/ዮሐ. 4፥4/።
እስራኤል የምንላት የቆዳ ስፏቷ ከሰሜን እስከ ደቡብ 480 ኪ.ሜ. ያህል ሲሆን ጎኗ በ80 ኪ.ሜ. መቀነት የተያዘ ነው ። ይህች እስራኤል በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን በሦስት ታላላቅ አውራጃዎች ትከፈላለች ። ሰሜኑ ገሊላ መካከለኛው ሰማርያ የደቡብ ክፍል ይሁዳ ይባላል ። ኢየሩሳሌም ያለችው በደቡቡ አውራጃ ነው ። ኢየሩሳሌም ጥንትም ዛሬም የሃይማኖት መዲና ናት። በነፍሳቸው ተወራርደው ሃይማኖታቸውን የሚያስከብሩ አጥባቂዎች ያሉባት ከተማ ናት ። ታዲያ በደቡቡ አውራጃ ያሉ ከገሊላ ጋር ሰፊ ግንኙነት አላቸው ። በመካከል ካለችው ሰማርያ ጋር ግን ምንም ዓይነት ግንኙነት የላቸውም ። እንደውም አይሁዳዊው ከቤቱ ሲወጣ ለአምላኩ የሚያቀርበው ልመና ሦስት ወገኖችን አታሳየኝ የሚል ነው ። ለምጻም ፣ ቀራጭና ሳምራዊ።
በደቡብ የሚኖሩ የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ወደ ገሊላ መሄድ ከፈለጉ የሰማርያን ምድር መርገጥ በራሱ ያረክሰናል ብለው ስለሚያስቡ ወደ ምሥራቅ አቅጣጫ በመሄድ የዮርዳኖስን ወንዝ በመያዝ ወደ ላይ ወደ ገሊላ ዞረው ይገቡ ነበር ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን በሰማርያ ሊያልፍ ግድ ሆነበት ። ግድ የሆነበት የሠራዊት ትእዛዝ መጥቶ ነው ? በሰማርያ ጻድቅ ተገኝቶ ነው ? ግድ ያለው የገዛ ምሕረቱና ቸርነቱ ነው ። በዚህም አምስት ግንቦችን አፍርሷል ፡-
1- የዘረኝነት
2- የጾታ
3- የመልክአ ምድር
4- የጠባይ
5- የመዐርግ
የዘረኝነት ግንብ
አይሁዳውያን ሳምራውያንን የሚጠሉአቸውና የሚጸየፉአቸው ከአሕዛብ ጋር በጋብቻ ተሳስራችኋል በማለት ነው ። ሳምራውያን ግን ይህንን በምርጫ የገቡበት ሳይሆን በቅኝ ተይዘው የወደቀባቸው ዕዳ ነው ። አይሁዳውያን ራሳቸውም በባቢሎናውያን ተማርከዋል ፣ መቅደሳቸው ፈርሷል ። በዘር ላይ የተመሠረተ ጥላቻ ምክንያት የለሽ ነው ። ሰው ስለ ጠባዩ ሊጠየቅ ይችላል ። ስለ ዘሩ ስለ አፍንጫውና ቀለሙ ግን እንዴት ይጠየቃል ? ከዚያ ዘር ለመወለድ ያቀረበው አሳብ ያጠፋው ጥፋት ምንድነው ? ዘረኞች ግን ይህን ለማሰብ አቅም የላቸውም ። ዘረኝነት ከጥንት እስከ ዛሬ የሰው ልጆች ትልቅ ፈተና ነው ። ያለንበት ዘመን ስለ ድንበር የለሽ ግንኙነት የሚያወራው ወሬ ከመሆን የማያልፍ ነው ። እንደውም በመጨረሻው ዘመን የአውሬው አሳብ ምድርን እየተቆጣጠረ ሲመጣ ዘረኝነት እያየለ መምጣቱ የማይቀር ነው ። ስለ ሰው ዘር እኩልነት እንሰብካለን እያሉ ሲመኩ የነበሩ አገሮች እንኳ መጋረጃው ድንገት እየወለቀባቸው የተደበቀ ስሜታቸው አፈትልኮ እየወጣባቸው የሚያስቡትን የሚናገርላቸው ሰው እየመረጡ እንዳሉ በግልጽ እያየን ነው ። ዘረኝነትን መሻር የሚቻለው በርእዮተ ዓለም ወይም በነገሥታት ጥንካሬ ሳይሆን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘረኝነትን የሻረባቸውን ተግባራዊ ክንውኖች እንመልከት፡-
1- በልደቱ ፡- ጌታችን ከሕዝብና ከአሕዛብ ተወልዷል ። በጌታችን የዘር ሐረግ ውስጥ ራኬብና ሩትን እናገኛለን ። እነዚህ ሴቶች ከአሕዛብ ወገን ናቸው /ማቴ. 1፥5/ ። ራኬብ ከነዓናዊት ሩትም ሞዓባዊት ሴቶች ናቸው። ጌታችን ዘረኝነትን በጽንሰ አሳብ ወይም በአመክንዮ የበላይነት ሳይሆን በደምና በሥጋ ሽሮታል ። እርሱ ዘረኝነትን መዋጋት የጀመረው ገና በጽንሰቱ ነው ። አይሁዳውያን ሰቃልያነ እግዚእ ናቸው ብሎ ሌላው ዘረኝነቱን የሃይማኖት ካባ እንዳያለብሰው በጌታችን ሞት መላው ዓለም ተባብሯል ። ጲላጦስና ሄሮድስ አይሁድ አይደሉም ። የሮማው መንግሥት ሕጋዊ ወኪሎች ፣ የአጥቢያ ነገሥታት ናቸው ። ስለዚህ በጌታችን ሞትም መላው ዓለም ተባብሯል ። በዛሬ ዘመን ያለነውም እኛ የለንበትም እንዳንል የተበላሸ ምርጫ ፣ ድሆችን ያገለለ ኑሮ ፣ መናቆር የበዛበት መንፈሳዊነት ፣ ቅድስና የራቀው ክርስትና ጌታን በታሪክ ውስጥ እንደገና መስቀል ነው /ዕብ. 6፥6/ ። አይሁድስ አንድ ጊዜ ሰቀሉት እኛ ስንት ጊዜ ሰቀልነው ?
2- በሰማርያ ሊያልፍ ግድ ሆነበት፡- ጌታችን ሥጋዊ ልደቱ ከአይሁድ ነው። አይሁዳውያን ሳምራውያንን ቀርቶ መሬታቸውንም እንደሚጸየፉ፣ ግድ ሆኖባቸው የሰማርያን ምድር ከረገጡ ጫማቸውን በዮርዳኖስ ወንዝ እንደሚያጥቡ ጌታችን ያውቃል ። እርሱ ግን ይህን የዘረኝነት አስተሳሰብ ሻረ ። ከየትኛውም ዘር ክፉና ደግ እንዳለ ለማስተማርም ስለ ደጉ ሳምራዊ አስተማረ /ሉቃ. 10፥33-35/ ። ሰማርያን መርገጡ ዘረኝነትን ለማፍረስ ነው።
3- በስቅለቱ፡- እርሱ የሞተው ለመላው ዓለም ነው ። እግዚአብሔር አብም የላከው ዓለምን እንዲያድን ነው /ዮሐ. 3፥16/ ። እግዚአብሔር በፍቅሩ አያዳላም ። በመስቀል ላይም በአራት መዐዝን ተወጥሮ መሰቀሉ መላውን ዓለም አድራሻ ያደረገ ሞት እንደሆነ ይገልጻል ።
4- በተልእኮው ፡- ደቀ መዛሙርቱን ወደ መላው ዓለም መላኩ ይህም ዘረኝነትን እንደ ተዋጋ ይገልጻል /ማቴ. 28፥20/ ።
5- ቤተ ክርስቲያንን መመሥረቱ፡- ቤተ ክርስቲያን ከሕዝብና ከአሕዛብ የተውጣጣች አንዲት የክርስቶስ አካል ናት ። አባ ፍሬምናጦስ በሙገሳ ስሙ አባ ሰላማ ፣ ከሣቴ ብርሃን የመጀመሪያይቱን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሲመሠርት “ማኅበረ ጽዮን ሰማያዊት” በማለት ሰይሟታል ። ይህ የተጠና ስያሜ ነው ። ማኅበረ ጽዮን ምድራዊት የምታቅፈው እስራኤል ዘሥጋን ብቻ ነው ። እስራኤል ዘሥጋ ለመሆን ከአብርሃም ዘር በሥጋ መወለድ ይጠይቃል ። አባ ፍሬምናጦስ ግን ማኅበረ ጽዮን ሰማያዊት በማለት ሕዝብና አሕዛብ በክርስቶስ አንድ የሆኑባት ማኅበር እንደ ተመሠረተች ገለጸ ። ይህ ስያሜ በወቅቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ለነበሩት አይሁድም መልእክት ነበረው ። እንደ ብሉይ ኪዳን ሐዲሱም የእኛ ብቻ ነው እንዳይሉ ሲከለክል በሁለተኛ ደረጃ ሐዲሱ እኛ አይወክልም ብለው እንዳይርቁ ጥሪ ያቀርባል ። ከብሉይ ኪዳንም ከአዲስ ኪዳንም ርቀው ለሚኖሩ ሁሉን ያቀፈ ኪዳን መምጣቱን የሚያበሥር ነው ።
በዓለም ላይ የሚታዩ ብዙ ነገሮች የቤተ ክርስቲያን ጥላ ናቸው ። ቤተ ክርስቲያን ዘረኛ ስትሆን ዓለምም ዘረኛ ትሆናለች ። እኛ ለክፋት ከደፈርን ዓለሙ ቦይ እንዳገኘ ውኃ መፍሰሱ ግድ ነው ። ቤተ ክርስቲያን እየተጠላችም ዓለሙን ታስከትታለች ። አቅሟ ትልቅ ነው ። ስታሊን ሊገጥመው ስለሚችል ጦርነት የምዕራቡ ይህን ያህል የምሥራቁ ይህን ያህል ብርጌድ ነው እያሉ የጦር አማካሪዎች ሲነግሩት እርሱ ግን ፡- “እኔን የጨነቀኝ የፖፑ ብርጌድ ምን ያህል መሆኑ ነው” በማለት አሳሳቢው የቤተ ክርስቲያን አቅም መሆኑን ተናግሯል ። ቤተ ክርስቲያን በሁለቱም ማለት በክፉም በደጉም ተጽእኖ ማምጣት ትችላለች ። ባለፉት ዘመናት በቤተ ክርስቲያን ምን ታውቃለህ? እንጂ አገርህ የት ነው? አይባልም ነበር ። ዛሬ ግን እንደ ጋኔን ወንዝ ለወንዝ መሄድ እየበዛ ነው ።
ጌታችን በሰማርያ ጉዞው የዘረኝነትን ግንብ አፈረሰ ። ሳምራዊቷ ሴት ይህን የዘረኝነት ጥያቄ አቅርባለታለች ። “አንተ የይሁዳ ሰው ስትሆን ሳምራዊት ሴት ከምሆን ከእኔ መጠጥ እንዴት ትለምናለህ? አለችው፤ አይሁድ ከሳምራውያን ጋር አይተባበሩም ነበርና” /ዮሐ. 4፥9/ ። ዘረኝነት አንተ ከሰሜን ነህ ፣ እኔ ከደቡብ ነህ ማለት ነው ። ሁላችን ግን አንድ እጅ የሠራን ፣ አንድ መድኅን የሞተልን ነን ። ዘረኝነት ይህን የእግዚአብሔርን ፈጣሪነትና አዳኝነት አለመቀበል ነው ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከጽንሰቱ እስከ ሞቱ የሻረውን ይህን የዘረኝነት ግንብ እንዳንገነባው መጠንቀቅ ያስፈልጋል ። ዘረኝነት ብዙ ዓይነት ነው ። የእውቀት ፣ የክህነት ፣ የምንኩስና ፣ የባለትዳሮች ፣ … ዘረኝነት አለው ። መገለጫው ከእኔ ውጭ ያለውን አልቀበልም ማለት ነው ። የራስን ለመውደድ የሌላውን መጥላት ነው ። ዛሬ ድርጅቶች ሳይቀሩ በሃይማኖት ተመሳሳይነት እንዲሞሉ ይፈለጋል ። ይህ ስህተት ነው ። የሃይማኖት ቤተሰቦችን መርዳት መልካም ቢሆንም ሌላውስ እንዴት ሆኖ ይኑር ? ይህች ዓለም የጋራ ቤታችን ናት ። የዘር ፣ የሃይማኖት ፣ የወገን ቤት አይደለችም ። ምጽዋታችን ሳይቀር የሃይማኖትና የዘር ምርጫ የሚያደርግ በመሆኑ ተወዳጅ አይደለም ። ጌታችን በሰማርያ ሊያልፍ ግድ ሆነበት ። ዛሬም እኛ ልናልፋቸው የግድ የሚሉን ብዙ ነገሮች አሉ ። የመጀመሪያው ነገር የዘረኝነትን ጋሬጣ ማለፍ አለብን ። አንድ ሰው ፡- “በዛሬው ዘመን ሰውና ሰውን የሚለያዩ ግንቦች በብዛት ሠራን ፤ የሚያገናኙ ድልድዮችን ግን በብዛት አልሠራንም” ብሏል ።
ሳምራውያንና አይሁዳውያን በዚህ ዘረኝነት አስተሳሰብ በመለከፋቸው ሁለት የአምልኮ ስፍራዎችን እንዲያቋቁሙ አድርጓቸዋል ። አንደኛው መቅደስ በገሪዛን ተራራ ሲሆን ሁለተኛው መቅደስ በኢየሩሳሌም ነበረ ። ሳምራውያን እግዚአብሔር የሚቀበለው የገሪዛንን አምልኮ ነው ይላሉ ፣ አይሁዳውያን ደግሞ በኢየሩሳሌም የሚቀርበውን አምልኮ ብቻ ይቀበላል ይላሉ ። ዘረኝነት ሁለት መቅደስ እስከማቋቋም ያደርሳል ። የሃይማኖት ካባ ይለብስና ፈውሱ ይዘገያል ። እነርሱ መናፍቃን ናቸው ፣ እነርሱ የሃይማኖት ህፀፅ አለባቸው በሚል ቋንቋ ተሸፍኖ ይፋለማል ። ተገልጦ ሲታይ ግን ዘረኝነት ነው ። የእኔ የሚሉት ወገን ሲያጠፋ ዓይናቸውን የሚጨፍኑ ወገናቸው ያልሆነ የመሰላቸውን ደግሞ በጽድቁ ሲያብጠለጥሉ ይታያል ። ብዙ ብዕሮች በዚህ ዘረኝነት ተመርዘዋል ። ብዙ ሙያዎች በዚህ ዘረኝነት ረክሰዋል ። የአማራ ቤተ ክርስቲያን የትግሬ እያልን እስከመጠራራት ደርሰናል ። የሚገርመው ዘረኝነት የሚይዘው የሚያወግዙትን ጭምር ነው ። ዛሬ ይህን በሽታ ለማስወገድ ግድ ሊለን ይገባል ። በዚህ ምክንያት ትዳራችን ቅሬታ ውስጥ የገባ ፣ ቤተ ክርስቲያናችን የታወከ ፣ ወዳጆቻችንን የተቀየምን ዛሬ ግድ ሊለን ይገባል ። እኛ የመሠረትነውን ልጆቻችን እንዳይጨርሱት ከሥሩ ልንነቅለው ያስፈልጋል ። ዘረኝነት ትውልድን ገዳይ ነው ። በሴራሊዮን የአንድ ወር ሕጻን እጁ እንዲቆረጥ የተደረገው በዘረኝነት ነው ። አድጎ መሣሪያ የሚይዝበት እጅ እንዲቆረጥ መደረጉን ስናስብ ያሳዝናል ። በሩዋንዳ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ አንድ ሚሊየን ሕዝብ ያለቀው በዘረኝነት ነው ። በጀርመን ስድስት ሚሊየን አይሁድ የተጨፈጨፉት በዘረኝነት ነው። ጌታችን ዛሬም በምድራችን ለማለፍ ግድ እንዲለው እንለምነዋለን ።