የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የነቢያት ጉባዔ ክፍል 3

ነቢዩ ሙሴ ሲናገር የቍጣ መልክ ያየሁበት መሰለኝ ። ቍጠኛ የሚመስሉ ሰዎች ብዙ ጊዜ የዋህ ናቸው ። የሚናገሩትም በልባቸው ምንም ላለማስቀረት ነው ። ስሜታቸውን በቀላሉ ማግኘት ይቻላል ። ውስጣቸው የዋህ ነው ፣ ፍቅር ብቻ ያሸንፋቸዋል ። ለወደዱት ሟች ናቸው ። በሽንገላም ማንንም አያታልሉም ፣ የሰው ዕድሜም አይበሉም ። ሰው ግን እየተቆጣ ከሚያቀናው ሰው ይልቅ እየሸነገለ ገደል የሚከተውን ይወዳል ። እየገሠጸ ከሚያበላው ሰው ይልቅ ማሬ ፣ ሆዴ እያለ ጦም የሚያሳድረውን ይፈቅዳል ። እውነተኞች ኮስታራ ይመስላሉ ፣ ቁምነገርን ግን እንደ ልብስ ለብሰውታል ። ደልለው አዳሪዎች ግን በለስላሳ ምላሳቸው ይዳስሳሉ ፣ ልባቸው ግን ከዓለት የጠነከረ ነው ። ለመቅረብ ይሞክራሉ ፣ ውስጣቸው ግን የመንፈቅ መንገድ ያህል ሩቅ ነው ። ፊታቸውን ብሩህ ያደርጋሉ ፣ ልባቸውን ግን ያጠቁራሉ ። ጥርሳቸውን አጽድተው ብልጭ ያደርጋሉ ፣ ውስጣቸው ግን ከሲኦል ጨለማ ይልቅ የጠቆረ ነው ። የማያደርጉትን “እሽ” ብለው ሰውን እንደ ዶሮ ያባርራሉ ፣ እሺታቸው ግን ከእንቢታ የጠነከረ ነው ። “በጊዜው የሆነ እንቢታ ፣ የእሺታ ያህል ነው” እንዲሉ ።

እግዚአብሔር ቀናተኞችን ፣ ትኩሶችን ፣ ተቆርቋሪዎችን ፣ ግልጾችን ይወዳል ። ከመንፈሰ ቀዝቃዞች ጋር ፣ ከተወዛዋዥ ሬሳዎች ጋር ኅብረት የለውም ። አንድም ቅዱስ ቸልተኛና ዳተኛ አይደለም ። ቅዱሳን ሁሉ ትኩስ ናቸው ። ሊቀ ነቢያት ሙሴ ለእግዚአብሔር አምልኮ ፣ ለወገን ነጻነት የሚቀና ነበር ። ቀናተኞች ቅንዓታቸው ደፋር ያደርጋቸዋል ፣ እነርሱ በሕይወት ሳሉ ፈሪዎች ይሞታሉ ። እውነተኛ ደፋሮች የሚነካቸው የለም ። ነቢዩ ኤልያስ ለእግዚአብሔር አምልኮ ቀንቶ ፣ እንዴት በገዛ በረከቱ ይካዳል ? ብሎ ሰማይን በሰማርያ ላይ የገዘተ ፣ ምድርን ፍሬ አትስጪ ብሎ ያዘዘ ነው ። እግዚአብሔር ስለ ስሙ ሲቀኑ ከአሳባቸው ጋር ይተባበራል ። ዮሐንስ መጥምቅ የሚገሥጽ መምህር ፣ መልክ አይቶ የማያደላ መምህር ወመገሥጽ ነበር ። ቅዱስ ጴጥሮስ ስሜቱ ቶሎ የሚነካ ፣ ዛሬ ካልሆነ ብሎ ለበጎ ነገር የሚሽቀዳደም ነው ። ቦአኔርጌስ የነጎድጓድ ልጆች ወልደ ነጎድጓድ የተባሉት ዮሐንስና ያዕቆብ ትኩስ ነበሩ ። /ዘጸ. 32፡19፤ 1ነገሥ. 17፡1፤ ማቴ. 3፡7 ፤ ማር. 3፡17 ፤ ገላ. 2፡11/

ዛሬ “በጌታ ፍቅር እወድሃለሁ” የሚሉ በዘመድ ፍቅር እንኳ መውደድ ያቃታቸው ፣ ልባቸውና አፋቸው የተለያየባቸው ፣ ነቢያትና ሐዋርያት ያልወለዱአቸው ፣ ዘመኑን እንጂ ክርስቶስ መምሰል የማይሹ ናቸው ።

ባለቤቱ ራሱ፡- “ያዕቆብንም ወደድሁ ፥ ዔሳውንም ጠላሁ” ብሏል ። ሚልክ. 1 ፡ 2 ። እግዚአብሔር ግልጽ ነው ። ሦስተኛ ነገር የለውም ። ሲወድዱና ሲያዝኑ ግልጽ ማድረግ የመንፈሳዊ ሰው ጠባይ ነው ። አማኝ እንደሚያምነው እግዚአብሔር ነው ። አሁንም ባለቤቱ እንዲህ ይላል፡- ሦስተኛ ማንነትን ይጠላል ። “በራድ ወይም ትኩስ እንዳይደለህ ሥራህን አውቃለሁ ። በራድ ወይም ትኩስ ብትሆንስ መልካም በሆነ ነበር ። እንዲሁ ለብ ስላልህ በራድም ወይም ትኩስ ስላልሆንህ ከአፌ ልተፋህ ነው።” ራእ. 3 ፡ 15-16 ። የሚተፋው ለበራድነቱ ወይም ለሙቅነቱ ሳይሆን ለለብታው ነው ። ለብታነት ሚና የለሽነት ፣ አዎ አይደለም የማይል የሚንቀዋለል ማንነት ነው ። ሦስተኛ ሰፈር በሕይወት ውስጥ ሊኖር አይችልም ። የለብታ መንደር የለም ። እግዚአብሔር ሲወድድ አያፍርም ፤ ሲያዝንም አያንቀራብጥም ። ልጆቹም እርሱን ይመስላሉ ። ሽንገላን መጸየፍ የዲያብሎስን ራስ መርገጥ ነው ።

በአሳብ ብዙ ሄድሁ ። ወደ መጣሁበት ምድር ተመልሼ ኑሮአችንን ቃኘሁ ። ራሴን መክሬ ወደ ነቢዩ ሙሴ መልእክት ጆሮዎቼን አነቃሁ ።
ይቀጥላል

የነቢያት ጉባዔ/3

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

መጋቢት 28 ቀን 2015 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ