የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ሰላም ለኪ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን

ደጆችሽ ለምሕረት የተከፈቱ ፣ ሕሙማነ ሥጋ ወነፍስ የሚታከሙብሽ ፣ ለአማንያንና ለዐላውያን የምትማልጂ ፣ የተፈጥሮ ወዳጅ ፣ ወቅታት ሲፈራረቁ የምስጋና ርእስሽ የምታደርጊ ፤ ለዝናባት ፣ ለወንዞች የምትለምኚ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሆይ ሰላም ለኪ !

ክርስቶስ በደሙ የገዛሽ ፣ ዐፅመ ሰማዕታት አጥር የሆነሽ ፣ በመስቀል ምጥ ተወልደሽ ፣ በመስቀል ጎዳና የምትሄጂ ፣ የተጠራሽ ፣ የተመረጥሽ አቅሌስያ ሆይ ሰላም እልሻለሁ ። በበረሃው ዓለም ላይ ጥላ ፣ ጭው ባለው ምድረ በዳ የምስጋና ድምፅ ያለሽ ፣ ሥሉስ ቅዱስን የምትቀድሺ ፣ ሥጋ ወልደ እግዚአብሔርን የምትመግቢ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሆይ ሰላም እልሻለሁ ። በመስቀል ተወልድሽ ፣ በመስቀል አድገሽ ፣ በመስቀል የምትፈጽሚ ፣ ያለ አገርሽ ያለሽ አገር ሆይ ሰላም እልሻለሁ ። ድንበር የሌለሽ ፣ መስፈርትሽ እምነት ብቻ የሆነ ፣ ቤተ ፍርድ ሳይሆን ቤተ ምሕረት የሆንሽ ፣ የኃጢአት መቃብር ፣ የምሥጢር ዋሻ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሆይ በዓልሽ ነውና ሰላም እልሻለሁ ።

ተመራማሪዎች ሳይሆኑ አማኞች የሚገናኙብሽ ፣ “ለምንና እንዴት” የሚል ጥያቄ የታገሠላቸው የሚዘምሩብሽ ማኅደረ መለኮት ሆይ ሰላም እልሻለሁ ። ድሆች የሚጽናኑብሽ ፣ ምስኪኖች እንጀራ የሚጠግቡብሽ ፣ አካላቸውን ያጡ ሊቅ የሚሆኑብሽ አምሳለ ኢየሩሳሌም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሆይ ሰላም እልሻለሁ ።

ፍጹምነትን ግብ ፣ የክርስቶስን መልክ የውበት ዳርቻ አድርገው ፣ ምእመናን በመንፈስ ቅዱስ የሚኳሉብሽ የሚዋቡብሽ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሆይ ሰላምታ ይገባሻል ። “ይባላል ፣ ሊሆን ይችላል” የሚሉ የጥርጥር ንግግሮች የማይሰሙብሽ ፣ ቃለ አሚን ፣ ቃለ ክርስቶስ የሚነገርብሽ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሆይ ሰላምታ ይገባሻል ። መፈቀርና መፈራት ፣ መወደድና መከበር ገንዘቡ የሆነ የመድኃኔ ዓለም ሙሽራይት ሆይ እያፈቀርን የምንፈራሽ ፣ እየወደድን የምናከብርሽ አዲስ ዓለም ሆይ ሰላምታ ይገባሻል ። እሳቱ ዓለም ሲፈጀን የምንቀዘቅዝብሽ ፣ ወደ ባሕሩ ዓለም ለመግባትም አየር የምንስብብሽ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሆይ ሰላምታ ይገባሻል ።

ሙሴ በናባው ተራራ ላይ ምድራዊት ኢየሩሳሌምን በርቀት አይቶ ተሳለመ ፣ ሰማያዊት ኢየሩሳሌምን የምናይብሽ ፣ የፀሐዩ ክርስቶስ ልጅ ፣ የጨለማ መብራት ጨረቃ ቤተ ክርስቲያን ሆይ ሰላምታ ይገባሻል ። አንቺ አካለ ክርስቶስ ፣ አንቺ የነፍሶች መዋቅር ፣ አንቺ የሕያዋን ስብስብ ፣ አንቺ ጉባዔ ሥላሴ ፣ አንቺ ክርስቶስ በምድር ሰላምታ ይገባሻል ። ፅውዕት ኅሪት የሆንሽው በምድር ያለሽ ሰማይ ፣ በጦርነት ዘመን ቅዳሴ ያለሽ መቅደስ ፣ ግንቦችን አፍርሰሽ ድልድይ የሆንሽ ፣ ከነገድ ከቋንቋ የተዋጀሽ ፣ ሁሉ የእኔ የሚልሽ ፣ የሁሉ የሆንሽ ፣ የልብ ስፋት የተሰጠሸ ፣ የክርስቶስ ብርሃን የሚታይብሽ የእኛ ታቦር ፣ የአማንያን ጉባዔ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሆይ ሰላምታ ይገባሻል ። መስቀል ጌጥሽ ፣ መስቀል መታወቂያሽ ፣ መስቀል ስብከትሽ ፣ መስቀል ሸክምሽ የሆነ ፣ የገደሉ ዘመን ከለላ ፣ የጨለማ ዓለም ፋና ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሆይ ሰላምታ ይገባሻል ።

በአንድ አካልነትሽ አንዱ እረኛ ፣ አንዱ መንጋ ፤ በአንድ ሕንፃነትሽ አንዱ ሠራተኛ አንዱ ጡብ የሆኑብሽ ፤ ሁሉም ልጆችሽ በግ ፣ ሁሉም የሚከወኑ/የሚሠሩ ቤቶች የተባሉብሽ ፣ ቤተ ፍጹማን ሳይሆን ቤተ ሕሙማን ቤተ ክርስቲያን ሆይ ሰላምታ ይገባሻል ። ባንቺ መወለድ ብዙዎች ተወልደዋል ። በተወለዱ ቀን ቋንቋ የሚያውቁ ልጆች በዓለም ላይ የሉም ። በተወለድሽ ቀን ሰባ ሁለት ቋንቋ የተናገርሽ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሆይ ሰላምታ ይገባሻል ። ከኢየሩሳሌም እስከ ሰማርያ ፣ ከሰማርያ እስከ አንጾኪያ ፣ ከአንጾኪያ እስከ ምድር ዳርቻ ምስክር የሆንሽ አፈ ክርስቶስ ፣ የምእመናን አንድነት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሆይ ሰላምታ ይገባሻል ። ሙሽራው ሊመጣ ነውና ተዘጋጂ ። ሙሽራው ወደ ቤቱ ሊወስድሽ ፣ ቀጠሮው ተሰብሮ የእርሱ ልትሆኚ ነውና እንኳን ደስ ያለሽ ! በዘላለም ርስቱ ሊያሳርፍሽ በደጅ ቀርቦአል ፣ የሙሽራው ዜማ ተሰምቷልና እልል በይ ! አንቺው ዜማ አውራጅ ፣ አንቺው እልል ባይ ሆይ ፣ በሚጠላሽ ዓለም ላይ የሚወድሽ ክርስቶስ አለና ደስ ይበልሽ ! በፊልጶስ ቂሣርያ ክርስቶስ ወልደ ዋሕድ – አንድ ልጅ መሆኑ በተመሰከረበት ቃለ አሚን ላይ ተመሥርተሻልና ወጀብ ማዕበሉን አይተሸ ሰምተሸ እንዳትፈሪ ። በዓልሽ በዓሌ ነውና ሰላም እልሻለሁ !

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ተጻፈ ሰኔ 21 ቀን 2015 ዓ.ም

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ