቶች ፣ ምስጋናዎች ፣ ቃል ኪዳንና ትንቢቶች ጋር የተስማማ ነው ። በዚህም እመቤታችን የቃለ እግዚአብሔር እውቀቷ ከፍ ያለ መሆኑን ያሳየናል ። ጸሎተ ማርያም፡- 

እውነተኛ አክብሮት የልብ መሆኑን ፣

እግዚአብሔር ነገርን የሚለውጥ አምላክ መሆኑን ፣

ትውልድን በብሩህ ዓይን ማየትን ፣

ብርቱ አምላክ በደካማ ሰው እንደሚገለጥ ፣

ማዳን የእግዚአብሔር መለኮታዊ ግብር መሆኑን ፣

እግዚአብሔር የዘረጋውን የማያጥፍ ፣ የሰጠውን የማይነሣ መሆኑን ፣

በችሎታው እንጂ በችሮታ የማይኖር ኃያል መሆኑን ፣

የትሕትና አፍቃሪ እንደሆነ ፣

ዘመናትን የሚለዋውጥ መሆኑን ፣

ችግረኛን እንደሚያስብ ፣

ሲነሣ ወይም ሲነጥቅ የሚወቅሰው እንደሌለ ፣

ከጥንት ጀምሮ ሲናገር መኖሩን ወይም ነባቢ አምላክ መሆኑን፣

የቃል ኪዳን አምላክ እንደሆነ ፣

ምሕረቱ አስታዋሽ መሆኑን ፣

እስራኤልን በልጅ ወግ መቀበሉን ወይም የሕዝቡ አባት መሆኑን የሚገልጥ ነው ። 

የእመቤታችን ምስጋና ታላቅ የነገረ መለኮት ትምህርት ቤት ነው ። በዘመናት ሁሉ የተነሡ ደጋግ አባቶች ክፉውን ከይሲ የቀጠቀጡበት የምስጋና በትር ነው ። ዘወትርም የሚጸለይ ፣ ከጸሎተ ነቢያት ጋርም የሚደርስ ታላቅ ግዳጅ የሚፈጽም ጸሎት ነው ። ስለ ሣራ ፣ ስለ ርብቃ ፣ ስለ ራሔል ፣ ስለ ሃና ፣ ስለ ኤልሳቤጥ ስንናገር ብዙዎች ደስ ይላቸዋል ። ስለ ድንግል ማርያም ሲንናገር ግን ይከፋሉ ። ለምን ይሆን ? ቀዳማዊት እመቤት እየተባለ በሚጠራበት ዘመን እመቤታችን ብለን የአምላክን እናት ስንጠራ ይነቅፉናል ። ተገቢ አይደለም ።

በአማኑኤል ስሙ ፣ በተወጋ ጎኑ ፣ በእንተ ማርያም እሙ ምሬአለሁ ፣ ይቅር ብያለሁ ይበለን ። ዘመኑን በሰላም ያሻግረን !

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ነሐሴ 2 ቀን 2012 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ