የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

አትጨነቁ

የዲያቆን አሸናፊ መንን ገጽ ዓርብ ጥር 13/2008 ዓ.ም.
 
ዘመናችን አካላዊ ጫናዎችን ያቃለለ፣ የተራራቁ አገሮችን ያቀራረበ፣ መረጃዎችን ያፈጠነ፣ ፕላኔቶችን አስሶ ያገኘ፣ ወደ ተዋቡ ሥልጣኔዎች ያደገ፣ ዓለም አቀፋዊ ማኅበራትን ያበረከተ . . . አስገራሚ ዘመን ነው፡፡ በአንድ ክፍለ ዘመን ላይ አንድ ሥልጣኔ ብቅ የሚልበት ያ ዘመን አልፎ አድረን ስንነሣ አንድ አዲስ ግኝት መታየት ጀምሯል፡፡ መገልገያዎችን እንዴት ቀላል እናድርጋቸው? የነበሩትን ሥልጣኔዎች እንዴት እናራቅቃቸው? የሚለው አሳብ የአዋቂዎችን እንቅልፍ እየተጋፋ ነው፡፡ ሁሉም የሰው ዘር ለዚህች ዓለም አንድ አዲስ ግኝትን ለማበርከት እያሰበ ይመስላል፡፡ ወንጌላችንም የዚህ ሥልጣኔ ተጠቃሚ ሆኗል፡፡ ይህን ሁሉ ምሥጢር ለሰው የገለጠ እግዚአብሔር ነው፡፡ ሥልጣኔው ካለ መኖር ወደ መኖር ያመጣው ምንም ነገር የለም፤ እግዚአብሔር ፈጥሮ በታትኖ ያስቀመጠውን፣ እግዚአብሔር በሰጠው አእምሮ ተሰብስቧል፡፡ ስለዚህ የሥልጣኔው ምስጋና ይህን አእምሮ ለፈጠረው ለእግዚአብሔር ነው፡፡
 
ሥልጣኔው ግን ችግሮችን ቢያቀልም የራሱ ችግር ነበረው፡፡ ተዘዋዋሪ ጉዳት የሌለው የእግዚአብሔር ሥራ ብቻ ነው፡፡ ሥልጣኔው አካባቢያዊ ችግሮችን አስወግዶ የቤተሰብን ችግር፣ የፍቺን ብዛት ግን ሊያስወግድ አልቻለም፡፡ በዓመታት ይደርስባቸው የነበሩ አገሮች በዕለት የሚረገጡ ሆኑ፡፡ የሰው መንፈስ ግን ባለመርካትና በባዶነት ተመታ፡፡ ከተሞች ተዋቡ፣ ሥነ ምግባር ግን ፈረሰ፡፡ የዓለም መንግሥታት ኅብረት ተመሠረተ፣ የትዳር አንድነት ግን የማይጸና ሆነ፡፡ ነባር በሽታዎች በክትባት ተወገዱ፣ መድኃኒት ያልተገኘላቸው በሽታዎች ግን ምድርን ሞሉ፡፡ አንዱ ሰው የብዙ ስልኮች ባለቤት ሆነ፣ የቤት ስልክ፣ የቢሮ ስልክ፣ የተንቀሳቃሽ ስልክ ባለቤት ሆነ፡፡ ያለ ስልክ ይገኝ የነበረው ሰው በሦስት ስልክ የማይገኝ ሆነ፡፡ ፍቅር በሽንገላ፣ ናፍቆት በጥቅም፣ ነጻነት በፍርሃት ተለወጠ፡፡ ሕዝቦች መንግሥታቸውን በአደባባይ ይቃወማሉ፣ በውስጣቸው የነገሠውን ብልግና ግን መቃወም አልቻሉም፡፡ ስለ ደኖች መመናመን ይናገራሉ፣ አንድ ዛፍ ግን በግቢያቸው አይተክሉም፡፡ ዐውዱን ስላልጠበቀ ስብከት፣ የሥነ ጽሑፍ ሕግጋቱን ስላላሟላ መጽሐፍ ዕንባ ቀረሽ ትችት ይዘንባል፣ ዐውዱን የጠበቀ ሕይወት ግን ጠፍቷል፡፡ እውነቱን እያወቁ ስለ መኖር ውይይት እንኳ የለም፡፡ ሥልጣኔው አስመሳይ፣ የአፍ ጻድቃን እያደረገን ነው፡፡ መሰልጠን መሰይጠን እንዳይሆን ብዙ አባቶች የፈሩትና የተናገሩት ደረሰ፡፡
 
ብዙ ችግሮች ቢኖሩም የሰው መንፈስ መረጋጋት አለመቻሉ የችግሮች አውራ ነው፡፡ ከቆዳ ቊስል የውስጥ ቊስል ባለቤቱን ያሰቃየዋል፡፡ የውስጥ ቊስል ለባለቤቱ ብቻ የሚታየው ለባለቤቱ ብቻ የሚሰማው ነው፡፡ ሥልጣኔው በራሱ ሙሉ፣ እግዚአብሔርንም የሚተካ ኃይል መስሎን ብዙ አዚመንለታል፡፡ እግዚአብሔር ግን ለፈቃዳችን ትቶን በትዝብት ይመለከተን ነበር፡፡ እግዚአብሔር የለም የሚል መፈክር የማደግ ምልክት ነበረ፡፡ አሁን ግን ያለ ማደግ ምልክት ሆነ፡፡ እግዚአብሔር የሌለበትን የራሳችንን ዓለም ለመመሥረት ያደረግነው ጥረት የማይታይ አውሬ በምድሪቱ ላይ ለቀቀ፡፡ የአውሬው ድምፅ ይሰማናል፣ ግን አይታየንም፡፡ አለመርካት፣ ፍርሃት፣ መናወጥ፣ ጭንቀት፣ ባዶነት፣ ተስፋ ማጣት፣ መረበሽ እነዚህ አናብስትና አናብርት ሆነው ምድርን እያመሷት ነው፡፡ እግዚአብሔር ግን ይህን የሰቆቃ ኑሮ፣ ይህን ትርጉም ያጣ ሩጫ፣ ይህን ፍርሃት የሚንጠውን ሕይወት ተመልክቷል፡፡ መንግሥታት፣ አዋቂዎች፣ የአካባቢ ተቆርቋሪዎች … አስፈሪ ነገር እንዳለ ይናገራሉ፡፡ እግዚአብሔር ግን ሁልጊዜ አዲስ በሆነው ቃሉ፣ ዘመናት በማያስረጁት ክብሩ “አትጨነቁ”ይላል /ማቴ. 6÷31/፡፡ እርሱ የሌለውን ወደ መኖር ማምጣት የሚችል፣ ለሞተው ነገር ሕይወት የሚሰጥ፣ ከመጨረሻውም የሚጀምር፣ የተቆረጠን የሚቀጥል፣ አዲስን ነገር የሚያደርግ ነው፡፡ ነገሥታት ፍርሃትን ቢያውጁ የነገሥታት ንጉሥ ግን “አትጨነቁ” ይላል፡፡ ጠቢባን ስጋትን ቢዘሩም የጠቢባን ጠቢብ “አትጨነቁ” ይላል፡፡ ከእጁ የሚያመልጥ ጉዳይ፣ ከእግዚአብሔር አቅም በላይ የሆነ ጭካኔ፣ የአማኑኤልን ጉልበት የሚገዳደር ጥያቄ የለም፡፡ እኛ ስናምነው እርሱ ይሠራል፣ መንገድ ስንለቅለት በድል ያልፋል፣ ዝም ስንል ይፈርዳል፡፡ አዎ “አትጨነቁ” ይላል፡፡

አንዳንዶቻችን አልፎ አልፎ የምንጨነቅ፣ ሌሎቻችን ያለ ማቋረጥ የምንጨነቅ ልንሆን እንችላለን፡፡ ሕይወት ከፍታና ዝቅታ፣ ሜዳና ገደል፣ አበባና እሾህ፣ ክረምትና በጋ ያለባት ባለ ሁለት ገጽ ናት፡፡ ሁሉም ነገር አስደሳች ሁሉም ነገር አሳዛኝ አይደለም፡፡ ሕይወት ከደስታና ከሀዘን የተመጠነች ወ/ሮ ምጥን ናት፡፡ ታዲያ በሕይወት ውስጥ የሚያስጨንቅ ነገር የሚያስጨንቃቸው እንዳሉ ሁሉ ባልተጨበጠ ችግርም የሚጨነቁ አሉ፡፡ እንዲህ ቢሆንስ እያሉ ያልተጀመረውን ጨርሰው፣ ያልተወለደውን ገድለው፣ ያልተሾመውን ሽረው የሚቃዡ ወገኖች ብዙ ናቸው፡፡ በጭንቀት ውስጥ የምንጨነቅበት ነገር በእርግጥ አለ ወይ? ብለን መጠየቅ ያስፈልገናል፡፡ አንዲት እህት በብርቱ ጭንቀት ውስጥ ታልፋለች፡፡ የጭንቀቷ መንስኤ በጣም ደግ የሆነው ያ ባሏ ቢሞትስ የሚል ነው፡፡ የሚገርመው እርሷ ቀድማው ልትሞት ነው፡፡ በዓለም ላይ ሳይኖሩ የሚሞቱ ብዙዎች ናቸው፡፡ ጭንቀት የኑሮ ደረጃን የሚመርጥ አይደለም፡፡ እንደውም ከፍ ያለ ሀብትና ሥልጣን ያላቸው የጭንቀት ተጠቂዎች ናቸው፡፡ ከፍ ባሉ ቊጥር አየርና እርካታ እየራቀ ይመጣል፡፡
 
ጭንቀት ባለቤቱን ብቻ አውኮ የሚቀር አይደለም፡፡ በአንድ ሰው መታወክ ቤተሰቡ ይታወካል፤ በአንድ ቤተሰብ መታወክ አካባቢው ይታወካል፡፡ ጭንቀት የሚተላለፍ ባሕርይ ስላለው ልጆቻችን የእኛን መጨነቅ እያዩ እነርሱም ፈሪና ይህችን ዓለም የሚሰጉ ይሆናሉ፡፡ ልጆች ከቃላችን ይልቅ በኑሮአችን ስለሚማሩ ጭንቀታችን እነርሱን ዕረፍት የለሽ ያደርጋቸዋል፡፡ የመጨረሻ ኃያል አድርገው የሚመለከቷቸው ወላጆቻቸው ሲጨነቁ በማየት የመጨረሻ ፈሪ ይሆናሉ፡፡ ጭንቀት በመልካም  ምርጫችን እንድንፀፀት ያደርገናል፡፡ ለጭንቀታችን መንስኤው የመረጥነው ትዳር መስሎ ይሰማናል፡፡ በዚህ ምክንያት ለትዳር ጓደኛችን ያለን ፍቅርና ተቀባይነት እየቀነሰ ይመጣል፡፡ በግድ መሳቅ የበለጠ ጭንቀትን እየጨመረ ስለሚመጣ ፍቺን እንደ ሰላም መቊጠር እንጀምራለን፡፡ ምክንያቱ ግን ያ ጭንቀት እንጂ ትዳሩ አይደለም፡፡ አዎ ጭንቀት ሁሉንም የሕይወት ክፍል የመጉዳት አቅም አለው፡፡
 
ጭንቀት ኑሮዬ ይበቃኛል ባለ ማለት ይወለዳል፡፡ የሰው ባሕርይ ስግብግብ ስለሆነ አንድ ነገር ሲሠራ ሁለተኛ ያምረዋል፡፡ አንድ መኪና ሲይዝ ሌላ ይፈልጋል፡፡ ያንን ለማግኘት ደግሞ አሁን አቅሙ አይፈቅድም፡፡ ለማግኘት ግን የጭንቀትን ዋጋ ይከፍላል፡፡ ቤት አተርፋለሁ ብሎ ራሱን ያጣል፡፡ ገንዘብ እጨምራለሁ ብሎ ሰላሙን ይቀንሳል፡፡ ጭንቀት ግምትን በማመን ይወለዳል፡፡ እየፈጠሩ መስጋት ጥንቃቄ የሚመስላቸው ከመሆኑ በፊት በቀብድ ሚሰቃዩ ብዙዎች ናቸው፡፡ የምንፈራው ነገር የመጣ ቀን እንደ ዛሬው አያስፈራንም፡፡ ምክንያቱም የሚመጣው ከመቻያው ጋር ነውና፡፡ ዛሬ ግን ዝናው ያስበረግገናል፣ የሆነ ቀን ግን ያስጨክነናል፡፡ የወዳጃችን ሕመም የሚያስፈራንን ያህል የሞተ ቀን አንፈራም፡፡ ቊርጥ ያጠግባልና እንጸናለን፡፡ ሰው የቻለው ለሰው አይከብድም፡፡  እገሌ እንዲህ ቢሆን ምን እሆናለሁ? ሳይሆን ዛሬ ላደርገው የሚገባኝ ምንድነው? ማለት ያስፈልጋል፡፡ አንድ አገልጋይ ትክዝ ብሎ ተቀምጦ ሳለ ሚስቱ፡-“ዛሬስ አምላክህ የሞተ ይመስላል” አለችው፡፡ ከዚያች ቀን ጀምሮ ትካዜውን አቆመ፡፡ ጭንቀት ክፉ ምስክርነት ነው፡፡
 
ጭንቀት ስለሆነውና ስላልሆነው ነገር ያለን ስጋት ነው፡፡ ይህ ስጋት ግን ሕይወትን እንደ ነቀዝ የሚበላ ነው፡፡ ከሁሉ በላይ ጭንቀት በቤታችን ሳይሆን በልባችን ውስጥ ያለ ነገር በመሆኑ እንደ ልብስ አስቀምጠን የምንወጣው አይደለም፡፡ ሰዎች በጭንቀታቸው እምነትን ከመለማመድ ወደ ባሕር ዳርቻ መሄድ፣ ወይም አገር ለቆ መጥፋትን ይመኛሉ፡፡ የሚያስጨንቀን ግን ትኬት የሚፈልግ ሳይሆን አብሮን የሚጓዝ ነው፡፡ ለጭንቀት ሲሸሹለት ይብሳል፡፡ አንዳንድ ጊዜ መጋፈጥ ያለብንን መጋፈጥ አለብን፡፡ ራሳቸውን ከመጠን በላይ አሳንሰው የሚመለከቱ ወይ ቆንጆ አይደለሁም፣ ወይ ትምህርት የለኝም፣ ወይ ቋንቋ አልችልም ብለው የሚያስቡ ሰዎች ይጨነቃሉ፡፡ ሰውን ሰላም ለማለት እንኳን ይፈራሉ፡፡ ወደ አንድ ቢሮ ጉዳይ ካላቸው ትንሽ መጠጥ ካልቀማመሱ ድፍረት የማይሰማቸው አያሌ ናቸው፡፡ ነገር ግን ለሰዎች ትልቁ ነገር መማር ወይም ቆንጆ መሆን ሳይሆን ታማኝነት መሆኑን ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ አያችሁ ጭንቀት ለመጠጥ፣ ለሱስና ለሽሽት ይዳርጋል፡፡ ይህች ዓለም የሁላችንም ናት፡፡ ደግሞም የአባታችን  የእግዚአብሔር ናት፡፡ ስለዚህ አንዱ አስፈሪ ሌላው ፈሪ የሚሆንበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ የሌላውን ድርሻ ጭምር እየወሰዱ አለ ልክ የሚደፍሩ እንዳሉ ሁሉ መብታቸውን እየጣሉም የሚፈሩ አሉ፡፡ ጭንቀት ብዙ መብላትን ብዙ መተኛትንም ያስከትላል፡፡ እልሃቸውን መብል ላይ ይወጡታል፡፡ ያልታዘዘላቸውን ኪኒን በመውሰድም ይህችን ዓለም በእንቅልፍ የሚደበቋት ዕለት ዕለት እየበዙ ነው፡፡ ነገር ግን የምንኖረው አንድ ጊዜ ያውም ለጥቂት ዘመን ነውና በትክክል ኖረን ማለፍ ይገባናል፡፡ የምንፈራውም ሰው በራሱ የሚፈራው ነገር አለው፡፡ ጠመንጃ የያዘውን ወታደር እስቲ አስቡት፡፡ እኛ እርሱን እንፈራዋለን፡፡ እርሱም መሣሪያ የያዘው ስለ ፈራ ነው፡፡ አለመነጋገራችን እንጂ የሚያስፈራን ምንም ነገር የለም፡፡ የጽዳት ሠራተኞች ከሆንን በደስታ እየዘመርን እናጽዳ፡፡ ዘበኞች ከሆንን ዳዊታችንን እየደገምን እንትጋ፡፡ ወፎች በሚቦርቁባት ዓለም እኛ ለምን እናለቅሳለን? አንበሶች በሚፋንኑበት ዓለም እኛ ለምን እንሸማቀቃለን? ከወፎች ይልቅ እኛ በዚህች ዓለም ላይ መብት አለን፡፡ ለእኛ የተፈጠሩት ድመትና ውሻ ዧ ብለው እየተኙ እኛ ለምን እንበረግጋለን? አምላካችን አለ፡፡ ከዚህ ድብርት እንደገና በስሙ ልንወጣ ይገባናል፡፡ ጌታችንም፡- “አትጨነቁ” ብሎናል /ማቴ. 6÷31/፡፡
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ