የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

መጠጊያችን

“አምላካችን መጠጊያችንና ኃይላችን ፥ ባገኘን በታላቅ መከራም ረዳታችን ነው።” (መዝ. 45፡1።)

ዓለም ከመቼውም ጊዜ ይልቅ የኃይል ጥገኛ ሆናለች ። ትልልቅ ማሽኖችን ፣ ግዙፍ ፋብሪካዎችን ለማንቀሳቀስ ኃይል አስፈላጊ ሆኗል ። ብዙ አምራች ድርጅቶች በኃይል አቅርቦት እጥረት ምክንያት ሥራ ያቆማሉ ፣ ሠራተኛ ይበትናሉ ። ደኖች በመመናመናቸው ፣ ቢኖሩም የሰውን የኃይል ፍላጎት ለማሟላት በቂ ባለመሆናቸው እያንዳንዱ ቤተሰብና ግለሰብ የኃይል ጥገኛ ሆኗል ። በእጃችን ላይ የያዝናት ትንሽ ተንቀሳቃሽ ስልክ ኃይልን ካልተሞላች አትሠራም ። ኃይል ለእያንዳንዱ ቤት የብርሃን ፍላጎት ወሳኝ ነው ። የዕለት ምግባችንን ለማብሰል የመንግሥታትና የባለጠጎች የኃይል ጥገኛ ከሆንን ሰንብተናል ። ኃይል እጅ መጠምዘዣ እየሆነባቸው የተቸገሩ አገራት የኃይል አማራጭን ያስጠናሉ ። እያንዳንዱ አገር የራሱ የሆነ ውድ ነገር ፣ ተፈላጊ የሆነበት ጸጋ ቢኖረውም ሁሉም አገር በተመሳሳይ መንገድ የኃይል ተጠቃሚ ነው ። ኃይል ብርሃን ለማግኘት ፣ ለመጓጓዝ ፣ በኮምፒውተር የሚሠሩ ነገሮችን ለመጠቀም ፣ ምግብ ለማብሰል ፣ በስልክ ለመገናኘት አስፈላጊ ሆኗል ። መንግሥታት መሠረታዊ ነገሮችን ካሟሉ ከተሞች በዜጋው ይመሠረታሉ ። ከእነዚህ መሠረታዊ ነገሮች ውስጥ መንገድ ፣ ውኃ ፣ መብራት ቀዳሚ ናቸው ። እነዚህን አንድ በረሃ ላይ ያሟላ መንግሥት ደርሶ ሲመለስ የሞቀ ከተማ ያገኛል ።

የኃይል አሰላለፍ እየተባለ የሚወራ ነገር አለ ። የምዕራብና የምሥራቅ አገራት በተሸከሙት አጥፊ መሣሪያ ፣ በኒውክለር ኃይል ጭምር ይፎካከራሉ ። የጦር ቃል ኪዳን ማኅበር ይመሠርታሉ ። ኃይል የምዕራብና የምሥራቅ ተፎካካሪ አገራትን ፈጥሯል ። ኃይል ዓለምን አንድ የሚያደርግ ወይም የሚያጠፋ ሊሆን ይችላል ። በቆዳ ስፋታቸው ፣ በሕዝብ ብዛታቸው አነስተኛ የሆኑ አገራት ከኃያላን መንግሥታት ጋር መጣበቅ ፣ የደኅንነት ዋስትና መጠየቅ አስፈላጊያቸው ይሆናል ። ኃያላን መንግሥታት የሚባሉት የስማቸውን ቅጽል ያመጣላቸው አንደኛው ኃይል ነው ። ኃይል የዓለምን ፖለቲካና ኢኮኖሚ ይዘውራል ።

ፍትሕን ከዓለም የሚጠብቁ የሚኖሩባትን ዓለም የማያውቁ ሞኞች ናቸው ። ዓለም ወላዋይ ፣ ዓለም ዋሾ ናት ። ዓለም ካሸነፈው ጋር የምትሰለፍ አድር ባይ ናት ። ሁለቱንም ተፋላሚ በርቱ እያለች ፣ እያጫረሰች ዜና የምትሠራ ናት ። ምንም እውነተኛ ቢሆን ደካማው የሚጮህለት የለም ። በኃይል የተካከሉ አገራት ሲጣሉ ሁሉም ገላጋይ ይሆናል ። ህንድና ፓኪስታን ሁለቱም የኒውክለር ባለቤቶች በመሆናቸው ጠባቸው ፈጣን ገላጋይ አለው ። ኒውክለር ዘመድ አያውቅምና ። ኃይል ለዓላማችንና ለዘመናችን ትልቅ ርእስ ነው ። እነዚህ ሁሉ ኃይላት አንድ ቀን የነበሩ እስከማይመስል ድረስ ይጠፋሉ ። ይደመሰሳሉ ። አንድ ኃይል ግን አለ ።

ሃይማኖት የለሾች፡- “አንድ ኃይል አለ ይላሉ” እየተባለ ይነገራል ። ለእግዚአብሔር የሰጡት ስም “አንድ ኃይል” የሚል ነው ። እውነተኛው ኃያል እርሱ ብቻ ነው ። የአንድ ዘመን ኃያላንን ዓለም ለማግኘት አልተቸገረችም ። ፈርዖንም ፣ ናቡከደነጾርም ፣ ቄሣርም ፣ ናፖሊዮንም የጊዜአቸው ጀግኖች ነበሩ ። ታላቁ እስክንድር ታሪኩ እንጂ አስፈሪነቱ ዛሬ የለም ። ኃያላን በድካም ፣ ባለጠጎች ቁራሽ በመለመን የሚጨርሱበት ዓለም ናት ። እግዚአብሔር ግን እውነተኛው ኃይላችን ነው ። ተናግሮ የሚረታልን ፣ ታግሎ የሚጥልልን ኃይል እግዚአብሔር ብቻ ነው ። ዘላለማዊ ብርሃንን ያገኘንበት ፣ በእባቡ ራስ ላይ ቆመን የፎከርንበት ኃይላችን እግዚአብሔር ነው ። የጦር ሠራዊት የነበረው ዝነኛው ንጉሥ ዳዊት “ኃይላችን እግዚአብሔር ነው” ማለቱ ድንቅ ምስክርነት ነው ። በዐፄ ምኒልክ ጎራዴ ላይ የተጻፈው ጽሑፍ እንዲህ የሚል ነው፡- “የምኒልክ ተስፋው እግዚአብሔር ነው ።”

እግዚአብሔር የኃይልን መንፈስ የሚሰጥ አምላክ ነው ። በማይታየውና በሚታየው ትግል ኃይላችን እግዚአብሔር ነው ። በመንፈሳዊ ዓለም ኃይል የሚፈልጉ ነገሮች አሉ ። የመጀመሪያው ፍቅር ነው ። ሁሉን በእኩል ለመውደድ ፣ ሰውን እንደ ራስ ለማፍቀር ኃይል ይፈልጋል ። ሁለተኛው ይቅር ለማለት ኃይል ያስፈልጋል ። በእርቅና ፍትሕ አፈላላጊ ኮሚቴ ፊት ተበዳዮች ሲሰድቧቸው ፣ እየከፈሉ እንደሆነ ስለሚሰማቸው በዳዮች ጠንከር ይላሉ ። “ይቅር ብዬሃለሁ” ሲባሉ ግን መቋቋም አቅቷቸው ይወድቃሉ ። ሦስተኛው ኃይል ፈላጊ አገልግሎት ነው ። የሚፈልገውን የማያውቅ ማኅበረሰብን ፣ ለነፍሱ ጉዳይ መጥቶ ሥጋዊ ጦርነት የሚከፍት ትውልድን ፣ በአጋንንት እስራት ተይዞ የሚወደውን የሚጠላ ወገንን ማገልገል አቅም ይፈልጋል ። በምድር ላይ በኃይለ መንፈስ ቅዱስ ካልሆነ በቀር ማገልገል ከባድ ነው ። አባቶች በምናኔና በምንኵስና ሕይወት ማገልገልን የፈለጉት አገልግሎት ትጥቅን አጠር ማድረግ የሚፈልግ ፣ እኔ ብሞት ማንንም አልጎዳም የሚል ቆራጥ ሰውን የሚሻ ስለሆነ ነው ። አገልጋዮች የሚከፍሉልንን ዋጋ ብናውቅ ሽቅብ መገላመጥ ባልደፈርን ነበር ።

እግዚአብሔር ለማፍቀር ፣ ይቅር ለማለት ፣ ለማገልገል ኃይላችን ነው ። አሜን!

ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ኅዳር 25 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ