የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቅ

“በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቅ እርሱ ነው አለኝ” /ዮሐ. 1፡33/
መጥምቁ ዮሐንስ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ልዕልና ከገለጠበት መንገዶች አንዱ በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቅ የሚለው ቃል ነው። በርግጥ ዮሐንስም ሆነ ያ ሕዝብ በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቀውን መሢሕ ይጠባበቅ ነበር። መጥምቁ ዮሐንስም ክርስቶስ በመንፈስ ቅዱስ እንደሚያጠምቅ የተረዳው ከሰማይ በሆነው መገለጥ ነው። መንፈስ ሲወርድበትና ሲኖርበት የምታየው፥ በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቅ እርሱ ነው አለኝ” ብሏል። መንፈስ ቅዱስ የወረደበት አንዱ ዓላማ በመንፈስ የሚያጠምቀው ክርስቶስ መምጣቱን ለመግለጥ ነው። ጥምቀት በብዙ ሃይማኖቶች የተለመደ ሥርዓት ነው። ጥምቀት ከክርስቶስ ልደት በፊትና በኋላ ሲደረግ የነበረና እየተደረገ ያለ ሥርዓት ነው። አይሁዳውያን ወደ ይሁዲ ሃይማኖት የሚመጣውን ሰው የሚቀበሉት በማጥመቅ ነው። ወደ ክርስትናም የሚመጣው የሚገባበት በሩ ጥምቀት ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ጥምቀት ብዙ ዓይነት ነው።
1-  የአይሁድ ጥምቀት፡- አይሁዳውያን የረከሰው እንዲነጻ፣ በድን የነካው፣ ከለምጽ የነጻው ብቁ እንዲሆን የማጥምቅ ልማድ ነበራቸው። ይህ የአይሁዳውያን ጥምቀት ውጫዊ አካልን ወይም ሥጋን የሚያነጻ ነው። ለኃጢአት ስርየት፣ ለመቀደስ ኃይል አይሰጥም ነበር። ስለዚህ በውስጡ ዕረፍትና ኃይል አልነበረውም። በዘመናትም የኃጢአት ይቅርታ፣ የቅድስና አቅም ሲናፈቅ ኖሯል።
2-  የዮሐንስ ጥምቀት፡- የዮሐንስ ጥምቀት የንስሐ ጥምቀት ነው። ሰዎች ኃጢአታቸውን ከተናዘዙ በኋላ ያጠምቃቸው ነበር። የዮሐንስ ጥምቀት ከአይሁድ ጥምቀት ከፍ ያለና ነፍስን አድራሻ አድርጎ ስርየትን የሚያውጅ ነበር። የዮሐንስ ጥምቀት ከአይሁድ ጥምቀት ከፍ ቢልም ከክርስትና ጥምቀት ግን ያንስ ነበር። ላለፈው ስርየትን ቢያውጅም ቅድስናን የሚሰጥ፣ ከኃጢአት ኃይል የሚያላቅቅ፣ ጸጋን የሚያፈስስ አልነበረም። ስለዚህ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ይናፈቅ ነበረ።
3-  የክርስትና ጥምቀት፡- ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፈለገ ዮርዳኖስ፣ በዕደ ዮሐንስ በመጠመቅ አርአያ የሆነበት የክርስትና ጥምቀት ነው። በዚህ ጥምቀት ላይ የሥላሴ ምሥጢር ተገልጿል። አብም የምወደው ልጄ በማለት መሥክሯል። መንፈስ ቅዱስም በርግብ አምሳል ወርዷል። እንዲሁም የክርስትና ጥምቀት በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም መፈጸም አለበት /ማቴ. 28፡19/። የምንወለደው ከሥላሴ ነውና። ኢየሱስ ሲጠመቅ አብ ልጄ ነው በማለት መመስከሩ ጥምቀት ልጅነትን የምናገኝበት መሆኑን ያሳያል። ከውኃው ሲወጣ መንፈስ ቅዱስ መምጣቱ የእኛም ጥምቀት ከውኃና ከመንፈስ መሆኑን ያረጋግጣል /ዮሐ. 3፡5/። ሰው ካልተጠመቀ የቤተ ክርስቲያን አባል እንደማይሆን እንዲሁም በመናቅ ጥምቀትን ችላ ቢል ወደ እግዚአብሔር መንግሥት አይገባም /ማር. 16፡16/።
4-  የመከራ ጥምቀት፡- ጌታችን ሞቱን በጥምቀት መስሎ ተናግሯል። “እኔ ልጠጣው ያለውን ጽዋ ልትጠጡ እኔም የምጠመቀውን ጥምቀት ልትጠመቁ ትችላላችሁን?” በማለት ስለ ሞቱ ተናግሯል /ማቴ. 20፡22/። የክርስትናም ጥምቀት ከክርስቶስ ሞት ጋር መተባበር ነው /ሮሜ. 6፡3/። ጥምቀት ሞትን አመልካች ነው። ከክርስቶስ ጋር ሞቻለሁ የምንልበት ኪዳን ነው። ከክርስቶስ ጋር መሞት የሚያስፈልገን ለመነሣት ነው። በራሱ የሞተ ትንሣኤ የለውም።
5-  የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት፡- የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት በዘመናት ሲጠበቅ የኖረ ክርስቶስ ብቻ የሚያጠምቀው ጥምቀት ነው። የጥምቀቱ ዓላማ ሦስት ነው። የመጀመሪያ ሕይወትን ይቀድሳል። ሁለተኛው ለአገልግሎት አቅም ይሰጣል። ሦስተኛ ጸጋን ያቀዳጃል።ይህ ጥምቀት በበዓለ ሃምሳ በደቀ መዛሙርት ላይ ተከናውኗል። እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስም በክርስቶስ የሚያምኑ ሁሉ የሚካፈሉት ነው።
6-  የእሳት ጥምቀት፡- ይህን ጥምቀት የሚያጠምቀው ራሱ ክርስቶስ ነው። የእሳት ጥምቀት ፍርድ ነው። ፍሬ የማያፈሩ ሁሉ በዚህ ፍርድ ይጠመቃሉ /ማቴ. 3፡11-12/።
7-  የደም ጥምቀት፡- በሰማዕትነት ምክንያት ያልተጠመቁ ሰዎች ሰማዕትነታቸው እንደ ጥምቀት ስለሚቆጠርላቸው ይህ የደም ጥምቀት ተብሎ ይጠራል።
እነዚህ የዘረዘርናቸው ሰባት ጥምቀቶች አፈጻጸማቸው ሦስት ክፍል አለው። የመጀመሪያው በአገልጋዮች የሚፈጸሙ ናቸው። እነርሱም የአይሁድ፣ የዮሐንስና የክርስትና ጥምቀቶች ናቸው። ሁለተኛው በአረማውያንና በአላውያን የሚፈጸም ነው። እርሱም የደም ጥምቀት ነው። ሦስተኛዎቹ ግን በክርስቶስ ብቻ የሚከናወኑ ናቸው። እነርሱም፡- የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት፣ የመከራ ጥምቀትና የእሳት ጥምቀት ናቸው።
 
1-  የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት፡- ክርስትናን ቀጣይ፣ ንስሐን ጽኑ የሚያደርገው ለአገልግሎት ጸጋን የሚሰጠው፣ ለወንጌል የሚያስጨክነው የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ነው። ይህን ጥምቀት የሚያጠምቀው ራሱ ክርስቶስ ነው። በእርሱ ስናምን ይህን ጥምቀት በእምነት ተካፍለናል ማለት ነው።
 
2-  የመከራ ጥምቀት፡- በሕይወት ውስጥ እያሳለፈ የሚገርዘን፣ ከማይገቡ ጠባያት የሚያላቅቀን ይህ የመከራ ጥምቀት ነው። ይህንን የሰው መምህር ሊያከናውን አይችልም። ራሱ ክርስቶስ በሕይወታችን የሚፈጽመው ግርዛት ነው። 
 
3-  የእሳት ጥምቀት፡- ይህም ጥምቀት በራሱ በክርስቶስ የሚፈጸም ነው። የማያፈሩት የሚቀበሉት ፍርድ ነው። ከሰው ወገን ማንም ፈራጅ ሊሆን አይችልም። ይህን መለኮታዊ ሥልጣን ብቻ ያከናውነዋል።
 አዎ በሕይወት ዝለት፣ በአገልግሎት ስንፈት ውስጥ ስንሆን ያንን የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ማሰብ ያስፈልገናል። በመከራ ውስጥ ስንሆን ክርስቶስ የሚገርዝልን ማንነት እንዳለ እያሰብን ደስ ሊለን ይገባል። በር የሌለው ቤት እንደሚደፈር መከራ የሌለውም ሕይወት ይደፈራል። በእሳት ጥምቀት ማለትም በፍርድ ማጥመቅ አንችልምና ማንንም ቀጪ በማንም ላይ ፍርድ አስተላላፊ ልንሆን አይገባንም።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ