የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ቅድስት ሆይ !

ባንቺ ላይ የተከናወነው የሰው እጅ የለበትም ። ድንግል መሬት ታብቅል ብሎ ዕለተ ሠሉስን የባረከ ፣ በትረ አሮን በተአምራት እንድታፈራ አድርጎ ሊቀ ካህኑን ያከበረ ፣ አንቺም እንበለ ዘርዐ ብእሲ ትወልጂ ዘንድ ፈቀደ ። ባንቺ ላይ በተከናወነው የሰው እጅ የለበትም ።

ቅድስት ሆይ !

ጃንደረቦች ደረቅ ዛፍ ነኝ እንዳይሉ ፣ አንቺ በባሕርያዊ መብት ልጄ የምትይውን እነርሱ በጸጋ ልጄ እንዲሉት ድንግል ሳለሽ ወለድሽ ። ባሕረ ኤርትራ ከመከፈሉ ፣ መና ከመዝነቡ በላይ ማኅተመ ድንግልናሽ ሳይገሰስ አምላክን መውለድሽ ፣ ኅብስተ ሕይወት ክርስቶስ ካንቺ ቤተ ልሔምነት መውጣቱ ትልቅ ተአምር ነው ።

ቅድስት ሆይ !

የአምላክ እናት በመሆንሽ ጠላት በዛብሽ እንጂ አልቀረልሽም ። ስትፀንሺ አመክንዮ ፈላጊ ረበናትን ትሳቀቂ ነበር ። ስትወልጂ ሄሮድስ ልጅሽን እንዳይገድለው ትሸሺ ነበር ። ልጅሽ በሮማውያንና በአይሁዳውያን ሲጠላ ታዝኚ ነበር ። ኀዘንሽ የእናትነት ብቻ ሳይሆን የአማኝነትም ነበር ። ፍጡር በፈጣሪው ላይ ባደረሰው በደል ትሰቀቂ ነበር ። ሁሉ እያለው ሁሉ እንደሌለው በሆነው ልጅሽ የሰዎችን የግፍ ጦር ባሰብሽ ጊዜ ፣ በነፍስሽ ሰይፍ ያልፍ ነበር ። የልጅሽ ጠላቶች ያንቺም ጠላቶች ነበሩ ። ስደቱ ስደትሽ ነው ። ሰማዕት ዘእንበለ ደም ሁነሽ እሞሙ ለሰማዕታት ተብለሻል ። ደናግል ተስፋ እንዳይቆርጡ ፣ ደረቅ ዛፍ ነኝ እንዳይሉ በድንግልና ወልደሽ ምክሐ ደናግል ሁነሻል ።

ቅድስት ሆይ !

ሴቶች ሁሉ ከወለዱ በኋላ ድንግል አይባሉም ። ድንግል ሁነው ያለ ዓላማ ቢቀሩ ተፈላጊነት ያጡ ተብለው ይዋረዳሉ ። ወልደሽ ድንግል የተባልሽ ፣ ዘላለማዊት ድንግል ተብሎ መጠራት ክብርሽ የሆነ አንቺ ብቻ ነሽ ። እንዴት ምንጩ ሳይከፈት ውኃው ይፈስሳል ! ማየ ሕይወት ክርስቶስ ከኅቱም ድንግል ፈልቋል ። ብዙ ልጆች እንዳሉሽ ትላንት አይሁድ ፣ ዛሬ ስሑታን አንቺን ለማሳነስ ይናገሩታል ። አዎ ያንቺ ልጆች አይቆጠሩም ፤ በልጅሽ ያመኑ ሁሉ ልጆችሽ ናቸው ።

ቅድስት ሆይ !

በሔዋን ያዘኑ ባንቺ ካልተደሰቱ ይገርማል ። በሥጋ ድንግል በመሆንሽ በዚህ ብቻ አልተደነቅንም ። በኅሊናም ድንግል ነሽ ። ድንግል በክልኤ/በሁለት ወገን ድንግል ነሽና ለቅዱሱ ቅድስቲቱ አስፈልገሽዋል ። ሊቀ ካህናቱ ብቻ በዓመት አንድ ጊዜ የሚገባባት ያቺ ኅቱም መቅደስ ፣ ቅድስተ ቅዱሳን ትባላለች ። ሊቀ ካህናት ክርስቶስ ብቻ ያደረበት ያንቺ ማኅፀን ከዚያች መቅደስ ይበልጣል ። ከሊቀ ካህኑ ሌላ በዚያች መቅደስ የሚገባ ሰው በሞት ይቀጣል ። እሳተ መለኮት በተቀመጠበት ባንቺ ማኅፀንም ፍጡር ይቀመጥ ዘንድ አይቻለውም ። መጠን የሌለው ክብር ሳለሽ መጠን የሌለው መከራ ተቀበልሽ ። ክብሩ ባየለ ቍጥር መከራውም ብዙ ይሆናል ። ሁሉ ያንቺ ይሆን ሁሉን አጣሽ ። ልጅሽ ብቻ ሀብት እንዲሆንሽ “እፎ ቤተ ነዳይ ኀደረ ከመ ምስኪን” ተባለልሽ ።

ቅድስት ሆይ !

የቀረበው የሰው ልጅ በአዳም በደል ራቀ ፣ ቀርቦ ወደ እርሱ ቢያቀርበው ሰው አሁንም ጌትነቱን ካደ ። የልጅሽን ጌትነት የማያምኑ ፣ በመስቀሉ ሥራ የማይታመኑ ሁሉ ያንቺ ወዳጆች አይደሉም ። አንቺን ለመምረጥ በተነሣ ጊዜ ማንንም አላማከረም ። በምክረ ሥላሴ ወላዲተ አምላክ ሁነሻል ። የልጅሽን አምላክነት የሚያምኑ አንቺን ወላዲተ አምላክ ለማለት አይሰቀቁም ። ባለ ሁለት ልደት የሆነው ልጅሽ ፣ ድንግልም እናትም በሆንሽው ባንቺ ገነነ ። የሴት ዓለም ክብር ብቻ ሳይሆን የሰው ልጆች ክብረት መገለጫ ነሽ ።

ቅድስት ሆይ !

ሰፊው ዓለም የጠበባቸው ፣ ነግቶ ምሽት የሚመስላቸው ፣ በነፍስ ማዕበል የሚንገላቱ በልጅሽ ሰላም ይረፉ ። ቅድስት ሆይ ለምኚልን !

አንቺን የወደደ እግዚአብሔር አብ ቡሩክ ነው !
ካንቺ ሰው የሆነ እግዚአብሔር ወልድ ቡሩክ ነው !
ያጸናሽ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስም ቡሩክ ነው ። ለዘላለሙ አሜን ።

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ነሐሴ 5 ቀን 2014 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ