የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

አንተ ኬፋ ትባላለህ

      “ወደ ኢየሱስም አመጣው። ኢየሱስም ተመልክቶ፡- አንተ የዮና ልጅ ስምዖን ነህ፤ አንተ ኬፋ ትባላለህ አለው፤ ትርጓሜው ጴጥሮስ ማለት ነው” /ዮሐ. 1፡43/።
      እንድርያስ ወንድሙን ጴጥሮስን ወደ ክርስቶስ እንዳመጣው የሚናገር ክፍል ነው። ወደ ክርስቶስ ሲያመጣው የተናገረው ቃል መሢሕን አግኝተናል የሚል ነው። ከዚህ ድምፅ ውስጥ የምንረዳው ነገር የመጀመሪያው መሢሑ በታላቅ ናፍቆት እየተጠበቀ መሆኑን ነው። ሳምራዊቷ ሴት “ክርስቶስ የሚባል መሲሕ እንዲመጣ አውቃለሁ፤ እርሱ ሲመጣ ሁሉን ይነግረናል” በማለት ለጌታ ለራሱ ተናግራለች /ዮሐ. 4፡25/። ከዚህ የምንረዳው ስለ መሢሑ መምጣት በየመሸታ ቤቱም ርእስ እንደ ነበር ነው። ሴት ልትወልድ ስትል እንድትከብድ፣ ሆዷም ወደ ታች እንዲወርድ እንዲሁ አየሩ ሳይቀር ክርስቶስን ለመግለጥ ከብዶ ነበር። እንደምናነበው ዮሐንስ ይጮኻል፣ እነ ናትናኤል በበለስ ሥር ተቀምጠው ትንቢቱን ያመሳክራሉ። እንድርያስ ወንድሙን ይጠራል። የተፋፋመ ጊዜ ነበር። “መሢሕን አግኝተናል” ከሚለው ጥሪ ውስጥ የምንረዳው ሁለተኛው ነገር ታላቅ ዕድለኞች ነን የሚል ነው። የዘመናትን ናፍቆት፣ የአበው ሱባዔ፣ የነቢያት ትንቢት ፍጻሜ የሆነውን ማግኘት ታላቅ ዕድለኛነት ነው። በርግጥ ያሉበት ድረስ የሄደውና ያገኛቸው ራሱ ክርስቶስ ነው። ዕድለኝነታቸውን ለመግለጥ ግን “መሢሕን አግኝተናል” አሉ። ክርስቶስን ማግኘታችን ልዩ ደስታችን ሆኖ ይሰማን ይሆን?
      ሐዋርያት በአንድ ጊዜ ጌታችንን አልተከተሉም። ስለ ሐዋርያት ጥሪ ብዙ ጊዜ የምንጠቅሰው የማቴዎስ ወንጌልን ስለሆነ፡- “በኋላዬ ኑና ሰዎችን አጥማጆች እንድትሆኑ አደርጋችኋለሁ አላቸው። ወዲያውም መረባቸውን ትተው ተከተሉት” የሚለውን ንባብ ይዘን ያን ቀን ጌታን እንዳወቁት፣ ያን ቀን እንደ ወሰኑ፣ ያን ቀን እንዳመኑ እናስባለን /ማቴ. 4፡19-20/። ማቴዎስ የዘገበው ፍጻሜውንና ውሳኔአቸውን ነው። የማርቆስም ዘገባ ተመሳሳይ ነው /ማር. 1፡16-20። ሉቃስና ዮሐንስ ግን የዘገቡት ከውሳኔው በፊት ስለተከናወኑት ነገሮች ነው። ሉቃስ ዘገባውን የጀመረው ጌታ የጴጥሮስ ወደምትሆነው ታንኳ ላይ ተቀምጦ እንዳስተማረ በመናገር ነው። ጴጥሮስ ሌሊቱን በሙሉ ለማጥመድ ሞክሮ አንድ ዓሣ አላገኘም። ተስፋ ቆርጦ መረቡን ያጥብ ነበር። ጌታ በዚያ ደክሞ ምንም ባላገኘባት ታንኳ ላይ ተቀምጦ አስተማረ። ከዚያ በኋላ መረቡን በቀኝ ጣለው ባለው ጊዜ ጴጥሮስ ሌሊቱን በሙሉ ደክመን ምንም አላገኘንም እንደ ቃልህ ግን እጥላለሁ ባለ ጊዜ መረቡ እስኪቀደድ እጅግ ብዙ ዓሣ አገኘ። በረከቱ ተትረፈረፈ። ጴጥሮስ ግን “እኔ ኃጢአተኛ ነኝ ከእኔ ተለይ” አለው። ለምን እንዲህ አለ? ትላንት ዮሐንስ በሚያጠምቅበት በዮርዳኖስ ተገናኝተው ነበር። ጴጥሮስ ግን ጌታን ለመከተል የኑሮ ፍርሃት ይዞት ፈቃደኛ አልነበረም። ጌታ ግን ያለበት ድረስ ወደ ጥብርያዶስ ባሕር ሄደ። እፈልጋለሁ በሚል ስሜት ከታንኳ መርጦ በጴጥሮስ ታንኳ ላይ ተቀመጠ። የነፍስን መግቦት ከጨረሰ በኋላ የሥጋውን ደግሞ ሰጠ። ሁሉም የእኔው ነው ማለቱ ነው። ይህ ብቻ አይደለም ልፋትን ሌሊቱን በሙሉ ደከመ። እውቀትህና ጉልበትህ ያላስገኘልህን እኔ እሰጥሃለሁ ሲለው ነው። ጴጥሮስም እኔ ኃጢአተኛ ነኝ ያለው የሕይወቴን ጌታ በዕለት እንጀራ ጠረጠርሁህ፣ ለጥሪህ አመነታሁ በማለት ነው። ይህ ተአምራት ሲፈጸም ዮሐንስና ያዕቆብም ነበሩ። በተለይ ዮሐንስ ትላንት የመጥምቁን ድምፅ ሰምቶ ከጌታ ጋር ውሎ ነበር። ግን አልወሰነም። ይህን ተአምር ባየ ጊዜ እርሱና ወንድሙ ያዕቆብም ወሰኑ።
      ዮሐንስ የዘገበው የመጥምቁን ድምፅ ሰምተው ጌታ ጋር ስለ መዋላቸው፣ እንድርያስም ጴጥሮስን ስለማምጣቱ ነው። ዮሐንስ ይህን ዘገባ የመረጠው ከጻፈበት ዓላማ በመነሣት ነው። ስለ ክርስቶስ ዘላለማዊነትና ታላቅነት እየጻፈ ነውና ለዚህም ምስክር ያደረገው ዮሐንስ መጥምቅን ነው። ዮሐንስ መጥምቅ መልካም ሽግግር እንዳደረገ፣ ደቀ መዛሙርቱን ሳይቀር ለክርስቶስ እንደ ሰጠ በመግለጥ የጌታን ታላቅነት ይጽፋል። ልብ አድርጉ ጌታ ትላንት በዮርዳኖስ አግኝቷቸው ብዙ ሲመክራቸው ዋለ። በተለይ ዮሐንስንና እንድርያስን። ጴጥሮስንም አግኝቶ ተስፋ ሰጠው። የምሽት ጀንበር እርሱ ነውና ከፀሐይ በላይ ዕድሜ ሰጠው። ዘመንህ ቢመሽም እንደገና ይነጋል የሚል ብርታት አጎናጸፈው።
      ሁሉን ትቶ ለመከተል በአንድ ጊዜ አልወሰኑም። በአንድ ጊዜም ጥሪውን አልተቀበሉም። በዮርዳኖስ የፈለጋቸው እንደገና በባሕሩ አገኛቸው። ዮርዳኖስ ፈሳሽ ነበርና ልባቸው ፈሰሰ። ጥብርያዶስ ግን ባሕር ነውና ረግተው አገኛቸው። በትክክል እንደሚፈልጋቸው ለመግለጥ የጴጥሮስ ታንኳ ላይ ተቀመጠ። በትክክል እንደሚያውቃቸው ለመግለጥ በስማቸው ጠራቸው። ዛሬም ሰዎች ወደ አገልግሎት ለመግባት ቶሎ መወሰን ቢያቅታቸው ጌታ ግን የፈለገውን ሰው እንደማይለቀው፣ ካለበት ድረስ ሄዶ ገንዘቡ እንደሚያደርገው፣ የሳሳለትን ኑሮ ሞልቶለት ተከተለኝ እንደሚለው እንረዳለን።
      እንድርያስ ጴጥሮስን ወደ ጌታችን ሲያመጣው ጌታችን እንግዳ ተቀባይ፣ ትሑት መንገድ መሪ፣ ነገን በብሩህ የሚያይ አባት ነውና በፈገግታ ብቻ ሳይሆን በአዲስ ዘመን ብሥራት ተቀበለው። ወንጌሉ፡- “ወደ ኢየሱስም አመጣው። ኢየሱስም ተመልክቶ፡- አንተ የዮና ልጅ ስምዖን ነህ፤ አንተ ኬፋ ትባላለህ አለው፤ ትርጓሜው ጴጥሮስ ማለት ነው” ይላል /ዮሐ. 1፡43/።
     ኢየሱስም ተመልክቶ፡- ኢየሱስ የተመለከተው የወየበ ፊቱን፣ የገረጣ መልኩን፣ ያረጀ ዘመኑን፣ ያልረጋውን ማንነቱን አይደለም። ጌታ ፍቅር ነውና ነቅሶ አያይም። አሟልቶ ግን ያያል። ኢየሱስ የተመለከተው የወየበው ሲበራ፣ የገረጣው ሲፈወስ፣ ያረጀው ሲታደስ፣ ብል የበላው ዘመን ሲመለስ ነው። ንጋትን ማታ ማድረግ የሚችለው፣ ማታንም ንጋት ማድረግ ይችላል። ሰው ከመጀመሪያው ቢጀምር እርሱ ግን ከመጨረሻው ይጀምራል። በርግጥ ኢየሱስ ክርስቶስ እኛንም ያየናል። ኑሮአችን የማይሞላ ሸለቆ፣ ውጦ ዝም ቢሆንም፣ አሊያም የማይጨረስ ተራራ ሁልጊዜ የሚቧጠጥ ከሆነም እርሱ በመፍትሔ ሰጪ ዓይኖቹ ያየናል። ማቃሰት በእልልታ፣ ማዘን በደስታ ተለውጦ ያያል።
     ስምን ይለውጣል። አንተ የዮና ልጅ ስምዖን ነህ አለው። ስሙን ለሚያውቀው ሰው ስምህ እንዲህ ነው ማለት ምን ማለት ነው? አንተን ብቻ ሳይሆን አባትህንም አውቃለሁ። አንተ ዛሬ ታውቀኛለህ። እኔ ግን አባትህ ሳያውቅህ አውቅሃለሁ ማለቱ ነው። ከእናት ከአባት በፊት የሚያውቅ ወዳጅ ማግኘት ደስ ይላል። ሁሉም ሰው ስሙን ሲጠሩት ደስ ይለዋል። ይልቁንም አብረውን ያደጉ፣ ድሮ የሚያውቁን ስማችንን ከነ አባታችን ይጠሩታል። ያን ጊዜ ደስ ይለናል። የተሰማን ባይተዋርነት፣ የከበደን አካባቢ ሁሉ ይለወጣል። የሚያውቀንን ማግኘት እፎይታ አለው። ጌታችን ያውቀናል። ለማየት የምናስፈራውን እኛን ከማኅፀን ሳለን ለዚህ ቀን አይቶን ነበር። ዛሬ አግኝተን ለመስጠት የምንሰስተው፣ ዛሬ በርትተን የምንገፋውን እኛን እንዴት ያየን ይሆን? ከራቁትነት የበለጠ ድህነት የለም። ስንወለድ እንዲህ ድሃ ነበርን። ከአራስነት የበለጠ ደካማነት የለም፤ ወደዚህ ዓለም ስንመጣ እንዲህ ነበርን። አንድ ቀን ይህ ካባ ይወልቃል። አንድ ቀን ይህ ብርታት በሰው ትከሻ ላይ ያርፋል። እርሱ ግን ያውቀናልና ደስ ይለናል።
      ጌታ ስሙን መጥራቱ ተአምር ይመስላል። የበለጠው ግን ስሙን ለወጠለት። ኬፋ ወይም ጴጥሮስ ትባላለህ አለው። በአራማይክ ኬፋ፣ በግሪክ ጴጥሮስ የሁለቱም ትርጉም ዓለት ማለት ነው። አፈር አዘል ድንጋዮች አሉ። ትንሽ ሲነኩ ይፈረካከሳሉ። ጌታ ግን ከድንጋይም ለይቶ ዓለት ነህ አለው። ጴጥሮስ ስሜታዊ፣ ደካማ፣ ችኩል፣ ፈጥኖ ወሳኝ፣ የማያስተውል ይመስለን ይሆናል። ጌታ ግን በመጀመሪያ ቀን ዓለት ነህ አለው። ጽኑ ነህ አለው። የሆነውን ሳይሆን የሚሆነውን ነገረው። ይህን ዓለትነት ጴጥሮስ መንፈስ ቅዱስ እስኪወርድ ድረስ አናይበትም። ጌታ ግን ከሦስት ዓመት በኋላ የሚላበሰውን ማንነት አየለት። ሰይጣን የትላንቱን፣ ሰው የዛሬውን፣ እግዚአብሔር ብቻ የነገውን ይናገራል። በብሉይ ኪዳንም ጌዴዎን የተባለ ሰው ጠላቶችን ፈርቶ በወይን መጥመቂያ ውስጥ ስንዴ ይወቃ ነበር። ስንዴ በውድማ እንጂ በጉድጓድ አይወቃም። ይህ ግን መጠን የሌለው ፍርሃት የወለደው ነው። እኛ ብንሆን ምን እንለዋለን? እግዚአብሔር ግን እንዲህ አለው፡- “አንተ ጽኑዕ ኃያል ሰው፥ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነው” /መሳ. 6፡12/። ምስጋና ለእግዚአብሔር ይሁን። እንኳን ሰዎች የሚሉንን ራሳችንም ለራሳችን የምንለውን እግዚአብሔር አይለንም። ተስፋው ኃይል ሆኖለት ስንቱ በረታ። ስሙ አቅም ሆኖት ስንቱ ከሞት መዳፍ አመለጠ?
      ዛሬ ስም የሚጠሩ ነቢያትን ሰዎች ይፈልጉ ይሆናል። ጌታ ግን ስም የሚጠራ ብቻ ሳይሆን ስምን የሚለውጥ ነው። ስምን መለወጥ የባለቤትነትን ስሜት ያሳያል። ጌታችን በጴጥሮስ ላይ ባለቤት ነውና ስሙን ለወጠለት። አንዳንድ ሰው የስሙና የታሪኩ እስረኛ ነው። እግዚአብሔር ግን ታሪኩን በምሕረት፣ ስሙን በአዲስነት ይለውጣል። እኛም ከብኩንነት የተሰበሰብን ልጆችህ ነንና እናመሰግንሃለን። ሳናልቅ ስላገኘኸን እንባ ባጀበው ቅኔ እናመሰግንሃለን።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ