• ባትማርም ዝም በል ፣ ሊቅ ነው ብለው ያከብሩሃል ።
• ባትሰጥም ዝም በል ፣ ቸር ነው ብለው ያወሩልሃል ።
• ባይገድህም ዝም በል ፣ ጸሎተኛ ነው ብለው ያደንቁሃል ።
- ተበሳጭተህ ዝም በል፣ ትዕግሥተኛ ይሉሃል ።
- መንግሥትን ተቃውመህ ዝም በል፣ ሰላማዊ ዜጋ ብለው ይሾሙሃል፣ ይሸልሙሃል ።
- ረግጠውህ ዝም በል፣ ቻይ ነው ፣ መሬት ነው ይሉሃል።
- እያወቅህ ዝም በል፣ የዋህ ነው ይሉሃል ።
- ምግቡ ባይጥምም ዝም በል፣ ጥሩ ባል ነው ብለው ያወሩልሃል።
• ባትራራም ዝም በል ፣ ሁሉ በልቡ ነው ብለው ያዝኑልሃል ።
• ባታለቅስም ዝም በል ፣ ኀዘን አንጀቱ ውስጥ ገብቷል ብለው ይተነትኑልሃል ።
• ባትመርቅም ዝም በል ፣ ኀዳጌ በቀል ነው ብለው ያውጁልሃል ።
• ባይገባህም ዝም በል አስተዋይ ነው ብለው ይቀኙልሃል ።
• ወገንተኛ ሆነህ ዝም በል ፣ ሁሉን ሰብሳቢ ነው ብለው ይማጸኑሃል ።
• ቂመኛ ሆነህ ዝም በል ፣ የይቅርታ ሰው ነው ይሉሃል ።
• አያገባኝም ብለህ ዝም በል ፣ የፍቅር ሰው ነው ብለው ይናገሩልሃል ።
• አገር ይገልበጥ ብለህ ዝም በል ፣ እርሱ ታይቶታል ብለው ነቢይ ያደርጉሃል ።
• ፈርተህ ዝም በል ፣ ያስፈራል ይሉሃል ።
• መልከ ቀና ሆነህ ዝም በል ፣ መልአክ የመሰለ ብለው ከፍ ያደርጉሃል ።
• መልከ ጥፉ ሆነህ ዝም በል ፣ ደርባባ አቡን የመሰለ ብለው ይኩሉሃል ።
• ሰድበውህ ዝም በል ፣ ሊበቀለን ነው ብለው ይሰግዱልሃል ።
• ግራ ገብቶህ ዝም በል ፣ ውስጥ ውስጡን እየሄደ ነው ብለው ይክቡሃል ።
• ተማርረህ ዝም በል ፤ አመስጋኝ ፣ ዳግማዊ ኢዮብ ነው ይሉሃል ።
ዝምታ ለጻድቃን ጥበብ ፣ ለብልጦች መሣሪያ ፣ ለፖለቲከኞች ማስገበሪያ ናት ። የዝምታህን ትርጉም የምታውቀው አንተ ብቻ ነህ ። ሁልጊዜ ዝምታ ፣ ሁልጊዜ ንግግር አይጥምም ።
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
የካቲት 8 ቀን 2015 ዓ.ም.