እግዚአብሔርን መከተል ልጅ ወላጁን ፣ ዓይነ ሥውር መሪውን ፣ ወታደር አዝማቹን፣ ሐረግ ጫፉን ፣ ሰንሰለት ቀዳሚውን ፣ ክር መርፌውን እንደሚከተል በፍጹም እምነትና ጽኑ በሆነ ኅብረት መከተል ነው ፡፡ እግዚአብሔርን መከተል ጨለማ የተባለ አለማወቅ ፣ አልጫ የተባለ ብቸኝነት ፣ ዓመፅ የተባለ አለማመን አይገጥመውም ፡፡ እግዚአብሔርን መከተል በፍጹም እረኝነቱ መተማመን ነው ፡፡ እግዚአብሔርን በፍጹም ልባቸው የተከተሉ አላፈሩም ፡፡ እውነት የልብን ብርሃን ታሰጣቸዋለች ፡፡ በክርስቶስ ከማየታቸው በፊትም ክርስቶስን እንዲያዩ ትነግራቸዋለች ፡፡ ብርሃን ያሳያል እንጂ አይታይም ፡፡ ክርስቶስ ግን የሚታይና የሚያሳይ ብርሃን ነው ፡፡
ፍጹም መምህር ክርስቶስን ቃሎቹን ልንሰማ ኑሮውንም ልንከተል ይገባናል ፡፡ ቃልና ኑሮ የተስማሙለት መምህር እርሱ ነው ፡፡ ያዘዘንንም እንድንፈጽም በንጉሣዊ ኃይሉ ያግዘናል ፡፡ እርሱ ብቻ ከልብ ዕውርነት ያድናል ፡፡ የልብ ዕውርነት የክርስቶስን ጽድቅ ትቶ የሰዎችን ኃጢአት ሲያዩ መዋል ነው ፡፡ የልብ ዕውርነት በማይጠቅሙና በፍርድ ቀን በማንከሰስባቸው በሰዎች ጉዳይ አሳብ ሲሰጡ መዋል ነው ፡፡ የልብ ዕውርነት የሚወዱንን አለመውደድ ፣ መልካም ያደረጉልንን ረግጠን መሄድ ፣ ለእኛ የኖሩትን ላጥፋችሁ ማለት ፣ ያጽናኑንን ማቁሰል ፣ ውለታ ቢስ ማንነት ነው ፡፡ ይህን ማንነት መያዝ ሲኦልን በቁም ተሸክሞ እንደ መዞር ነው ፡፡ የልብ ዕውርነት የእኔ የብቻዬ ፣ የሌሎች ግን የጋራ ብሎ ማሰብ ነው ፡፡ ራስ ወዳድነት የተጠናወተው ፣ ለግል ምቾት ብቻ ሌሎችን መፈለግ ያለበት ኑሮ እርሱ የልብ ዕውርነት ነው ፡፡ ከዚህ የልብ ዕርነት የሚያድነው የጌታችን ፍቅር ብቻ ነው ፡፡ የልብ ዕውርነት የተሰቀለውን ክርስቶስን አለማየት ፣ ለእርሱ በሚቀርበው የምስጋና ሽቱ እንደ ይሁዳ መበሳጨት ነው ፡፡ የልብ ዕውርነት ስለ ገንዘብ እንጂ ስለ ፍቅር ማሰብ አለመቻል ነው ፡፡ ስለ ጥቅም እንጂ ስለ ምስጋና ግዴለሽ መሆን ነው ፡፡
ክርስቶስ አለማወቅን ኃጢአትን እንደ ትላንት ቀን ፣ እንደ ፈሳሽ ውኃ የሚያሳልፍ ነው ፡፡ በምክሩ ወዳጅነቱን ፣ በተግሣጹ አባትነቱን እናያለን ፡፡ ከሁሉ በላይ የምንኖርበት ሕይወት ነው ፡፡ ቃሎቹን በሰማን ቁጥር እርሱ ከእኛ ጋር መሆኑን እናረጋግጣለን ፡፡ በታላቅ ፀጥታና ፈተና ውስጥም እርሱ ከእኛ ጋር ነው ፡፡ ከእኛ ጋር የሆነበት ፊርማው ደሙ ፣ ማኅተሙም አማኑኤል የተባለው ስሙ ነው ፡፡ ዋነኛው ተግባራችን ክርስትናን እንዴት ልኑረው ሳይሆን ክርስቶስ እንዴት ነው አርአያ የሆነው ብለን ማሰብ ነው ፡፡ ያን ጊዜ የማያሳስተውን መንገድ ፣ የተፈተነውን እውነት ፣ የማይጠፋውን ሕይወት እናገኛለን ፡፡ የክርስቶስን ሕይወት ለማሰብ ከዓለም ግርግር ፣ ከማይመለከቱን ጉዳዮች መራቅ ይገባናል ፡፡ ጸሎትና ቃሉን ማጥናት ያለበት ጽሞና ያስፈልገናል ፡፡