የትምህርቱ ርዕስ | ፍቺ

 

በዚህ ዓለም ላይ የቤተሰብ ፍቅር ፣ የጓደኝነት ፍቅር ፣ የትዳር ፍቅር የታወቁ ናቸው ። ቤተሰብን በመወለድ ስናገኘው ፣ ጓደኝነትን በማደግ ፣ ትዳርን ደግሞ በመምረጥ እናገኘዋለን ። ከጓደኝነት ቀጥሎ እስከ ዕለተ ሞት የሚዘልቅ የትዳር ሕይወት ነው ። የቤተሰብ ኅብረት ተፈጥሮአዊ ጥምረት ሲሆን ያንን የመረጠልን እግዚአብሔር ነው ። የጓደኝነት ኅብረት ደግሞ በልጅነትና በተማሪነት እንዲሁም በሥራ ጎዳና ላይ የሚገጥመን መሳሳብ ነው ። ጓደኝነት ጊዜና ፍቅር የሚካፈሉበት ከጥቅም የጸዳ በመሆኑ እጅግ አስደሳች ነው ። ጓደኝነት ወንዱ ከወንድና ከሴት ጋር የአሳብ ትብብር ያለበት ነው ። ትዳር ግን ሁለት የተለያዩ ጾታዎች በቃል ኪዳንና በእግዚአብሔር ምሥጢር አንድ የሚሆኑበት ነው ። ሁለት ሰዎች በሂሳብ ሕግ ሁለት ናቸው ፣ በምሥጢረ ተክሊል ግን አንድ ይሆናሉ ። የሥጋ ፣ የነፍስና የመንፈስ አንድነት የሚደረገው ከትዳር አጋር ጋር ነው ። ጓደኝነት ግን የነፍስና የመንፈስ አንድነት ይኖረዋል ። 

በሕይወት ውስጥ ብዙ ምዕራፎች አሉ ። የመወለድ ፣ የማደግ ፣ የመማር ፣ የማፍራት ፣ የማረፍ፣ አደራን የመስጠት ምዕራፍ አለ ። ትዳር የማፍራት ምዕራፍ ሲሆን ከዚያ በኋላ የማረፍና አደራን የመወጣት ክፍሎች አሉት ። ማረፍ መጥለል ሲሆን ከቍጣና በጉልበት ከመመካት የሚዳንበት ነው ። አደራን መወጣት ደግሞ ልጆችን ማሳደግ ለትውልድ የቤተ ክርስቲያንና የአገር ፍቅርን ማስተላለፍ ነው ። ትዳር የማፍራት ምዕራፍ ነውና ማፍራት ደግሞ መገረዝና መቆረጥ ያለበት ነው ። ብዙ እጮኞችን ያሳለፈው ብዙ ሚስቶች ሊኖሩት አይችሉም ። ብዙ ፍላጎቶቹን ቆርጦ ወደ ትዳር ይገባል ። ወደ ትዳር ከገባ በኋላ የተሻሉ የሚመስሉ ቢያይም ከእርሱ ዓይን የጌታ ምርጫ ይሻላል ። ትዳሩ መስቀል ቢኖርበት ሰማዕትነት ይሆነዋል ፣ ደስታ ቢኖርበት የተጣሉትን ያስታርቅበታል ። 

ቃል ኪዳን ካለባቸው ኅብረቶች ሁለቱ ጽኑ ናቸው ። የጓደኝነትና የትዳር ኅብረት ቃል ኪዳን ይፈልጋል ። የጓደኝነት ቃል ኪዳን በዳዊትና በዮናታን መካከል ነበረ ። የጓደኝነት ኪዳን ትዳሩን ለማጽናት ፣ ሲጣሉ ለማስታረቅ ፣ በሞት ጊዜ የወዳጅን ልጆች ለማሳደግ እጅግ አስፈላጊ ነው ። ሰዎች ወደ ትዳር ሲገቡ ጓደኝነትን ይጥላሉ ፣ አሊያም ጓደኝነትህን ካልጣልህ ካልጣልሽ የሚል ሙግት ይመጣል ። በዚህ ምክንያት በጋራ የሚያከብሩት ሰው የለምና ጠባቸው እርቅ የሌለው ይሆናል ። ትዳር ሁለት ሰዎች የሚኖሩበት ደሴት አይደለም ። የሁለት ቤተሰብ ፣ የሁለት ወዳጆች ኅብረትም ነው ። ጓደኝነትን ከማፍረስና የትዳር አጋርን የግል ንብረት ከማድረግ ጓደኝነቱ በትዳር ውስጥ ግብዣ እየተደረገለት ቢቀጥል መልካም ነው ። ወንዶች በትዳራቸው ያላቸውን መከፋት የሚያነጋግሩትና የሚያማክሩት የወንድ ጓደኛ ሲያጡ ሌላ ሴት በመያዝ ይተኩታል ። ሴቶችም ከባላቸው ያላገኙትን ከሌላ ወንድ ለማግኘት ይነሣሉ ። ልብ አድርጉ ባልና ወንድ ይለያያሉ ። ብዙ ሴት አለ ፣ ብዙ ሚስት ግን ላይኖር ይችላል ፤ ብዙ ወንድ አለ ፣ ብዙ ባሎች ግን ላይኖሩ ይችላሉ ። ጌታ ያቺን ሳምራዊት ሴት ባልሽን ጠርተሸ ነይ ሲላት እርስዋ ባል የለኝም አለችው ፤ እውነት ተናገርሽ አላት ። ወንድ እንጂ ባል አልነበራትም ። ጌታ፡- “አምስት ባሎች ነበሩሽና፥ አሁን ከአንቺ ጋር ያለው ባልሽ አይደለም፤”  አላት ። ዮሐ. 4፡18። አብሯት ያለው ወንድ እንጂ ባል አይደለም ። አምስት ደርሶ ባል ሊኖር አይችልም ።  አንድ ባል ቢኖራት ኖሮ እርሱ እስከ ዕለ ሞት አይለያትም ነበር ፣ እስከ ስድስት ሙከራ አታደርግም ነበር ። ባል ነበር ሲሆን አስገራሚ ነው ፤ ምክንያቱም እስከ ዕለተ ሞት የሚጸና ባለ ቃል ኪዳን ነውና ። 

እግዚአብሔር ለትዳር ኅብረት ግድ ይለዋል ። ከቤተሰብ ሕግ ፣ ከሴቶች መብት ተቆርቋሪ ድርጅት ፣ ከወጣቶችና ሴቶች ጉዳይ ሚኒስቴር ፣ ከፍርድ ቤት ይልቅ ትዳር ለእግዚአብሔር ይቀርበዋል ። አሁን አላውቅም ፣ ከዛሬ አሥር ዓመት በፊት ስለ ሥራ ቅልጥፍና በሚናገር የክፍለ ከተማ ማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ “ፍቺ በ45 ደቂቃ” ይላል ። ከአሜሪካን አገር ከሦስት ትዳር ሁለቱ ፣ በእንግሊዝ አጋር ከሦስት ትዳር አንዱ ወደ ፍቺ ያመራል ። በአገራችን የተጠና ነገር የለንም ፣ በተጋቡ በወራት ውስጥ ግን ወደ ፍቺ የሚመጡ ብዙዎች ናቸው ። የአሥራ አምስት ቀን አራስ ልጅ ይዘው ፍርድ ቤት የሚመላለሱ ብዙ ናቸው ። 

እግዚአብሔር ግን መፋታትን እጠላለሁ አለ ። /ሚል. 2፡16/ ፍቺ ብዙ ኪሣራዎች አሉት ። የተፋታ ሰው ወደ ወላጆቹ ቤት መመለስ እንኳ አይፈልግም ። ለሚያገኛቸው ሁሉ ማስረዳት ሥራ ይሆንበታል ። የንብረት ኪሣራ ይመጣል ። አእምሮ ስለሚወጠር በተሰማሩበት መስክ ውጤት እያነሰ ይመጣል ። ከሁሉ በላይ ሞት ይለየናል ተባብለው ትንሽ ጉዳይ ሲለያያቸው ትዝብት ላይ ይወድቃሉ ። የልጆች የተመሰቃቀለ ሕይወት ከፍቺ ውስጥ ይገኛል ። ለቀጣይ ሰባና ሰማንያ ዓመት የሚያነክሱ ትውልዶች የሚፈጠሩት በፍቺ ነው ። መፋታት እፈልጋለሁ አለች አንዲት ያስተማርኳት ልጅ ። እናትዋ አጠገቤ ነበሩና “ደኅናውን ሰውዬ ሚስቱም ስለማትለቅልሽ አርፈሽ ተቀመጪ” አሏት ። ሌሎችም የማውቃቸው እኅትማማቾችን ያገቡ ተበሳጩና አባት ጋ ሄዱ ። “ልጆቹን ይረከቡን” አሏቸው ። “ስትወስዱአቸው እንደ ነበሩ አድርጋችሁ ስጡኝና እቀበላለሁ” አሉ ።  እነዚህ ከላይ የጠቀስኳቸው አሁንም በትዳራቸው ጸንተው አሉ ። 

ጌታ ሆይ ያዘመመውን ቤት ደግፈው !

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን 

ሐምሌ 28 ቀን 2013 ዓ.ም.

እውነት 8

ለልባችሁ የቀረላችሁን አሳብ እስቲ ግለጡ ። እግዚአብሔር ይጠብቃችሁ !

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ

አዳዲስ መጻሕፍት

ትርጉሙ:- ቀይ ዕንቈ

ለምድራችንና ለአገልግሎታችን በረከት የሆነ መጽሐፍ
የመጀመሪያ እትም ጥቅምት 2016 ዓ.ም

1ኛ ጢሞቴዎስ ትርጓሜ – ክፍል አንድ

የመጀመሪያ እትም ሐምሌ 2013 ዓ.ም

ምክር አዘል መጽሐፍ

የመጀመሪያ እትም