የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ፈቃደ እግዚአብሔር

“በበጎ ፈቃዱ እንደ ወደደ ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ለእርሱ ልጆች ልንሆን አስቀድሞ ወሰነን ።” ኤፌ. 1 ፡ 5 ።

አንድ የቆየ ዝማሬ ከነዜማው ትዝ ይለኛል ።

ማንም ሳያስገድድ በራስ ፍላጎት ፣
ምን ዓይነት ፍቅር ነው ራስን መስጠት ?!
ወየው ፣ ወየው መቱት ያን መድኅን ።

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በበጎ ፈቃዱ እንደ ወደደ ይለዋል ። እኛን ለመውደድ ፣ ለእኛ ለመሞት ፣ ራሱን ለመስጠት ያስገደደው የእኛም ቁምነገር ፣ የፈጣሪነትም ግዳጅ አልነበረም ። መፍጠር የእርሱ ሥልጣን ሁኖ እንደ ፈጠረ ፣ መፍረድም ሥልጣኑ ነውና ፈርዶ መቅጣት ይችል ነበር ። እርሱ ግን ፍትሑን ሙሉ አድርጎ ፣ ፍቅሩንም ገልጦ አዳነን ። ቃልን ለነቢያት ቢሰጥ አምላክነቱ ነው ፤ እርሱ ግን ንስሐ ግቡ የሚል ሰባኪ ሁኖ መጣ ። መሥዋዕትን ተቀብሎ ለዓለም ምሕረት ቢልክ የሚገባው ትልቅነቱ ነው ። እርሱ ግን መሥዋዕቱም ራሱ ፣ አሳራጊ ካህንም ራሱ ሁኖ መጣ ። በዙፋኑ ሁኖ ኃይልና ብርታትን ቢሰጥ የማይጠረጠር አሠራሩ ነው ። እርሱ ግን የእኛን መስቀል ተሸክሞ ደከመ ። ንስሐ ግቡ እያለ ኃጢአታችንን በመስቀል ላይ ተሸከመ ። መሥዋዕትን እያቀረበ ሥጋዬን ብሉ ደሜን ጠጡ ብሎ ሰጠን ። አዳም በበደለኛነቱ ፣ ጴጥሮስም በወዳጅነቱ መስቀሉን ያግዙት ዘንድ አልፈቀደም ፣ ራሱ መስቀሉን ተሸክሞ ወደ ቀራንዮ ኮረብታ ወጣ ። ይህ ሁሉ የሆነው እንደ ወደደ ነው ።

ቅዱስ ኤፍሬም፡- “እስመ በፈቃዱ ወበሥምረተ አቡሁ ወመንፈስ ቅዱስ መጽአ ወአድኃነነ” ይላል ። እግዚአብሔር አንድ ፈቃድ አለው ። ፈቃዱም በጎና ምንም አስገዳጅ ኃይል የሌለበት ነው ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም የመጣው በአንዲት የሥላሴ ፈቃድ ነው ። አብ ለራሱ ልብ ሁኖ የወልድና የመንፈስ ቅዱስ ማሰቢያቸው ፣ ማቀጃቸው ፣ መወሰኛቸው ነው ። የሥላሴ አካላት ሦስት ቢሆኑም እያንዳንዱ አካል የራሱ ልብ ፣ ቃልና እስትንፋስ አለው አይባልም ። ይህ ሦስት ፈቃድን ፣ ሦስት ግብርንና ሦስት ህልውናን ያመጣል ። ሥላሴ በኩነታት ሦስት ቢሆኑም በኩነታት መገናዘብም እየተዋሐዱ ፣ አንድ ፈቃድ ፣ አንድ ተግባር ፣ አንድ ሕይወት አላቸው ይባላል ። በዚህም አንዱ አካል ያለ ሌላኛው አካል አልኖረም ፤ አይኖርምም ።

እግዚአብሔር ፈቃዱ በጎ ነው ተብሏል ። ከአፍቃሪነቱና ከቅዱስነቱ የሚወጣው ፈቃዱ በጎ ነው ። ይህ በጎ ፈቃድም ዘመን የወለደው ፣ ሁኔታ ያመጣው ሳይሆን ከአካሉና ከባሕርይው ጋር ለዘላለም የኖረ ነው ። ሴቶች ልጅ ሁነው ያድጋሉ በዚህም ብላቴና ይባላሉ ። ለአቅመ ሔዋን ሲደርሱም ደናግላን የሚል መጠሪያ ያገኛሉ ። አብረዋቸው የተወለዱ ካሉም እኅት አበባ የሚል መጠሪያ ይቀበላሉ ። ሲያገቡ ሚስት ይባላሉ ። ሲወልዱ እናት ሁነው አንጀተ ስስ ይሆናሉ ። እግዚአብሔር ግን በጎ ፈቃድና ፍቅርን የመላእክትና የሰው መፈጠር አላመጣለትም ። እርሱ በበጎ ፈቃዱ ፈጠረን እንጂ ። የእግዚአብሔር ፈቃድ በጎ መሆኑን በነቢዩ ተናግሯዋል ። “ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ አውቃለሁ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም” ኤር. 29፡11። ይህ ቃል የተላከው በባቢሎን በምርኮ አገር ኑሮ ለጀመሩት እስራኤላውያን ነው ። ወደ አገራቸው ቶሎ የሚመለሱ መስሏቸው ነበርና ተረጋግተው እንዲቀመጡ የተላከ መልእክት ነው ። በግዞትም ፣ በቅጣትም ውስጥ እግዚብሔር ለእኛ ያለውን በጎ ፈቃዱን አይለውጥም ። እርሱ በቀል የሆነ ቅጣት ፣ ማሳደድ የሆነ ፍርድ የለውም ። እርሱ በምርኮም ፣ እርሱ በኃጢአታችን ውጤት ውስጥ ስናልፍም በጎ አሳብ አለው ።

የሰው ፈቃድ ሥጋ ፣ ዓለምና ሰይጣን የሚባሉ ፈታኞች ስለሚጫኑት በጎነት ያጣል ። ቁሳዊነት ላይ እንዲመሠረት ሥጋ ፣ ብልጭልጭነት ላይ እንዲመሠረት ዓለም ፣ ክህደት ላይ እንዲመሠረት ሰይጣን ይጫኑታልና የሰው ፈቃድ በጎ ላይሆን ይችላል ። ቁሳዊነት ሲጫን ስግብግብነት ፣ በቃኝ አለማለት ፣ ነግዶ አትርፎ አለማመስገን ፣ ሌላው ሞቶ እኔ ልኑር ባይነት ይከሰታል ። ይህ ስግብግብነት አገርን ያፈርሳል ። ሁሉ ካልተደጋገፈ ፣ እኩል ካልተጠቀመ አገር እየተናጠ ይመጣል ። ባለጠጋው ድሀውን እንደ ስጋቱ ፣ ድሀው ባለጠጋውን እንደ ጠላቱ ያያል ። ተረጋግቶ ለመብላት የጎረቤትን ረሀብ ማስታገሥ ያስፈልጋል ።

ብልጭልጭነት ሲበዛ የላይ ማንነት እየነገሠ ፣ ውስጣዊ ሰውነት እየወደቀ ይመጣል ። ሰዎች ለፀጉራቸው እንጂ ለቅንነታቸው ፣ ለፊታቸው እንጂ ለልባቸው የማይጨነቁ ይሆናሉ ። የሰው ግንኙነትም የላይ የላይ የጥርስ ጨዋታ ያለበት ይሆናል ። ብልጭልጭነትም ሰውን የተዋበ ሬሳ ፣ ተንቀሳቃሽ ሙት ያደርገዋል ። ክህደትም እግዚአብሔርን በመካድ ይጀምራል ። ከሀዲ የሰውን ዋጋ አያውቅም ። በሰው ሞትም ይነግዳል ። ከሀዲ ቀጥሎ ወላጆቹን ይክዳል ። መርዳት እየተሳነው ይመጣል ። መልካም ያደረጉለትንም ከማመስገን ግዳጃቸው እንደሆነ ያስባል ። የራሱን የግሉ ፣ የሌላውን የጋራው እንደሆነ ያስባል ። ወይ እምነት ወይ ይሉኝታ ፣ ወይ ሰብአዊነት ወይ መንፈሳዊነት የሌለው የሚለሰልስ ቋጥኝ ይሆናል ። ለመስጠት ስንኩል ፣ ለመቀበል ስልጡን ይሆናል ። ሁሉ ለእኔ ይኑር ባይነት ፣ በልቶ ካጅነት ፣ አገር ሻጭነት ይወለዳል ። ይህ የሰይጣን ቀጥተኛ ፈተና የሚወልደው ነው።

የሰው ፈቃድ ይህ ሁሉ ፈተና ያለበት ነው ። የእግዚአብሔር ፈቃድ ግን በጎ ነው ። ዘላለሙን ያየልን ፣ ውስጣዊ ማንነታችን ላይ ያተኮረ ፣ በአምልኮት የተቃኘ ሕይወት እንዲኖረን የሚሻ ነው ። ይህ በጎ ፈቃድ የመደበልን እንደ አቤል ሰማዕትነት ከሆነ ሳንወልድ ስማችን ሲጠራ ይኖራል ። እንደ ኖኅ ዓለም ሁሉ ጠፍቶ ብቻ መትረፍ ከሆነ በአምላክ ፍትሕ ልብ ያርፋል ። ከተማ ተቃጥሎ ፣ ቤት አልባ ሁኖ እንደ ሎጥ መውጣት ከሆነ ያለኝና የሚኖረኝ እግዚአብሔር ብቻ ነው ያሰኛል ።

የኤፌሶን መልእክት ትርጓሜ /9

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
የካቲት 11 ቀን 2014 ዓ.ም.

እባካችሁ ለሌሎች አካፍሉት

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ