የትምህርቱ ርዕስ | ፈቀቅ በል

 “ወደ ጥልቁ ፈቀቅ በል” ሉቃ. 5፡4
ጌታችን ከደቀ መዛሙርቱን አራቱን ጴጥሮስና እንድርያስን ፣ ዮሐንስና ያዕቆብን የጠራበት ድንቅ ምዕራፍ ነው ። እግዚአብሔር ሰውን የሚጠራው  ለወዳጅነት ነው ። ወዳጅነት ከዝምድናም ከጓደኝነትም በላይ ነው ። ዝምድና የሥጋ እንጂ የአሳብ ቋጠሮ ላይኖረው ይችላል ። ጓደኝነት እኩል እውቀት ነውና በነጻነት ማጥፋት ሊኖርበት ይችላል ። ወዳጅነት ግን መመካከርና መሸፋፈን ያለበት ፣ ቅን የሆነውን መንገድ የሚከተል ፣ በዘላለማዊ ፍቅር የታሸ ነው ። ጓደኛ ያላቸው ወዳጅ ላይኖራቸው ይችላል ። በፍቅር ዓለም ወዳጅነት እግዚአብሔር ቋንቋ የሆነበት ተግባቦት ነው ። እግዚአብሔር ወዳጅነትን ሲመሠርት በራሱ መለኮታዊ ፍቅር ላይ ተመሥርቶ ነው ። ምንጊዜም በፍቅር ቀዳሚው እግዚአብሔር ነው ። ስለወደደን ወደድነው እንጂ ስለወደድነው አልወደደንም ። እግዚአብሔር ሰውን ሲጠራ አፍኣዊ ሕይወትን አይቶ ሳይሆን ልብን አይቶ ነው ። እግዚአብሔር የጠራቸው ሁሉ ሲጠሩ በሥራ ላይ የነበሩ ናቸው ። የያዝነውን ካላከበርን የምንይዘውን አናከብረውም ። ትንሽዋ ድርሻ ለትልቁ ሹመት የምታበቃ ናት ። ታማኝ የበግ ጠባቂ የነበሩት ሙሴና ዳዊት ለመሪነት ታጭተዋል ። ነገ ለሚሠራው ታላቅ ሥራ እግዚአብሔር ዛሬ በተባለች ቤተ ሙከራ ውስጥ እያሳለፈን ነው ።
እግዚአብሔር ሰውን ሲጠራ እንቢታቸው እንጂ ድካማቸው አላስቸገረውም ። ከሰዎች የሚጠቀመው ባይኖርም ሰዎችን ለመጥቀም ግን በዘመናት ሲጣራ ይኖራል ። ስለ ራሳችን ጥቅም ደጅ የሚጠናን ፣ በራችንን የሚያንኳኳ ፣ በፍቅር የሚለምነን እርሱ ቡሩክ ነው ። ዳዊትን እግዚአብሔር ያነሣው ከወለል በታች ሳለ ነው ። ሸለቆው ተራራ የሚሆነው በእግዚአብሔር ነው ። ያለንበትን ሁኔታ ጌታ እያየ እንዳላየ ፣ እየሰማ እንዳልሰማ አያልፈውም ። እነዚህን ደቀ መዛሙርት ሲያገኛቸው ተስፋ ቆርጠው ሳሉ ነው ። ሐዋርያው ጴጥሮስ እስከ ዛሬ ድረስ ይሠራ የነበረው በሙያና በራስ አስተሳሰብ ነው ። ዛሬ በተአምራት እግዚአብሔር ሲሠራ ያያል ። እውቀቱ እውቀት አልባ ፣ ብልሃቱ ሞኝነት ሲሆንበት ያን ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ምክር ዘወር አለ ። እግዚአብሔር ካልረዳን ያለን ነገር እንደሌለን ነው ። ይህች ዓለም እውነተኛ ድሆችንና የባለጠጋ ድሆችን የምታስተናግድ ዓለም ናት ።
ሌሊቱን በሙሉ ዓሣ ለማጥመድ ወጥተው ምንም አላገኙም ነበር ። ሲነጋም ተስፋ ቆርጠው ሳለ በባሕሩ ዳርቻ ጌታ አገኛቸው ። ዓሣ አጥማጆቹ መረባቸውን ያጥቡ ነበር ። ሌሊቱን በሙሉ ሲያጠምዱ ያደሩ ሲነጋ ማጠባቸው እረፍት እንደሌላቸው ያሳያል ። መረብን ማጠብ ግን ያገኙና ያላገኙ የሚያደርጉት ተግባር ነው ። ያገኙ በደስታ ሲያጥቡ ያላገኙ በኀዘን የሚከውኑት ሥራ ነው ። በትልቋ መርከብ ላይ ከፊት የሚቆመው የኋላው ጴጥሮስ ነው ። የመርከቧ ባለቤት ክርስቶስ በጴጥሮስ ታንኳ ላይ ተሳፈረ ። በታንኳዋ ላይ ሁኖ ያስተምር ነበር ። መጀመሪያ የነፍስን ረሀብ አጠገበ ። መድረኩም የጴጥሮስ ታንኳ ነበረች ። ይህ ሁለት ነገር ያሳየናል ። የመጀመሪያው ጴጥሮስ መፈለጉን ፣ ሁለተኛ ጌታችን ሕዝቡን እያስጨነቀ ሳይሆን እያስደሰተ ማስተማሩን ነው ። አሁን ታንኳውን የለቀቀው ጴጥሮስ፣  ቀጥሎ ሕይወቱን ይለቅቃል ። ጌታ ሳይጋብዘውና ሳያስፈቅድ በጴጥሮስ ታንኳ ላይ መሳፈሩ እንኳን ታንኳው ባሕሩም የእርሱ ስለነበረ ነው ። አንድ ቀን ሳያስፈቀደን በሞት ይወስደናል ። ሥልጣን የእርሱ ነውና ።
ጌታችን ትምህርቱን ከጨረሰ በኋላ ጴጥሮስን፡- ወደ ጥልቁ ፈቀቅ በል መረቦቻችሁንም ለማጥመድ ጣሉ አለው ።” ዳር የወጣው ሰዓቱ አልፏል ብሎ ነው ። ዓሣ የሚገኘው በሌሊት ነው ። ከነጋ በኋላ የሰው ጥላና የፀሐዩ ሙቀት ያሸሻቸዋል ። ጌታ ፈቀቅ በል ሲለው ሰዓቱ አልፏል ፣ ነገር ግን ሰዓት የማያልፍበት አምላክ ነው ። ጴጥሮስ ተስፋ ቆርጦ ነበር ። ባቆመው ነገር ጅማሬ ሊሰጠው ክርስቶስ መጣ ። ሰው ሲጨርስ እግዚአብሔር ይጀምራል ።ትልቅ የሆነብን ጉዳይ ጌታችን ሲመጣ ትንሽ ይሆናል ። ጌታ ወደ ጥልቁ ፈቀቅ በል ካለው ጴጥሮስ ዳር ወጥቶ ነበር ። ዳር መውጣት ሥራን ለመተው መሰናዳት ነው ። ካለቀው ነገር ላይ ጌታ ሊያስጀምረው ፣ ከዳሩ ወደ ጥልቁ መራው ።
ፈቀቅ በል የሚለው ቃል የሚገርም ነው ። ከራስህ ፈቀቅ በል ማለት ነው ። ከራስህ ማስተዋል ፣ ከስሌትና ከግምትህ ፈቀቅ በል ማለት ነው ። ከተስፋ መቊረጥህና ከልብ ዝለትህ ፈቀቅ በል ማለት ነው ። ወደ ጥልቁ ወደ መካከለኛው ባሕር ፣ ያለፈውን ሰዓት ገና እንደሆነ አድርገህ ሥራህን ጀምር ማለት ነው ። ሌሊቱን በሙሉ ያደከመውን ጥልቅ እርሱም በኃይለ እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲያደክመው አዘዘው ። ዳር ላይ መረብ ከምናጥብበት ፣ ቀቢፀ ተስፋ ፣ ወደ እግዚአብሔር ጥልቅ ፈቀቅ እንድንል ዛሬም ጌታ ይናገረናል ። ራሳችንና ሁኔታዎችን ስናይ ይደክመናል ። የእግዚአብሔርን ጥልቅ ስንመረምር ግን ኃይሉ ያበረታናል ። ሕይወት ጥልቅ ናት ። በሚገኝበት ጊዜ ባዶ ልትሆን በማይገኝበት ጊዜ ሙሉ የምትሆን ናት ። የሕይወትን ጥልቅ ባሕር ያለ ክርስቶስ መቅዘፍ አይቻልም ። ሕይወት ያለ ጌታ አጥምደን አንይዛትም ።
ወደ ጥልቁ ፈቀቅ ለማለት እምነት ፣ ራስን ባዶ ማድረግ /አለመመራመር/ መታዘዝ ያስፈልጋል ። ክርስቶስ የሌለበት ልፋት ሁሉ የዜሮ ድምር ነው ። ጌታ የተናገረው ለሁኔታው የማይመች ነው ። ሰዓቱ አልፏል ፣ ልብም ደክሟል ፣ ሁሉም ነገር ባዶ ሁኗል ። እርሱ ካዘዘ ግን ሁሉም ነገር ቀላል ነው ። በእግዚአብሔር ምክር ውስጥ ኪሣራ የለም ። ሽምግልና በዘይት የሚዋበው በእግዚአብሔር ነው ። ሽምግልና መገርጣት ያለበት ፣ የተፈጥሮ ቅባት የሚባክንበት ነው ። እግዚአብሔር ግን ሽምግልናን በዘይት ያለመልማል ። ያ ባሕር ዓሣ አላጣም ፣ እነ ጴጥሮስ ግን ማግኘት አልቻሉም ። ጌታችን በዚያ ባሕርም ዓሣ አልጨመረም ። እያለ ማየት አልቻሉም ። ጌታ ግን ዓይኖቻቸውን አበራላቸው ። ዛሬም ያለው ችግር አቅርቦት ሳይሆን የዕይታ ነው ። አለ ግን አላገኘነውም ። የጌታ ትእዛዝ ግን ዓይንን ያበራል ።
ጴጥሮስ ለጌታ ታዝዞ መረቡን ሲጥል ሊጎትተው እስኪያቅተው ብዙ ዓሣ አገኘ ። ራሱ መሸከም አቅቶት ከጎረቤት ረዳቶች ጠራ ። እግዚአብሔር ሁሉን የማይሰጠን ስለማንችለው ነው ። ጴጥሮስ በዚህ ጊዜ ልቡ ተነካ ። እግዚአብሔር የሚወደው ሰው ቶሎ ልቡ የሚነካ ሰው ነው ። እንዲህ ያለውን ሰው ለአገልግሎት ይጠራዋል ። ደንዳኖች የእግዚአብሔርን ፍቅር ማየት አይችሉም ። እግዚአብሔርን ለማየት የልብን መስተዋት መወልወል ያስፈልጋል ።
ጌታችን ችግራችንን ያያል ። ተስፋ የቆረጥንበትን ፣ ትተነው ዳር ላይ የቆምንበትን ነገር ይመለከተዋል ። ክብሩን ለማየት ግን መታገሥ ያስፈልጋል ። ጌታችን ሲያዘን እንዴት ብለን የአቅምና የግምት ጥያቄ ማንሣት የለብንም ። መታዘዝና ከራሳችም ሁኔታ መላቀቅ ብቻ ይገባል ። ጥልቅ ወደ ሆነው ወደ እግዚአብሔር አሳብ ለመጠጋት ብዙ ጊዜ አንፈልግም ። ዳር ዳሩን መዞር እንወዳለን ። ጥልቅ ወደሆነው ክርስትናም መዝለቅ አንሻም ። ወደ ጥልቁ ሕይወት ካልገባን ልናተርፍ አንችልም ። በራሳችን ሞክረን ካልቻልን ጌታን መታዘዝ አለብን ። እንደ ቃሉ ማድረግ ያተርፈናል እንጂ አያከስረንም ። ውለታውና እየበደልነው እንኳ የሚያደርግልን ቸርነት ለንስሐ ሊጋብዘን ይገባል ። በእግዚአብሔር ፍቅር የማይነካ ሰው ጉደኛ ነው ። ክርስቶስን አስተካክለን አንወደውም ፣ አስበልጠን እንጂ ። ስለዚህ ሁሉን ትተን ልንከተለው ይገባናል ።
ዳር የወጣነው በምን ይሆን ? አገሩ ሊለወጥ የማይችል ነው ብለን ዳር ወጥተን ይሆን ? አገልግሎቱ የማይሰምር ነው ብለን ዳር ላይ ቆመን ይሆን? በብዙ ነገሮች ተስፋ ቆርጠን ፣ የራሳችንን ግምት እያዳመጥን ይሆን ? ጌታ ግን ገና ነው ፣ ወደ ጥልቁ ፈቀቅ በሉ ፣ የተዋችሁትን ሥራ ጀምሩ ይላል ። ያ ነገር የሚገኝበት ዕድሜውም ፣ ጉልበቱም ፣ ተፈላጊነቱም ፣ … አብቅቶ ይሆናል ። እግዚአብሔር የሚመቸው የእኛ ነገር ሲያልቅ ነው ። ፈቀቅ ማለት መልካም ነው ። እልፍ ሲሉ እልፍ ይገኛል ።
አምላኬ ረዳቴ ሆይ ፣ ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ ። ተስፋ መቊረጥን ሳልጨርሰው እንደገና ትንፋሽህን ዝራብኝ ። ደስ በማያሰኙ ቀኖችም አንተን እንዳይህ እርዳኝ ። በገባዖን ሰማይ ፀሐይን ያቆምህ ለእኔም አድርግልኝ ። ውጊያዬን ሳይሆን ውጊያህን እንድዋጋ እርዳኝ ። አለማመኔን አግዘው ። ለዘላለሙ አሜን ።
የዕለቱ መና 23
ግንቦት 23 ቀን 2011 ዓ.ም.
ዲአመ
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ

አዳዲስ መጻሕፍት

ትርጉሙ:- ቀይ ዕንቈ

ለምድራችንና ለአገልግሎታችን በረከት የሆነ መጽሐፍ
የመጀመሪያ እትም ጥቅምት 2016 ዓ.ም

1ኛ ጢሞቴዎስ ትርጓሜ – ክፍል አንድ

የመጀመሪያ እትም ሐምሌ 2013 ዓ.ም

ምክር አዘል መጽሐፍ

የመጀመሪያ እትም