የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እንደ እኔ ከተሰማችሁ ክፍል 1

አንባቢው የዕለቱን ምንባብ ከኢሳይያስ የትንቢት መጽሐፍ ምዕራፍ 61 ገልጦ አነበበ፡፡ የምኲራቡ ረቢም ሊቀ ካህኑን እጅ ነሥተው ለሕዝቡ ለመተርጎም ወደ አትሮኖሱ ተጠጉ፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ሲነበብም ሲተረጎምም በደስታ ላይ ደስታ ይጨምራል፡፡ የተገለጠውን መጽሐፍ ከድነው አሳለሙን፡፡ አንብበው ሲስሙት መልካም ነው፡፡ በረከትን ተቀብለን ከምኲራቡ ወደ ዕለት ኑሮአችን ወጣን፡፡ ቀኑ በስሙ ካልተከፈተ፣ የቃሉ ኃይል ካልተጨበጠ ያታግላል፡፡ አሁን ግን ድል ጨብጦ ውጊያ ነውና በልበ ሙሉነት ወጣሁ፡፡ ከምኲራቡ ቅጽር ግቢ እንደ ወጣሁ በልቤ ላይ የጸሎት ደመና እንደ ሞላ አስተዋልሁ፡፡ ያንን ካላፈሰስኩ ዕረፍት የለኝምና እንደገና ወደ ምኲራቡ ተመለስኩ፡፡ የሚዋደዱ ወዳጆች ከተሰነባበቱ በኋላ ጨዋታ ይጀምራሉ፡፡ መለያየቱ እያስፈራቸው እንደገና ይጨባበጣሉ፡፡ እግዚአብሔርም ሊሰናበቱት የሚያቅት ወዳጅ ነው፡፡ ሆዴ ይርገበገባል፡፡ የእናትነት ርኅራኄ ሳይሆን የመንፈስ ቅዱስ ርኅራኄ ውስጤን ሞላው፡፡ የማያስጨንቀው ቅዱስ ርኅራኄ ወደ እኔ መጥቷል፡፡ እግዚአብሔር ሊሰማኝ ሲፈልግ ጸሎቱንም እንደሚሰጠኝ ልምድ አለኝ፡፡
“ዘንድሮስ ጨክኛለሁ፣ ተለውጫለሁ” እያልኩ ስደነቅ ሰነበትሁ፡፡ ዛሬ ግን ራሴን ሳየው አላለቅሁም፣ ገና በጅምር ነኝ፡፡ “አይ ሰው መቼ ይሆን ተሠርቶ የሚያልቀው?” ያ ጎረቤቴ “ሰው ተጠንቶ የማያልቅ ፍጡር ነው” ያለኝ ለካ እውነት ነው፡፡ እንኳን ስለ ሰዎች ስለ ራሴም በእርግጠኝነት መናገር ተሳነኝ፡፡ ከምኲራቡ ዛፎች አንዱን ተጠግቼ ቆምኩ፡፡ ከጸሎቴ ዕንባዬ ቀደመ፡፡ ብዙ ነገሮች የተበላሹ፣ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ሁሉም ሰው የጠፋ መስሎ ተሰማኝ፡፡ ስለዚያ ስለ አንዱ ልጄ አሰብኩና ሁሉም ልጄ እንደሆነ፣ በጸሎት አድልኦ እንደሌለ፣ ለጠፉት ሁሉ መጸለይ እንደሚገባኝ አሰብኩ፡፡ ጸሎቴ በዕንባ ታጀበ፡–
የእስራኤል አምላክ እኛ ስንተኛ የማትተኛ፣ በእንቅልፋችን ከተዘራው እንክርዳድ የምትጠብቀን፣ ለደካሞቹ ብርቱ መጠጊያ የሆንከን አንተ ነህ፡፡ አንተ ያልከበርክበት ማንነት ሐፍረት አለበት፡፡ እባክህ ጌታዬ አንተን ለማወቅ ልቡን የዘጋውን ይህን ትውልድ፣ በሮማ ጭካኔ፣ በግሪክ ዝሙት የተያዘውን ይህን ወገኔን እባክህ አሁን አስበው፡፡ ዓይኔን አሽተህ እንዳይህ ያደረግኸኝ፣ እስካውቅህ በብዙ የመራኸኝ አንተ ነህ፡፡ እባክህ ሕዝብህ ቃልህን የመረጠ፣ አንተን የተቆራኘ፣ አንተን ከፍ አድርጎ በልዩነት የሚያከብርህ ይሁን፡፡ ከፍልስጤማውያን ጣዖትና ከአሞራውያን ሟርት ለየው፡፡ ዘመንን ከማምለክ ጠብቀው፡፡ ከኪስ ጣዖት ከገንዘብ አምልኰ አድነው፡፡ አንተ የአብርሃም አምላክ በመንፈሳዊው ቦታ መንፈሳዊ ሰው አስቀምጥበት፡፡ ለመንጋው የሚራሩ፣ ቃልህ ሲነገር የሚደሰቱ፣ በሙሉ ልብ ለቤትህ ሥራ የሚተጉ አባቶችን አሥነሣልን፡፡ ዕንባችንን ከዓይናችን፣ ብሶታችንን ከልባችን አብስልን፡፡ ፊታችንን በደስታ ዘይት ቅባ፡፡ ሕጻናቱን ባርክ፣ ወጣቱን በሥነ ምግባር ገንባልን፡፡ ወንጀለኛ ዳኞችን፣ የጠፉ አገልጋዮችን፣ የጨከኑ መሪዎችን ፈውስልን፡፡ ሽማግሌዎች ምድርን የሚያጎሳቁሉ አይሁኑ፡፡ የምንናገረው እንደ ቃልህ፣ የምናገለግለው በእምነት ይሁንልን፡፡ የቅባትህን ጉልበት ይለቀቅልን፡፡ እኔን ሰው ብለህ ስለሰማኸኝ ተመስገን፡፡ ፍቅርህን ያሳዘንበትን፣ እውነትን ያሳበልንበትን፣ ወንጀለኛን ንጹሕ ነህ ያልንበትን፣ ለጽድቅ ጀርባችንን የሰጠንበትን ዘመን ይቅር በል፡፡ ስለ አገልጋዮች ክፋት፣ ስለ ሕዝብህ ስህተት ይቅርታ እጠይቅሃለሁ፡፡ የኃጢአታችንን ብዛት፣ የሰውነታችንን ርኲሰት አትይብን፡፡ አንተን የተውንበትን፣ ክብርህን የጋረድንበትን፣ ብርና ወርቁን ወደን ሕዝቡን የገፋንበትን ዘመን ይቅር በል፡፡ በሞራል ነቀዝ የተበላውን፣ በሱስ የተጠቃውን ትውልድ ይቅር በል፡፡ እውነትን በጥንቃቄ ያየንበትን፣ ውሸትን በር ከፍተን የተቀበልንበትን ወራት ይቅር በል፡፡ ካንተ የሸሸነውን ራሳችንን ያመነውን፣ ሞትን መንገድ አጋምሰን የተቀበልነውን፣ ፍርሃትን ያስተናገድነውን፣ በቂም በበቀል፣ በዘረኝነት የታወርነውን ይቅር በለን፡፡ አንተን ስለሚጠላ የጠላንን፣ ተኝተን ሳለን እንክርዳድ የዘራብንን ጠላት ገስጸው፡፡ በቃል ኪዳን ፍቅርህ፣ በአርያም ፈውስህ ጎብኘን ለዘላለሙ አሜን!
አሁን ልቤ ረሰረሰ፡፡ ጸሎቴን ለሚሰማው ጌታ አፈሰስኩ፡፡ ሰሚ አጥቼአለሁና ልስማሽ ካላችሁኝ፣ ሰው ካልረከሰባችሁ እንግዲያው ላዋራችሁ፡– ኑሮዬን የመሠረትኩት በሰሜን እስራኤል በናይን ከተማ ነው፡፡ ዓመተ ፍዳና ዓመተ ምሕረትን ለማየት በቅቻለሁ፡፡ ቋሚ አድራሻዬ የእግዚአብሔር መዝገብ ነው፡፡ ዓለም ስንቴ ጽፋ ስንቴ ሰርዛኛለች፡፡ ብዙ ጊዜ ተሠርቼ ብዙ ጊዜ ፈርሻለሁ፡፡ ሰዎች ታሪኬን ያስሳሉ፡፡ ከታሪኬ በፊት የወደደኝ ግን ዛሬም በዙፋኑ ነው፡፡ ወዶ መጥላት፣ ታምኖ መክዳት፣ ጽፎ መሠረዝ አይሆንለትምና ይኸው አለሁ፡፡ ቤትሽ የት ነው? እግር ቢጥለኝ እጎበኝሻለሁ የሚለኝ ካገኘሁ በሉቃስ ወንጌላዊ መኖሪያ ቤት አለፍ ብሎ ሰባተኛው መጠምዘዣ ላይ እገኛለሁ፡፡ ሰው አግኝታችሁ ያቺ ስም የለሽ፣ ያቺ ባልቴት፣ ያቺ ልጇን እንደገና ወልዳ የሳመች ብላችሁ ብትጠይቁ በሉቃስ ሰፈር ሰባተኛው መንገድ ላይ እገኛለሁ፡፡
ዕድሜ እየገፋ ሲሄድ መደነቅ እየበረደ ይመጣል፡፡ የፈሩት እንደሚደርስ የጠሉት እንደሚወርስ ዕድሜ መስተዋት ሆኖ ያሳያል፡፡ ዕድሜ ሲገፋ አይሆንም ከማለት ይሆናልን መጠበቅ፣ ጠርጣሪነት እየበረከተ ይመጣል፡፡ አሉታዊነት ሕይወትን መዋጋት ይጀምራል፡፡ ጠርጣሪነት የእምነትን ቦታ ይይዛል፡፡ የኑሮ ልምድ ፈሪ፣ ቃሉ ግን አማኒ ያደርጋል፡፡ አሳብ ያውም የራስን ኑሮ እንዲሰርዙ የሚያደርገው የልጅ አሳብ አቅምን እንደ ነቀዝ ይበላታል፡፡ የወላጆች ውለታ ይታወሳል፣ ለመክፈል ግን ጊዜው አልፏል፡፡ ልጅነት ይናፈቃል፣ ልሁን ቢሉት ያስተቻል፡፡ የበላይ ወላጆችን፣ የበታች ልጆችን እያሰቡ መወዝወዝ የባልቴትነት ፈተና ነው፡፡ የሽምግልና ትምህርቱ ብዙ ነው፣ ትምህርቱን በኑሮ ለመተርጎም ግን ጊዜ ያለፈ ይመስላል፡፡ እውነትን ለመምረጥ አንድ ቀንም በቂ ነው፡፡ ከአእላፋት የማስመሰል
ዘመን፣ እውነትን የኖርንባት አንዲት ቀን እርሷ ትበልጣለች፡፡ ብቻ ዕድሜዬን ከሚያረዝሙ ነገሮች አንዱ ጸሎት ማብዛት ሁለተኛው በማይመለከቱን ነገሮች አለመግባት ነው፡፡ ዕድሜ የመለወጥ ዕድል እንጂ የትካዜ አደባባይ አይደለም፡፡ አውታታ አሮጊት ነኝ አልልም፡፡ አካሌ እንጂ መንፈሴ አላረጀም፡፡ ቃሉ ሽምግልናዬን አለምልሞታል፡፡ ስለ ትውልድ እንጂ ስለ ራሴ የምፈራውና የማፍረው ርቆልኛል፡፡ በአካል ጠንክረው በመንፈስ ለሸመገሉት ትውልዶች የማዝን የምጸልይ ነኝ፡፡
የኖርኩበት ዘመኔ ረጅም ይመስለኛል፡፡ መከራ ከቀኑ በፊት ብዙ ነገሮችን ያሳውቃልና መከረኞች ነገን ዛሬ ላይ የሚማሩ ናቸው፡፡ የመከራ ዘመን ረጅም ነው፡፡ አንዱ ቀን የዓመት ያህል ነው፡፡ የዕድል ነገር ሆኖ ሁሉም ነገር በቀላሉ አይሆንልኝም፡፡ እኔ ጋ ሲደርሱ ቀጤማ የሆኑ ችግሮች ብረት ይሆናሉ፡፡ የተወለዱበት አካባቢ አድጎ ሥራ መጀመር፣ ተድሮ መውለድ ለሕሊና ሙቀት የሚሰጥ ቢሆንም ኑሮ እልፍ አይልም፡፡ አእምሮም አዲስ ዕውቀት አያገኝም፡፡ ሁልጊዜ አንድ ዓይነት ነገር የሚያይ በአንድ ዓይነት ፈተና ውስጥ የሚያልፍ ነፍሱ አታድግም፡፡ እልፍ ብሎ መኖር ዕውቀትን ያበረክታል፣ ወዳጅን ያበዛል፡፡ ታዲያ ያለ ጥንቃቄ ከእግዚአብሔር ጋር እንኖራለን፡፡ ዓሣን መብላትና ሰውን መቅረብ ከብልሃት ጋር ነው፡፡ ከተወለዱበትና ካደጉበት ራቅ ብለው ሲኖሩ ወዳጁ አይበረክትም፡፡ እኛ የጀመርነው እኛ ጋ ይመስላቸዋል፡፡ እንደ ምልምል ዛፍ ይቆጥሩናል፡፡ ተወልደው ባደጉበት ሰፈር ግን ስለ እኛ ብቻ ሳይሆን ስለ ወላጆቻችን ይወራል፣ ሰዎች ሲጠሩን ስማችንን እስከነአያታችን ነው፡፡ የረሳነው ታሪካችንን አስታውሰው ይነግሩናል፡፡ ፕሮቶኮል የለም፣ በእውነት ይቀርቡናል፡፡ ቢሆንም ባደግንበት ሰፈር ዕውቀትን ብንገልጥ በየት በኩል እኛን አልፋ አገኘችው በማለት ይቃወሙናል፡፡ ባደጉበት ሰፈር ጆሮን ማግኘት ይከብዳል፡፡ እግዚአብሔር ባስቀመጠን ስፍራ ስንኖር ግን ሁሉ ይዋባል፡፡
በናይን ሰፈር ካለፋችሁ እንጀራ ባይኖረኝ ፍቅርን ላቀርብላችሁ ዝግጁ ነኝ፡፡ የአሮጊት አቅሜን እወቁልኝ፡፡ ዓመታትን በሰዓታት መተረክ ይከብደኛል፡፡ ሲኖሩት ረጅም ሲተርኩት አጭር ነው የዚህ ዓለም ኑሮ፡፡ እንደ እኔ ከተሰማችሁ መኖር መልካም ነው፡፡ የበለጠ ያሳያል፡፡
ማለዳ ለጉባዔ ጸሎት ሳልወጣ እንገናኝ፡፡ ነገን ኖረን ለክብሩ ለመቆም ያብቃን፡፡
ይቀጥላል
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ