የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ፍርሃት አያልቅም 2

ደቀ መዛሙርቱ ብዙ የፍርሃት ታሪኮችን አስተናግደዋል። የማዕበሉን ያህል ከማዕበሉ የሚያድናቸውን ጌታ ፈርተዋል። የክፉዎችን ያህል ደጎችን መፍራት ከባድ ፈተና ነው።  የጎዱን ሰዎች ትልቁ ጉዳታቸው፣ ያስፈሩን ሰዎች ከፍተኛው ወንጀላቸው ደጎችን እንዳናምን ማድረጋቸው ነው ። ደቀ መዛሙርቱ የሚያጠፋቸውን ማዕበል የፈሩትን ያህል  የሚያድናቸውን ጌታ ፈሩ ። “እባብ ያየ በልጥ ይበረግጋል” ይባላል። እባብ ያየ ሁሉም ነገር እባብ  ሆኖ ይታየዋል። እባብን የምንፈራው ነድፎን አይደለም። ውሻን በምን ይፈሩታል ? ቢሉ  በአጥንት ይባላል። ክፉዎችን የምንፈራቸው ስለ ደረሱብን ብቻ አይደለም፣ ወዳጆቻቸውን እንዴት ገድለው እንደ ቀበሩ በማየትም ነው ። ሰውን በሰው እንወደዋለን፣ ሰውን በሰው እንጠነቀቀዋለን።

አንዳንድ ሰዎች ለጥቅም ቀርበውን ዘርፈውን ሄደው ሊሆን ይችላል፣ ሁሉም ሰው ግን ለጥቅምና ለዝርፊያ እንደ ቀረበን ማሰብ የለብንም። አንዳንድ ሰዎች እየሳቁ ገድለውን፣ እየሸነገሉ ቀብረውን ይሆናል። ሁሉም ሰው ግን የሚስቅልንና የሚስመን ሊያታልለን አይደለም። ሁሉን መፍራት የሕይወት ትልቅ ፈተና ነው። ገጣሚው እንዳሉት እየሆነ ነው:—

ፍቅርን ፈራን መቀራረብ ፈራን
እንዳልተዛመድን እንዳልተዋለድን
ፈርተን መዋደድን ጉርብትናን ናድን
እኛነትን ትተን እኔነትን ለመድን
“ፈራን”
ፍቅርን ፈራን ጥላቻን ሠራን ብቸኝነት ጠራን
በጋራ ቤታችን አጥር ድንበር ሠራን
“ናቅን”
በልዩነት ደምቀን ያልኖርን ያህል አንድም ቀን
እልህ ተናነቅን
“ናቅን”
መቻቻልን ናቅን ለፀብ አሟሟቅን
ለዓመፅ ስንነሣ ለሰላም ወደቅን
አገር ስትቃጠል ከዳር ሆነን ሞቅን::

መውደዳችንን የምንፈራው ጊዜ ጥቂት አይደለም ። ወደን ከመጎዳት ጠልተን መጠንቀቅ ይሻላል እያልን የቀን ቅዠት እንቃዣለን። የጥላቻን ያህል ፍቅር እያስፈራን ነው። በፍርሃት ዘመን የእግዚአብሔር ፍቅር ፣ ሌሎችን በነጻ መውደድ የመሻገሪያው ድልድይ ነው።

ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መስከረም 28 ቀን 2017 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ