የትምህርቱ ርዕስ | ፈቃደ እግዚአብሔር

“በእግዚአብሔር ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ ፥ በኤፌሶን ላሉት ቅዱሳን በክርስቶስ ኢየሱስም ላሉት ምእመናን ፤ ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን ።” ኤፌ. 1 ፡ 1-2 ።

ለብዙ ሰዎች ያለቀስንላቸው ለሞታቸው ሳይሆን ለዕቅዳቸው ነበር ። የሰርጋቸው ዕቃ ሳይመለስ ለልቅሶአቸው ሲሆን ፣ ጨቅላ ልጆቻቸውን ሳያሳድጉ አደራ ትተው መሄዳቸው ፣ የጀመሩትን ቤት ሳይፈጽሙ ሕንፃ ገትረው ማለፋቸው ያሳዝናል ። አብረው ለማርጀት ተጋብተው በጫጉላው ሲሞቱ ፣ ልጆቼን አሳድጌና ድሬ እያሉ ገና በሕፃንነታቸው ሲለዩ ፣ ቤቴን ጨርሼ ከወዳጆቼ ጋር አመስግኜ ብለው ሲያቅዱ ከቤቱ ቀድመው ሲያልቁ ልብ ይሰብራል ። ሰው ስለ ቅድሙ እንጂ ስለ ኋላው በእርግጠኝነት መናገር አይችልም ። ብዙዎች ለዓመት አቀዱ ፣ ቀናቸው ግን ዛሬ ነበረ ። ብዙዎች ለከርሞ ተለሙ ፣ አዳራቸው ግን በሰማይ ነበረ ። ብዙዎች ለፍጻሜው ቀጠሮ ያዙ ጅምራቸው ላይ መሸ ። ያላለቁ መንገዶች ፣ ያላለቁ ቤቶች ፣ ያላለቁ ውጥኖች ፣ ያላለቁ ራእዮች … በየስፍራው ይታያሉ ። ዛሬ ላይ የመሸባቸው ፣ አለሁ ሲሉ የሌሉትን ሰዎች ስናይ ወደን ባንታዘዝለትም በግድ የሚገዛን አንድ ፈቃድ እንዳለ እንረዳለን ። በእኛ ዘመን ላይ ከተለመዱ ሰላምታዎች አንዱ “ሰላም ነህ ?” የሚል ነው ። ሁላችንም ለምዶብን እንላለን ። ሰላም ግን ክርስቶስ ነው ፣ እኛ ሰላም አይደለንም ። “ደኅና አድርህ?” መባል ይገባናል ። ምላሹ ደግሞ ከጥያቄ ይከፋል ። “አለሁ” የሚል ነው ። ያለነው ግን በእግዚአብሔር ነው ።

የእግዚአብሔር ፈቃድ ሉዑላዊ ፈቃድ ነው ። ነገ ላይ በምድር ለመኖራችን እርግጠኛ ሁነን ቀጠሮ እንይዛለን ፣ ይህ ቀጠሮ ተሰርዞ በሰማይ እንድንውል የሚያደርገን ፈቃደ እግዚአብሔር ነው ። የሰው ልጅ ከፈቃድ ጋር የተፈጠረ ክቡር ፍጥረት ነው ። ፈቃደ እግዚአብሔርም የእግዚአብሔር ክብር ነው ። ፈቃደ ሰብእ በፈቃደ እግዚአብሔር ይታረማል ። ክፉዎች ቢከማቹ ፣ አራዊት አፋቸውን ቢከፍቱ ፣ በላተኞች ጥርሳቸውን ቢስሉ ፈቃደ እግዚአብሔር ግን “ልጆቼን አትንኩ” ብሎ ያግዳቸዋል ። ፈቃደ እግዚአብሔር ጠላቶቻችንን በማቆሙ ደስ ካለን የእኛንም ማስተዋል የሌለበት ጉዞ ቢያስቆመው ደስ ሊለን ይገባል ። የማይለወጥ የእግዚአብሔር ፈቃድ አለ ። በጊዜ ውስጥ የሚባርከን የእግዚአብሔር ፈቃድ አለ ። ያ ፈቃድ እንኩ ብሎ ይሰጣል ፤ ባለጠጋ ነውና ። ያ ፈቃድ አይሰጣችሁም ብሎ ይከለክላል ፣ ፍቅር ነውና ። ያ ፈቃድ ጠብቁ ብሎ ትዕግሥትን ያለማምዳም ፤ አስተማሪ ነውና ። ይሞታሉ ያልናቸው መኖራቸው ፣ ይኖራሉ ያልናቸው ማለፋቸው የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው ።

ሐዋርያው በዚህ ክፍል ላይ ፈቃደ እግዚአብሔርን የጠቀሰው ለአገልግሎት መጠራቱን ነው ። በሌላ ስፍራም ግድ ደርሶብኝ ነው ይላል ። ግዳጅ መጥቶብኝ ነው ማለቱ ነው ። መንግሥት አገር አደጋ ውስጥ በሚገባበት ሰዓት ግዳጅ ይወስዳል ። ግዳጁ ሙያን ብቻ ሳይሆን ሕይወትን ለመስጠትም ይጠይቃል ። እንቢ የሚልም የለም ። ለአገር መኖርም መሞትም የዜጋው ግዴታ ነውና ። ማን በሞተበት አገር ማን ይኖራል ? በዚህ ግዳጅ ላይ የሚሞትም ሞቱ ተራ ሞት ሳይሆን መሥዋዕትነት ይባላል ። ሐዋርያው ጳውሎስም ወንጌልን የእግዚአብሔር ግዳጅ ይላታል ። እኛ አገልጋይ ይሆናሉ ብለን የምንጠብቃቸው ሰዎች ወደ ዓለም ሲሄዱ የማይጠበቁ ሰዎች ደግሞ አገልጋይ ይሆናሉ ። ሽፍታው ባሕታዊ ፣ ሌባው ሰባኪ ሲሆን መቀበል እየከበደን ስም እናወጣላቸዋለን ። “ስቪል ቄስ እኔ ብቻ ነኝ” ብለዋል አንድ አባት ። የጦሩ ንስሐ አባት ሁኖ ሌላው ቄስ ሁሉ እስከ ሻምበል ማዕረግ አግኝቷል ። በዚያ በወታደር ከተማ የወታደራዊ ማዕረግ ያላገኙ ቄስ በአደባባይ ሲናገሩ፡- “ስቪል ቄስ እኔ ብቻ ነኝ” አሉ ።

ነገር ግን ፈቃደ እግዚአብሔር አህያ ሊፈልግ የወጣውን ሳኦልን ንጉሥ ያውም የመጀመሪያው የእስራኤል ንጉሥ ፣ ቤተ ክርስቲያንን ሊያሳድድ የዘመተውን ጳውሎስን የቤተ ክርስቲያን ማኅቶት በማድረግ ማርኳል ። በቤተ ክርስቲያን ታሪክም እነ አባ ሙሴ ጸሊም ፣ እነ ማርያም ግብጻዊት ፣ እነ ቅዱስ አውግስጢኖስ ከዓለም በረሃ ወጥተው የእግዚአብሔር አገልጋይ የሆኑ ናቸው ። እገሌ እኮ ወታደር ነበረ ፣ እገሌ አሳሪ ፈቺ የነበረ ዛሬ ደግሞ አገልጋይ ነኝ ይላል እንላለን ። በሰው መመለስ የማይደሰት ሰይጣን ብቻ ነው ። እግዚአብሔር ታሪክን በመለወጥ ሲመሰገን የሚኖር ነው ። የውርደት ዕቃ የሆነውን የክብር ዕቃ ማድረግ የሁልጊዜውም ተግባሩ ነው ። ሐዋርያው ጳውሎስን የመጣባቸው ፈሪሳውያን ከዳተኛ ይሉታል ፣ የመጣላቸው አንዳንድ ክርስቲያኖች ደግሞ እንደ ባንዳ ይቆጥሩታል ። የቀደመው ታሪኩ ዛሬ ያገኘውን ጸጋ እንዳያዩ መሰናክል ሆነባቸው ። ሰው ሁነው በሰው መለወጥ ካላመኑ ሰው አልሆኑም ማለት ነው ። ፍጹም ሁኖ የጀመረ ማንም የለም ። ፍጹም ሁኖም የሚሞት የለም ። ፈቃደ እግዚአብሔር የጠራቸውን አገልጋዮች እኛ መክሰስ አይገባንም ። “እግዚአብሔር የመረጣቸውን ማን ይከሳቸዋል?” ሮሜ. 8፡33።

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ኤፌሶን ትርጓሜ 1

ጥር 17 ቀን 2014 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ

አዳዲስ መጻሕፍት

ትርጉሙ:- ቀይ ዕንቈ

ለምድራችንና ለአገልግሎታችን በረከት የሆነ መጽሐፍ
የመጀመሪያ እትም ጥቅምት 2016 ዓ.ም

1ኛ ጢሞቴዎስ ትርጓሜ – ክፍል አንድ

የመጀመሪያ እትም ሐምሌ 2013 ዓ.ም

ምክር አዘል መጽሐፍ

የመጀመሪያ እትም