የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ጊዜ ይመጣል

“ኢየሱስም እንዲህ አላት፦ አንቺ ሴት፥ እመኚኝ፥ በዚህ ተራራ ወይም በኢየሩሳሌም ለአብ የማትሰግዱበት ጊዜ ይመጣል” /ዮሐ. 4፥21/ ።
ጌታችን ሳምራዊቷ ሴት የሕይወትን ውኃ ፈልጋለችና ለንስሐ ጋበዛት። ሳምራዊቷ ሴት ግን ወደ እርስዋ የመጣውን ቀስት አቅጣጫውን አዞረችው ። ራስን ለማየት ፈተና የሆነውን የሃይማኖት ክርክር አነሣች ። በንስሐ የሚያልቀውን ርእስ ወደማያባራው የሃይማኖት ክርክር ውስጥ መክተት ከጥንት እስከ ዛሬ የሰዎች ጠባይ ነው ። አንተ ከአባታችን ከያዕቆብ ትበልጣለህን ? የሚለው መስቀለኛ ጥያቄ ወደ ሌላ ጥያቄ ተለወጠ ። አባቶቻችን በዚህ ተራራ ሰግደዋል ፣ እናንተ ደግሞ ስግደት በኢየሩሳሌም ነው ትላላችሁ በማለት ሁለተኛውን መስቀለኛ ጥያቄ አቀረበች ። ከዚህች ሴት አንደበት አባቶቻችን የሚለው ቃል አይጠፋም ። አባቶችን የሚመስል ሕይወት ግን አልነበራትም ። ለመለያየትና ለመከፋፋት አባቶች የሚል ድምፅ ታሰማለች ። አባቶቻችን እነ አብርሃም በዚህ ተራራ ሰግደዋል እናንተ ግን ስግደት በኢየሩሳሌም ነው ትላላችሁ አለችው ። ስግደት በገሪዛን ተራራ ብቻ መሆን እንዳለበት አምናለች ። ምክንያቱም አባቶቻችን በዚህ ተራራ ሰገዱ ብላለችና ። ወስና ትጠይቀዋለች ። መልሱን አውቃ ያቀረበችው ጥያቄ መፈተኛ ነበር ። የሴቲቱ ጭንቀት ግን እኔ ራሴ ላስበው የማልፈልገውን የእኔን ሕይወት አታስበው የሚል ነው ። ሥራ አላሠራ ለሚል ሕጻን ልጅ የጨዋታ ካርታ ሰጥተው እንደሚገላገሉት ፣ ለንስሐ የመጣውን ድምፅም በሃይማኖት ክርክር በመለወጥ ለመገላገል ፈለገች ። ክፉ ሴት ስለነበረች አይደለም ። ሕይወቷን ማሰብ ስለማትፈልግ ነው ። እኔ አልድንም ብላ ስለተቀመጠች መምህርንም ነቢይንም ማድከም አትፈልግም ። በራሷ ተስፋ ስለቆረጠች ተስፋ በሚያደርጉባት ትስቃለች ።
ጌታችን ግን ለምታቀርብለት የመገላገያ ጥያቄ ይመልስ የነበረው ውይይቱን በሚያስቀጥል ንግግር ነው ። አንድ ታማሚ ሁለተኛውን ጉርሻ አልቀበልም ብሎ ሲቆጣ አስታማሚው ቀስ አድርጎ አባብሎ ይሰጠዋል እንጂ የራሱ ጉዳይ ብሎ ጥሎት አይሄድም ። ጌታችን ኃጢአተኞችን እንደ በሽተኛ ያያቸው ነበር ። የሚራራላቸውም በፍቅር ዓይን ስላያቸው ነው ። የእግዚአብሔር መንግሥት በዚህ መንገድ ቢሰበክ ኑሮ ስንቱን ሰው ባሳረፍነው ነበር ። ጌታችን ስግደት በገሪዛን ነው ወይስ በኢየሩሳሌም የሚለውን ጥያቄ የመለሰው በልዩ ጥበብና ግልጽነት ነው ። በኢየሩሳሌም ነው ቢላት ጥላው ትሄድ ነበር ። ጌታችን ጥለው ለመሄድ ለሚፈልጉ ምስኪኖች መንገድ አይሰጥም ። ሆድ ለባሰው ማጭድ አታውሰው ይባላል ። ለብዙ መቶ ዓመታት የቆየው ክርክር የስግደቱ ማዕከል ኢየሩሳሌም ነው ፣ አይ አይደለም ደብረ ገሪዛን የሚል ነው ። እግዚአብሔርን የሚያከብረው ግን ከቦታው በላይ የልጆቹ አንድነት ነው ። በዘር ፣ በሃይማኖት ፣ በጾታ ተከፋፍለው እናመልክሃለን ቢሉት እግዚአብሔር አይደሰትም ። ልጆቹ ሁሉ መሥዋዕታቸውን ፣ ጸሎታቸውንና ምስጋናቸውን ቆም አድርገው ንስሐ ቢገቡ ፣ እርስ በርስ ቢታረቁ እግዚአብሔር ይደሰታል ። ፍቅር የሌለበት አገልግሎት ወደ ተዘጋ ሰማይ የሚደረግ ግስጋሴ ነው ። እየዘመርን ደስ የማይለን ፣ እየጸለይን የማንቀበለው ፣ እየተማርን የማንለወጠው ፍቅርንና ይቅርታን ስለጣልን ነው ።
“ኢየሱስም እንዲህ አላት፦ አንቺ ሴት፥ እመኚኝ፥ በዚህ ተራራ ወይም በኢየሩሳሌም ለአብ የማትሰግዱበት ጊዜ ይመጣል” አላት /ዮሐ. 4፥21/ ። ለአብ ለምን አለ ? እርሱስ ከአብ ጋር አምልኮ ተቀባይ አይደለም ወይ ? ቢሉ የሴቲቱን አእምሮ ለመጠበቅ ነው ። ስግደት ለእርሱ እንደሚገባ ቢነግራት ገና ነቢይ ነው ብላ ላመነች ሴት ብን የሚያደርግ ነው ። የሚገርመው በደብረ ገሪዛንም በኢየሩሳሌምም ለአብ እንደሚሰግዱ ጌታ ተናገረ ። ለሁለቱም እውቅና ሰጠ ። በደብረ ገሪዛን መሥዋዕቱ ሲያርግ ፣  በኢየሩሳሌምም መሥዋዕቱ ሲያርግ አብ በመገረም ያየዋል ። ምክንያቱም ሁለት ልጆች የወለደ አንድ አባት ሁለት ልጆቹ በየራሳቸው ስጦታ ይዘውለት ሲመጡ ሁለቱ ግን ተኳርፈው ደግሞም ለሞት ሲፈላለጉ ያያል ። ከስጦታችሁ በላይ መጀመሪያ ታረቁልኝ አይልም ወይ ? ጌታችን ለአብ በሚል ቃል መናገሩ ድንቅ ነው ። እግዚአብሔር የሁለት ልጆች አባት መሆኑን በጠፋው ልጅ ታሪክም እናያለን ። በቤት የሚያቆስልና በደጀ ፋንኖ የወጣ ሁለት ልጆች ያሉት አባት ነው ። ከአገልግሎት በፊት እርሱን ማወቅን ፣ ከመሥዋዕት በፊት መፋቀርን ይፈልጋል ። ምክንያቱም እርሱ አብ ወይም አባት ነውና ። እግዚአብሔር የሌለበት ለእግዚአብሔር መቅናት ከባድ ነው ። እግዚአብሔርን የራስ ዓመፅ ተባባሪ ማድረግ ነውና በደሉ ከፍ ያለ ነው ። በራስ ስም ከሚሠራ የዓለማውያን ኃጢአት በእግዚአብሔር ስም የሚሠራ የአማንያን ኃጢአት ከባድ ነው ።
እግዚአብሔር የደብረ ገሪዛንና የኢየሩሳሌምን እውቅና የሚያነሣበት ጊዜ እንደ ቀረበ ጌታችን ተናገረ ። ምክንያቱም እግዚአብሔር የሚፈልገው አምልኮ ቢያንስ ሦስት ነገሮች ያሉት ነው ።
1-  እውቀት
2-  መመሰጥ
3-  እውነት
ጌታችን ትልቅ ትንቢት ነገራት ። ከአርባ ዓመት በኋላም ይህ ትንቢት ተፈጸመ ። መላው እስራኤል በሮማውያን ተደመሰሰ ። ደብረ ገሪዛንም ሆነ የኢየሩሳሌም መቅደስ ወደመ ። ይልቁንም ደብረ ገሪዛን በአይሁድ ወድሞ ነበርና የኢየሩሳሌም መቅደስ ግን በሮማውያን ተደመሰሰ ። የመቅደሱ እያንዳንዱ ድንጋይ ተለቅሞም በደቡብ ኢየሩሳሌም ባለው ሸለቆ ተወረወረ ። ጌታችን ይህን የሚያህል ምሥጢር ለአንዲት ሴት መናገሩ ይገርማል ። የሕዝብ ተወካይ ለነበረው ለኒቆዲሞስ ያልነገረውን ለዚህች ሴት መንገሩ ይገርማል ። ለኒቆዲሞስ ግላዊ ሕይወቱን በሚመለከት ተናገረ ፣ ለዚህች ሴት ግን ብሔራዊና ሃይማኖታዊ እንዲሁም መጻኢ ጉዳዮችን ነገራት ። ለኒቆዲሞስ ብሔራዊ ጉዳይን ለዚህች ሴት ግላዊ ሕይወቷን ቢነግር መልካም ነበር ። ይህ የእኛ ቀመር ነው ። እግዚአብሔር ግን መንገዱ ከሰው መንገድ የተለየ ነው ።
ስግደት የሚለው ቃል አምልኮተ እግዚአብሔር ማለት ነው ። ስግደት የሰውን ሥጋ ፣ ነፍስ እንዲሁም መንፈስ የሚያስተባብር ነው ። ትልቅ የአምልኮ መገለጫም ነው ። ለእግዚአብሔር የመዋረድ ፣ ክብርን የመጣል ምልክት ነው ። ስለዚህ አምልኮተ እግዚአብሔር ስግደት በሚል ቃል ሊጠራ ይችላል ። ጌታችንም ለእግዚአብሔር የምትጸልዩበት ፣ የምትዘምሩበት ፣ መሥዋዕት የምታቀርቡበት ከማለት የምትሰግዱበት ብሏል ። ይህ የሚያሳየን በስግደት ውስጥ ፡-
–     ስብሐት /ስለ ህልውናው ስለ ጌትነቱ ክብር መስጠት/ ፣
–     ውዳሴ /ስለ ባሕርዩ ስለ ተግባሩ አድናቆት/ ፣
–     አኮቴት /ስለተደረገልን ነገር ምስጋና/ ፣
–     አስተብቊዖት /ለወደፊት እንዲፈጽምልን ልመና/ ስላለ ነው ።
ስግደት ለሰገደው ልብ መግለጫ ሲሆን ብዙ ኃይል አለው ። ጌታችን አምልኮን ስግደት በሚል ቃል ገለጠው ። ሰግደን የምናናግረው እግዚአብሔርን በመሆኑ ስግደት ለእግዚአብሔር አምላክነት እውቅና የምንሰጥበትም ነው ።
“ኢየሱስም እንዲህ አላት፦ አንቺ ሴት፥ እመኚኝ፥ በዚህ ተራራ ወይም በኢየሩሳሌም ለአብ የማትሰግዱበት ጊዜ ይመጣል” /ዮሐ. 4፥21/ ። አዎ ጊዜ ይመጣል ። የተጣላንበት ፣ የተባላንበት ፣ የተገዳደልንበት ነገር ሁሉ የሚያበቃበት ፤ ራሳችንን የምንታዘብበት ጊዜ ይመጣል ። ዛሬ የሚያጸጽቱን ነገሮች ትላንት ላይ ልክ የነበርንባቸው ነገሮች ናቸው ። ዛሬ ላይ ልክ መስሎን ያደረግናቸው ነገሮች ነገ ላይ እናዝንባቸዋለን ። ጊዜ ይመጣል ። የቆመም የሚወድቅበት ፣ የወደቀም የሚቆምበት ጊዜ ይመጣል ። ትላንት እየተሳደቡ ይሰጡ የነበሩ ዛሬ ለምነው ሲያጡ አይተናል ። ጊዜ ይመጣል ። ያለው እንደሌለው የሌለው እንዳለው የሚሆንበት ጊዜ ይመጣል ። ጊዜ ያልነውም እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ ሰው የወሰነለት የምሕረት ወራት ነው። ሀብቱ የከበደውን መንጠቅም ምሕረት ነው ። ሥልጣን የከበደውን ማሳረፍም ምሕረት ነው ። እግዚአብሔር ጽዋን የሚያለዋውጥበት ጊዜ ይመጣል ። መስቀል አሸካሚዎች መስቀል የሚሸከሙበት ፣ እርጥብ መስቀል ያሸከሙ ደረቅ መስቀል የሚሸከሙበት ጊዜ ይመጣል ። በጅራፍ የገረፉ በጊንጥ የሚገረፉበት ፣ ነፋስ የዘሩ አውሎ ነፋስ የሚያጭዱበት ጊዜ ይመጣል ። ምርቱ ከተዘራው በላይ ነውና ።
ጌታ ኢየሱስ ሳምራዊቷን ሴት ፡- “እመኚኝ” አላት ። ሰዎች ማመን የሚቸግራቸው ጊዜ እንደሚመጣ ነውና ። አሁን ያለው ሙግትና ክርክር ዘላለም የሚኖር ይመስላቸዋል ። እንዳለ የሚኖር እግዚአብሔር ብቻ ነው ። ያለፈው የነበረ እስከማይመስል አሻራ እንኳ ሳይተው ሂዷል ። ያለውም የማይጠፋ እስኪመስል ያስጨንቃል ። ያለው የሚያልፈው እንዳለፈው ጊዜ ነው ። ሁሉም ተረት ለመሆን ይቸኩላል ። ከዘመናት በፊት የነበረው የታላላቅ ጀግኖችና የጦርነት ውሎአቸው ዛሬ የሕጻናት መጫወቻ ሁኗል ። የሚታየው ወደ አለመታየት ይለወጣል ። የማይታየው ከታየ ፣ የታየውም የማይታይ ይሆናል ። ዛሬ የሚንጎማለለው ሰው ከልደቱ በፊት የማይታይ ነበረ ። አሁን ታይቷል ። ነገ ደግሞ የማይታይ ይሆናል ። ጊዜ ይመጣልና ተጽናኑ ። እግዚአብሔር ለሁሉ ሰው ጊዜ አዘጋጅቷል ። ሳትሰለቹ በበጎ ሥራ ጽኑ ። ብድር ከፋዩ ይመጣል ። አንድ የሰሜን ኢትዮጵያ አባባል አለ ፡- “ክፉዎች ይጕዱህ እንጂ ክፉ አያድርጉህ።”
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ