“ሴቲቱ፡- ጌታ ሆይ፥ መቅጃ የለህም ጕድጓዱም ጥልቅ ነው፤ እንግዲህ የሕይወት ውኃ ከወዴት ታገኛለህ? …አለችው” /ዮሐ. 4፥11/ ።
ጌታችን የሳምራዊቷን ሴት ሕሊናዋን ጠበቀ ። እውቀቷንም ቀስ በቀስ አሳደገ ። እርሱ ሥጋ በለበሰ ጊዜ ቀስ ቀስ አደገ እንጂ አምላክ ነኝ ብሎ ዕለቱን ልደግ አላለም ። ቀስ በቀስ ማደግ እርሱ የዘረጋው የውበትና የጥንካሬ ምንጭ ነውና ። ከቀናቸው በፊት የሚያድጉ ነገሮች ብዛት እንጂ ጣዕም ፣ ሆድ መሙላት እንጂ በሽታ መከላከል ፣ ርካሽነት እንጂ ውበት እንደሌላቸው ከምንመገበው ምግብ እያየን ነው ። እነዚህ ምግቦች በጊዜ ማደግ ቢችሉ ተፈጥሮአቸውንና ገጸ በረከታቸውን በጠበቁ ነበር ። ስለዚህም ለማይድኑ በሽታዎች እየተዳረግን ፣ የምንበላውን ምግብ ሳይቀር እየሰጋን ነው ። ቀስ ብሎ ማደግ በመንፈሳዊ ዓለምም ብዙ ጤና አለው ። መሬት እየያዙ ፣ ሥር እየቆነጠጡ ፣ ቅጠል እያወጡ ፣ ግንድ እያጸኑ ፣ ቅርንጫፍ እየዘረዘሩ ማደግ ለብዙ ፍሬ ያበቃል ። ተራሮች ለሺህ ዘመናት ጸንተው የሚታዩበት ምሥጢር መሠረታቸውን ሰፋ ስላደረጉ ነው ። ከመሠረታቸው ሰፋ ብለው ከጫፉ ጠበብ ይላሉ ። የግብጽ ፒራሚዶች ሦስት ሺህ ዓመታትን ያስቆጠሩት ከመሠረታቸው ሰፋ ብለው ወደ ላይ ጠበብ ስላሉ ነው ። ፒራሚድን ብንገለብጠው እንኳን ሦስት ሺህ ዓመት ሦስት ደቂቃ መቆየት አይችልም ። ሁሉን ነገር አውቀን ማደር የለብንም ። የምንኖረው የማናውቀውን አዲስ ነገርም ለማወቅ ነውና ሕይወት ነገም ትቀጥላለች ። ግሪኮች፡- “እስክንሞት ለዘላለም የምንማር ነን” ብለዋል ። ትምህርት እስከ ሞት ብቻ ሳይሆን እስከ ዘላለምም ነው ። ወደ ሰማይ የምንሄደውም ዘላለም የማይጠገበውን የእግዚአብሔርን አዲስነት ለማመስገን ነው ።
ምግቦች ብቻ ሳይሆን ሥልጣንም ፣ እውቀትም ፣ ሀብትም የዕድገት ሕግን እያፈረሱ እንደሆነ እያየን ነው ። ሰዎች ከመጨረሻው ከጀመሩ ወደ መጀመሪያው ይሄዳሉ ። ይህ ሕግ ነው ። ገና ከኮሌጅ ወጥቶ የሥራ ማስታወቂያ የሚያየው ወጣት የሚያስበው ስለሚሊየነርነት ነው ። የአንድ ወር ደመወዝን ሳይበላ ስለሚሊየን ማሰብ በራሱ ጤንነት አይደለም ። በሕዝብ አገልግሎቶችና በወታደራዊ ተቋማት መዐርጎች በተራ መሰጠት አለባቸው ። አሊያ ይረክሳል ። መዐርግ ደረጃን መውጣት ነው ። አንደኛውን ደረጃ በትክክል ስንረግጥ ሁለተኛውን መርገጥ እንችላለን ። አሁን ግን የምናየው ደረጃው ቀርቶ በሊፍት መውጣት ነው ። ያለ ደረጃ የወጣ ያለ ደረጃ ይወርዳል ። ተኝተው ሲነቁ ሚሊየነር ከሆኑ ቀኑን ተስፋ ቆርጠው ይውላሉ። አንድን ነገር ለማግኘት የሚደረግ ትግልና ያንን ነገር ካገኙ በኋላ ያለው ደስታ በሕይወት ውስጥ ቅዱስ ሕመምና ቅዱስ ደስታ ነው ። በዛሬው ዘመን ሰዎች በአንድ ቀን ተዋውቀው “እገልዬ” ይባባላሉ ። ካወቁት አንድ ሰዓት ያልሞላውን ሰው ለሌላ ሰው በደንብ ያስተዋውቁታል ። ቅልጥፍ ያለ ዘመን ቢመስልም እውነተኛነትና ዘላቂነት ግን የለውም ። በዚህ ምክንያት ተረኛ ወዳጅ እንጂ ዘላቂ ወዳጅ እየጠፋ ነው ። ሁሉም ነገር እፍፍ ነው ። ለማቀጣጠል እፍ ፣ ለማጥፋትም እፍ ተገቢ አይደለም ። የድግስ ዕቃው ተሟልቶ ሳይመለስ ብዙ ትዳሮች አደጋ ገጥሟቸዋል ። በፌስ ቡክ የተጀመረ ግንኙነት መሬት ላይ ሲወርድ መቆም ያቅተዋል ። በረቂቅ ቴክኖሎጂ የጀመረ ፍቅር አካላዊ ሲሆን መጸያየፍ ይመጣል ። በፎቶ የጀመረ መደናነቅ በአካል ያለውን መልክ ሲያይ አልወደድኩም ያሰኛል ። ቅዱስ ለማለትም ርኩስ ለማለትም ወረፋ ማጣት ተገቢ አይደለም ። ሳናውቀው ይህን አኗኗር እየተላመድነው ነው ። የሚያሰጋው መሳሳታችን ሳይሆን መልመዳችን ነው ። ምንጣፍ እያነጠፍን ፣ ከከተማው ወጥተን የተቀበልናቸውን አገልጋዮች አቧሯ እያጨስን ይጥፉ ማለት የተለመደ ነው ። እንደውም የተፈቀደ ይመስላል ። ስንገናኝ ያዙኝ ልቀቁን ማለት ስንለያይ ወዲያው መረሳሳት ፣ በስልክ እንኳ ለመገናኘት መጸያየፍ የለመድነው ነው ። የናፈቁንን ቤተሰቦች ለማግኘት ከሩቅ መጓዝ ካገኘናቸውና ከተደሰትን በኋላ ወደ መጣንበት ስንመለስ ባወጣነው ወጪ ብስጭት ውስጥ መግባት የብዙ ስደተኛ ጠባይ ነው ።
ሁሉም ነገር የዕድገት ሕጉን ቢጠብቅ ኑሮ ዛሬ የምናያቸው ቀውሶች ባልመጡ ነበር ። መዐርገ ክህነቱም ከአናጕንስጢስ ወይም ከአንባቢ ጀምሮ ወደ ዲቁና እያለ ቢያድግ ጳጳስነት ትልቅ መሆኑ አደራም መሆኑ እየታየን ይመጣል ። ደረጃ የሌላቸው አገልግሎቶች በቤተ ክርስቲያን ይህን ሁሉ ትርምስ አምጥተዋል ። በዓለም የክብር ዶክትሬት ይሰጣል ። የክብር ቅስና ግን ሊኖር አይችልም ። ምክንያቱም ራሱን የቻለ ጥሪና አገልግሎት ነው ። ዛሬ ግን ይህ አልሆነም ብለን አንዋሽም ። ተምሮ መያዝ ቢያቅተን ይዘን መማርም መልካም ነበር ። ካልሆነም የያዙትን ይጥፉ ባይባል መልካም ነበር።
ሳምራዊቷ ሴት ስለ መንፈሳዊ ነገር ያላት እውቀት አሁን ገና ነው ። ስለ ጌታ ያላት እምነት ግን አድጓል ። ጌታን በአለባበሱ ብቻ የይሁዳ ሰው ብላው ነበር ። ስለ ዘላለም ሕይወት ሲነግራት ግን “ጌታ ሆይ” አለችው ። የይሁዳ ሰው ከሚለው አጠራሯ ወደ ጌትነቱ አደገች ። ትሕትና ፣ አድራሻ ያደረገ የፍቅር መልእክት ፣ ነቀፋ የሌለው ትምህርት ይለውጣል ። እሳት የማያበስለው ድንጋይን ብቻ ነው ። ትምህርት የማይለውጠው ሊቅ ነኝ ብሎ የተቀመጠውን ብቻ ነው ። አፍሪካ አሜሪካውያን፡- “ስለ እሳት ማውራት ድስቱን አያበስለውም” ይላሉ ። መለኮስ ያስፈልጋል ማለት ነው ። ትምህርት አካላዊ ለውጥን አይሰጥም ። ልባዊ ለውጥን ግን ያመጣል ። የዚያን ጊዜ አካላዊ ለውጥም እየፈካ ይመጣል። ትምህርት ማነሣሣት እንጂ በራሱ ኃይል የለውም ። ትምህርት ኃይልን ተፈላጊው ቦታ የሚያደርስ መሪ ነው ።
“ሴቲቱ፡- ጌታ ሆይ፥ መቅጃ የለህም ጕድጓዱም ጥልቅ ነው፤ እንግዲህ የሕይወት ውኃ ከወዴት ታገኛለህ?” አለችው /ዮሐ. 4፥11/ ። ጌታችን ምንም እንኳ የራሱ ቤት በምድር ላይ ባይኖረውም ውኃ መጠጫ መንቀል እንኳ በእጁ አልነበረም ። ሁሉ ቤቱ እንደነበር ስለሚያስብ ነው ። ይህ ትልቅ ብርታትን የሚያመጣ አስተሳሰብ ነው ። በልጅነታችን ስናድግ ማንም ሰው እቤት ሲመጣ ይህ አጎትህ ነው ፣ ይህች አክስትህ ናት ፣ ሂድ ሳማቸው እየተባልን ነው ። ይህን ያህል አጎትና አክስት እንዳለው ያወቀ ልጅ ልቡ በፍቅር ይሞላል ። ዓለም ከቤቱ ይልቅ ሰፊ ፣ የምትጠብቀውም ጎጆው እንደሆነች ይሰማዋል ። አንድ ዘመዴን አስታውሳለሁ ። የምትሠራበት ቦታ በልጅነቴ ስሄድ ሠራተኞቹን በሙሉ ዘመድህ ነው ሳመው እያለች ከመላው ኢትዮጵያ እንደምንወለድ ትነግረኛለች ። እየሸነገለች ሳይሆን ከእውነቷን ነበር ። ሁሉንም ሰው መጋበዝ ፣ መጫወት ትፈልጋለች ።
ጉድጓዱ ጥልቅ ነው ። የጉድጓድ ውኃዎች ጥንቃቄ ይፈልጋሉ ። ተጠቃሚው ብዙ በሆነ ቊጥር በጥልቀት እየተቆፈሩ መምጣት አለባቸው ። ደለል ሊሞላቸው ስለሚችልም መጠረግ ያስፈልጋቸዋል ። ያ ጉድጓድ ጥልቅነቱ በየዕለቱ አድክሟታል ። ጌታችንን እንኳ አትችለውም ማለቷ ምን ያህል ጥልቅ እንደ ነበር መረዳት ይቻላል ። ዛሬ እንኳ ይህ ጉድጓድ 32 ሜትር ጥልቀት አለው ። እርስዋን ግን ጠንካራ ሴት አደረጋት ። ጉድጓዱ በጠለቀ ቊጥር የእርስዋ ትዕግሥትና ጥንካሬ እየሰፋ መጣ ። ሰው የቆፈረው ጉድጓድ ነውና ጥልቅ ነው ። “የወፍ ወንዱ ፣ የሰው ልቡ አይታወቅም” እንደሚባለው ሰዎችም ጥልቅ ናቸው ። ከሰው ጋር መኖራችን ፈቃድ ብቻ ሳይሆን ግድም ነው ። ከጥልቅ ሰዎች ጋር በኖርን ቊጥር ትዕግሥትና ጥንካሬን እንይዛለን ። “ኖላዊ” በሚለው መጽሐፋችን ላይ “ጉድጓዱ ጥልቅ ነው” የሚል ጽሑፍ አለ ፡-
ጉድጓዱ ጥልቅ ነው
(ዮሐ.4፡11)
ሳምራዊቷ ሴት ነኝ። የምጠራው በአገሬ እንጂ በግለሰብነቴ ስም የለኝም። ዜግነት የጨዋነት ሽልማት አይደለም፣ ሁሉም ክርስቲያን ባይሆንም ሁሉም ዜጋ መሆን ይችላል። ወገኖቼ ሳምራውያን ገፍተውኝ እርሷ ባጠለቀችበት ጉድጓድ እኛ አንቀዳም ብለው ተፀይፈውኝ በሰማርያ ቃጠሎ በቀትር እገሰግሳለሁ፣ ፀሐዩ ከሰው አፍ በላይ አያቃጥለኝም። ትንሹ ድሃ ትልቁን ድሃ ይንቃል፣ ትንሹ ኃጢአተኛም ትልቁን ኃጢአተኛ ይጠላል። የጉድጓዱ አፍ በትልቅ ቋጥኝ የሚዘጋ፣ በኅብረት ካልሆነ ብቻ የማይንከባለል ነው። እኔ ግን ብቻዬን አንከባልለዋለሁ። ውሃው እየጎደለ ከጥልቅ መሙላት ተቸግሬአለሁ። በየዕለቱ በንቀት፣ በቃጠሎ፣ በጥልቀት እኖራለሁ። ጌታ ሆይ ጉድጓዱ ጥልቅ ነው፣ ጥልቁ ሰው የቆፈረው ነውና። ቆሜም ተንበርክኬም የማልደርስበት ወደ ጉድጓዱ በግማሽ ገብቼ ጭላጭ የምሰፍርበት ጉድጓዱ ጥልቅ ነው። ተናገር ጌታዬ የቀትር ጓደኛዬ፣ ሰው የዘረጋው የኑሮ መዋቅር፣ ከጥልቁ የወጣው ጥልቅ ዘዴ፣ ስደርስበት የሚርቀው ጥላው ኑሮዬን ተናገረው። ድካሙ ብዙ፣ እርካታው ትንሽ የሆነውን ጉድጓድ አስጥለኝ። ካለሁበት ድረስ የመጣኸው አንተ ምንጭ ኢየሱስ ሆይ ፍለቅ። ዓለት ኃይልህን በበትር ሲመቱህ ለእስራኤል የፈለቅህ አንተ የበረሃው እርካታ ዛሬ ፍለቅ። እንደገና ከሰው ጉድጓድ እንዳልመላለስ አንተ ቡሩክ ምንጭ በሆዴ ፍለቅ። የቀዱት ያልቃል፣ የማታልቀው ምንጭ ሆይ ዛሬ በነፍሴ ፍለቅ። ከጥያቄዬ በላይ መልስ የሆንከው የማትደፈርሰው ምንጭ ሆይ ዛሬ በደረቀው ነገሬ ላይ ፍለቅ። ፍለቅ፣ ፍለቅ፣ ተፍለቅለቅ የደስታ ነዶ የብርሃን ጎርፍ ሆይ ፍለቅ፣ ከማለቅ የምታድን ፍለቅ፣ ስስት የሌለብህ ወደ ራስህ የማታስቀር ሆይ ፍለቅ፣ የማትጨረስ ቸርነት ኢየሱስ ሆይ ፍለቅ። ጉድጓዱ ጥልቅ ነው፣ አንተ ግን ፍለቅ…..፡፡