የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ሰነፍ አዋቂ ፣ ቸልተኛም ባለ ድል አይሆኑም

አባ እንጦንስ በበረሃ በሚኖርበት ጊዜ ብዙ የኃጢአት አሳቦች እየመጡበት መፈተን ጀመረ ፡፡  ወደ እግዚአብሔርም ጸለየ ፡- “ጌታ ሆይ ከዚህ ክፉ አሳብ መዳን እፈልጋለሁ ፣ እነዚህ የኃጢአት አሳቦች ግን ሊለቁኝ አልቻሉም፡ ይህን የፈተና ጊዜ እንዴት ማለፍ እችላለሁ ? ” በማለት ጠየቀ፡፡ ከትንሽ ቆይታ በኋላ ተነሥቶ ለመሄድ ሲል እርሱን የሚመስል አንድ ሰው በተግባረ ዕድ ተጠምዶ አየ ፡፡ ከሥራው ቀጥሎ ይጸልያል ፣ እንደገና ሥራውን ይሠራል ፣ ገመዱን ይጎነጉናል ፡፡ በመቀጠልም ለጸሎት ይነሣል ፡፡ ያ በትጉህ ሠራተኛ አምሳል የተገለጠው ግን እንዲያጽናናውና እንዲያርመው የተላከው መልአከ እግዚአብሔር ነው ፡፡ መልአኩም ቅዱሱን ፡- “ይህን አድርግና ትድናለህ” አለው ፡፡
ተግባረ ሥጋ የሰው ልጅ ከተፈጠረበት ዓላማ አንዱ ነው ፡፡ እግዚአብሔር አምላክ አዳምን በገነት ያስቀመጠው ተኝቶ እንዲበላ አይደለም ፡፡ “እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ወስዶ ያበጃትም ይጠብቃትም ዘንድ በዔድን ገነት አኖረው” ይላል /ዘፍ. 2፡15/፡፡ ገነት ሥራ ካለ እዚህ ምድር ላይማ ግድ ነው ፡፡ አዲስ ኪዳንም፡- “ሊሠራ የማይወድ አይብላ” የሚል ትእዛዝ አስተላልፏል /2ተሰ. 3፡10/፡፡ በገዳምም ፡- “ሥራ የፈታ መነኩሴ ቆቡን ቀዶ ይስፋ” የሚል ትእዛዝ አለ ፡፡ ምክንያቱም ሥራ ሲፈታ ክፉ አሳብ ይፈታተነዋል ለማለት ነው ፡፡ ከተሜውም ሥራ ከፈታ ንጹሕ ጨርቁን መልሶ ቢያጥብ የተሻለ ነው ፡፡ “ሥራ ከምፈታ ልጄን ላፋታ” የሚባለው ሥራ የፈታ ሰው እልል ብሎ የዳራትን ልጅ ኡኡ ብሎ እንደሚያፋታ የሚያሳይ ነው ፡፡አእምሮ በአንድ ጊዜ ብዙ አሳቦችን ያስባል ፡፡ አእምሮ ከመደበኛ ሥራ ባሻገርም በንባብ ፣ አካባቢን በማሳመር ፣ ራስን በመጠበቅ ወይም በንጽሕና ማረፍ ይገባዋል ፡፡ ማረፍ ማለት ከሥራ መለየት ሳይሆን በሥራ ማረፍ የተሻለ ነው ፡፡ ተፈጥሮአችን ተቀምጠን ስንነሣ እንድንታደስ ሁነን ነው፡፡ በተቀመጥን ቊጥር ዕረፍት አለ ፡፡ ሰው እንደ ደከመው ቢቀር ምን ይሆን ነበር ? ዕረፍትን ስንቆም ፣ ስንቀመጥ ፣ ስንተኛ ያዘጋጀልን አምላክ ስሙ ቡሩክ ይሁን !
ሰይጣናዊ አሳቦች ከሚመጡበት መንገድ አንዱ ሥራ ፈትነት ነው ፡፡ “ሥራ የፈታ አእምሮ የሰይጣን ወርክ ሾፕ ነው” የሚባለው ለዚህ ነው ፡፡ የኃጢአት አሳቦች ፣ ጭንቀቶች የሚመጡት ሥራ ስንፈታ ነው ፡፡ ሥራ ስንፈታ አካላችን ይተሳሰራል ፡፡ ደማችን በቅጡ አይዘዋወርም ፡፡ አካላዊ ጫናችን አእምሮአዊ ጫናም እያስከተለ ይመጣል ፡፡ የክብደት መጨመርም ባለመንቀሳቀስ ይመጣል ፡፡ ጡንቻዎቻችን  ካልሠራንባቸው ይሟሟሉ ፡፡ ስንሠራ ግን ይበረታሉ ፡፡ ፀሐፊውም ከጽሑፉ አጠገብ የሚበላና የሚሠራ ቢያስቀምጥ ፤ ጸሎተኛውም ከጸሎቱ ቀጥሎ ተግባረ ዕድ ቢያከናውን እየበረታ ይመጣል ፡፡ ነገን ለማረፍ ዛሬ መሥራት ይገባል ፡፡ የሠሩ አገሮች ዛሬ የሚያግዙ ማሽኖችን ፣ እንኳን ሰውን እንስሳን የሚያሳርፉ መንኮራኩሮችን ሠርተዋል ፡፡ ኑሮአቸውን ቀላል አድርገዋል ፡፡ እነርሱ ዛሬም ሌት ተቀን እየሮጡ ነው ፡፡ እኛ ግን ዳዴ በምትል አህጉር ውስጥ ተቀምጠን በስንፍና ተይዘናል ፡፡ የትርፍ ሰዓት ጉዳዮችን ዋና አድርገን ቀኑን በሙሉ ስለ ኳስ እናወራለን ፡፡ ከምግብ ቀጥሎ የሚወራውን ምግብ አድርገን ይዘናል ፡፡ ባዕድ አገር ላይ ስንሄድ ብዙ እንሠራለን ፡፡ ጉልበታችንን ግን ለአገራችን ነፍገናታል ፡፡ “የአገሬ አገሯ የት ነው” የሚል ርእስ ሰምቻለሁ ፡፡ ቻይኖች፡- “ኢትዮጵያውያን ሌላ አገር አላቸው ወይ ?” አሉ ይባላል ፡፡
መሥራት የአእምሮ እርካታን ያመጣል ፡፡ የነፍስ ኃይል የሆነውን አሳብን ያሳርፋል ፡፡ የመሥራት ክፍያው ገንዘብ ብቻ አይደለም ፣ ኅሊናን መያዙም ነው ፡፡ በተሰጠን እንትጋ ፡፡ ሳንሠራ ታገኛላችሁ የሚሉንን እኛን የሚያራቁቱን እንጂ የሚጠቅሙን አይደሉም ፡፡ ምክንያቱም ቀጥሎ ገንዘብ አምጡ ይላሉ ፡፡ ይሁንላችኋል ይሉናል ፤ እነርሱ ግን የሚሆንላቸው በእኛ ኪስ ነው ፡፡ “አገልግሎት ቢሆን በአገልግሎታችን እንትጋ፤ የሚያስተምርም ቢሆን በማስተማሩ ይትጋ፤ የሚመክርም ቢሆን በመምከሩ ይትጋ፤ የሚሰጥ በልግስና ይስጥ፤ የሚገዛ በትጋት ይግዛ፤ የሚምር በደስታ ይማር” /ሮሜ. 12፡7-8/፡፡ ስንፍና ድህነትን ፣ ቸልታም እርግማንን ያመጣል ፡፡ ሰነፍ አዋቂ ፣ ቸልተኛም ባለ ድል አይሆኑም ፡፡
ሴትዬዋ ጥጡን ባዝተው በመሶብ ላይ ከምረውታል ፡፡ ሰነፉን ሰው ጠርተው አንሣው ሲሉት አልችለውም አለ ፡፡ ሲቆጡት አነሣለሁ ብሎ መሶቡን ገና ሊነካው ሲል ነፋሱ አመለጠው ፡፡ እውነቱ መክበዱ ሳይሆን ኅሊናው ትንሹን ማክበዱ ነው ፡፡ ስንፍናም የተሳነን ነገር ማለት አይደለም፡፡ ሳይሞክሩ ደከመኝ ማለት ነው ፡፡ የዐሥር ደቂቃ መንገድን ሠላሳ ደቂቃ ታክሲ የምንጠብቅ ስንቶች ነን ? ለመቶ ብር ጉዳይ ሁለት መቶ ብር ጉቦ የምንከፍል አያሌ ነን ፡፡ ደመወዛችንን ረስተን  ባለ ጉዳዩን ይህን ያህል አምጣ የምንል ፣ ጉቦ መብት የመሰለን ስንት ሃይማኖተኞች አለን ፡፡
ሰውዬው እዚህ ቦታ ሄደህ ፣ ይህን ይዘህ ና ተብሎ ይላካል ፡፡ ሳይሄድ ውሎ ምሽት ላይ ምን አደረግኸው ሲሉት ፡- “ሳስበው ፣ ሳስበው ደከመኝ” አለ ይባላል፡፡ አዎ ሳንሠራ ግን ስናስበው ከደከመን ስንፍና ነው ፡፡ ስንቀመጥ ቅርቡ ሩቅ ነው ፡፡ አንድ ርምጃ ስንራመድ ግን ወደ ግቡ እየተጠጋን ነው ፡፡
ሥራ ፈትነት ተሳዳቢ ያደርጋል ፡፡ የብዙ ተሳዳቢዎች ችግር ሥራ መፍታት ነው ፡፡ የምሰድበው ሰው አጣሁ እያሉ የሚጨነቁ የመንደር ሰዎች ብዙ ናቸው ፡፡ ሴትዬዋ የሚሳደቡት ሰው አላልፍ ብሎ ረፈደባቸው ፡፡/ይህንንም ሥራ ብለውት/ ታዲያ ነጠላቸውን ለብሰው ራቅ ወዳለ ሰፈር ሊሄዱ ሲሰናዱ አንድ ሰው “እንደምን አደሩ” ብሎ ድምፁን አሰማ ፡፡ ሲወጡ መንገድ አላፊ ነው ፡፡ ቆይ መጥቷል አሉና፡- “ባድር ባላድር ምን አገባህ?” ብለው ሰደቡት ፡፡ እርሱም “ለነገረኛ ሰው እንደምን አደሩም ነገር ነው” አለ ይባላል ፡፡ ባለጌ ቢሻለው እንጂ አይድንም እንደሚባለው ተሳዳቢዎች ክርስቶስ ካልለወጣቸው ፣ ሥራ ካላገኙ በሽታቸው ይቀጥላል ፡፡
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ