የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

አንቀጸ ብፁዓን/2/

የንጉሥ ጎዳና
የንጉሥ ጎዳና ከመካከሉ ነው ፡፡ እንደ ፈሪሳዊው ወግ አጥባቂነት ብቻ እንደ ሰዱቃዊው ዘመናዊት ብቻ አይደለም ፡፡ በየትኛውም ዘመን የሚያውኩ እነዚህ ሁለት ጽንፎች ዛሬም እያመሱን ይገኛሉ ፡፡ ፍቅር የሌለው እውነትና  ፣ እውነት የሌለው ፍቅር እየናጠን ይገኛል ፡፡ ፍቅር የሌለው እውነት ብዙዎችን እየሰበረ ፣ እውነት የሌለው ፍቅር ብዙዎችን በጅምር እያስቀረ ይገኛል ፡፡ የንጉሥ ጎዳና ግን እውነትን በፍቅር እንያዝ ይላል /ኤፌ. 4፡15/ ፡፡ በዛሬው ዘመን ክርስትና በአማኞቹ እየተንገዳገደ ይመስላል ፡፡ የሚያጠፋን ሲዘገይ ለመጠፋፋት ቢላዋ እየሳልን ሳይሆን አይቀርም ፡፡ ሰውዬው እንቅፋት ግጥም አድርጎ ሲመታው፡- “ይህ መንግሥት አላኖር አለን፣ የት ሄደን እንኑር” አለ ይባላል ፡፡ ክርስትናውን መኖር ሲያቅትም መጠቋቆም ይበዛል፡፡ ለአንዳንዶች ክርስትና እምነት ብቻ ነው ፤ ስለዚህ ሥርዓት የላቸውም ፡፡ ለአንዳንዶች ሥርዓት ብቻ ነው ፤ ስለዚህ እምነት የላቸውም ፡፡ ለአንዳንዶች ክርስትና በሥራ ብቻ ለመዳን የሚታገሉበት ነው ፤ ለአንዳንዶች ደግሞ ድኛለሁ ብሎ ልቅ የሆነ ኑሮ የሚኖሩበት ነው ፡፡ ሥራ የሚመስል ትዕቢትና እምነት የሚመስል ልቅነት እያወኩ ይገኛሉ ፡፡ ክርስትና ለአንዳንዶች የምቾት መንገድ ነው ፡፡ ለሌሎች የስቃይና የሰማዕትነት መንገድ ብቻ ነው ፡፡ ትንሽ ምቾት ሲያዩብን ክርስቲያን የማንመስላቸው አያሌ ናቸው ፡፡ ትንሽ መከራ ሲያዩብንም አላመናችሁም ብለው የሚከስሱን እየበዙ ነው ፡፡ ክርስትና በእግዚአብሔር ማረፍና የመስቀልን ሕይወት መኖር ወይም ዋጋ መክፈልም ነው ፡፡ ክርስቶስ መስቀልና ክብር ነውና ፡፡
“ሁን” የሚል ስብከት እየጠፋ ይሆንልሃል የሚል ትምህርት እየተስፋፋ ነው ፡፡ ክርስትና ሆነን የምናልፈው የተግባር ሕይወት ነው ፡፡  “ይሆንልሃል” የሚል ስብከት ብቻውን የስህተት ትምህርት ነው ፡፡  ሳትሆን አይሆንልህም ብለን እንመልሳለን ፡፡ ተማሪ ጥሩ ውጤት ሲያገኝ አገኘሁ ይላል ፡፡ መጥፎ ውጤት ሲያገኝ መምህሩ ሰጠኝ ይላል ፡፡ መልካም ነገሮች የራሳችን ፣ ክፉ ነገሮች ደግሞ ከራሳችን ውጭ ከመሰሉን አስቸጋሪ ነው ፡፡ እግዚአብሔር የሚባርክ አምላክ ነው ፡፡ ነገር ግን ምንህን ልባርክልህ ? ይላል ፡፡ እግዚአብሔርን እንደ ምትሐተኛ አምላክ ማሰብ ማለት ዘላለም መና እየወረደልኝ እኖራለሁ ማለት ነው ፡፡ በሕይወታችን የሚያጋጥሙን ብዙ ነገሮች የሥራችን ውጤቶች ናቸው ፡፡ ስምረትም ውድቀትም ፡፡ ብዙ የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት ያስፈልገናል ፡፡  መለወጥ ስህተትን ከማመን ይጀምራል ፡፡
አንዲት ሴት ወልዳ ወደ እናቷ፡- “እናቴ ሆይ ቅቤ ላኪልኝ” ብላ መልእክተኛ ላከች ፡፡ በርቀት ያሉት እናቷ በጋን ወተት ላኩላት ፡፡ እርስዋም ተበሳጭታ “ቅቤ አልኩሽ እንጂ ወተት አልኩሽ ወይ ?” ብላ መለሰችው ፡፡ እናትም ፡- “አይ የልጅ ነገር ሲያምርሽ ወተቱን እንድትጠጪ ፣ ሲያምርሽ አርግተሸ እርጎ እንድትጠጪ ፣ ሲያምርሽ ወተቱን ንጠሸ እንድትመገቢ ነበር” አሉ ይባላል ፡፡ ዛሬም እምነት ጥቅል ስጦታ መሆኑ ያልገባቸው እንዲህ ይላሉ ፡፡ ቁንጽል አሳብ ይዞ መሄድ እየተለመደ ነው ፡፡ የክርስቶስን ፡-
·       አምላክነቱን ትቶ ሰውነቱን ብቻ
·       ትምህርቱን ትቶ ተአምራቱን ይዞ መሄድ እየበዛ ነው ፡፡
በብፁዓን አንቀጽ ውስጥ መጀመሪያና መጨረሻ ላይ የተቀመጠው ሽልማት መንግሥተ ሰማያት ነው ፡፡ ማንኛውም በረከት የሚገኘው እንደ ሳንዱች በመንግሥተ ሰማያት ጅማሬና ፍጻሜ ውስጥ ነው ፡፡ መንግሥተ ሰማያት ወደ ፊት የሚገኝ የቦታ ለውጥ ሳይሆን አሁን የምንኖረው ሕይወት ነው ፡፡ የእግዚአብሔር መንግሥት የተጠቀሰው በአሁንና በሚመጣ ጊዜ ነው ፡፡
የተራራው ስብከት ከማቴዎስ 5-7 ተጠቅሷል ፡፡ በማቴዎስ 4 ላይ መንግሥቱ መመሥረቷን ገለጠ፡፡ መንግሥቱ ከተመሠረተ መመሪያው መታወጅ አለበት ፡፡ የተራራው ስብከት የመንግሥቱ አዋጅ ነው ፡፡ ያስተማረበት ስፍራ ተራራ ሲሆን በዙሪያው የጥብርያዶስ ባሕር አለ ፡፡ እጅግ ውብና ያማረ ስፍራ ነበር ፡፡ ጌታችን ለማስተማር ምን ያህል ሁለንተናን የሚያስደስት ነገር እንደሚመርጥ ስናይ ይገርመናል ፡፡ እርሱ እንዲህ ባማረ ሁኔታ ያስተማረውን ትምህርት እኛ በወዮልሽ ሽብር አጨልመነዋል ፡፡
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ