የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ጾም

                                      የዲ/ን አሸናፊ መኰንን ገጽ….. ቅዳሜ የካቲት 7/ 2007 ዓ.ም.
እንኳን ለጌታችን ዐቢይ ጾም አደረሳችሁ!
ጾም ኃይልን ከሚሰጡ ምግቦች እንዲሁም ከሚያሰክር መጠጥ ለተወሰኑ ሰዓታትና ቀናት መለየት፣ በትሕትናና በተዋረደ መንፈስ እግዚአብሔርን ለመለመን፣ ለድሆችና ለጦም አዳሪዎች በልዩ ሁኔታ ለማሰብ፣ ለተጨነቁ ሁሉ ምሕረት ለመጠየቅ የሚረዳ መንፈሳዊ መስመር ነው፡፡ በጾም አድልኦና ወገናዊነት ስለሌለ ‹‹ለሚያሳድዱህ ጹምላቸው›› ተብሎ በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ተደንግጓል (ዲድ.1፡3)፡፡ ይህም የሚያሳየን ጾም ፍጹም የፍቅር መንገድ መሆኑን ነው፡፡
ጾም በማንኛውም ሃይማኖት ውስጥ ክብረት ያለው ሥርዓት ነው፡፡፡ በይሁዲ፣ በክርስትና፣ በሂንዱ፣ በቡድሃ፣ በእስልምና… ጾም የታወቀና የጎላ ሥርዓት ነው፡፡ የጾም ዓላማው ከመብልና መጠጥ መከልከል ብቻ ሳይሆን በልዩ የልብ ዝግጅት እግዚአብሔርን ማሰቢያና ምሕረቱን መለመኛ ነው፡፡ የጾም ዓላማው፡-

  1. በተዋረደ መንፈስ፣ በመገዛት ስሜት ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ
  2.   ግላዊና ብሔራዊ ንስሐን ለማቅረብ፣
  3. ለታላቅ ተልእኮ ኃይልን ለመቀበል፣    
  4. የእግዚአብሔርን መገኘት ለመጠባበቅ፣  
  5.  ለድሆችና ለተጨነቁት ካለን መብልና ሀብት ለማካፈል፣ 
  6.   እርስ በርስ ይቅር ለመባባል፣ 
  7.  እግዚአብሔርን በልዩ ለማግኘት ቀጠሮ ለመያዝ ነው፡፡

ጾም ከብሉይ ኪዳን እስከ አዲስ ኪዳን፣ ከቤተ ክርስቲያን ልደት እስከ ዛሬ ታላቅ የሃይማኖት ሥርዓት ነው፡፡ ጾም የኦርቶዶክስ፣ የካቶሊክ… የሚባል ሳይሆን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ነው፡፡፡ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥልቅ ዕውቀት የሌላቸው ወገኖች ጾምን ሲቃወሙ ይታያሉ፡፡ የጾም አስፈላጊነት አጠያያቂ አይደለም፡፡ የምጾምበት መንፈስ ግን በቃሉ ሚዛን መለካት አለበት፡፡ አንዳንድ ሰዎች፡-


  1.    ለምግብ መለወጫነት ጾምን ይወዳሉ፡
  2.  ሁልጊዜ ሥጋ መብላት ጤናቸውን እንዳይጎዳ በማሰብ ይጾማሉ፡
  3. ባልጾምስ ምን አገኛለሁ ብጾም ይሻለኛል በማለት ከድህነት የተነሣ ይጾማሉ፡፡  
  4.   ለሰውነት ቅርጽ ጾምን ይጠቀማሉ፡፡
  5. ለኑሮ ቁጠባ ይጾማሉ፡፡ 
  6. ባሕል መስሎአቸው የለመዱት እንዳይቀር ይጾማሉ፡፡
  7. ጎረቤት ምን ይለኛል በማለት ይጾማሉ፡፡

 እነዚህ ለምሳሌ ያህል የጠቀስናቸው የአጻጻም ምክንያቶች ሊነቀፉ ይገባቸዋል፡፡ ጾም በራሱ ግን ሊነቀፍ አይገባውም፡፡ ጾም የመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓት ነውና፡፡

ሙሴ ኦሪትን ለመቀበል ዐርባ ቀንና ዐርባ ሌሊት ጾመ፡፡ ከእግዚአብሔር ዘንድ ታላቅ መመሪያዎችን ለመቀበል ጾምና ጸሎት ወሳኝ ነው፡፡ ጌታችንም ወደ ወንጌል አገልግሎት ከመግባቱ በፊት በገዳመ ቆሮንቶስ ዐርባ ቀንና ዐርባ ሌሊት ጾሟል (ዘጸ. 34፡28፤ ማቴ.4፡2፤ ሉቃ.4፡2) ሐዋርያት ቀሳውስትን ለመሾም ይጾሙ ነበር (የሐዋ. 13፡2)፡፡ ሕዝበ እስራኤል ንስሐቸውን በጾምና በጸሎት ይፈጽሙ ነበር፡፡ አብሮ አደግ ጋኔን፣ የተቆራኘ ፈተና በጾምና በጸሎት ይወጣል (ማቴ.17፡21)፡፡ ጾም በግልና በማኅበር፣ በህቡዕና በአዋጅ ይፈጸማል፡፡ ጾም ምግብን መተው ሳይሆን በትሑት መንፈስ ለመጸለይ እንዲረዳ ሥጋን የሚያስገዛ ድንቅ ሥርዓት ነው፡፡
በጾም ውስጥ ሰዎች ለኃጢአታቸው ኑዛዜ ያደርጋሉ፡፡ ክርስቶስን እያሰቡ በዕንባ ይታጠባሉ፡፡ የድሆችን ረሀብ በፈቃዳቸው በማየት ቁርስና ምሳቸውን ለድሆች ይሰጣሉ፡፡ ጾም ኢኮኖሚ ሳይሆን ያልበላነውን ምግብ ለጦም አዳሪዎች የምንሰጥበት መሥዋዕትነት ነው፡፡
ወደ ጾም ከመግባታችን በፊት ሦስት ነገር ያስፈልጉናል፡-
<1.ርዕስ መያዝ
<2. ይቅር መባባል
<3.ንስሐ መግባት ናቸው፡፡ እነዚህ ሦስት ነገሮች ያልተሟሉበት ጾም ትክክለኛ ጾም አይደለም፡፡
ጾምን ከንቱ ወይም የረሀብ አድማ የሚያሰኙ ነገሮች አሉ፡፡ ይኸውም ከምግብ እየጾሙ ከክፋት  አለመራቅ የመጀመሪያው ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድ፡- ‹‹ይጹም ዓይን፤ ይጹም ልሳን፣ እዝንኒ ይጹም እምሰሚዓ ሕሡም በተፋቅሮ›› ብሏል፡፡ ሌላው የጾም ክፋት የማይጾሙትን ሰዎች ሲያሳየን ነው፡፡ ሕዝባችን ጾምን በሥጋ ብቻ ሳይሆን በዝሙትም ይቀበላል፡፡ የሚፈታውም በዚሁ ነው፡፡ ኃጢአት ግን ቅበላና ፋሲካ የሌለው ጾም ነው፡፡ ከጾም በኋላ ማሰብ የሚገባን እግዚአብሔር ተቀብሎናል ወይ? የሚለው ነበር፡፡ በጾሙ ፍጻሜ የምናስበው ግን ስለዶሮ ዋጋ መጨመር መሆኑ እጅግ ያሳዝናል፡፡
ጌታችን የጾመውን ጾም የጌታ ጾም እንለዋለን፡፡ ደግሞም ዐቢይ ጾም ወይም ታላቅ ጾም እንለዋለን፡፡ ታላቁ ጌታ የጾመው ጾም ነውና፡፡ ሕዝቡም ሁዳዴ ይለዋል፡፡ ሁዳድ የመንግሥት እርሻ ማለት ነው፡፡ የመንግሥት እርሻ በሚታረስበት ጊዜ ሁሉም ይሳተፋል፡፡ እንዲሁም ልጅ አዋቂ ሳይል ሁሉም የሚጾመው በመሆኑ የጌታ ጾም ሁዳዴ ተብሏል፡፡
ቅዱስ ያሬድ በዐቢይ ጾም የሚውሉትን ስምንት እሑዶች ዝማሬ ስለሠራባቸው በመዝሙሮቹ አርእስት እያንዳንዱ እሑድ ተሰይሟል፡፡ እነርሱም፡-
1-ዘወረደ
2-ቅድስት
3-ምኩራብ
4-መጻጉ
5-ደብረ ዘይት
6-ገብር ኄር
7-ኒቆዲሞስ
8-ሆሳዕና
ከሆሳዕና ቀጥሎ ያሉት ቀናት ሰሙነ ሕማማት ሲሆኑ በትንሣኤውም ጾሙ ይጠናቀቃል፡፡ የጾሙ የመጨረሻው ሳምንት የጌታን ሕማምና መከራ የምናስብበት በትንሣኤውም ደስ በመሰኘት የምናጠናቅቅበት ነው፡፡ የዛሬው እሑድ ዘወረደ ይባላል፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ ከሰማያት ሰማይ ወርዶ ከድንግል መወለዱን በማሰብ የምናደንቅበትና የምንዘምርበት ነው፡፡ የተባረከ የጾም ወራት፣ በፍቅርም የሆነ ጸሎት የምናቀርብበት፣ ቤተ ክርስቲያን የሰላም ደሴት ሆና ደስ የምንሰኝበት፣ ሁከተኞችና የወንድሞች ከሳሾች የሚታገሡበት፣ ሰውን እያሰብን ሳይሆን እግዚአብሔርን እያሰብን የምንሰነብትበት ያድርግልን!
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ