ቅዳሜ፣ጥር 26 2004 ዓ.ም.
አንድ ገበሬና ዶክተር ተጣሉ፡፡ ገበሬውም ዶክተሩን አንተ መሃይም እያለ ይሰድበዋል፡፡ አለቃ በድንገት ደረሱና ነገሩን በውይይት ለመፍታት ቁጭ አሉ፡፡ እነዚህን ሰዎች እያነጋገሯቸው ሳሉ አንድ ሰው በዚያ ሲያልፍ አለቃ እንደምን አሉ፣ ምን እያደረጉ ነው አላቸው፡፡ አለቃም አይ ወንድሜ ስድብ ቦታ ተለዋውጦ ከቦታው ለመመለስ እየታገልኩ ነው አሉ ይባላል፡፡ በእኛም አገር ሥነ መለኮትን የሚያውቅ መናፍቅ፣ ያልተማረው ደግሞ ሃይማኖተኛ ይባላል፡፡
ሃይማኖት ተብሎ የሚጠራው ሁለት ነው፡፡ እርሱም የእግዚአብሔር አንድነትና ሦስትነት ዳግመኛም የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነትና አዳኝነት ማመን ነው፡፡ ከዚህ ያለፈው ሥርዓት ነው፡፡ ካልተማረው ሰው በቀርም በሥርዓት የሚጣላ የለም፡፡ ክብር ብቻ ነውና፡፡ የገዛ ቤታቸው ሲደራጅ የእግዚአብሔር ቤት እንዳይፈርስ ይቀናሉ፡፡ ነቢዩ ‹‹የቤትህ ቅንዓት በልታኛለች፡፡›› እንዳለ (መዝ.68(69)÷9)፡፡ እግዚአብሔር በየዘመናቱ የራሱን ሰዎች በማስነሣት ለዓለም የእውቀትን ብርሃን አብርቷል ፍቅር፣ ፍትሕና እውነት እንዲገለጥ አድርጓል፡፡ ነቢያትና ሐዋርያት በምድር ላይ ባይነሱ ኖሮ የድንቁርና ጨለማ እስከዛሬ የመፍሰስ አቅም በኖረው ነበር፡፡ እነዚህ የእግዚአብሔር መልዕክተኞች የራሳቸውን ፈቃድ ለእግዚአብሔር ፈቃድ የሠዉና የእኔ የሚሉት የራሳቸው ኑሮ ያልነበራቸው ነበሩ፡፡ ብርሃናቸው ወደራሳቸው ቢሆን ጨለማ በሆኑ ነበር፡፡ ሁልጊዜ ግን በመፍሰስ መርህ ይጓዙ ነበር፡፡
እነዚህ የእግዚአሔር ሰዎች መናንያን ነበሩ፡፡ ለገንዘብና ለሰው ክብር የማይኖሩ ዓለምን የናቁ ነበሩ፡፡ የሚናገሩትን ለመኖር በብርቱ የተጉ፣ ዓላማ እንደያዘ ሰልፈኛ ወደ ድላቸው የሚሮጡ ነበሩ፡፡ ለሚጠፋ መብል አልኖሩም፤ በመጠን ለመኖርም ራሳቸውን አስለምደዋል፡፡ ስለዚህ የእነርሱ ጭንቀት ለብዙዎች መጽናናት ሆነ፤ ረሀብተኞች ሳሉም ብዙዎችን ያጠግቡ ነበር፡፡ በዚያው መጠን የተላኩበት ሕዝብ ሲሞቱ ጠብቆ ከማዘከር ውጭ በሕይወት ሳሉ ቁራሽ እንጀራ እንኳ ለመጣል ተፈትኗል፡፡
ሰዎች ስኬታማ ለመሆን በሁለት መንገድ ይጠቀማሉ፡፡ ቀጥተኛ በሆነ መንገድና ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ፡፡ ስለዚህ የታወቂነት ጥማት ያለባቸውና በእግዚአብሔር ስም ለመነገድ የሚፈልጉ ነቢያትና አገልጋዮች ነን በማለት በየዘመናቱ ራሳቸውን እየሾሙ መጥተዋል፡- ያ የተጨነቁለት ሆዳቸውና ክብራቸው ሲያልፍ ሐሰቱ ግን ትውልድን የሚበክል መርዝ ሆኖ ቀርቷል፡፡ የተተኮሰ ጥይት ተመልሶ እርሳስ እንደማይሆን ሁሉ እንዲሁም ዓላማው ከሰውዬው ከወጣ መመለሻ የለውም፡፡ እርሱ ተጸጽቶ ቢመለስ እንኳ ዓላማውን የተቀበሉ ግን አይመለሱም፡፡
እ.ኤ.አ በ1978 ዓ.ም በአሜሪካን አገር የተነሣው ዝነኛ ሰባኪ ጂም ጆንስ በትምህርቱ ብዙዎችን ማረከ፤ ስምንት መቶ የሚያህሉ ተከታዮቹን ይዞ ወደ ሌላ ከተማ ሄደ፡፡ በዚያም እኔ ክርስቶስ ነኝ ሲላቸው ተቀበሉት፡፡ በመጨረሻ መርዝ በብርጭቆ ቀድቶ ጠጡ ሲላቸው ጠጡ፡፡ ያ ሁሉ ሕዝብና ራሱም ሞቱ፡፡ ሕዝብ ለሐሰተኞች መምህራን የተሰጠ ነው፡፡ ለእውነተኞቹ ግን ጥቂት እንኳ አይታዘዝም፡፡ አዎ ሐሰተኞቹን መምሀራን ስንቀልብ እውነተኞቹ ግን በጣም ይከብዱናል፡፡
ተሰጥኦ ማንነት አይገልጥም፡፡ ችሎታም ቅን ሰው አያስኝም፡፡ በደጋፊ ብዛት ትልቅ መሆን ይቻላል፣ በደጋፊ ብዛት ግን መንፈሳዊ መሆን አይቻልም፡፡ በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት ማንነት ይፈተናል እንጂ ያደረግነው ተአምር አይቆጠርም፡፡ ሁሉም ዛፍ ቅጠሉ አረንጓዴ ነው፡፡ አንዱ ካንዱም በቅጠል ሳይሆን በፍሬ ይለያል፡፡ የብርቱካን ፍሬ ስናይ የብርቱካን ዛፍ ነው እንላለን፡፡ እውነተኛ አስተምሪዎችም በሚኖሩት ኑሮ ይታወቃሉ፡፡ በፍሬ ይታወቃል፡፡