የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የኤማሁስ መንገደኞች

የኤማሁስ መንገደኞች
“እኛ ግን እስራኤልን እንዲቤዥ ያለው እርሱ እንደ ሆነ ተስፋ አድርገን ነበር ፤ ደግሞም ከዚህ ሁሉ ጋር ይህ ከሆነ ዛሬ ሦስተኛው ቀን ነው ።” ሉቃ. 24፡21
. . .
ወምድርኒ ትገብር ፋሲካ
ተሐፂባ በደመ ክርስቶስ
በክርስቶስ ደም ታጥባ
ምድር ፋሲካን/ደስታን ታደርጋለች ።
የአርማትያሱ ዮሴፍ ለክርስቶስ መቃብሩን ለቀቀ ። ክርስቶስ እንደ ድሀ ኑሮ በባለጠጎች መቃብር ተቀበረ ። በቁማቸው የሚላስ የሚቀመስ አጥተው ፣ የሞቱ ቀን በሬ ታርዶ የሚሸኙ ሙታንን ሥቃያቸውን ለመካፈል ክርስቶስ ኑሮው የምስኪን ፣ መቃብሩ የባለጠጎች ሆነ ። በቁማቸው ሲሰደቡ ኑረው ሲሞቱ የሚመሰገኑትን ፤ በቁማቸው መናፍቅ ተብለው ሲሞቱ ታላቅ አባት ተብለው የሚወደሱትን ሕመማቸውን ሊካፈልላቸው ክርስቶስ በባለጠጎች መቃብር ተቀበረ ። የቆመ ደግ ፣ የሬሳ ክፉ አላውቅም የምትለዋን ዓለም ለመኰነን ክርስቶስ በባለጠጎች መቃብር ተቀበረ ። ዮሴፍ ዘአርማትያስ እንደሚሞት እንጂ መቼ እንደሚሞት አያውቅም ነበረ ። በሞቱ ላይ ድራማ የሚሠሩትን ለመኰነን በቁሙ መቃብሩን ከውቅር ድንጋይ አሠራ ። ይህንን መቃብሩን ለክርስቶስ ቅዱስ ሥጋ ለቀቀ ። መቃብራቸውን የሚለቁ ቀርበው የሚገንዙ አይደሉም ፣ በዘመድ መልክ ቀርቦ የገነዘው ፣ ቅዱስ እያለ ሽቱ የቀባው ዮሴፍ ዘአርማትያስ ነበረ ። ጌታችን በሥጋ ዘመኑ ከእናቱ ድንግልናዊ ወተትን ለመነ ። ሁለት ጊዜም ላይጠጣው ውኃ ለመነ ። አንዱ ከሳምራዊቷ ሴት ሲሆን ሁለተኛው በመስቀል ላይ ሁኖ ተጠማሁ በማለት ሆምጣጤ ያመጡለት ሰዓት ነው ። ከልደቱ ቦታ የመቃብሩ ስፍራ ያማረ ነበረ ። ሁለት ዓመት ያህል በቤተ ልሔም እንደ ቆየ ፣ ለሦስት ቀን ያህል በመቃብር ቆየ ። ሟችም ቢሞት ፣ ገዳይም ቢገድል ለሦስት ቀን ነውና ተስፋ አትቍረጡ ሊለን ፈለገ ።
ጌታችን ከሙታን በተነሣ ቀን ልባቸው አዝኖ ወደ ኤማሁስ የሚጓዙ ሉቃስና ቀለዮጳ የሚባሉ ደቀ መዛሙርት ነበሩ ። ዓለም ክርስቶስን በመስቀሏ ታላቅ ተስፋ መቍረጥ ገጥሟቸው ነበረ ። ደግ ገድሎ ደግ ነገር መጠበቅ ፣ ውኃ ቅዳ ውኃ መልስ የዓለም ጨዋታ ነው ። ሰባኪ ገድሎ ሰባኪ መናፈቅ ፣ ፀሐፊ ቀብሮ ፀሐፊ መሻት ፣ አፍቃሪን አደንዝዞ አፍቃሪ ማሰስ የጥላ ዓለም ጠባይ ነው ። በነጻ የመጣው ከሄደ በዋጋ ፣ ያለ ልፋት የመጣው ከሸሸ በታላቅ አሰሳ አይገኝም ። የፈወሰ እጅ መቸንከሩ ፣ ያጽናና አንደበት ሆምጣጤ መጋበዙ ፣ አልዓዛርን የፈለገ እግር በምስማር መታሠሩ ፣ ዮሐንስ ወልደ ዘብዴዎስን የሸሸገ ጎን በጦር መወጋቱ እንደ ሰው ሰውኛ ሲያዩት ተስፋ የሚያስቆርጥ ነው ። ክርስቶስ ግን የሞተው በአብ ፈቃድ ፣ በራሱ ውድ ፣ በመንፈስ ቅዱስ ስምረት ፣ በነቢያት ትንቢት ፣ በአበው ተስፋ መሠረት ነው ። የክርስቶስን ሞት በሥጋዊ አእምሮ ሲያስቡት ዕለቱን ተከስሶ ዕለቱን መሞቱ ፣ ሊሰቀል ታስቦ ቀድሞ መገረፉ ፣ ዳኛው ቀያፋ ምስክሩ ሎሌው መሆኑ በዓለም ተስፋ አስቆርጧቸው ነበር ። ከሕግ አኳያ የክርስቶስን ሞት ሲያዩት ፍርድ አጉዳይ ዓለም አሳዝናቸው ነበር ።
መግደላዊት ማርያም ተኝቶ አገኘዋለው ስትል በአትክልቱ ስፍራ ቆሞ አየችው ። የኤማሁስ መንገደኞች ከጀርባቸው ጥለውት በኀዘን ሲጓዙ አብሮአቸው ይጓዝ ነበረ ። ክርስቶስ የለም እያሉትም ከአጠገባቸው አለ ። ሲክዱት የማይክድ ነው ። ተስፋ መቍረጥ የእግዚአብሔር ሀልወት በአጠገባችን እንዳለ ያስረሳል ። ተስፋ የሚሆኑ ነገሮች ተስፋን አይሰጡም ። ተስፋ ራሱ እግዚአብሔር ነው ። በራሱ እግዚአብሔር ተስፋ ካላደረግን ጭላንጭሎች ወደ ጨለማ ፣ ፀሐይ ወደ ጽልመት ፣ ጨረቃ ወደ መሰወር ፣ ከዋክብት ወደ ደመና ሲገቡ ልባችን መፈራረስ ይጀምራል ። ጭላንጭል አዲስ ወዳጅ ፣ ፀሐይ የንጉሥ ፊት ፣ ጨረቃ ደግ መካሪ ፣ ከዋክብት ትውልድ ናቸው ። አዲስ ወዳጅ ብቅ ጥልቅ ሲል ፣ ንጉሥ ቃሉን ሲያብል/ሲዋሽ ፣ ደግ መካሪዎች አኪጦፌል ሲሆኑ ፣ ትውልድ የሞት ልጅ ሲሆን ልብ ይደክማል ። ተስፋ ግን እግዚአብሔር ነውና አሁንም ይቀጥላል ። ተስፋ ከልብ ሲታጣ ፊት የኀዘን አደባባይ ይሆናል ። አካል ቀፎ ነው ፣ ተስፋ ግን ሞተር ነው ። እግር ካላቸው ተስፋ ቢሶች እግር የሌላቸው ተስፈኞች ይደርሳሉ ። ፍትሕ ከዳኞች ፣ እውነት ከመሪዎች ፣ ጽድቅ ከካህናት ፣ እምነት ከደቀ መዛሙርት ቢጠፋም ገና ተስፋ አለ ። ተስፋ የጋረደንን ደመና ሰንጥቀን መንበረ ሥላሴን ስናይ የሚመጣ ነው ። ሁሉም ነገር ከስፍራው ይታጣል ፣ እግዚአብሔር ግን በማይናወጥ መንግሥት ይኖራል ። የፕሮቴስታንት እምነት መሥራች የነበረው ማርቲን ሉተር የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃሎች ለማመን አቅም አጥቶ በትካዜ ተውጦ ሳለ ሚስቱ አየችና የኀዘን ልብስ ለብሳ፡- “ዛሬ የኀዘን ልብስ ለብሻለሁ ፣ ምክንያቱም አምላክህ እንደ ሞተ ያህል ተጨንቀሃል” አለችው ይባላል ። ጭንቀት አምላክን ገድሎ ጠላትን ሕያው ማድረግ ነው ።
ተስፋ በጆሮ ሹክ ሲል ገና ነው ይላል ። ሬሳ እየተጋዘም ገና ነው ። ተስፋ በዓይን ላይ ሲያርፍ ከተራራው ጀርባ ያለውን ያያል ። ተስፋ አፍንጫ ላይ ሁኖ የሕይወትን መዓዛ ያውዳል ። ተስፋ አፍ ላይ ሁኖ “ይህም ያልፋል” ይላል ። ተስፋ እጅ ላይ ሁኖ ድሆችን ከውድቀት ያነሣል ። ተስፋ ደርሶ ወደ ጨለሙ መንደሮች ይገባል ። ተስፋ ሰማይ ቆሞ ምድርን ያስጀምራል ። ተስፋ የአሁኑን ሳይሆን የሚመጣውን ፤ የሆንነውን ሳይሆን የምንሆነውን ያወራል ። ተስፋ ዜና አይሰማም ፣ ተስፋ አንድ ቀን ዜና ነኝ ይላል ። ተስፋ ትዕግሥትን ጣፋጭ ፣ ፍቅርን ብርሃን ፣ እምነትን ቆራጥ ያደርጋል ።
ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ሞቱ ላይ ቀርተው ትንሣኤውን አልሰሙም ነበር ። ኀዘን በደስታ መተካቱን ያበሰራቸው አልነበረም ። ሐዋርያ ባይሄድላቸው የተነሣሁ ጌታ ሐዋርያ ሁኖ ሄደላቸው ። ሐዋርያ ተነሣ ይላል ፣ ክርስቶስ ግን ተነሣሁ ይላል ። በብርቱ ስናዝን ራሱ ይመጣል ። አገልጋዩ ሲያጽናና ፌዝ ለሚመስላቸው አልቃሾች ራሱ ክርስቶስ ለልባቸው ሊናገር ይመጣል ። ሉቃስና ቀለዮጳ ከኢየሩሳሌም ወደ ሰሜን አቅጣጫ ቀጥሎ ወደ ምዕራብ አድርገው ወደ ኤማሁስ አሥራ አንድ ኪሎ ሜትሮችን ተጉዘዋል ። መንገዳቸው ግን ፋሲካ በዓል ላይ እንደ ቆየ በደስታና በጉልበት ሳይሆን ዓለም ስለ ሰቀለችው ስለ ክርስቶስ በማሰብ ኀዘን የሞላበት ነበረ ። ስለ ዓለምና ስለ ሰው በጥልቀት ለማወቅ መሞከር በመጨረሻ ተስፋ መቍረጥ ያመጣል ። ገብስ ገብሱን ካላዩ የሰውና የዓለም ነገር ይሰብራል ። ተስፋ ቢቆርጡም የሚያወሩት ስለ ክርስቶስ ነበረ ። ስሙ በተነሣበት ለመቅረት የማያስችለው ጌታ ከእነርሱ ጋር ነበረ ። ሰዓቱ ሠርክ እየተቃረበ ያለበት ፣ አቅጣጫው ወደ ምዕራብ ወደ ፀሐይ መጥለቂያ ነበረ ። የማታው ፀሐይ ዓይናቸው ላይ አርፋ መንገዳቸውን በእምነት እንጂ በማየት እየረገጡ አልነበረም ። አጠገባቸው ያለውንም ጌታ ማየት አልቻሉም ። ፀሐይ ስትጠልቅ የማይጠልቅ የጽድቅ ፀሐይ አለ ። እርሱም ያመነው ክርስቶስ ነው።
የልባቸው ስብራት አርያም ደርሶ ክርስቶስ ሊታደጋቸው አብሮ ይሄድ ነበረ ። ለቀባሪው አረዱት እንደሚባለው ስለ ክርስቶስ ለክርስቶስ ይናገሩ ነበረ ። ጥልቅ ስሜታቸውን ሲገልጡ ጥልቅ እውቀትን ነገራቸው ፤ ልባቸውን ሲቆርሱለት እንጀራ ቆረሰላቸው ። ስለ ቅርቡ የዓርብ ፍርድ ሲያወሩ ስለ ነቢያት ትንቢት ተረከላቸው ። ድብቆች ከክርስቶስ ምንም አያገኙም ። እንደ ሰው ተሸንፈው እንደ መልአክ ለመግደርደር ይፈልጋሉ ። “ደክሞኛል ያዘኝ” ለሚሉት የክርስቶስ እጆች ተዘርግተው ይኖራሉ ። አላዩትም ማለት አላያቸውም ማለት አይደለም ። አላመኑም ማለት አልተነሣም ማለት አይደለም ። እስክናየው ቢጠብቅ እስከ ዛሬም አንድንም ነበረ ፣ እስክናምነው ቢጠብቅ እስከ ዛሬም መልካም አይሆንልንም ነበረ ።
እግዚአብሔር ሁሉን አዋቂ ነው ። በማወቁ አይጠረጠርም ። እግዚአብሔር ግን የማያውቃቸው ነገሮች አሉ ።
1-  ይቅር ያለውን ኃጢአት አያውቀውም ፣
2-  ተስፋ የሌለውን ኃጢአተኛ አያውቀውም ፣
3-  ብቻውን የሚበረታ ፍጡርን አያውቀውም ፣
4-  የፈጠረውን ትንሽ ሰው አያውቀውም ፣
5-  የሠራውን ከንቱ ቀን አያውቀውም ፣
6-  የማይነጋውን ሌሊት አያውቀውም ፣
7-  የማያልፈውን መከራ አያውቀውም ፣
8-  የማይችለውን ኃይለኛ አያውቀውም ፣
9-  ፍቅሩ ያልያዘውን ሰው አያውቀውም ፣
10-         የማይጠገነውን ሰባራ አያውቀውም ።
ይቀጥላል
የመስቀሉ ገጽ 7/ሀ
ሚያዝያ 17 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ