የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የፋሲካ በዓል

የእስራኤል ልጆች ከግብጽ ባርነት ነጻ የወጡት የፋሲካው በግ ከታረደ በኋላ ነው ፡፡ የፋሲካው በግ ነጻነትን ያገኙበት የእውነተኛው በግ የክርስቶስ ምሳሌ ስለ ነበር ነው ፡፡ በአዲስ ኪዳን የሚደረገው በሙሉ በብሉይ ኪዳን በምሳሌ ተደርጓል ፡፡ ይህም የሚያስተምረን ነገር ፡-
1-  እግዚአብሔር በየትኛውም ዘመን የጠራቸውን ሕዝብ የሚቀበልበት መንገድ አንድ መሆኑን
2-  ብሉይና አዲስ ተናባቢ ኪዳናት እንጂ ተቃራኒ አለ መሆናቸውን
3-  የብሉይ ተስፋ ፣ የአዲስ ኪዳንም ፍጻሜ አንዱ ክርስቶስ መሆኑን እንረዳለን ፡፡
በአዲስ ኪዳን ዋነኛ ከሆኑት ሥርዓቶች ሁለቱን ብንጠቅስ ጥምቀትና ቁርባን ጉልህ ሆነው እናገኛቸዋለን ፡፡ የእስራኤል ልጆች ቁርባንን በፋሲካ ፣ ጥምቀትን በግዝረት ሲፈጽሙት እናያለን ፡፡ ፋሲካ የሚለው ቃል አለፈ ማለት ነው ፡፡ ምንድነው ያለፈው? ስንል ሞትና ጭንገፋ ፣ አጥፊና ቀሳፊ አለፈ ማለት ነው ፡፡ በግብጻውያን ላይ ከወረዱት መቅሰፍቶች አሥረኛው መቅሰፍት ሞተ በኩር ነው ፡፡ እግዚአብሔር የግብጽ በኩርን ሁሉ በሞት መቅጣት ፈለገ ፡፡ ምክንያቱም እስራኤል ለእግዚአብሔር የበኩር ልጅ ነው ፡፡ የበኩር ልጁ የሆነውን የእስራኤል ወንድ ሁሉ ገድለዋልና እግዚአብሔር  የግብጽ በኩር ሁሉ ከሰው ጀምሮ እስከ እንስሳ ፣ ከልዑል ጀምሮ እስከ ትሑት ለመቅጣት ተነሣ፡፡ በዚያች ሌሊት የሚያልፈው ቀሳፊ መልአክ በእስራኤላውያን ቤት እንዳይገባ የሚከለክለው ምልክት አስፈለገ ፡፡ እርሱም የፋሲካው በግ ደም ነው ፡፡ ትእዛዙ ቀጥሎ እንዳለው ነው ፡፡
የሚታረደው የፋሲካው በግ አቋም ፡-
1-  አንድ የበግ ጠቦት
2-  ነውር የሌለበት
3-  የአንድ ዓመት ተባት
የፋሲካው በግ የሚከናወንበት ሥርዓቱ፡-
1-  በአቢብ ወር በ14ኛው ቀን
2-  ሲመሽ ይታረዳል
3-  ከደሙም ወስደው በቤታቸው መቃንና ጉበን ላይ ይቀቡታል
4-  ከመራራ ቅጠል ጋር ይበሉታል
5-  ጥሬውና በውኃ የበሰለው አይበላም
6-  የተጠበሰው ብቻ ይበላል
7-  እስከ ጥዋት ተበልቶ ማለቅ አለበት፡፡ የቀረው በእሳት መቃጠል አለበት ፡፡
8-  ሲበላ ወገብ መታጠቅ ፣ ጫማን ማሰር ፣ በትርን በእጅ መያዝ ያስፈልጋል ፡፡
የእስራኤል ልጆችም እግዚአብሔር እንዳዘዛቸው አደረጉ ፡፡ የፋሲካው በግ በቤታቸው ሥጋው ጥጋብ ፣ በደጃቸው ደሙ ዘብ ሆነላቸው ፡፡ በዚያች ሌሊት ቀሳፊ መልአክ በግብጽ ምድር አለፈ ፡፡ ደሙ የነበረበትን ቤት እያለፈ የደም ምልክት በሌለበት በግብጻውያን ቤት ገባ ፡፡ ከሰው ጀምሮ እስከ እንስሳ በኩርን ሁሉ ገደለ ፡፡ በዚያችም ጥዋት እስራኤላውያን ከ430 ዘመን ባርነት ነጻ ወጥተው ወደ ተስፋ አገራቸው ጉዞ ጀመሩ ፡፡ ይህ የፋሲካ በዓልም የቀን መቁጠሪያቸውን ለወጠው ፡፡ ከግብጽ ባርነት ነጻ የወጡበት የአቢብ ወር በእኛ ሚያዝያ የወሮች የመጀመሪያ ወር ፣ የዓመቱም የመጀመሪያ ወር ሆነላቸው /ዘጸ. 12፡1-51/ ፡፡
የፋሲካው በግ የክርስቶስ ምሳሌ ስለሆነ ብቻ እስራኤልን ከሞት ከለለ ፤ ነጻነትን አጎናጸፈ ፡፡ ክርስቶስ በምሳሌነትም ሕዝብን ሲያድን ኑሯል ፡፡ እውነተኛው የፋሲካ በግ ክርስቶስ መሆኑን ሐዋርያው ጳውሎስ ገልጧል፡- “እንግዲህ ያለ እርሾ እንዳላችሁ አዲሱን ሊጥ ትሆኑ ዘንድ አሮጌውን እርሾ አስወግዱ። ፋሲካችን ክርስቶስ ታርዶአልና” /1ቆሮ. 5፡7/፡፡ የፋሲካው በዓል ሰባት ቀን የቂጣ በዓል አለው ፡፡ እርሾ የሌለበት ቂጣ የሚበሉበት ሳምንት ነው ፡፡ ይህ ከግብጽ ምድር በችኮላ እንደ ወጡ የሚያሳይ ነው ፡፡ ለዘመናት አልለቅም ያለች ግብጽ የፋሲካው በግ ከታረደ በኋላ ግን አንድ ቀን እንዳይውሉ አቻኩላለች ፡፡ ስለዚህ ይህ የቂጣ በዓል እግዚአብሔር ማዳንን ሲፈጽም ጠላትም እንደሚያስቸኩል የሚገልጥ ነው ፡፡ ሐዋርያው ያንን ይዞ እርሾ ልማድን አስወግዱ ፤ አዲሱን ሊጥየማይቆመጥጥ ሕይወት ያዙ ፡፡ ምክንያቱም ፋሲካችን ክርስቶስ ታርዶልናልና ይላል ፡፡
የፋሲካው በግ ወደ ክርስቶስ ያመለክታል ፡፡ ለአንድ ቤት አንድ በግ መሆኑ ክርስቶስም አንድ መሥዋዕት መሆኑን ያስረዳል ፡፡ የእስራኤል ልጆች ነጻ ለመውጣት አንድ ጊዜ ሠውተውታል ፡፡ በየዓመቱ ግን ያንን ለማሰብና ለማመስገን ያርዱታል ፡፡ እንዲሁም ጌታችን አንድ ጊዜ ለሁሌውም የሚበቃ መሥዋዕት ሁኗል ፡፡ በየጊዜው ግን ሥጋውን ደሙን በመቀበል ማዳኑን በአዲስነት እናስባለን ፡፡ ሕይወቱን እንካፈላለን ፡፡ የፋሲካው በግ ነውር የሌለበት መሆን ነበረበት ፡፡ ቀንዱ ያልከረከረ ፣ ጠጉሩ ያላረረ እንከን የሌለበት መሆን አለበት ፡፡ ጌታችንም በሰውም በእግዚአብሔርም ፊት ንጹሕ የሆነ መሥዋዕት ነው ፡ጠላቶቹ እንኳ በእርሱ ላይ የሚናገሩት እንከን እስኪያጡ ቅድስናው ሁሉን ዲዳ ያደረገ ነው ፡፡ የፋሲካው በግ የአንድ ዓመት ተባት መሆን ነበረበት ፡፡ ይህ ለበግ ዕድሜ የጉብዝና ዕድሜ ነው ፡፡ ጌታችንም ለመኖር በሚያሳሳ ፣ የጉብዝና ዕድሜ በሠላሣ ሦስት ዓመቱ ስለ እኛ ታርዷል ፡፡
የፋሲካው በግ የዘመን መቁጠሪያን ለውጧል ፡፡ ጌታችንም የዓለምን ዘመን ለሁለት ከፍሎታል ፡፡ ከክርስቶስ ልደት በፊትና በኋላ ተብሏል ፡፡ እርሱ ታሪክንና ሕይወትን የሚለውጥ ኃይል ነው ፡፡ ዘመንን መቁጠር ያለባቸው ከዳኑበት ቀን ጀምሮ መሆኑን ለእስራኤል ተነግሯል ፡፡ እኛም ዘመንን መቁጠር የሚገባን እግዚአብሔርን ካወቅንበት ጊዜ አንሥቶ ነው ፡፡ ከዚያ በፊት የነበረው የሞት ታሪክ ነው ፡፡ የሚያጸጽት እንጂ የሚያኮራ ታሪክ የሌለው ነው ፡፡ በጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት የተወለዱበትን ቀን የሚቆጥሩት “እገሌ በዚህ ቀን ተጠመቀ” በማለት ነው ፡፡
 
የፋሲካው በግ ሲመሽመታረድ ነበረበት ፡፡ ጌታችንምየተሰቀለበትሰዓት ከ6- 9 ሰዓት በምድር ላይ ጨለማ ነበር ፡፡ ዛሬ የጌታ ሥጋና ደም ሲፈተት የሚጋረደው ከብሉይ ፋሲካ ፣ ከአዲስ የጌታችን የመሥዋዕትነት ሰዓት ተወስዶ ነው ፡፡ ምሳሌውም እውነቱም በምሽት ስለሆነ ቅዱስ ቁርባንም ሲፈተትይጋረዳል ፡፡ የፋሲካውን በግ ከመራራ ቅጠል ጋር እንዲበሉ ታዘዋል፡፡ በግብጽ ያሳለፉትን የመከራ ዘመን እንዲያስታውሱ ነው ፡፡ እንዲሁም ጌታችንን ስንይዝ መራራ ነቀፋና ስደት እንደሚገጥመን የሚያሳይ ነው ፡፡ ቅዱስ ቁርባንም በመራራ አፍ በጦም መወሰዱ ይህን ተከትሎ ነው ፡፡
የፋሲካው በግ ጥሬውን መብላት በውኃ የበሰለውን መብላት ተከልክሏል፡፡ የተጠበሰውን መብላት ብቻ ተፈቅዷል ፡፡ ለእስራኤል የነበረው ትርጉም መከራው ጨርሶ እንዳላጠፋቸው የሚገልጥ ነው ፡፡ ጥብስ እሳቱና ሥጋው በእኩል የተዋሐዱት እንደሆነ ክርስቶስም ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ መሆኑን የሚገልጥ ነው ፡፡ ጥሬው ክርስቶስን ሰው ብቻ የሚሉ ፣ ቅቅሉ ባሕርየ መለኮት በባሕርየ ትስብእት ላይ አይሏል የሚሉ መናፍቃንን የሚገልጥ ነው ፡፡ የፋሲካው በግ ተረፍ እንደሌለው ሙሉ በሙሉ እንደሚባክን እንዲሁም ክርስቶስ ፍጹም መሥዋዕታችን እንደሆነ ያሳየናል ፡፡ እንዲሁም ከክርስቶስ መሥዋዕትነት ጋር ጽኑ ዝምድና ያለው አማናዊው የጌታ ሥጋና ደም የሚቀርብበት ቅዱስ ቁርባንም ከተፈተተ በኋላ ሙሉ በሙሉ ይከናወናል ፡፡ አያድርም ፡፡
የፋሲካው በግ ሥጋው መብል ደሙ ምልክት እንደሆነ ክርስቶስም የሕይወት ጥጋብ ፣ የኑሮ ዋስትና ነው ፡፡ ደሙ በቤታቸው ሦስት አንጻር መቃንና ጉበኑን ይረጫል ፡፡ አራተኛውን መድረኩን ግን አይረጩም ፡፡ ይህ ደሙን መርገጥ እንዳይሆን ነው ፡፡ እንዲሁም ሐዋርያው፡- “የእግዚአብሔርን ልጅ የረገጠ ያንንም የተቀደሰበትን የኪዳኑን ደም እንደ ርኵስ ነገር የቆጠረ የጸጋውንም መንፈስ ያክፋፋ፥ እንዴት ይልቅ የሚብስ ቅጣት የሚገባው ይመስላችኋል?” ያለውን እንድናስታውስ ያደርገናል /ዕብ. 10፡29/ ፡፡
የፋሲካውን በግ መብላት የሚገባቸው ወገባቸውን ታጥቀው ፣ ጫማቸውን አስረው ፣ በትራቸውን ይዘው ነው ፡፡ ይህ ለመጓዝ ዝግጁ ሆነው ይበላሉ ማለት ነው ፡፡ እንዲሁም መታጠቂያው እምነት ፣ መጫሚያው ጽድቅ ፣ በትር ቃሉን ይዘን የጌታችንን ሥጋና ደም መቀበል ያስፈልጋል ፡፡
ጌታችን በሠላሣ ዓመቱ የፋሲካን በዓል ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም እንደሄደ ወንጌላዊ ዮሐንስ ዘግቦልናል /ዮሐ. 2፡13/ ፡፡ አማናዊው ፋሲካ ምሳሌውን ሊያከብር ሄደ ፡፡ አንድ ቀን እንደሚተካው እያወቀ አከበረው ፡፡ እስራኤላውያንም ምሳሌውን አክብረው አማናዊውን ግን ገፉት ፡፡ የፋሲካውን በግ የሚያርደው የቤቱ አባ ወራ እንደሆነ የሃይማኖቱ አባ ወራ ሐናና ቀያፋ ሊቃነ ካህናቱ ለሞት አሳልፈው ሰጡት ፡፡ እስራኤል ያረዱትን ፋሲካ ይበላሉ፡፡ ክርስቶስን አርደው ግን አልበሉትም ፡፡ ፋሲካን መጻተኛና እንግዳ አይበላውም ነበር ፡፡ አሁን ግን እስራኤል ወጥተው መጻተኛና እንግዶች የሆኑት አሕዛብ ተመገቡት ፡፡ ፋሲካን የሚበላ የተገረዘ መሆን ነበረበት ፡፡ እንዲሁም የጌታን ሥጋና ደም ለመቀበል መጠመቅ ግድ ነው ፡፡ ሁለቱ ጥምቀትና ቁርባን ተናባቢ ናቸው ፡፡ ጌታችን በመስቀል ላይ በጦር በተወጋ ጊዜ ከጎኑ የወጣው ውኃና ደም ጥምቀትና ቁርባንን ያመለክታል ፡፡
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ