የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ሥራህን ፈጽም

መስከረም 1

“በዓመታት መካከል ሥራህን ፈጽም ፤ በዓመታት መካከል ትታወቅ” ዕንባ. 3፡2።

ዕንባቆም በጥያቄ ጀምሮ በመልስ የፈጸመ ነቢይ ነው ። ግፍ በከተማው ፣ ደም በሰው እጅ ላይ ሞልቶ በፈሰሰ ጊዜ ፣ ይህ ዓለም ለራሱ የተተወ መስሎት ግራ ተጋብቶ ነበር ። ፍትሐዊነትን በሰው ነፍስ ያስቀመጠ እግዚአብሔር ፍትሕን አዘገየ ብሎ አዝኖ ነበር ። ዕንባቆም ጥያቄን ለማይፈራው እግዚአብሔር ጥያቄን አቀረበ ። እግዚአብሔርም ጥያቄን አይቀየምምና በፍቅር መለሰለት ። ለጆሮው ሳይሆን ለልቡ ተናገረው ። ዕንባቆምም በጸሎት እንደ ሞገተ ፣ በምስጋና ጌታውን አከበረ ። ያነሣቸው ችግሮች ስለተወገዱ ሳይሆን ችግሮቹ እያሉ በእግዚአብሔር ተደሰተ ። እግዚአብሔር ችግሩን ትቶ ዕንባቆምን በመለወጥ ሥራ ጀመረ ። ጌታችን ከወጀቡ በፊት የሐዋርያትን ጥርጣሬ ገሠጸ። ከውጭው ማዕበል የውስጥ ማዕበል ይበረታልና ። ማቴ. 8፡26 ።

ዕንባቆም የጸለየው ጸሎት ድንቅ ትርጓሜ ይዟል ። እግዚአብሔር በትውልድ ላይ ሥራ አለው ። ዓመታትም ሥራ መሥሪያ መክሊት ናቸው ። ሁሉም ሰው ሥራውን የሚሠራው በራሱ ዘመን ነው ። አሠሪ ፣ ሥራ ፣ መሥሪያ ፣ ሠሪ አሉ ። አሠሪው እግዚአብሔር ፣ ሥራው ነፍስ ማዳን ፣ መሥሪያው ጊዜ ፣ ሠሪው ያመነ ሰው ነው ።

እግዚአብሔር ሥራውን ከጅምር እስከ ፍጻሜ ይመራል ። በአባቶች ዘመን የጀመረውን በልጆች ይፈጽማል ። በእኛ የተጀመረም በልጆቻችን ይቀጥላል ። እግዚአብሔር በትውልድ ላይ ሥራ እንዳለው መታወቅ አለበት ። ምድር ሁሉ እግዚአብሔርን በማወቅ ስትሞላ በእኔ ላይ ሥራ አለው ብሎ ትውልድ ባለ ራእይ ይሆናል ። የምንኖረው ታሪክ ለመተረክ ሳይሆን ታሪክን ለመድገም ነው ። እግዚአብሔር በዓመታት ሕያው ነው ። ግፍን ሲዳኝ ጊዜ አያልፍበትም ፣ የወደቀውን ሲያነሣ አይሳነውም።

ከፊት ለፊታችን እግዚአብሔር የሚሠራባቸው 365 ቀናት ተቀምጠዋል ። ኑሮአችን የመለኮት ግብር የሚገለጥበት አደባባይ እንዲሆን ንስሐ መግባት ፣ በቅዱስ ሥጋውና በክቡር ደሙ መታተም ይገባል ። “ሠርተህ ሥራብኝ” ብሎ መጸለይ ያሻል ። ሁሉም ልክ አለው ። እግዚአብሔር ሥራውን ሲሠራ ግፈኛ አይንጎማለልም ። ፍርድን ከእርሱ መጠየቅ መንግሥቱን ማክበር ነው ፣ ፈራጅ መሆን ግን እግዚአብሔርን ዙፋን አልባ ማድረግ ነው ። ዓመቱን እንደ ተከፈተ ደጃፍ አድርጎ ይስጠን ።

ጸሎት

ጌታ ሆይ አባቶቻችን ያልሠሩትን እኛም ለነገ አስቀምጠን የምንቀባበለውን ዕዳ እባክህ ሥራህን ሠርተህ ፈጽምልን ። የትላንት እስረኞች ፣ የነገ ባለዕዳዎች ከመሆን አድነን ። አንተ የምትመሰገንበትን ሥራ በዕድሜአችን ፈጽም ። ባንተ ስም ራሳችንን ከማገልገል ሰውረን ። ፍርድ እንዳለ አስበን መቀደስ ይሁንልን ። ባለ ዝና በሆነው ስምህ ለዘላለሙ አሜን !

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መስከረም 1 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ