የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የቤተ ክርስቲያን ታሪክ /10

የቤተ ክርስቲያን ታሪክ /10
/አንብቡ ፣ አንብቡ ፣ አንብቡ ፣ ኧረ እባካችሁ አንብቡ !!!/
3-  ጸሐፍት
ጸሐፍት ሥራቸውን የጀመሩት በዘመነ ነገሥት ሲሆን ደብዳቤዎችን በማርቀቅ ፣ የታሪክ ሰነዶችን በማዘጋጀት ይታወቁ ነበር ። /2ነገሥ.18፡18፤ 22፡8/ ከሕግ መጻሕፍት ጋርም የቀረበ ግንኙነት ስለነበራቸው የነገሥታት አማካሪዎችና ሕግ አስተማሪዎች ነበሩ ። ወደ ሃይማኖት ሥራ የገቡት ከ586 ዓመት ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ነው ። ይህም ከባቢሎን ምርኮ በኋላ ማለት ነው ። የነገሥታት ሥርዓት በመፍረሱ የቤተ መንግሥት ሥራቸው ያከተመ ሲሆን ቅዱሳት መጻሕፍትን በመገልበጥ ፣ ሕግን በመተርጎምና ብይን በመስጠት እስከ ክርስቶስ ዘመን ድረስ ቆይተዋል ። ከጸሐፍትም ብዙዎቹ ፈሪሳውያን ነበሩ ። ጥሩ ልብስ ለብሰው የቀለም ቀንድ በወገባቸው ይይዙ ነበር ። በዚህም ሰዎች ጸሐፍት መሆናቸውን ያውቁ ነበር ። /ሕዝ. 9፡2/ ።
የባቢሎን ምርኮ መቅደስ የፈረሰበትና ቅዱሳን መጻሕፍት የተቃጠሉበት በመሆኑ የሕዝቡ መንፈሳዊ ቱንቢ የሆኑትን ቅዱሳን መጻሕፍትን መገልበጥ አስፈላጊ ሁኖ ተገኝቷል ። ጸሐፍቱ እነዚህ መጻሕፍት የሚገለብጡት በታላቅ አክብሮትና ጥንቃቄ ነበር ። እያንዳንዱን ፊደል ስለቆጠሩት ከጨረሱ በኋላ በመቊጠር ያረጋግጡ ነበር ። አንድ ፊደል ከጎደለም መልሰው ይጽፉ ነበር ። “ያህዌ” ወይም “እግዚአብሔር” የሚለው ስም ጋ ሲደርሱ ወደ መሬት ሰግደው ፣ እጃቸውን ታጥበው “ያህዌ” ብለው ይጽፉ ነበር ። በብሉይ ኪዳን ውስጥ ምን ያህል ጊዜ እግዚአብሔር ተብሎ ተጽፎአል ? በዚህ ሁሉ ልክ ጸሐፍቱ ስግደት አቅርበዋል ። በግርድፉ ብንቆጥር 6287 ጊዜ ያህል እግዚአብሔር የሚለው ስም ተጠቅሷል ። ይጽፉ የነበረው እንደ ዛሬው በተመቸ ወረቀት ላይ ሳይሆን ከዓባይ ወንዝ ዳርቻ ላይ በሚበቅል የሸምበቆ ቅጠል ወይም ፓፒረስ ተብሎ በሚጠራው ሰሌዳ ላይ ነው ። እንዲሁም የእንስሳት ቆዳ አዘጋጅተው በብራና ላይ ይጽፉ ነበር ። የሕትመት መሣሪያ የተፈለሰፈው በ1456 ዓ.ም. በጀርመን በጆሐን ጉተንበርግ ሲሆን መጀመሪያ የታተመውም መጽሐፍ ቅዱስ ነው ። እስከዚህ ዘመን ድረስ ላለፉት ሦስት ሺህ ዓመታት መጻሕፍትን በእጃቸው በመገልበጥ ባለውለታ የሆኑት ጸሐፍት ናቸው ። ሕጉን ብዙ ጊዜ በመገልበጣቸው በቃላቸው ይዘውት ነበር ። እንዲህ ይደክሙ የነበሩ ሰዎች ግን ክርስቶስ ሲመጣ አለመቀበላቸው የሚገርም ነው።
4- ሄሮዳውያን
እነዚህ ወገኖች አይሁዳውያን ሲሆኑ ከሌሎች አይሁዳውያን በተለየ የሄሮድስን አገዛዝ የሚደግፉ ነበሩ ። ለቤተ መንግሥቱም ታማኞች ሁነው ይሠሩ ነበር ።/ማቴ. 22፡16፤ ማር፣ 3፡6፤ 12፡13/ ። ዜና አይሁድ እንደሚናገረው እነዚህ ሰዎች አድር-ባዮች ነበሩ ። አድር-ባይነት ንጉሡ፡- “ስንት ሰዓት ነው ?” ሲሉ “ስንት እንዲሆን ይፈልጋሉ ?” ማለት ነው ።
5- ኤሤያውያን
እነዚህ ገለልተኛና የዓለምን ውጣ ውረድ ጠልተው በተወሰነ ቦታ በመገለል የሚኖሩ ፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን በመገልበጥ ሥራ የተሠማሩ ነበሩ ። ጋብቻን አጥብቀው የሚቃወሙ ፣ የእንስሳትን ሥጋ የማይበሉ ነበሩ ። የሚኖሩበትም “ኩምራን” በተባለ ቀበሌ ነበር ። ከክርስቶስ ልደት በፊት 20 እስከ 45 ዓ.ም የነበረው ፊሎ የተባለው ብሉይ ኪዳንንና የግሪክን ፍልስፍና አስማምቶ በመተርጎም የሠራው ይህ ሰው አራት ሺህ የሚደርሱ ኤሤያውያን እንደ ነበሩ ተናግሯል ። እነዚህን ሰዎች ከኦርቶዶክሳውያንና ገዳማውያን አባቶች ጋር አመሳስለው የሚተረጉሙ አሉ ። ይህ ፍጹም ስህተት ነው ። ኦርቶዶክሳውያን መነኮሳት ጋብቻ ርኩስ ነው ብለው የሚያምኑ ሳይሆኑ ስጦታ ነው ብለው የሚያምኑ ናቸው ። ድንግልናዊ ሕይወትም ስጦታና ጥሪ እንደሆነ ሲታመን ምንኩስናም የጥሪው ኪዳን ነው ። መነኮሳትም ብዙ ጥንዶችን በመጋባትና ጋብቻን ለማጽናት በሚደረገው ጥረት ዛሬም ያልደከማቸው እንደሆኑ እናያለን።
በ1947 እ.አ.አ. በሙት ባሕር አካባቢ በኩምራን ቀበሌ አንድ የዓረብ እረኛ የኮበለሉ ፍየሎቹን ለመመለስ በዋሻ ውስጥ ሲገባ በማሰሮ የተቀመጡ የብሉይ ኪዳን ጥቅልሎችን አግኝቷል ። ይህም ትልቅ ግኝት ነበር ። ምክንያቱም ተቺዎች አሁን የያዝነው መጽሐፍ ቅዱስ ሲገለባበጥ የመጀመሪያውን ይዘቱን አጥቷል የሚል መላ ይሰነዝሩ ነበርና ነው ። በዚህ እረኛ የተገኙት መጻሕፍት ግን በክርስቶስ ዘመን የተጻፉ ናቸው ። አሁን ካለው መጽሐፍ ቅዱስ ጋርም መመሳከር ተደርጎላቸው የአሳብ አንድነት እንዳላቸው ታውቋል ። በዚህም መጽሐፍ ቅዱስ አምላካዊ ጥበቃ ያለው መጽሐፍ መሆኑ ይበልጥ ታውቋል ። እነዚህ ጥቅልሎች እስኪገኙ ድረስ በእጃችን የነበሩት ጥንታዊ ቅጂዎች ከዘጠነኛው እስከ አሥራ አንደኛው ክፍለ ዘመን ድረስ የተጻፉ ሲሆኑ የሙት ባሕር ጥቅልሎች ግን ወደ ኋላ አንድ ሺህ ዓመት የሚበልጥ ዕድሜ አላቸው። እነዚህ የሙት ባሕር ጥቅልሎች የተጻፉት በኩምራን ይኖሩ በነበሩት ማኅበረሰቦች ነው ። እነዚህ ማኅበረሰቦችም ከክርስቶስ ልደት በፊት 130 ዓመት ጀምረው ኑሮአቸውን በኩምራን መሥርተዋል ። ኤሤያውያን ከፈሪሳውያን ተገንጥለው የገቡ በፈሪሳውያንና በመቃብያን ቅሬታ የነበራቸው ሲሆኑ በመሢሕ መምጣት የሚያምኑ ነበሩ ። ኤሤያውያን የሚለው ስያሜ ከምን እንደ መጣ በውል አልታወቀም ። ነገር ግን ከግሪኩ “ሆሲዮስ” የተገኘና “ቅዱስ” ማለት እንደሆነ አንዳንዶች ይነገራሉ። ጌታችን እንዲህ ባለ ልዩነት በነገሠበት ጊዜ ወደዚህ ዓለም መጥቷል ።
6- የአይሁድ ሸንጎ
በአይሁድ ሃይማኖታዊና ምድራዊ ኑሮ ውሳኔ የሚሰጥ “የአይሁድ ሸንጎ” የሚባል ትልቅ ችሎት ነበር ። ይህ ሸንጎ ሰባ አንድ አባላት ያሉት ሲሆን ሰባ ሁለተኛው ሊቀ ካህናቱ ነው ። በዚያ ዘመንም በዚህ ምድር ላይ የነበረው ከፍተኛው ፍርድ ቤት ይህ የአይሁድ ሸንጎ ነበር ። /ማቴ. 26፡3፤ 57-59/። ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን የዚህ ሸንጎ አባል ነበሩ ። የሸንጎ ሥልጣን ሃይማኖታዊ ጉዳይን በተመለከተ በመላው ዓለም ባሉ አይሁዳውያን ላይ የሚወስን ሲሆን በፖለቲካ ረገድ ግን በይሁዳ ግዛት ላሉ አይሁዶች ብቻ የሚሠራ ነው ። የሮም መንግሥት አካባቢውን የሚመለከቱ አንዳንድ ጉዳዮችን እንዲመለከት ለዚህ ሸንጎ ሥልጣን ሰጥቶት ነበር ። ሸንጎው ብይን ቢሰጥም የሞት ውሳኔን ማስተላለፍ ግን የሮም መንግሥት ሥልጣን ብቻ ነበር። ጌታችንን ወደ ሄሮድስና ጲላጦስ የወሰዱትም የሞት ፍርድ መስጠት ስለማይችሉና ሊገድሉትም ስለፈለጉ ነበር ።
ከሸንጎው ደንብ መካከል ጥቂቱን እንጥቀስ፡-
1-  ፍርድ በበዓል ቀን ማከናወን የለበትም ፤
2-  ምርመራ በሚካሄድበትና ምስክርነት በሚሰማበት ቀን የፍርድ ውሳኔ አይሰጥም ፤
3-  የምስክሮች ቃል እርስ በርሱ ባይስማማ ተከሳሹ በነጻ ይለቀቃል፤
4-  አንድ ምስክር በሌላ ምስክር ፊት ቃል መስጠት አይችልም ፤
5-  ከሳሹ ተከሳሹን በራሱ እንዲመሰክር ለማድረግ አይፈቀድለትም፤
6-  ለተከሳሹ ቢያንስ አንድ ጠበቃ ሊቆምለት ይገባል ፤
7-  ሊቀ ካህናቱ ሸንጎው ድምፅ እንዲሰጥ ይጠይቃል ፤
8-  ተከሳሹ ለምስክሮቹ መስቀለኛ ጥያቄ እንዲያቀርብ ይፈቀድለታል፤
ጌታችንን በከሰሱት ጊዜ ይህን ሁሉ አላሟሉም ። በዚህም ለዘመናት ይመኩበት ከነበረው ሕጋቸው ጋር ተጣልተዋል ። በበዓል ቀን ችሎት አስዋሉ ፣ በተመረመረበት ቀን እንዲሞት ወሰኑ ። ምስክር አልተሰማበትም ። ምስክሮች ነን የሚሉም በሸንጎ ወጥተው ዛቱበት ። አንድ ጠበቃ እንዲቆምለት አይደለም እንዲናገር አልተፈቀደለትም ። ሊቀ ካህናቱ ሸንጎውን ሳይጋብዝ በራሱ ወሰነበት ። መስቀለኛ ጥያቄ እንዲጠይቅ ዕድል አልተሰጠውም ፤ የፋሲካ እራት እንዳያመልጣቸው ሲቻኮሉ ለተዛባው ፍርዳቸው ግን እግዚአብሔርን አልፈሩም ።
7- ቀነናውያን
ከመቃብያን ዘመን ጀምሮ እስራኤልን በትጥቅ ትግል ነጻ እናወጣለን የሚሉ የአርበኞች ስብስብ “ቀነናውያን” ይባላል ። ይህ ቃል የተገኘው “ከነነዓት” ከሚለው የአራማይክ ቋንቋ ሲሆን “ቀናኢ” ማለት ነው ። የገሊላው ይሁዳ ተብሎ የሚጠራው የቀነናውያን የግልጽ መሪ ሲሆን በ6 ዓ.ም. “እስራኤል ለአሕዛብ መንግሥት ለሮም ግብር መክፈል የለባትም” ብሎ ጦርነት ያካሄደ ነው ። /የሐዋ. 5፡37/። ቀነናውያን በልብሳቸው ውስጥ ስለት ይዘው በመሄድ ለሮማ መንግሥት ያደረ ነው የሚሉትን አይሁዳዊ ይወጉ ነበር ። ከጌታችን ደቀ መዛሙርት አንዱ “ቀነናዊው ስምዖን” ወይም ናትናኤል ነው ። /ማቴ. 10፡4፤ የሐዋ. 1፡13/ ።
ቀነናውያን በ68 ዓ.ም. እስራኤልን ከሮም ነጻ ለማውጣት ባደረጉት እንቅስቃሴ ለሁለት ዓመት ያህል ከተከበቡ በኋላ በ70 ዓ.ም. ኢየሩሳሌምና መቅደሱ ተደመሰሱ ። በዚህም የእስራኤል በምድራቸው መኖር ፍጻሜ ሁኖ እንደገና የተሰባሰቡት ከ1900 ዓመታት በኋላ በ1948 ዓ.ም. ነው ። ጌታችን በተወለደ ጊዜ እነዚህ ሁሉ የሃይማኖትና የፖለቲካ ቡድኖች ነበሩ ።
ይቀጥላል
ዲ.አ.መ
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ