ያለፈውን በትምህርትነቱ ፣ ነገን በብልጫነቱ ፣ ዛሬን ግን በተጨባጭነቱ ውደደው ፡፡ ከትላንት ከመማር በቀር ወደ ኋላ መልሰህ ማደስ አትችልም ፡፡ ትላንት ላይ መዘግየት አመድ ላይ እንደ መንከባለል ነው ፡፡ መቆሸሽ እንጂ መንጻት የለውም ፡፡ ታሪክን ትማረዋለህ እንጂ አትቀየመውም ፡፡ ዛሬ ከትላንት የተሻለ እንደሆነ ነገም ከዛሬ የተሻለ ይሆናል ፡፡ ከትላንት ዛሬ እውቀትህ ጨምሯልና ዛሬ ከትላንት ትሻላለች ፡፡ ነገም ከዛሬ የተሻለ ታውቃለህና ብልጫ አላት ፡፡ ነገ እንደፈራኸው አይደለም ፣ ትላንት ላይ ዛሬ ነገ ነበረች ፡፡ እንደ ፈራሃት ግን አይደለችም ፡፡ ቀኑ ላይ ኃይል አለ ፡፡ እግዚአብሔር በቦታው አቅም ይሰጥሃል ፡፡ ራስህን እንደ ገመትከው አይደለህም ፡፡ በአስቸጋሪ ቦታዎች ላይ አቅም ይሰጥሃል ፡፡ በክፉ ቀኖች ቆራጥ ያደርግሃል ፡፡ ዘረኝነት የሁለት ነገር ችግር ነው ፡፡ የበታችነት ስሜትና የመጨረሻው የግብረ ገብ ውድቀት ነው ፡፡
የከሰርከውን በገንዘብ እንደ ተማርከው ትምህርት ቁጠረው ፡፡ ያገኘኸውን እንደምታጣው አድርገህ ያዘው ፡፡ የምትመኘውን በትዕግሥት ጠብቀው ፡፡ ወደፊት ምን ይመጣ ይሆን ብለህ አትጨነቅ ፡፡ የፈራኸው ቢመጣም ከዚህ በላይ አትታወክም ፡፡ ባልመጣ ቀን የመጣውን ቀን አትረብሸው ፣ የመጣውን ቀን ትተህም ባልመጣ ቀን አከናውናለሁ አትበል ፡፡ አንተ የአሁን ሰው ነህ፡፡ ስትተኛ ለመንቃትህ ፣ ስትወጣ ለመመለስህ ምንም ዋስትና የለህም ፡፡ በማይረቡ ነገሮች አእምሮህን አታጣብ ፡፡ ችግሮችን ከምንጫቸው ትተህ ከወራጁ ከገደብህ ይደገማሉ ፡፡ እነዚያን ቀኖች ካልረሳህ ዛሬን ይረብሻሉ ፡፡ ፍቅር የሰጡህን ሰዎች ካላመሰገንህ ነፍስህ በውለታ እስረኛ ትሆናለች ፡፡ ሞተህም የምትወቀሰው አደራ በማጥፋትህ ነውና ታማኝ ሁን ፡፡ የሞተ ሰው የገደለውን ያውቃል ፣ ነገር ግን ነቅቶ አይከስስም ፡፡ ትልቁ ዳኛ ጋ እየሄደ ነውና ፡፡ እግዚአብሔር ከተናገረልህ አንተ ዝም በል ፡፡ እግዚአብሔር ሲናገር አንተ ከተናገርህ ታበላሻለህ ፡፡
ሰዎች ሲጠሉህ ጠባይህ ከፍቷል ወይም ጠባያቸው ከፍቷል ማለት ነው ፡፡ ራስህን ስለማሻሻል እንጂ ሰዎችን ለመለወጥ ሥልጣን ያንተ አይደለም ፡፡ ከመጸለይ ወጥተህ በምክሬ ሰውን እለውጣለሁ ብለህ አትታገል ፡፡ እንኳን ያንተ ምክር የእግዚአብሔር ቃልም ያለ እርሱ ረዳትነት አይፈጸምም ፡፡ በሌሎች ላይ እጅህን አትጠቁም ፣ እኔ እያልህ ግን ንስሐ ግባ ፡፡ ቂም መሸነፍ ነው ፡፡ የተወረወረው ጦር ነፍስህን ሲያጠቁራት እርሱ ቂም ይባላል ፡፡ የጊዜ እንጂ የሰው ጎበዝ የለውም ፡፡ ከተመቻቸ የማይማር ደደብ ፣ መንገድ ካገኘ የማይበለጥግ ድሀ የለም ፡፡ ይህን ዓለም ለመልቀቅ 15 ደቂቃ ቢቀርህ ምን ታደርጋለህ ? ያንን ነገር አሁን ፈጽመው ፡፡ ሥራ የማንሠራው ጊዜ ያለን ስለሚመስለን ነው ፡፡ ዘመኑ አጭር መሆኑን አስተውል ፡፡
የተቆረጠ ቅርንጫፍ ከዚያች ደቂቃ ጀምሮ እንደሚጠወልግ ሰውም ከተወለደበት ቀን ጀምሮ እየሞተ ነው ፡፡ የወንዝ መነሻና መድረሻ አልተለያዩም ግን አይተያዩም ፡፡ የሚጸልዩልህ ሰዎችህ ልክ እንደዚህ ናቸው፡፡ መመኘት ኃጢአት አይደለም ፣ ምኞትን ግን የደስታ ጥግ ማድረግ እርሱ ኃጢአት ነው ፡፡ የምትኖረው ስላልተሞከረ ሳይሆን እግዚአብሔር ጣልቃ ስለገባና ሕይወትህን ስላዳነ ነው ፡፡ ያለ ወላጅ በማደግህ አትዘን ፣ ያለ ወላጅም የሚያሳድግ አምላክ እንዳለ እያሰብህ ተደነቅ ፡፡ ምኞት ተግባር ካልሆነ የማይሞቅ እሳት ነው ፡፡ ማሰብ መልካም ነው ፡፡ አሳብን ግን ተግባር አድርጎ መኖር ከባድ ነው ፡፡ በትር ካልሰነዘሩበት ተልከስካሽ ዞር አይልም ፣ ሥልጣንም ካልሠሩበት የደነዘ ቢላዋ ነው ፡፡ ግድግዳ ላይ የተሳለ አንበሳ እንደማያስፈራ ተግባር የሌለው ምኞት እንዲሁ ነው ፡፡ በደስታ መፈንጠዝ ፣ በመከራ መጨነቅ ሁለቱም የቀላልነት ጠባይ ነው ፡፡ በአንድ ማሳ እህልና እንክርዳድ ፣ ተክልና አረም አሉ ፡፡ እንክርዳዱ እህሉን ፣ አረሙ ተክሉን ይመስላሉ ፣ ያህላሉ ፡፡ የሚለዩት በማደጋቸው ሳይሆን በጥቅማቸው ነው ፡፡ ሰዎች እንዲወዱህ እንጂ ፍጹም አድርገው እንዲያዩህ አትፍቀድላቸው ፡፡ እንዲያምኑህ እንጂ እንዲያመልኩህ በጀ አትበላቸው ፡፡ መጀመር ፈተና እንዳለው የተጀመረውም ያለ ፈተና አይፈጸምም ፡፡ ከግል ደስታ ይልቅ ለወል ደስታ ቅድሚያ ስጥ ፡፡
ራስህን ካድ እንጂ ራስህን አትጣል ፡፡ አገርህ ያልተጠቀመችበት እውቀትህ ርግማን ነው ፡፡ ለኪስህ እንጂ ለኅሊናህ መኖር ካልጀመርህ ገና አልተወለድክም ፡፡ ብዙ መኖር ሳይሆን ብዙ መሥራትን ተመኝ ፡፡ ሁልጊዜም የሚያስፈልግህ ትዕግሥት ነው ፡፡ ማፍቀርህም ትዕግሥት ይኑረው ፡፡ ጨው ያለፈውን ሕመም የሚጠግን ፣ የዛሬውም ምግብ የሚያጣፍጥ ፣ ለነገ እንዳይበላሽ የሚከላከል ነው ፡፡ ፍቅርም ያለፈውን ስብራት ይጠግናል ፣ የዛሬውን በረከት እንድታመሰግንበት ያደርጋል ፡፡ የነገውን መንገድ ብርሃን ያደርጋል ፡፡ አሜን ካለ ማለት በረከት ይቀራል ይባላል ፡፡ አሜን ያሰኝልን፡፡
የደስታ ቋጠሮ/18
ሐምሌ 22/2010 ዓ.ም
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን