የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ዐርፍ ዘንድ ተወኝ (4)

“ወደማልመለስበት ሳልሄድ ዐርፍ ዘንድ ተወኝ ።” (መዝ. 38፡13) ።

የቅዱስ ዳዊት ትግሎች ብዙ ነበሩ ።

3- ማንም ያልተረዳው ሰው ነበረ

ነቢዩ ዳዊት ያለበትን ሁኔታ ተቀብሎ የሚኖር ሰው ነበረ ። ቤተሰቡ አራዊት ካሉበት ዱር ፣ በጎች ይጠብቅ ብሎ ሲሰደው የመጨረሻ ልጅ ቢሆንም የተጨከነበት ነበረ ። ዳዊት ግን ወደ ዱር ሲገባ በገናውን ይዞ የገባ ነበር ። ሰዎች ደስታውን ይቀሙት ዘንድ አይፈቅድላቸውም ነበር ። ተጽናንቶ ያጽናና ፣ ለመጽናናትም ያጽናና ሰው ነበር ። በሕይወት ውስጥ ተጽናንቶ ማጽናናት ፣ ለመጽናናትም ማጽናናት መልካም ነው ። ታመን ከሆነ ስለ ታመሙት መጸለይ ፣ የታመሙትን ማገዝ የእኛን በሽታ እያቀለለው ይመጣል ። የራስን ችግር በአጉሊ መነጽር ማየት “የእኔ ነገር” እያሉ ማዜም አንዳች ጥቅም የለውም ። ዳዊት በመጣው ነገር ሁሉ ይደሰት ነበር ። ጉዳዩ የሚያስደስት ሆኖ ሳይሆን ማንም የማይቀማው ደስታ እግዚአብሔር ስለሆነለት ነው ። ስለዚህም ሊጎዱት የፈለጉት ገና ነው እያሉ ሌላ ሸክም ይጭኑበት ነበር ። እያለቀሰ ሲስቅ ፣ እያመመው ደኅና ነው ሲል ቢደላው ነው እያሉ አዳዲስ መስቀል ያሸክሙት ነበር ። ራሱን ሳቅን ካልተወዳጁ በቀር በዓለም ላይ የሚያስቅ ነገር የለም ።

አንዳንድ ሰዎች ሁሉን ለእግዚአብሔር ሰጥተው ይደሰታሉ ። የእስራታቸውን ሰንሰለት እንደ ወርቅ ጌጥ ፣ መስቀላቸውንም እንደ ማዕረግ ይቆጥሩታል ። ሊያሳዝኑን ለመጡ ሰዎችና ሁኔታዎች አለማዘን ትልቅነት ነው ። ተጎድተን ካልጠበቅነው በቀር ማንም ሊጎዳን አይችልም !!!

ዳዊት የወንድሞቹን ደኅንነት ለማወቅ ወደ ጦር ሜዳ ነፍሱን ሸጦ ሲመጣ ፣ የእስራኤል የውርደት ዘመኑ እንዲያጥር ራሱን ለማሰለፍ ሲዳዳ ወንድሞቹ ፍቅሩን እርባና ቢስነት ፣ እምነቱን ትዕቢት ብለው ይተረጕሙት ነበር ። በጦር ሜዳ መሐል ያገኘው ታላቅ ወንድሙ ኤልያብ፡- “እኔ ኵራትህንና የልብህን ክፋት አውቃለሁና ሰልፉን ለማየት መጥተሃል አለው።” (1ሳሙ. 17፡28) ። ዳዊት ግን የመጣው የአባቱን ልብ ለማሳረፍ ፣ የወንድሞቹን ጤንነት ለማወቅ ነው ። ዳዊት ከቤት ወደ ዱር ሲልኩት ፣ የአንበሳና የድብ ጓደኛ ሲያደርጉት ትንሽ ነው አላሉትም ፣ ለአገሩ ሲያስብ ግን ትንሽነቱ ታያቸው ። ዳዊት እምነቱ እንደ ትዕቢት ፣ ፍቅሩ እንደ አስብቶ አራጅ የሚታይበት ፣ ስንዴ ዘርቶ እንክርዳድ ያጨደ ሰው ነበር ። ወንድሙ ልበ ክፉ ይለዋል ፣ እግዚአብሔር ግን እንደ ልቤ የሆነ ይለዋል ። በምድር ላይ የሚያስደስተው ሰዎች የሚሉንን እግዚአብሔር የማይለን መሆኑ ነው ።

ዳዊት ጎልያድን በጠጠር ባሸነፈ ጊዜ ሳኦል ሺህ ገዳይ ፣ ዳዊት እልፍ ገዳይ በማለት ሴቶች ዘፈኑ ። ሴቶቹም ሕዝቡም ዘፍነው ገቡ ። የተዘፈነለት ሰው ግን በሳኦል ተመረዘ ። ሳኦልም ከጎልያድ በላይ ዳዊትን ጠላው ። (1ሳሙ. 18 ፡ 7)። ዳዊት የዜማው ደራሲ ፣ የግጥም ገጣሚ አልነበረም ። ሕዝብን ማፈን አይቻልም ። በሰዎች ስሜትም እርሱ አይለካም ። ሳኦል የቀረው ዙፋኔ ነው ብሎ በቅንዓት ተነሣበት ፣ የንጉሥ ቅንዓት እሳት ይተፋልና ዳዊት በሞትና በእርሱ መካከል አንድ እርምጃ እስኪቀር ድረስ ብዙ ጊዜ ተሰቃየ ። ስደት ኑሮው ሆነ ። በደስታ በግ ሲጠብቅና በስደት ዱር ሲገባ ልዩነት አለው ። ነጻ ድሀ የነበረው ፣ አሁን ነጻነት የሌለው ድሀ ሆነ ። ኑሮው ያው ነው ፣ መከራው ግን ያው አልነበረም ። ዳዊት ሥልጣን ፈላጊ አልነበረም ። በእግዚአብሔር ተቀብቶ ነበረ ፣ ግን አሁንም ባሪያ ነኝ ብሎ የሚያስብ ነበረ ። ዳዊት ሰዎች ያልተረዱት ሰው ነበረ ።

የሳኦል ልጅ ዮናታን ዳዊትን እጅግ ወደደው ። ነፍስ የሚሰጣጡ ባልጀሮች ሆኑ ። አባት ያሳድደዋል ፣ ልጅ ይደብቀዋል ። እንኳን ከአንድ አገር ፣ ከአንድ ቤትም ክፉና ደግ አለ ። ልጅ በአባቱ አይለካም ። “የመጥረቢያ ልጅ መዘለፊያ” እንላለን ። አባት ሌላ ፣ ልጅ ሌላ ነው ። ሳኦል ልጄንም ዳዊት ቀማኝ ብሎ እንደገና ተነሣበት ። ፍቅር ከሥልጣን በላይ ነውና አልጋ ወራሽ የነበረው ዮናታን ወንበሩ ያንተ ነው እያለ ያበረታታው ነበር ። ፍቅር ለሚወደው ዙፋን ይለቅቃል ።

ዳዊት የገዛ ልጆቹ አልተረዱትም ነበር ። አንዱ ልጅ አሞኛል እኅቴ ታስታመኝ ይለዋል ። በአባት ፈቃድ የመጣችውን ልጅ አምኖን ይደፍራታል ፣ አባቱንም ያሸማቅቃል (2ሳሙ. 13.)። አቤሴሎም አባትና ልጅ እኅቴን አዋረዱ በማለት አምኖንን ይገድላል ። የአባቴን ልብ ሰበርኩት ብሎ አንጀቱ ቅቤ ይጠጣል ። ዳዊት ለማልቀስም ለመፍረድም እስኪቸገር ስሜት አልባ አደረጉት ። ነቢዩ ዳዊት ከልቡ ያምናል ፣ የሚታመንለት አላገኘም ። ከእረኝነት እስከ ንጉሥነት ዘመን የልቡን የሚረዳለት አጣ ። ስለዚህ አፍ እያለው ዱዳ ቢሆን “ዐርፍ ዘንድ ተወኝ” አለ ። ሥልጣን እያለሁ ተጠቃ ። የጎዱት ልጆቹና ወዳጆቹ ነበሩና ሥልጣን ወዳጅና ልጅን ለመቅጣት አይረዳም ። እጅ እያለው ሽባ ነበረ ። ስለዚህ “ዐርፍ ዘንድ ተወኝ” ብሎ ጸለየ ።

እናንተስ ሰው የማይረዳችሁ ሆናችሁ ይሆናል ። ስለምትዘምሩ የምትከፉ አይመስላቸው ፣ ችግራችሁን ስለማታወሩ እንዳልተቸገራችሁ ታስባችሁ ይሆናል ። ሕመማችሁን መቻላችሁ እንዳልታመመ ሰው ፣ ንጹሕ መልበሳችሁ እንዳልተጎዳ ሰው ተገምቶባችሁ ይሆናል ። ሊገባቸው በማይፈልጉ ፣ ስለ እናንተ ትክክለኛውን ሐቅ መረዳት በማይቻላቸው ሰዎች ፣ ለእናንተ በጎ ሊደረግ ሲል “ምን ጎደለባቸው ?” እያሉ በሚያከላክሉ ወገኖች ግራ ተጋብታችሁ ይሆናል ። በዚህ ሁሉ ግራ መጋባት ውስጥ የልብ አውቃ መድኃኔ ዓለም ከእናንተ ጋር መሆኑን እናበስራለን ። ከነቢዩ ዳዊት ጋር “ዐርፍ ዘንድ ተወኝ” ብላችሁ መጸለይ ትችላላችሁ ። እንደ ሰውነታችሁ ጸልዩ ፣ እንደ አምላክነቱ ይመልስላችኋል ።
ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥቅምት 10 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ