የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ፍርድህ የጠራ

እንደ ውቅያኖስ ምሕረትህ የሰፋ ፣ እንደ ባሕር አሠራርህ የጠለቀ ፣ እንደ ምንጭ ፍርድህ የጠራ ፣ እንደ ወንዝ ርቀህ የምትሄድ ፤ የመልክን ቀለም ፣ የባለጠጎችን ሽቱ ፣ የጎበዞችን ቁመና አይተህ የማትመርጥ ፤ በልቡ ጉልበት የሰገደልህን የምትወድድ ፤ በመቅደስህ የቅኔ ማዕበል ፣ በማደሪያህ የምስጋና ጅረት የሚፈስልህ ፤ እኔ አንተን ብሆን የማልወደውን እኔን የወደድህ ምስጋና ይገባሃል ። ዛሬ እንደ ትላንት እየመሰለኝ ፣ መምሸት መንጋቱም ግዴታው እንደሆነ እያሰብሁ ፣ ክረምትና በጋ ሲፈራረቅ ልማዱ ነው እያልኩኝ ያንተን ስጦታ ማቃለሌ ፣ አዲሱን አሮጌ ማድረጌ ከቶ ለምንድነው ? የዘመን ክፋት ደግነትህን ፣ ማለቂያ ያጣው የሰው ተንኮል አምላክነትህን ፣ ድንበር ገፊ ድሀ አጥፊዎች ፈራጅነትህን የሚያስረሱኝ እስከ መቼ ነው ? የጥበበኞች ጥበብ በፊትህ ሞኝነት ፣ የኃያላን ጉልበትም ድካም ነው ። ጥበበኛውን በመናኛ ነገር ታስጨንቀዋለህ ፣ ኃያል ነኝ ያለውንም በአንድ ቀን ትኩሳት ታንበረክከዋለህ ። አንተ በፍጡር ፊት ግርማዊ ነህ ፣ ባንተ ፊት ግርማዊ የሆነ ማንም የለም ። የአስደንጋጮች ማስደንገጥ በአንተ ዘንድ ከንቱ ነው ። የጨካኞች ፉከራና ዘመቻ እንደ ኢምንት ነው ። ያላንተ የቆነጁ የሬሳ ውቦች ናቸው ። በራስህ የታወቅህ አንተ ነህ ። ብናውቅህ ራሳችንን እናውቀው ነበር ። ባናውቅህ ግን አንተ ራስህን ታውቃለህ ። የለህም ሲሉህ አትሰጋም ፣ መቼም አትታጣምና ። ይህ ሁሉ ክብር ያለህ የእኔ አምላክ ነህ ። ምስጋና ይገባሃል ።
ያለ ቃልህ ዕውር ነኝ ። ያለ መሪነትህ እግሬም አያደርሰኝ ። ልቤን ካለፈወስከው አፌ የምስጋና በረሃ ነው ። ጆሮዬን ካልዳሰስከው የእሾህ መከማቻ ነው ። ያየሁትን መውረስ አሁንስ ይቅርብኝ ። ያየህልኝን አውርሰኝ ። ከአገር አስወጥተህ አገር የምትሰጥ ፣ ወዳጅ ወስደህ ወዳጅ የምትሆን ነህ ። ሳሙኤል ልቤ ኤልያብን ሲመርጥ ልበ ሥላሴ ግን ዳዊትን ምረጥልኝ ። ባለ ቁመናው ቀርቶ ባለ በገናው ይሁንልኝ ። መልክ ያለው ሳይሆን እግዜር ያለው ይሰጠኝ ። ቅቤ አፍ ያለው ሳይሆን ዝማሬ አፍላቂው ይደረግልኝ ። የአሳብ መንገደኛ የእግር እስረኛ ነኝ ። በአሳቤ ስንቱ ገደልኩ ፣ ሁሉን ጨርሼ እኔ ብቻ ቀረሁ ። ዓለምን እንኳን ለእኔ አልሰጠሃት ። ዓለምን በእፍኝህ የያዝሃት አንተ አዋቂ ነህ ። አንተ የሕይወት ግብ ሁነኝ ። አንደበቴን እንደ ተቀደሰ ምንጭ አጣፍጥልኝ ፣ በልቤ ከተማ አንተ ንገሥ ። ጆሮዬም ናፍቆቷ አንተ ብቻ ሁንላት ። የሰማሁትን ሳልፈይደው ሌላ መስማት ያምረኛል ።
አምላኬ እግዚአብሔር ሆይ ለለመኑህ ስጣቸው ። የሻቱትን የልባቸውን ምኞት ፈጽምላቸው ። የሚያንኳኩ ደጅህ ላይ እንዳይቀሩ ክፈትላቸው ። ከዘመን ትኩሳት አንተ ጠልላቸው ። አባራሪውን አባርላቸው ። የተሳሳተውን መንገድ የምንጠቁም ነንና መንገድ መሪ ሁነህ ትውልድን አድን ። ወደ አንተ መጥቶ በባዶ የሚመለስ አይኑር ። ስምህን ጠርቶ ማንም አይፈር ። በልቅሶ የዘራ በደስታ ይጨድ ። የሆዱን የነገረህ በአደባባይ ልመናው ይመለስለት ። ከቀን ወራሪ ፣ ከሌሊት ሰባሪ ማዳን ትችልበታለህ ። እኔ ያላንተ የተራቆትኩ ነኝ ። እንኳን በመዘናጋቴ በመንቃቴም የተኛሁ ነኝ ። ንቁ ሆይ ጠብቀኝ ። በሳጥኔ ያስቀመጥሁህ ወርቄ አንተ ነህ ። ለችግሬ ቀኔ ያልኩህ አማኑኤል ሆይ ክበር ። እሬትነቱን በማር የምልሰው ዓለም ሲያጓጓኝ ይገርመኛል ። ደሊላ ዓለም የልቤን ምሥጢር አስጨርሳ እንዳትገድለኝ ወልድ ሆይ አንተ ሰውረኝ ። በልዑልነትህ እየፈራሁህ ፣ በዝምድናህ እያቀረብሁህ የሠራኸው ሲፈርስ ለምን ዝም አልክ እልሃለሁ ። ዛሬም ቅኑ እየፈረሰ ፣ ምስኪኑ እየተደቆሰ ነው ። የኃያላኑን በር አንተ ክፈት ። ጽኑዓን ነን የሚሉትን በክብርህ መልስ ።
ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ አንድ አምላክ ለሚሆን ክብር ምስጋና ይገባል ፤ ከልባችን እስከ አርያም ፣ በማይፈጸም ዘመን ለዘላለሙ አሜን ።
የነግህ ምስጋና 17
መጋቢት 18 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ