የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የሰው ግብዣ

“አሁን ቀድታችሁ ለአሳዳሪው ስጡት አላቸው፤ ሰጡትም። አሳዳሪውም የወይን ጠጅ የሆነውን ውሃ በቀመሰ ጊዜ ከወዴት እንደ መጣ አላወቀም፤ ውኃውን የቀዱት አገልጋዮች ግን ያውቁ ነበር፤ አሳዳሪው ሙሽራውን ጠርቶ፡- ሰው ሁሉ አስቀድሞ መልካሙን የወይን ጠጅ ያቀርባል፥ ከሰከሩም በኋላ መናኛውን፤ አንተስ መልካሙን የወይን ጠጅ እስከ አሁን አቆይተሃል አለው” /ዮሐ. 2፡8-10/ ፡፡
ጌታችን ጋኖቹን እስከ አፋቸው ሙሉአቸው አለ ፡፡ እስከ አፋቸው ከሞሉአቸው በኋላ ውኃው ወደ ወይን ጠጅ ተለወጠ ፡፡ ለሰርጉ አስተናጋጅነት የተመደበው አሳዳሪ ምሥጢሩን አያውቅም ነበር ፡፡ አገልጋዮቹ ግን ውኃው ወይን ጠጅ እንደሆነ ያውቃሉ ፡፡ እነዚህ አገልጋዮች በጓዳ የሚቀመጡ ፣ የሰርጉን ደስታ ከማየት ይልቅ በብዙ የሚሯሯጡ ናቸው ፡፡ ጌታ የተነጋገረው ከሚያስተናግደው አሳዳሪ በዓይኑ ድግሱን ከሚቃኘው ከሙሽራው ጋር አይደለም ፡፡ የሚደክሙትን አገልጋዮች የምሥጢሩ ተካፋይ አደረጋቸው ፡፡ እነርሱም ወይን ጠጅ የሆነው ውኃው እኮ ነው ብለው ግርግር ሲፈጥሩ አይታዩም ፡፡ ተአምሩ ራሱ እንዲናገር ዝም ብለዋል ፡፡ የመጀመሪያውን ቅምሻ ግን ለአሳዳሪው ስጡት አላቸው ፡፡ እግዚአብሔር ክብሩን የሚያሳያቸው አገልጋዮች አራት ዓይነት ጠባይ ይታይባቸዋል፡-
1-  በስፍራቸው ሁነው ይጠብቃሉ ፡፡
2-  ድርሻቸውን ብቻ ይፈጽማሉ ፡፡
3-  በሚለወጠው ነገር የተለወጠው ራሱ እንዲናገር ዝም ይላሉ ፡፡
4-  አሳዳሪው አስተያየት እንዲሰጥበት ያቀርባሉ ፡፡
በስፍራ ሁኖ መጠበቅ
 በአገልግሎት ላይ የሚያምረንን ከማድረግ የሚያምርብንን ቦታ መያዝ የተሻለ ነው ፡፡ አገልግሎት የጸጋ ፣ የችሎታና የልምድም ስፍራ ነው ፡፡ እኔ ከእገሌ በምን አንሳለሁ ብለን የምንሰየምበት የቁመት መለካኪያ ቦታ አይደለም ፡፡ ከትልቁ እግዚአብሔር የምንቀበለው ትንሽ ጸጋ የለም ፡፡ አሳዳሪው በቦታው ፣ ሙሽራውም በቦታው ፣ አገልጋዮቹም በቦታቸው ሲሆኑ ውበትና ተአምር አለ ፡፡ ሙሽራው የአገልጋዮቹን ቦታ ቢይዝ ፣ አገልጋዮቹ የሙሽራው ቦታ ላይ ቢቀመጡ ውበት የለውም ፡፡ በስፍራው ሁኖ መጠበቅ ይገባል ፡፡
ድርሻ ብቻ መፈጸም
 ድርሻው አሁን የሚችሉት የታዘዙትን ውኃ መሙላት ነው ፡፡ ጌታ ሙሉ ባይላቸውም እነዚያን ድንጋዮች ለማንጻት ሥርዓት መሙላታቸው አይቀርም ነበር ፡፡ ልዩነት ያመጣው ግን እንደ ጌታ ቃል መሙላታቸው ነው፡፡ እንዲሁም አገልጋዮች ዝም ብለው ሊኖሩ አይችሉም ፡፡ እንደ ታዘዙት ሲያገለግሉ ግን የጌታን ክብር ያያሉ ፡፡ አገልጋይ ማስተማር እንጂ መለወጥ አይችልም ፡፡ ብቻ ጋኖቹን እስከ አፋቸው መሙላት ይገባል ፡፡ አንዱን ሞልቼ ልሞክረው ሳይሆን ሁሉንም ሞልተው ሊጠብቁ ይገባል ፡፡
ራሱ ይናገር
በአገልጋይ እጅ ብዙ ተአምራት ሊደረግ ይችላል ፡፡ ተአምራቱ ግን እግዚአብሔር ለፍጥረቱ ያለውን ርኅራኄ ማሳያ እንጂ የብቃት መለኪያ አይደለም ፡፡ ተአምሩ ራሱ ይናገር እንጂ ማስታወቂያ መሥራት አይገባም ፡፡ ሰው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊመጣ የሚገባው በመስቀሉ ፍቅር ተስቦ ሊሆን ይገባዋል ፡፡ ይልቁንም ምልክት ለማያምኑ ሰዎች ልብን መክፈቻ እንጂ ለሚያምኑ አይደለም ፡፡ አማንያን በቤዛነቱ እንጂ በምልክት የሚደነቁ አይደሉም ፡፡ ምልክት አምላክ በኃይሉ የሚያደርገው ሲሆን ቤዛነት ግን የማይታመመው አምላክ በእኛ ሥጋ መታመሙና መሞቱ ነው ፡፡ የዳንነው በቃና ዘገሊላ ተአምር አይደለም ፣ በመስቀሉ ፍቅር ነው ፡፡ ተአምራት እንደ ፈቃዱ የሚደረግ ሲሆን መዳን ግን ለፈለገ ሁሉ የሚሰጥ የተለቀቀ ጸጋ ነው፡፡
አገልግሎታችን ማሳየት
ክርስትናው ዘረ ክህነት ያለው እንጂ በማንኛውም ቦታ የሚጀመር ወፍ ዘራሽ ትምህርት አይደለም ፡፡ አብርሃም ይስሐቅን ፣ ይስሐቅ ያዕቆብን ፣ ያዕቆብ 12ቱን ነገድ ፣ ሙሴ እስራኤልን  ፣ ዳዊት ሰሎሞንን ፣ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርትን አደራ ያለበት ቅብብሎሽና በረከት የሚተላለፍበት ሐረግ ነው ፡፡ ይህ ሐረግ እስከ ሌለ የእግዚአብሔር በረከት አያልፍም ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የትውልድን ሐረግ የሚቆጥረው ለዚህ ነው ፡፡ በእግዚአብሔር ቃል የወለዱና በማመን የቀደሙ ስፍራ ሊሰጣቸው ይገባል ፡፡ በእግዚአብሔር ቃል የወለዱ አገልጋዮች በረከቱን ማስተላለፍ አለባቸው ፡፡ በማመን የቀደሙ ስፍራ ሊለቀቅላቸው ይገባል ፡፡ በአገልጋዮች እጅ የሚደረጉ ድንቅና ተአምራት ካሉ አባቶችን ቀድሞ ማሳየት ማስመርመር ተገቢ ነው ፡፡ ጳውሎስ ይህን አድርጓል ፡፡ ጌታም ለሕዝቡ ስጡ አላለም ፡፡ ቀድታችሁ ለአሳዳሪው ስጡት አላቸው ፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ፡- ከዚያ ወዲያ ከአሥራ አራት ዓመት በኋላ ከበርናባስ ጋር ቲቶን ደግሞ ይዤ ወደ ኢየሩሳሌም ሁለተኛ ወጣሁ፤ እንደ ተገለጠልኝም ወጣሁ፤ ምናልባትም በከንቱ እንዳልሮጥ ወይም በከንቱ ሮጬ እንዳልሆን በአሕዛብ መካከል የምሰብከውን ወንጌል አስታወቅኋቸው፤ ዋኖች ግን መስለው ለሚታዩ ለብቻቸው አስታወቅኋቸው” ብሏል /ገላ. 2፡1-2/ ፡፡ ማገልገል ከጀመረ ከአሥራ አራት ዓት በኋላም ትምህርቱን ያስገመግም ነበር፡ እንዴት ያለ ትሕትና ነው ! ደቀ መዛሙርትን ካፈራ በኋላ ለምክር ወደ ቀደሙት ሐዋርያት ይመጣ ነበር ፡፡ አባት የሌለው ልጅነት ፣ መምህር የሌለው ደቀ መዝሙርነት ፣ አሰልጣኝ የሌለው ትምህርት የሙት ልጅ ነውና ይሞታል ወይም በጣር ያድጋል፡፡
አገልጋዮቹ የነበሩበት ቦታ ዝቅ ያለ የሚመስል ፣ ከዕይታም የተሰወረ ነው፡፡ በበረት የተወለደው ፣ ልደቱንም ለእረኞች የገለጠው አምላክ ግን የቃና ዘገሊላውን ተአምር ገለጠላቸው ፡፡ ዛሬም ከአሳዳሪዎች ይልቅ አገልጋዮች የእግዚአብሔርንም የሕዝቡንም ምሥጢር ያውቃሉ ፡፡ እግዚብሔር የሚገኝበትና ጸጋ የሚበዛበት መንገዱ አንድ ነው ፡፡ እርሱም ትሕትና ነው ፡፡ ሐዋርያው ጴጥሮስ እግዚአብሔር ለትሑታን ጸጋ ይሰጣል ይላል /1ጴጥ . 5፡5/፡፡ በዚህ ክፍል ላይ የተጠቀሰው ትሕትና ለአገልጋዮች የመታዘዝ ትሕትና ነው ፡፡
አሳዳሪው በተአምራት የተለወጠውን ውኃ ከወዴት እንደ መጣ አላወቀምና ሙሽራውን ለመውቀስ መጣ ፡፡ በዚህ ሰዓት የለመነችው ድንግል ማርያም በምን ዓይነት ደስታና ዝምታ እንዳለች መገመት ያስቸግራል ፡፡ የሰው ኀዘን ያሳዘናት ፣ ደስታቸውም ይበልጥ ያስደስታታል ፡፡ አሳዳሪው ግን፡- ሰው ሁሉ አስቀድሞ መልካሙን የወይን ጠጅ ያቀርባል፥ ከሰከሩም በኋላ መናኛውን፤ አንተስ መልካሙን የወይን ጠጅ እስከ አሁን አቆይተሃል አለው” አሳዳሪው የተናገረው ታላቅ መደነቅ ያለበት ንግግር ነው ፡፡ ስለ ሰው እርግጠኛ ጠባይም ተናገረ ፡፡ ሰው ሁሉ አስቀድሞ መልካሙን የወይን ጠጅ ያቀርባል ፣ ከሰከሩም በኋላ መናኛውን ፡፡ ይህ ሰው ብዙ ድግሶችን በማሳለፍ ልምድ ያለው ነው ፡፡ በሰው ድግስ ላይ መጀመሪያ ደህናው ይቀርብና ማጣጣም በማይችሉበት ስካር ላይ ደግሞ ቅራሪው ይቀዳል ፡፡ የሰው ግብዣ ከላይ ወደ ታች የሚወርድ ነው ፡፡ ከመልካሙ ወደ መናኛው ይጓዛል ፡፡ የእግዚአብሔር ግብዣ ግን በተቃራኒው ነው ፡፡ አስቀድሞ መራራውን ቀጥሎ ጣፋጩን ያቀርባል ፡፡ ይህ የሰው ዘር ጠባይ መሆኑን እየተናገረ ነው ፡፡
“የማይዘልቅ ማኅበር በጠጅ ይጀመራል” እንዲሉ በትልልቅ ፍቅርና ክብር የጀመሩ ግንኙነቶች እንደምትጠልቅ ጀምበር ማዘቅዘቅ ይጀምራሉ ፡፡ ጌታ ከሰይጣን ይልቅ ከሰዎች እንዲጠበቁ ደቀ መዛሙርቱን አስጠንቅቋል ፡፡ ሰዎች ከእውነት ይልቅ የሚያገለግሉት ስሜታቸውን ነውና ፡፡ አስቀድሞ ፍቅርን ቀጥሎ ጥላቻን ፣ መጀመሪያ አድናቆትን ቀጥሎ ስድብን ሊያወርዱ ይችላሉ፡፡ እንደ አሳዳሪው የሰውን ጠባይ ያላወቀ ልቡ ሊሰበር ይችላል ፡፡ በሰው ፍቅር የሰከረ ሰው ቀጥሎ ቅራሪው ይቀርብለታል ፡፡ ሰው ሁሉ ይላልና እኛስ ወረት ቤቱን ሠርቶብን ይሆን ?

ያጋሩ