የምእመን ድምፅ
ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ !
ጌታዬ ሆይ ሰው የዘጋውን አንተ ትከፍታለህ ። አንተ የዘጋኸውንም አንተው ብቻ ትከፍታለህ ። በሰው ችሎታ አትገመገምም ። በኃያላን ጉልበት አትለካም ። ተራራው ለእኛ ተራራ ፣ ላንተ ትቢያ ነው ። የአሕዛብ ቍጥር ለእኛ እልፍ ፣ ላንተ እፍኝ ነው ። ሰማይ ከፍ ያለ ነው ፣ የሰማዩ ሰማይ ግን አንተ ነህ ። ሰማይን ለማየት ቀና እንላለን ፣ የሰማዩን ሰማይ አንተን ለማየት ግን ዝቅ እንላለን ። ለፍጥረታት እንኳ መግለጫ ተስኖን የአሳብ ልኬቶችና ግምቶች እንሰጣለን ። ፈጣሪው አንተ ግን በምንም አትለካም ። ትንኝ ስለ እኔ አድናቆትን ብታሰማ አይገርመኝም ። እታዘባታለሁ እንጂ ደግሜም አላወራውም ። እኔ ደቃቃ ፍጥረትህ ያንተን ደግነት ፣ ዘላለማዊ ውበት መግለጥ እንደምን ይቻለኛል ! አንተ ግን ከብዙ ምሬት ውስጥ የሚወጣውን ምስጋናዬን አብዝተህ ትቀበለዋለህ ። ርግማን ከበዛበት አፌ የሚወጣውን ልመናዬንም በአፈ ቅዱሳን ትቀበለዋለህ ። ስትወደኝ አንድ ቀን እንኳ እንዳልበደለህ ሰው አድርገህ ነው ። አቤቱ ሆይ! ወደ ልዕልናህ ከፍ አድርገኝ ። ከኋላ እንዳልቀር በፍቅርህ ገመድ ሳበኝ ። የጠላቶቼ ግፊት ወዳንተ አቀረበኝ ፣ የራሴ አለመርካት ግን ካንተ እንዳያርቀኝ እባክህ አማኑኤል ሆይ እርዳኝ !
ጻድቅ ዳኛዬ ሆይ !
የጣለው በረዶ መውጫ ሲያሳጣ ፣ ድፍሮ የረገጠውን አንሥቶ ሲጥል ፤ የወረደው ዶፍ ጣራውን ሲነድል ፣ የዘመናትን ሀብት ጠራርጎ ሲወስድ ፣ ከአንተ በቀር በትከሻው የሚያሳፍር ፣ ሞገደኛ ቀንን የሚያሳልፍ ማንም የለም ። አቤቱ እባክህን በመስማትህ የልቤን ድለቃ ፣ በመናገርህ የነፍሴን ንውጽውጽታ አጽና ። የወገን ዕርቃን አደባባይ ሲወጣ ፣ ገፋፊ እንጂ አልባሽ ሲታጣ፤ በነጠላ ላይ ጋቢ ፣ በጋቢ ላይ ካባ ይደርቡ የነበሩት እነዚያ ደጋጎች ናፈቁኝ ። እኔ ነኝ የበደልሁት ብለው የወንድማቸውን በደል የሚሸከሙት ንጹሐን ውል አሉኝ ። የሰውን ድካም እንደ ተሸከምከው ፣ ክርስቶስ በምድር የሚያሰኙህ ቅዱሳንን አብዛልን ። እንደ ጲላጦስ እጁን ታጥቦ ከሚገድል ሸንጋይ አድነን ። ሲታይ የሚያምረው ቁመናችን ፣ አንተ ስታየው ተበልቶ ካለቀ በእውነት ከንቱ ነን ። ተሸፋፍኖ ከመቃጠል ፣ ተከናንቦ ከመጥፋት አድነን ። አገርም እንደ ሰው ይታመማልና ምድራችንን ፈውስ !
ክርስቶስ መለሰ፡-
ልጄ ሆይ !
ሰውን ወደ እኔ የሚያቀርብ ጠፍቶ የሚያርቅ በበዛበት ዘመን ፣ ያላመነውን ከማሳመን ያመነውን ለማስካድ የሚተጉ በፋነኑበት ወራት አንተ ግን የልቤን ፈለግ ተከተል ። ጥያቄዎችህን አታምልካቸው ፣ መልሶችህን አመስግንባቸው ። እግዚአብሔር በምድር ተገልጦአል ፣ ይኸውም ሰው ሆኜ አንተን መምሰሌ ነው ። ገነት በምድር ግን አትገለጥም ። እውነትን ለመቀበል ልብህን ጨካኝ አድርግ ። በመቀበል ከግማሽ በላይ እፎይታ ታገኛለህ ። ዳዊት በበገና ጭንቀትን ያክም ነበረ ። አንተም ማዜምና የዜማ ዕቃ መጫወትን ስትወድ ከስቃይ ስሜት ትወጣለህ ። የራቀውን አቅርቤ እሰጥሃለሁ እንጂ ላንተ ፍላጎት የምፈጥረው አዲስ ነገር የለም ። መልስህ ሩቅ አይደለም ።
ልጄ ሆይ !
እኔ ስላንተ ታምቻለሁ ። የቀራጭና የኀጥእ ወዳጅ ተብያለሁ ። አንተም ስለ እኔ መታማትን አትፍራ ። ስምህን ሲያጠፉህ ደስ ይበልህ ። በምድር ስምህ ካልጠፋ በሰማይ አይጻፍም ። ሁለት መታወቂያ የያዘ ወንጀለኛ እንደሆነ እወቅ ። ሰውን ባየህ ጊዜ ከእኔ ደም ጋር አብረህ እየው ። ያን ጊዜ ከድካሙ ይልቅ ፍቅርን ትሰጠዋለህ ። የማይቻሉ ነገሮች የሚቻሉት ፣ የሚቻሉ ነገሮች ሲሠሩ ነውና የምትችለውን ዛሬ ከውን ። ሥራህን ሁሉ ስትሠራ ጌታዬን ያስደስተዋል ወይ ? ብለህ ሥራ ። ያን ጊዜ የእኔ ደስታ ኃይልህ ይሆናል ። ትልቅ ለመሆን አትጣር ፣ ትልቅ ሁነህ እንደ ተፈጠርህ እመን ። አንተ የውበት መደምደሚያዬ ፣ የፍጥረት ጉልላቴ ነህ ። በምሠራበት ቀን አስብሃለሁ ። በበረከት ዋል ። የምወድህ ክርስቶስ ወልደ እግዚአብሔር ።
ሰማያዊ ወግ / 7
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
የካቲት 13 ቀን 2015 ዓ.ም.