የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

መንፈሳዊነትና ማመናፈስን ለይ

እግዚአብሔርን እያየህ ሥራህን ፈጽም እንጂ ይህን እባላለሁ ብለህ አትስጋ ።ስትሮጥ እግርህን ብታይ ትወድቃለህ ፣ ተመልካቾችን ብታይም ትወድቃለህ ፤ ግብህን ስታይ ግን ታሸንፋለህ ። የተለመዱ ነገሮችን መከወን አያጣላም ። አንዳንድ መፍትሔዎች ግን ያልተለመዱ ናቸው ። ያልተለመዱ ነገሮችን መጀመር ሁሉ ሰው ይፈራል ፤ ከተጀመረ ግን ሁሉ ይከተላል ። ሰው ምን ይላል ? ሳይሆን እውነት ምን ትላለች ? ብለህ ሥራህን ቀጥል ። በኳስ ሜዳ በጣት የሚቆጠሩ ተጫዋቾች አሉ ፣ ተመልካቹ ግን በመቶ ሺህ የሚቆጠር ነው ። በሕይወትም ሃያ ሁለት ሰው ይጫወታል ፣ ሚሊየኖች ያያሉ ። ሕይወት ግን መዝናኛ አይደለችምና ሃያ ሁለት ተመልካችም ሊኖርባት አይገባም ። አገር የተሰጠን በጋራ እንድንለውጠው እንጂ አንድና ሁለት ሰው እንዲለውጠው አይደለም ። “የአንድ አሳቢ ፣ የአንድ በሬ ሳቢ” የለውም ፤ ደግሞም የትም አይደርስም ። ሥራህን ሌሎች ይናገሩት እንጂ በአንተ አፍ አይደነቅ ። የሥራህን ዋጋ የምትጥለው አንተ ስታወራው ነው ። ለእርካታ የሠራኸው ከሆነ አታወራውም ፤ ረክተሃልና ። የጠጣኸውን ውኃ እንደማታወራው መልካምነትም ለራስ የሚሠራ እንደሆነ እወቅ ። የሚናገር ሥራ ያልሠራ ሰው አፉ ይናገራል ። ሥራ ከቃል በላይ የመናገር አቅም አለው ። ሰማይ ዝምተኛ ነው ፣ ነገር ግን ስፉሕ ስለሆነው እግዚአብሔር ባለ መድከም የሚናገር ነው ። ተፈጥሮ የጸጥታ ትምህርት ቤት ነው ። ድምፅ አልባ መምህራን ተፈጥሮ መሆናቸውን እወቅ ። ተፈጥሮ እንኳ ዝም ብሎ አንተ ሠራሁ ብለህ አትለፍልፍ ። ስለ ሥራህ የምታወራ ከሆነ ወደፊት የምትሠራው የለም ማለት ነው ። እግሩ የቆመ አፉ ይራመዳልና ።
በመንገድህ ሁሉ ሰዎች ሳይሆኑ እግዚአብሔር ካንተ ጋር መሆኑን ጠንቅቀህ መርምር ። ብቸኝነት ማለትም ከሰው ሳይሆን ከእግዚአብሔር መራቅ ነው ።መልካም አሳብ ለኅሊና ምቹ ዕረፍትን ይሰጣል ። ቆመው የማይጠብቁ ሁለት ነገሮች አሉ ፡- ጊዜና ዕድል ። ጊዜና ዕድል ሲገጥምህ ቶሎ ተጠቀመው ። ብዙ ሰው የሚቆጨው ጊዜና ዕድልን ሸኝቶ ነው ። በነጻ የመጣ ነገር ከሄደ በኋላ በዋጋም አይመለስም ። ከመንገድ ምልክቶች አንዱ “ቁም” የሚል ነው።መቆምም የመጓዝ አንዱ ክፍል ነው ። ቆም ብለህ ሥራህን ገምግም ። አባት ሳለ መማር ፣ እናት ሳለች መሥራት ፣ ንጉሥ ሳለ መሮጥ ተገቢ ነው ። መኪና በፍሬን ካልቆመ ነዳጅ ጨርሶ ወይም ተጋጭቶ ይቆማል ። ሁሉም መቆም ቢሆንም እንደገና የሚጓዘው በፍሬን ሲቆም ነው ። አንተም ለቃልህና ለምኞትህ ፍሬን ይኑርህ ። በመንገድ ሁሉ አይኬድም ፣ በሚያደርሰው መንገድ እንጂ ። ያየኸው ሁሉ አይመርህ ። ሁሉም ያንተ እንዲሆን አትፈልግ ። ሁሉንም ታጣለህና ። መቀበሪያ እንኳ ያጡ ነገሥታት ሁሉ የእኔ ይሁን ያሉ ናቸው ። የከበረ ቀብር የምታገኘው ያነሰ ምኞት ሲኖርህ ነው ። ስግብግብ ሰው በሥጋው ጨርሶ በነፍሱ ሲወቀስ ይኖራል ። የሹም ሌባ ያጸይፋል ። ሁሉም የእርሱ ሳለ የራሱን የሚሰርቅ ነውና ። በዝምታ የዋልህበት ቀን ኃይልህ ያልባከነበት ቀን ነው ። የእግዚአብሔርን ቃል የተናገርህበት ቀን ደግሞ ኃይልህ የሚታደስበት ቀን ነው ። ከመከራ ይልቅ ዕድልን ታገሠው ። ከቀን በኋላ ሌሊት እንደሚመጣ ከዕድል በኋላም ችግር ይመጣል ። ዕድል ማለት እግዚአብሔር የሰጠህ ጊዜ ማለት ነው ። እግዚአብሔር በሚበልጠው ሊሾምህ በሚያንሰው ይፈትንሃል ። ከእጅ ሌባ የአፍ ሌባ ይከፋልና አንደበትህን ተቆጣጠር ።
ሰዎች አታከቱኝ ባልህበት ቀን ምናልባት ሰዎችን አታክተህ ይሆናልና ራስህን ተመልከት ። ክፉ ስትሆን የሰዎች ክፋት ይታይሃል ፣ ወደ ጽድቅ ስትቀርብ ስለ ሰዎች ኃጢአት ማልቀስ ትጀምራለህ ። ይገባሃል ተብሎ የተሰጠህን አይገባኝም ብለህ በትሕትና ያዘው ። የመንፈሳዊነት ግለት ያለው በዝማሬና በእንባ ነውና ሁለቱን እንዲሰጥህ ለምነው ። እንባ ለሠራኸው ኃጢአትና ላልሠራኸው ጽድቅ ነው ፤ ዝማሬም መልካም ላደረገልህ እግዚአብሔር ነው ።ሥራ ፈት ስትሆን ለሰይጣን ትልቁን የጊቢ በር እንደ ከፈትህለት እወቅ ። ሥራ ከምትፈታ ንጹሕ ልብስህን እንደገና እጠብ ። አእምሮና የተተኮሰ ጥይት ማረፊያ ካላገኙ ገዳይ ይሆናሉ ። እግዚአብሔር የረዳውን ሰው አንተ እጥለዋለሁ ብለህ አትነሣ ። የምትታገለው ከማትችለው ጋር ነውና ። መጽናናት ቋሚ የሚሆነው በመጽናት ነው ። መጽናናትን ከመለመን ጽናትን መለመን መልካም ነው ። ያለ ምክንያት የወደደህን እግዚአብሔር እያሰብህ ያለ ምክንያት የሚጠሉህን ሰዎች ልትረሳ ይገባሃል ። ምክንያት የሚጥመው ለራሱ ለምክንያት ብቻ ነው ። ውሸት ከመሆን የማያመልጡ ሁለት ነገሮች አሉ ይባላል ፡- የማይፈጽሙትን ተስፋ መስጠትና ምክንያተኝነት ናቸው ። የቆምከው በእግዚአብሔር ረዳትነት ነውና አመስግነው ። ስለ ነገ ከመጸለይ ስለ ትላንት አመስግን ።
ዮርዳኖስ እንዳያስፈራህ ቀይ ባሕርን እንደ ተሻገርህ አስብ ። ረጃጅሞች እንዳያስደነግጡህ ፈርዖንና ሠራዊቱን እንዳለፍህ አስተውል ። በምንም መንገድ ከትላንት የባሰ ቀን አይመጣምና አትደንግጥ ።
በዓለም ላይ ከሌለህ አትኖርም ፤ ከሌለህ የምትኖረው እግዚአብሔር ጋ ብቻ ነው ። ደግሞም እግዚአብሔርን ያተረፈ የሚያተርፈው ነገር ወደፊት የለም ። የማይካስ ድህነት በጎ ኅሊናን መክሰር ነው ። ከጠማሞች ጋር እየዋልህ በጎ ኅሊናህን እንዳትሰረቅ ተጠንቀቅ ። ኪስህን እንጂ ኅሊናህን መጠበቅ ለምን አቆምህ ? አባቶች አልቀዋል ብለህ ስትናገር አንተ ራስህ ልጅ ነኝ ወይ ? ብለህ መጠየቅ ይገባሃል ። ልጅ በሌለበት አባት ይታጣልና ። የተደበላለቁ አሳቦች ሲመጡብህ ጊዜ ሰጥተህ አስብ እንጂ አትከውናቸው ። ከቤትህ ለመውጣትህ እንጂ ለመመለስህ እርግጠኛ አይደለህምና መንገድህን ለእግዚአብሔር አደራ ስጥ ። ዕድልህ ያለው በእግዚአብሔር እጅ ነውና የሰው ድምፅ አጣሁ ብለህ አትጨነቅ ። ሰዎች እንዲወዱህ ሳይሆን እንድትወዳቸው ፈልግ ። ነገ ግን በእግዚአብሔር የሥልጣን እጅ ናትና ስለ ነገ በሰው ተስፋ አታድርግ ። ነገ ያደርግልኛል የምትለው ነገ ለማኝ ሊሆን ይችላል ። ሰው ሁሉ ነገን ቢያውቀው ዛሬን አይታበይም ደግሞም አይሸማቀቅም ነበር ።
የበለጠ ምሥጢር እንዲገለጥልህ የተገለጠልህን ምሥጢር አክብረው ። የሰው ምሥጢር የማይነገር ነው ፤ የእግዜር ምሥጢር ግን የሚነገር ነው ። የሰው ምሥጢር የሚያስጨንቅ ነው ፤ የእግዚአብሔር ምሥጢር ግን የሚያስደንቅ ነው ። ሰው የሚከብረው ሲሸፈን ነው ፣ እግዚአብሔር የሚከብረው ሲገለጥ ነው። ከተዋረዱ ሰዎች የሚመጣ ክብር ጊዜያዊ ነው ፤ ደግሞም የውርደት ያህል ነው ። ባለጌ የሚያከብርህ ለዛሬ የሚያዋርደው ሰው ስላለው ነው ። የሚሰድበው ያጣ ቀን ይሰድብሃል ። ትሑት ሰው በደረሰበት መከራ ሳይሆን በሰዎች ላይ በደረሰ መከራ እንደ ራሱ አድርጎ ያዝናል ። በሩቅ የሚያዩት ዓለም የቅርብ ጎረቤት ይሆናልና ። የመሰለህን ነገር አትመነው ። ግምትህ ኑሮህን እንዳይፈታው ተጠንቀቅ ። ግምት ከእውነት ይልቅ ለሐሰት ቅርብ ነውና ። መሳሳትን አትፍራ ። የጠራ ሥራም የብዙ ሙከራ ውጤት ነው ። የመሞከር ዕድል የማይሰጥ ፣ ፍጹማዊ አስተሳሰብን የሚያራምድ ማኅበረሰብ የማያድግና የእውቀት ልምሾ ያለበት ነው ። ሰው ሆነው በሰው የሚደነቁ ፤ ውዳቂ ሁነው በውዳቂዎች የሚስቁ ያልተማሩ ሕዝቦች ናቸው ። ዛሬ ድል ባገኘህበት መንገድ ነገም አገኛለሁ አትበል ። ድል ስጦታ እንጂ ሁኔታ አይደለምና ።
ሌሎችን ከታገሥኸው በላይ የታገሡህ ይበዛል ። ለእግዚአብሔርም ቀጪ እንደሆንህ ተሰምቶህ ሰዎችን አታሳድድ ። እግዚአብሔር ሲፈርድ ያንተን ምስክርነት አይፈልግምና ከሳሽ አትሁን ። ቤተ ክርስቲያንን ካንተ ወንድነት የመለኮት ኃይል እንደሚጠብቃት ካላወቅህ አማኝ አይደለህም ። በጸጋ እየኖርህ በሕግ አትፍረድ ። አሁን ልታደርገው የሚገባህን ኋላ አትበል ። መኖሪያህ ቤትህ ብቻ አይደለምና ስለ ዓለም ፈውስም ትጋ ። ለውጭ ሰው ምቹ ለትዳርህ ግን እሬት አትሁን ። መልከ ብዙ ሰዎችን በአንድ ላይ አታስተናግድ ። ባላጋራንም በአንድ ላይ አትጋብዝ ፤ የሰነፍ ድግስ ያሰኝብሃል ። ሁሉን ነገር መንፈሳዊ አታስመስል ። በስንፍናህ ባረረው ድስትህ ሰይጣን እየተዋጋኝ ነው አትበል ። ጸሎትህን ለኅብረት እንጂ ለውጊያ አታድርገው ። የምክር ምጽዋት በቃኝ አይባልምና የሚበልጡህን ምከሩኝ በል ።
መንፈሳዊነትና ማመናፈስን ለይ ። በእሳት ፣ በልብስ… ላይ ጋኔን ያርፋል እያልህ ከመገሠጽ ስለ ሰጠህ ልብስ ብታመሰግን ይበልጣል ። ያዘነን ስታጽናና በወጉ አጽናና እንጂ እግዚአብሔር እንዲህ ይለኛል አትበል ። ሁሉ የእግዚአብሔር ነውና ። የተበደርከውን ለመመለስ የእግዚአብሔርን ድምፅ አትጠብቅ ። ግመል እየዋጥህ ትንኝን አታጥራ ። የቆምከው በቸርነቱ እንጂ በደግነትህ እንደሆነ አትቊጠር ። ከሚዋጉህ ይልቅ የሚረዱህ መላእክት እንዳሉ እመን ። ሳይዘናጋ በሚጠብቅህ በእግዚአብሔር ደስ ይበልህ ። ጥንቃቄህ ፍርሃት ፣ ማስተዋልህ ማጥራት እንዳይሆን ተጠንቀቅ ።
ወደ ክርስቶስ መገስገስ 15
ተጻፈ አዲስ አበባ
ኅዳር 2 ቀን 2011 ዓ.ም.
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ