“ላልጠየቁኝ ተገለጥሁ ፥ ላልፈለጉኝም ተገኘሁ በስሜም ያልተጠራውን ሕዝብ፡- እነሆኝ ፥ እነሆኝ አልሁት ።” ኢሳ. 65 ፡ 1 ።
ሰፈሩ ለድሮ በቀበሌው ስም ይጠራ ነበር ። በ13 እና በ14 ቀበሌ መካከል ያለው መንገድ ምቹ ያልነበረ ፣ ለማየትም የሚማርክ አልነበረም ። ከመንገዱ ቤቶቹ የተሻሉ ነበሩ ። ዘመን ሰለጠነና እንደ ቅቤ ያለ መንገድ ተሠራ ። መንገዱ ሲሠራ የገባው ሥልጣኔ ብቻ ሳይሆን ኃጢአትም ሆነ ። ታዲያ ሰፈሩን “ቺቺንያ” ብለው ሰየሙት ። ትርጉሙን ብጠይቅ በቺቺንያ ጦርነት ሕፃናት ይሳተፉ ነበርና በዚህም ሰፈር ሕፃናት ለዝሙት ንግድ ተላልፈው ተሰጥተዋል ፤ ስለዚህ ሰፈሩ “ቺቺንያ” ተባለ የሚል መልስ አግኝቻለሁ ። ያንን አካባቢ የማውቀው በ1986 ዓ.ም. ጀምሮ ነው ። እግዚአብሔርን የሚወዱ ፣ ሰውንም የሚወዱ ሰዎች እንደ ነበሩበት አስታውሳለሁ ። አቅም የነበራቸው ወጣቶችም ነበሩበት ። ታዲያ ከሁለት ቀን በፊት በዚያ “ቺቺንያ” ተብሎ በተጠራው ሰፈር ጎዳና ላይ በመኪና ሳልፍ ድንገት አንድ አባት ሕፃን ልጅ ይዞ መልሶ ደግሞ እያቀፈ ቀጥሎ እያወረደ በቅጽበት አየሁ ። አባቱን ሳየው ዕድሜው 35 ዓመት ቢሆነውም ያለ ጊዜው ግን አርጅቷል ። መልኩ ክልስ ይመስላል ። መልሶ ደግሞ ጠቍሯል ። መለስ ብዬ ልጁን ሳየው ሕፃኑ ጠይም ነው ። በጠይምነት ጀምሮ በጠይምነት የቀጠለ የ6 ዓመት ልጅ ቢሆን ነው ። አባቱን ኑሮ ያጠቆረው መሆኑን አረጋግጬ ልጁን መልሼ ያየሁት ምናልባት የእኛው አየር ንብረት ያጠቆረው ሶርያዊ ይሆን ብዬ ነው ። በቅጽበት የሰማሁት የአባትና የልጅ ንግግር ግን ኢትዮጵያዊ እንደሆኑ መሰከረልኝ ። ያ አባት በዓይኔ በቅጽበት ውስጥ ገባ ። የለበሰው ሙሉ ልብስ ውድ ልብስ ነው ። ነገር ግን ከወለቀ ብዙ ጊዜው ሆኖ ደክርቷል ። ያ አባት የሆነው ወጣት መልኩ በቀይ ጀምሮ እንደነበር እርግጠኛ ነኝ ። አሁን ግን ጠይም ቢሆን ሂደት ነበር ። የቀይ ዳማ ቢሆንም በቅላትና በጠይምነት መካከል ነው ። ነገር ግን አመድማና መግለጥ የማይቻል መልክ ይዟል ። እስቲ የውኃን መልክ ግለጹልኝ ፣ ያ ወጣትና አባትም እንዲሁ ነው ። ኑሮ በደንብ እንደ ጎዳው ያስታውቃል ። ጥርሶቹ ተጎድተዋል ፣ ለመቦረሽም እድል አላገኙም ። ጫማው አዘንብሏል ። አሁን ያለው ሀብት ፍቅር ብቻ ይመስላል ። ልጁ ሲከብደው ያወርደዋል ፣ መልሶ ፍቅሩ አላስችል ብሎት ይሸከመዋል ። ልጁ የጫጨ ቢሆንም ለአቅመ ደካማው ወጣት አባት ግን ከባድ ነበረ ። አካሉ የተሟላ አባት ነው ፣ አቅም ግን ጥሎት ከሄደ የሰነበተ ይመስላል ። ማናልባት ሱስ ይሆናል ካላችሁ እኔ ግን አልመሰለኝም ። የአባቱ አቅም እንደ ተዳከመ ልጁ አያውቅም ። ልጁ የሚያውቀው አባቱ አፍቃሪና ኃያል መሆኑን ብቻ ነው ። አዎ አባቱ አፍቃሪ ነው ፣ ግን በጊዜ ደክሞታል ። በዕድሜ ሳይሆን በኑሮ አርጅቷል ። ያንን አባት ለማወቅ ቤቱን ማየት አያስፈልግም ፣ ቁመናው ቤቱን ያሳያል ።
መገመት መልካም ነው ። ይህ የተዋበ አባት በውበት ጀምሮ በመወየም እየደመደመ ነው ። በቅላት የሚያውቀው ሰው ብዙ ይኖራል ። አሁን ግን አመድማም ከሰልማም ለመባል አስቸጋሪ ሁኗል ። ሳየው አዘንኩለት ። ማግኘትና ማጣትን የሚያውቅ ሰው ፣ በልዑልነት ጀምሮ የባሪያን መልክ እንኳ ያጣ ወገን ብቻ የሚያውቀው ሰው ነው ። መኪናው ለቅጽበት ቆም ያለው ከፊት ለፊቱ ጭንቅንቅ ስለነበረ ነው ። ይህን ሰው ያየሁትም የሰማሁትም ከአንድ ደቂቃ ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ነው ። ልጁን ቁልቁል እያየ ምነው በኖረኝ ? የሚል ስሜት ይታይበታል ። ልጁንም ሳብ አድርጎ ወደ ላይ ካወጣው በኋላ አቀፈው ። ልጁም ከፍ ያለው ማማ ላይ ሲወጣ ዓይኖቹ ማዶ ላይ አሻግረው የተዋቡ ጫማዎች የሚሸጥበት ሱቅ ላይ አረፉ ። ውድ ቤት እንደሆነ ሱቁም ጫማውም ይናገራል ። ልጁ ግን፡- “አባ” አለው ። አባትም እንደ ልጁ ጮክ ብሎ ሳይሆን ዝቅ አድርጎ መለሰ ። የአባትነት ስሙ እንጂ አቅሙ የለኝም ብሎ ይሆናል ። ልጁ “አባ” አለ፡- “አቤት” በማለት በዝቅታ ፣ በኀዘኔታና በፍቅር ድምፅ መለሰለት ። ልጁ እጁን እየጠቆመ “አባ ጫማ ግዛልኝ” አለው ። ያ አባትም፡- “እሺ እገዛልሃለሁ” አለው ። የአባት መልስ ልጁን ቢያሳርፈውም አባት ግን ያረፈ አይመስልም ። አነጋገሩ እንደማይገዛ ያሳያል ። ግን ድምፀቱን ወደ ኋላ እየፈተሽኩ ስሰማው አንድ ቀን እገዛልሃለሁ ፣ እንደ መሸ አይቀርም የሚል ነው ።
መንገዱ ተለቀቀና መኪናው አፈተለከ ። እኔም ያንን አባትና ልጅ በአሳብ ይዣቸው ወደ ቤቴ ገባሁ ። አሁንም ፊት ለፊቴ ይታዩኛል ። ጥጋብ ሰውን ቢፈትንም ማጣት ግን ከዚያ በላይ ፈታኝ ነው ። ለወለዱት ልጅ መስጠት አለመቻል ትልቅ ሕመም አለው ። ስሙን ተሸክሞ በተግባር አባት መሆን ሲሳን ቁጭት አለው ። “እሺ እገዛልሃለሁ” አለ ። ልጁም አጭር የማስታወስ አቅም ስላለው ይረሳዋል ። በተስፋ ግን ደስ ብሎታል ። ጥያቄዬ ተመለሰ ብሎም ዝም ብሏል ። ያ አባት ግን የልጁ ጥያቄም የራሱ መልስም ሲያጫውተው ይውላል ።
ያ ልጅ ጠይቆ ማግኘት አልቻለም ። አባቱ ፈቃድ ቢኖረውም አቅም የለውም ። እግዚአብሔር ግን ላልጠየቁት ሕይወትን ፣ ብርሃንን ፣ የዛሬዋን ቀን ሰጥቷል ። ከሁሉ በላይ ቃሉንና ልጁን ክርስቶስን ሰጥቶናል ። ሳንለምን በተቀበልነው ነገር ውስጥ ለምነን ያላገኘናቸውን ነገሮች አስቡ ። ሦስት ነገሮች ብልጭ ይላሉ ። የመጀመሪያው፣ ሳንለምን የተቀበልነው ውድ ነገር ነው ። ሁለተኛው፣ ለምነን የከለከለን ፣ ጌታችን ክፉ ስለሆነ ሳይሆን ዓላማ ስላለው ነው ። ሦስተኛ፣ የተሰጠን ከሚሰጠን የሚበልጥ ነው ።
አይዘለቅም እስቲ ተዉኝ ። ብቻ በቸር ዋሉ !
ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሰኔ 25 ቀን 2013 ዓ.ም.