የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ልሳን ዛሬ አለ ወይ ?

ልሳን ዛሬ አለ ወይ ?
ልሳን ማለት ቋንቋ ማለት ነው ። ሐዋርያው፡- በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር” ይላል ። 1ቆሮ. 13፡1 ። ልሳን ባለቤት ያለው ሲሆን ባለቤቶቹም ሰውና መላእክት ናቸው ። እግዚአብሔር በሰዎች አለመታዘዝ ምክንያት ቋንቋን በባቢሎን ደባልቋል ። በበዓለ ሃምሳ ደግሞ ቋንቋን ሀብተ መንፈስ ቅዱስ አድርጎ ሰጥቷል ። አንድ አምባሳደር የሚላክበትን አገር ቋንቋ ማወቅ እንዳለበት ሁሉ ሐዋርያትም ወደ ዓለም ሲላኩ የዓለምን ቋንቋ ማወቅ ነበረባቸው ። የላካቸው ትልቁና የዘላለሙ መንግሥት በቋንቋ ጸጋ ሞልቶ ሰዷቸዋል ። የልሳን ጸጋ ዓላማው ወንጌልን ለማስተላለፍ ነው ። ልሳንን በሚመለከቱ በዘመናችን የተሳሳቱ ትምህርቶችና ልምምዶች ይታያሉ ። ልሳንን የሚቀበሉ የፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናት ሦስት ዓይነት ልሳን እንዳለ ይናገራሉ ። ከእግዚአብሔር ፣ በልምምድና ከሰይጣን የሚነገሩ ልሳኖች እንዳሉ ያስተምራሉ ። ስለዚህ ከሦስቱ ሁለቱ ተቀባይነት የሌለው እንደሆነ ያምናሉ ። ሁለት ሦስተኛው ሐሰት ከሆነ ልሳንን መመርመር ያስፈልጋል ማለት ነው ።
ልሳን በዘመናችን አለ ወይ ? የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ነውና በዘመናችን ካለ አንቀበልም ማለት አንችልም ። ልሳን ቋንቋ በመሆኑ መናገርና መስማትን ካላሟላ ልሳን ነው ማለት አይቻልም ። ሐዋርያው፡- ነፍስ የሌለበት ነገር እንኳ ዋሽንትም ክራርም ቢሆን ድምፅ ሲሰጥ የድምፁን ልዩነት ባይገልጥ በዋሽንት የሚነፋው ወይስ በክራር የሚመታው መዝሙር እንዴት ይታወቃል? ደግሞም መለከት የማይገለጥን ድምፅ ቢሰጥ ለጦርነት ማን ይዘጋጃል?” በማለት ይናገራል 1ቆሮ. 14፡7-8 ። ከዋሽንትና ከመለከት ድምፅ ያነሰ ልሳን ፣ ልሳን ተብሎ መጠራት አይችልም ። ተናጋሪው ሲናገር ሰሚዎቹ ካልሰሙት ልሳን አይደለም ። ምክንያት በልሳን ያለው ጩኸት ሳይሆን የመንፈስ ቅዱስ መልእክት ነው ። የልሳኑን ትርጉም ካላወቀው ሰው በግሉም ሊጸልይበት አይገባም ይላል ። የምንጸልየው በአእምሮም በመንፈስም ነውና ። ስለዚህ ትርጉሙን እስኪያውቀው መጸለይ እንጂ በግል መጠቀምም አይቻልም ። 1ቆሮ. 14 ፡ 13-15 ።
ልሳንን የመዳንን ምልክት አድርጎ ማቅረብ ፍጹም ስህተት ነው ። ጌታችን የዳኑትን በፍሬአቸው ታውቁአችኋላችሁ አለ እንጂ በልሳናቸው ታውቋችኋላችሁ አላለም ። ማቴ. 7፡16 ። ልሳን የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ነው ።ጸጋ ማለት አንዱ የሌለውና ሌላኛው ያለው ማለት ነው ። ሐዋርያው፡- ሁሉስ በልሳኖች ይናገራሉን?” ይላል 1ቆሮ. 12፡30 ። ሁሉ በልሳን የማይናገሩ ከሆነ ልሳን የመዳን ምልክት ሊሆን በፍጹም አይችልም ። ደግሞም፡- ልሳኖች ቢሆኑ ይቀራሉ” ይላል 1ቆሮ. 13፡8 ። ስለዚህ ሁሉ ወንጌልን ከሰማ በኋላ የሐዋርያት ዘመን ሳይፈጸም የልሳን ጸጋ እየቀረ መጥቷል ።
ልሳን እንዲሰጠን ሱባዔ መግባት ይገባልን ? ስንል የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ባለቤቱ በጎደለው ቦታ ላይ የሚሾመው ብልት በመሆኑ ሱባዔ መግባት የሚያስፈልገው አይደለም ። በብርቱ መፈለግ ካለብን ትንቢት መናገር ወይም ስብከትን እንድንሻ ተነግሯል ። 1ቆሮ. 14፡1 ። ምክንያም በስብከት ሁሉ ስለሚታነጽ ስብከት ከልሳን በላይ ለቤተ ክርስቲያን ሕንጸት አስፈላጊ ነው ። ልሳን ግን ለአማንያን ሳይሆን ለአሕዛብ ምልክት ነው ። እግዚአብሔር በቋንቋችን የሚያናግረን ቢፈልገን ነው ብለው አሕዛብ ንስሐ እንዲገቡ የተሰጠ ምልክት ነው ። እንግዲያስ በልሳኖች መናገር ለማያምኑ ምልክት ነው እንጂ ለሚያምኑ አይደለም፥ ትንቢት ግን ለሚያምኑ እንጂ ለማያምኑ አይደለም” ይላል ። 1ቆሮ. 14፡ 22 ።
ምእመናን ሊጋደሉ የሚገባው ለመንፈስ ቅዱስ ፍሬ እንጂ ለጸጋ አይደለም ። ጸጋ መንፈስ ቅዱስ ባወቀ የምንቀበለው ነው ። ጸጋ የሌለው ክርስቲያን የለም ፣ ፍሬ የሌለው ክርስቲያን ግን ይኖራል ። ፍሬ ችላ ተብሎ ስለ ጸጋ ማውራት ከእውነቱ ለመሸሽ የሚደረግ ጥረት ነው ። ወንጌል በሁሉ ቋንቋ ስለተነገረ ፣ ከሁሉም ቋንቋ ሰባኪ ስለተገኘ ልሳን በዚህ ዘመን አንገብጋቢ አይደለም ። አለን ከተባለ ደግሞ ልሳኑ ባለቤት ያለው ነውና ሊፈተሽ ይችላል ። ዛሬ የሚደመጡት ልሳኖች ግን ባለቤት አልባ ናቸው ። በአፍህ ላይ የመጣውን ቃል ደጋግመህ በል እየተባለ በልምምድ የሚመጣ ነው ። ልምምድ ከሆነ ጸጋ መሆኑ ቀረ ። በዚያውም ለሰይጣን ፈተና መጋለጥ ይመጣል ። እግዚአብሔር ሲሰጠን እንቀበላለን እንጂ እጅ ጠምዝዘን የምንወስደው ሀብተ መንፈስ ቅዱስ የለም ።
በዓለም ላይ ቋንቋ አይደገምም ። አሳብ ይደገማል ። ቅድም ያወራችሁትን ቋንቋውን ሙሉ በሙሉ መድገም አትችሉም ። አሳቡን ግን መድገም ትችላላችሁ ። ይህ የቋንቋ ሕግ ነው ። ልሳን እየተባለ የሚነገረው ግን የሚደጋገም ቋንቋ በመሆኑ አብረው የሚኖሩ ሕፃናት ሳይቀር ደግመው ይሉታልና ቋንቋ አይደለም ። ደግሞም ልሳኑ መልእክት ማስተላለፊያ ነው ። ለምሳሌ በዚያ ልሳን “የኬንያ ሕዝብ ንስሐ ግቡ” የሚል ከሆነ ሃያ ዓመት አዲስ አበባ ላይ ተቀምጦ “የኬንያ ሕዝብ ንስሐ ግቡ” እያለ ነውና ዓላማውን ስቷል ።
በእውነት ብዙ ወገኖቻችን በየጓዳው ባለ ልምምድ ለክፉ ሰይጣን እየተዳረጉ ነው ። ቢኖር በጣም ደስ ይለን ነበር ። አያስፈልጋችሁም ከተባልን በተሰጠን ጸጋ መጠቀም ተገቢ ነው ። “መንገድ ላይ ስሄድ ፣ ሳሎን ውስጥ ተቀምጬ ልሳን ተሞላሁ” ሲሉ የነበሩ አሁን ይቅርታ እየጠየቁ ባለበት ዘመን ልሳንን መለማመድ ዕድሜን ማቃጠል ነው ። አገሩን የናደው ሐሰተኛ ትንቢትና ልሳን እንደሆነ እያየን ነው ። የሚያስፈልገን ፍቅር የተባለው ፍሬ እንጂ ጸጋስ አላነሰንም ። ፍሬ ተጋድሎ ይፈልጋል ፣ ጸጋ ግን የምንቀበለው ነው ።
እግዚአብሔር ሆይ ዓይነ ልቡናችንን አብራልን !
ጳጕሜን 1 ቀን 2011 ዓ.ም.
ዲአመ

አስተያየት ይስጡ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

ያግኙን

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ስልክ ፡ +251930006086                             +251911699907

ኢሜል፡ ashumekon@gmail.com

የገጹ ዓላማ

የዚህ ገጽ ዓላማ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶችን ማስተላለፍ፣ ትውልድን በእግዚአብሔር ቃል ማነጽና የተሻለ ዘመንን መናፈቅ ነው።

አሸናፊ መኮንን
Ashenafi Mekonnen
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
Commercial Bank of Ethiopia
1000165078482

አቢሲኒያ ባንክ
Bank of Abyssinia
23202573

ሕብረት ባንክ
Hibret Bank
1030416569497017

ወጋገን ባንክ
Wegagen Bank
0870286030101

አዋሽ ባንክ
Awash Bank
01320034656200

በማህበራዊ ሚዲያ ይወዳጁን።

copyright @ 2021 ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

የዚህ ገጽ ዓላማ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶችን ማስተላለፍ፣ ትውልድን 
በእግዚአብሔር ቃል ማነጽና የተሻለ ዘመንን መናፈቅ ነው።