የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ጸጋ እንዲበዛ

“እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማልና ፥ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል ።” 1ጴጥ. 5፡5
ትሑቱ ሐዋርያ ስለ ትሕትና ሲገልጥ በእውነት ደስ ይላል ። በሽምግልናው ፣ በተቀበለው አደራ እኔ የበላይ ነኝ የሚል ስሜት የሌለው ሐዋርያው ጴጥሮስ በርግጥም ትሑት ነበር ። በአምስተኛው ክፍለ ዘመን “የሮም መንበር ፣ መንበረ ጴጥሮስ ነው ፤ ስለዚህ እኛ ከሁሉ እንበልጣለን” የሚል አስተሳሰብ በመጀመሩ የቤተ ክርስቲያን መከፋፈል ሆነ ። እኔ እበልጣለሁ ፣ እኔ እበልጣለሁ ማለት አንዲቷን ቤተ ክርስቲያን ምዕራብና ምሥራቅ ብሎ ለሁለት ከፈለ ። መንበረ ጴጥሮስ ትሕትና እንደሆነ ማሰብ የፈለግን አይመስልም ። ትሑቱ ጴጥሮስ በጸጋ ላይ ጸጋ ተጨመረለት ። መውደቅንም መነሣትም የሚያውቀው ጴጥሮስ ፣ ኋላ በገባው ሐዋርያ በጳውሎስ ሲገሠጽ ያልከፋው ጴጥሮስ ፣ እንደ ጌታዬ አትስቀሉኝ የቁልቁሊት ስቀሉኝ ብሎ የተማጸነው ጴጥሮስ በርግጥም ትሑት ነው ። የወንጌላዊው ማርቆስ  መምህር እንደሆነ ይታወቃል ። የማርቆስ ወንጌልም የጴጥሮስ ወንጌል ነው ተብሎ ይታመናል ። ምክንያቱም ጴጥሮስ እየነገረው እንዳጻፈው ታምኗልና ። ታዲያ ጴጥሮስ በማርቆስ ወንጌል ውስጥ በጌታ መገሠጹን /ማር. 8፡32/ ፣ ፍርሃቱን /ማር.9፡5/፣ ከንቱ ትምክሕቱን /ማር. 14፡29/ በጸሎት አለመትጋቱን /ማር. 14፡37/፣ ጌታን መካዱን /ማር. 14፡70/ በግልጽ እንዲጻፍ አድርጓል ። ከፈተናዬም ከውድቀቴም ይማሩ የሚል ትሑት ሐዋርያ ነበር ። የዛሬ አገልጋይ ደግሞ ዕለት ዕለት በደመና እንደሚረማመድ የሚናገር ፣ በእያንዳንዱ ነገር ድምፅ ከሰማይ እንደሚሰማ የሚተርክ ፣ ማታ የጀመረው ጸሎት ጠዋት ላይ እንዳለቀ ስሙልኝ ብሎ የሚያውጅ ነው ። ደካሞችን የማያበረቱ አገልጋዮች ያተረፍነው ትሕትናን በመሸጣችን ነው ። የራሳቸውን ዝና ለመካብ የሰውን ዝና የሚያወርዱ ፣ በአደባባይ የሰውን ገመና የሚያወሩ ልክ የለሾችን ያመረትነው ትሕትና በመጥፋቱ ነው ።
ስለ ትሕትና ትምህርቶች እየተሰጡ አይመስሉም ። አብዛኛዎቻችን በትዕቢት ተወጥረናልና ። ጭንቀትና ፍርሃት ሲበዛ ከንቱ ፉከራ ይወለዳል ። ከንቱ ፉከራ የትዕቢት ልጅ ነው ። ስለ ትሕትና ትምህርት ከተሰጠም ምእመናን ፀጥ ብለው እንዲገዙ ሊሆን ይችላል ። በትሕትና መማርና ማስተማር ፣ በትሕትና መምራትና መመራት ግን ለሁሉም አስፈላጊ ነው ። ትሕትና እንደ ልምጥምጥነት መታየቱ አሳዛኝ የዘመናችን አተረጓጎም ነው ። ትሑታንን ካልተቀበልን ትዕቢተኞችንና ዕቡያንን ደግሞም በደም ሰርግ የሰከሩትን መጋበዛችን አይቀርም ። “አህያ ተማልላ ጅብ አወረደች” እንዲሉ ። ትዕቢት እብጠት በመሆኑ መፈንዳቱ ወይም መበጣቱ አይቀርም ። ትዕቢት ነፋስ የተሞላ ፊኛ በመሆኑ መተንፈሱ አይቀርም ። ትዕቢት እንደ ባሎን በመሆኑ ወዴት እንደሚያደርስ አይታወቅም ። ገጣሚው ስለ ትዕቢት ሲናገር እንዲህ ብሏል፡-
በሥልጣን ከፍ ከፍ ፣
በዝና ከፍ ከፍ ፣
ወደ ላይ ከፍ ከፍ ፣
ከፍ ከፍ … ከፍ ከፍ ፣
ከዛ የወደቅህ ዕለት አጥንትህ እንዳይተርፍ ።
ርእሰ መናፍቃን የተባለው ሲሞን መሠርይ ጴጥሮስና ዮሐንስ በተአምራት ወደ ላይ ከፍ ከፍ ብለው ደመናን ሲሳፈሩ እርሱም በምትሐት እንደ እነርሱ እሆናለሁ በማለት ሕዝብ ሰብስቦ ያሳይ ነበር አሉ ። ታዲያ ከላይ ያለው ጴጥሮስ ከሥር እየመጣ ያለውን ሐሳዊ ለማሳፈር “እናማትብበት” ሲል ዮሐንስ ግን “ጴጥሮስ ሆይ አትቸኩል ፣ ከፍ ከፍ ይበል ላወዳደቁ እንዲመች” አለው ይባላል ። ያለ ልክ ከፍ ከፍ ማለት ያለ ልክ ለመውደቅም ነው ። ሆ ሆ ሲበዛ ፣ እገሌ እገሌ ሲባል ፣ ፎቶ በዓይነት ሲለቀቅ ፣ በደማቅ አካባቢ መለስ ቀለስ እያሉ መታየት ዘላለም ለመጨለም ነው ። እስቲ እንታይ ብለው ያለ ጉዳይ ከተማውን ይዞሩ የነበሩ ውብ መኪና አሽከርካሪዎች ዛሬ የት አሉ ? ዓለም ተረኛ እንጂ ቋሚ ወዳጅ የላትም ። ከአዲስ አበባ ለንደን ይገላበጡ የነበሩ ዛሬ እስራት ዕጣቸው ሲሆን እሰይ ከማለት እኔን አውጣኝ ማለት ትልቅ ጸሎት ነው ። ሰዎች ጠባያቸውን ቀይረው ይቀርቧት ይሆናል እንጂ ዓለም እንደሆነ ፈርዖንን ቀይ ባሕር ከታ የተሰናበተች ፣ ናቡከደነጾርን ሣር ያስጋጠች ፣ ቄሣሮችን የተናቁ ያደረገች ፣ እነ ናፖልዮንን የደሴት እስረኛ ያደረገች ናት ። ዓለም ጅምር እንጂ ፍጻሜ የላትም ።
አንቺ ዓለም ፣ አንቺ ዓለም ፤
የጀመረሽ እንጂ የጨረሰሽ የለም ።
ዓለም ውሽማ እንጂ ባል አትሆንም ። ውሽማ ለዛሬ ብቻ መጠቀሚያ የሚያደርግ ነው ። የዓመቱን በዕለት ይጋብዛል ፣ ባል ግን ለነገም አለና በመጠኑ ይሰጣል ። ዓለም ውሽማ መሆኗን የሚዘውራት ሰይጣን ተናግሯል ።ጌታን ሲፈትነው ወድቀህ ብትሰግድልኝ የዓለምን ክብርና ሥልጣን እሰጥሃለሁ ብሎታል ። ለአንድ ስግደት የዓለምን ክብርና ሥልጣን ሁሉ መደበ ። ዓለም በአንደ ጊዜ ገናና ታደርጋለች ። ውሽማ ናትና ከዛሬ በላይ ጊዜ የላትም ። እግዚአብሔር ግን ለዘላለም ስላሰበን ቀስ እያለ ይባርከናል ። ታዲያ ዓለምን የታዘቡ ፣ ከኪሳራቸው የተማሩ እንዲህ አሉ፡-
“በላነው ጠጣነው ፣
ለበስነው አለቀ ፤
ዓለም መች ይለቃል ካላጨማለቀ።”
ትሕትናን የትዕቢት ያህል የሚቃወማት ነገር ቢኖር ግብዝነት ነው ። ግብዝነት የሆኑት አለመሆን ፣ ያልሆኑትን መምሰል ነው ። ግብዝነት ጭንብል ማጥለቅ ነው ። የልጆች ፊልም የሚሠሩ ፣ ደግሞም ሌቦች ጭንብል ይጠቀማሉ ። ሕፃናት በግብዝነት ይታለላሉ ። የተሰረቁ ሰዎችም ማን እንደ ሰረቃቸው ለማወቅ ይቸገራሉ ። ግብዝነት ያታልላልና ሕፃናት ያደርገናል ። የግብዝነት የመጨረሻው ዓላማ ግን እምነታችንን ፣ አቋማችንን ለመስረቅ ነው ። ከሚያገሱ አንበሶች የሚለሰልሱ እባቦች አደገኛ ናቸው ።
“እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማልና ፥ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል ።” ይላል 1ጴጥ. 5፡5 ። ይህ ምክር የተላለፈው ለወጣቶች ነው ። ወጣቶች ለመንፈሳውያን አገልጋዮቻቸው እንዲታዘዙ የተላለፈ ነው ። በወጣትነት ፍላት ወንበር ካልገለበጥሁ የሚሉ ፣ እግዜርን በእምነት ሳይሆን በዱላ ሊያስከብሩ የሚሹ ፣ አማኝነት ሳይሆን ወንድነት የሚሰማቸው ፣ በዘራፍ አድገው በዘራፍ ለማመን የሚከጅሉ ብዙ ምስኪን ወጣቶች አሉ ። ለእነርሱ ዕድሜአቸው የሚረዝምበት መድኃኒት ትሕትና ብቻ ነው ።
አገልጋዮችም በፍቅር እንጂ በኃይል እንዲያስተዳድሩ አልተፈቀደም ። መንፈሳዊ ቤተሰብ የሆነችውን ማኅበረ ምእመናን በትሕትና ማስተዳደር አለባቸው ። ብዙ አገልጋዮች ምእመኑን አሥራት እንደሚያመጣ ደንበኛ ያዩት ይሆናል ። ምእመኑ ግን ልጃቸው መሆኑን መረዳት ያስፈልጋቸዋል ።በትክክል ካገለገልን እግዚአብሔር ለቤቱ በጀቱን አያጓድልም ። ቢጎድልም የምንፈተንበት ርእስ ሊሆን ይችላል ።
ታዲያ ወጣቶች ጸጋ ቢበዛላቸው ይመኛሉ ፣ ይጸልያሉ ። ጸጋ ግን የሚበዛው በትሕትና ብቻ ነው ። ትዕቢት ያለውን ጸጋ ይነሣል እንጂ አይጨምርም ።
የሁላችን ተስፋ ፣ ልባችንን በቃልህ የደገፍህ ፣ አለማወቃችንን ያገዝህ እግዚአብሔር ሆይ ስምህ ቡሩክ ቅዱስ ይሁን ። ጌታ ሆይ በራሳችን የምናበጀው መስሎን በብዙ መንገድ ባከንን ። እባክህን በትሕትና ጌጠኛ ልጆችህ አድርገን ። መልካችን ጠፍቶ ክርስትና ጣዕም አልባ ሁኖብናልና ትሑት አድርገን ። ጌታ ሆይ እንኳን ትሑት ልንሆን ትሑታንን እየናቅን ነውና ከዚህ ሚዛን ካጣ ማንነት አድነን ። ለዘላለሙ አሜን ።
የዕለቱ መና 16
ግንቦት 15 ቀን 2011 ዓ.ም.
ዲአመ
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ