ልዩ ትምህርት
(የወጣት አገልጋይ ፈተና)
በጎዳናው ሁሉ የአገልግሎት ፈተናዎች ይታወሱኝ ነበር ። ወጣት የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ከበላይ ሁኖ ፍቅር የሚሰጠው አባት ፣ ምክር የሚለግሰው መምህር ፣ የሚያጽናናው ካህን ፣ ከውድቀት የሚያነሣው ሐዋርያ ያስፈልገዋል ። “አባት የሌለው አባት እግዚአብሔር አብ ብቻ ነው ።” ወጣቱ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ አባት ያስፈልገዋል ። ጉልበት ቢኖረው ብልሃት ያጥረዋልና ። ትጋት ቢኖረውም ሁሉም ነገር ዛሬ ካልሆነ ይላል ። ሰዎች የእርሱን የዲሲፕሊን ሕግ ስላልፈጸሙ ያዝናል ፣ ነገር ግን የአምላክን ሕግ መጠበቅ እንዳቃታቸው ይረሳል ። እርሱ ስለተቆጣ ክፉን ጥለው ፣ ደጉን የሚጨብጡ ይመስለዋል ። የሰው ቍጣ የእግዚአብሔርን ጽድቅ እንደማይሠራ የሚገባው ዘግይቶ ነው ። የአያያዝ ችግር እንጂ ምእመንን ማቅናት ቀላል ነው ብሎ ያስባል ። በአባቶቹም ይፈርዳል ። አንዳንድ ሥርዓቶች ታሪክና ችግር ለወለደው ጉዳይ የተሠሩ መሆናቸውን ዘንግቶ ቀንበር ላንሣ ብሎ ይነቃቃል ። ሥርዓቱን ላንሣ ከማለት ለምን ተሠራ ? ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል ። “ከበሮ በሰው እጅ ያምር ፣ ሲይዙት ያደናግር” እንዲሉ ቀላል የሚመስለው እረኝነት ከባድ መሆኑን የሚረዳው ብዙ ከቆሰለ በኋላ ነው ። እመራዋለሁ የሚለው ሕዝብ ልምራህ ሲለው ፣ አንዳንዴም የምእመናን አቅም ሙሴን ያህል መሪ ከምድረ በዳ ያስቀረ መሆኑን ቶሎ ላይረዳ ይችላል ። በመሪ የተሰናከለ ምእመን ሊኖር ይችላል ፣ በምእመን የተሰናከለ መሪም ብዙ አለ ።
ወጣት የቤተ ክርስቲያን መሪ ብዙ በመናገር ያምናል ። ለጥበበኛ ሰው አንዲት ቃል እንደምትበቃው ይዘነጋል ። ብዙ ንግግር የፊቱን እየጣሉ የኋላውን የሚረሱበት ነው ። “ብዙ ቢያወጉ ይዘነጉ ፣ ብዙ ቢተቹ ይሰለቹ” ነው ። ወጣቱ አገልጋይ ሁሉንም ነገር ወደ ቅኔና ትርጓሜ መውሰድ ይሻል ። በሁሉም ክስተት ካልሰበክሁ ይላል ። ቍጡና ፊት ለፊት ከሁሉ ጋር የሚጋጭ በመሆኑ በቀላሉ ጠላት ያተርፋል ።
ወጣት የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ልዩ ትምህርት የሚያስተምሩ ሰዎች ይገጥሙታል ። እነዚህ ሰግደው የገቡ ፣ አንገት ደፍተው የከረሙ ናቸው ። ተናጋሪ ምእመን ያፈራሉ እንጂ እነርሱ አይናገሩም ፤ በድብቅ እየሞሉአቸው ምእመናን በግልጽ ማውራት ይጀምራሉ ። ልዩ ትምህርት መባሉ አዲስ ነገርን ሁሉ እንደ መገለጥ ለሚያየው ትውልድ ነው ። ኑፋቄ የጀመረው በዓለመ መላእክት ሲሆን ጀማሪውም ሰይጣን ነው ። ሰይጣን በገዛ ኑፋቄው ተሰናክሎ ብዙዎችን ያሰናከለ ነው ። ኑፋቄ ክህደት አይደለም ። ግማሽ እውነት ፣ ግማሽ ምግባር ፣ ግማሽ እምነት ነው ። ውሸታም እንዳይባል የተወሰነ እውነት አለው ። ዓመፀኛ እንዳይባል ከፊል ምግባር ይታይበታል ። ከሀዲ እንዳይሉት ስመ እግዚአብሔርን ይጠራል ። ሰይጣን ከሙሉ ውሸት ይልቅ ከፊል እውነት ሥራውን ያስፈጽምለታል ። ሰይጣን የተሳካለት ክርስቲያኖችን በመግደል ሳይሆን ክርስቲያኖችን በማጋደል ነው ።
ኑፋቄ አንዳንዶች በጥመት ሲይዙት ሌሎች ግን ፈተና ሆኖባቸው ይቆራኛቸዋል ። ኑፋቄ ነቃፊ ስለሚያደርግ እኔ ብቻ ድኜ ሌላው ጠፋ ያሰኛል ። የራስን ችግር ላለማየት በሌላው ስህተት ውስጥ ይደብቃል። ኑፋቄ ፈሪሳዊ ጠባይ ያላብሳል ። የራሱን ትቶ የሌላውን ኃጢአት ይናዘዛል ። እግዚአብሔር ስላደረገለት ነገር ከማመስገን እንደ እገሌ ስላላደረግኸኝ አመሰግንሃለሁ ያሰኛል ። ራሱን ትንሽ አምላክ አድርጎ ይቆጥራል ። ራስ ተኮር የሆኑ ወሬዎችን ይወዳል ። እኔ ፣ እኔ ያበዛል ። ውስጣዊ ቅንነትን በውጫዊ ጌጥ ለመሸፈን ይሞክራል ። የማስተዳድራት የኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን ልዩ ትምህርት ይዘው የገቡ ሰዎች ነበሩባት (1ጢሞ. 1 ፡ 3) ።
እነዚህ ሰዎች እኛ በአደባባይ ስናገለግል እነርሱ በጸሎትና በጽሞና ስም በየቤቱ ምእመናንን ይዘው እንክርዳድ ይዘሩባቸው ነበር ። “እንዲህ ብላችሁ ጠይቁ” በማለት ከአስተማሪዎቻቸው ጋር ትግል ውስጥ እንዲገቡ የዋሆችን ያሰለጥናሉ ። ምእመናንም አብረዋቸው ያለቀሱትን ፣ ለታላቅ ዕድል ያበቁአቸውን አባቶች ጠልተው በቤተ ክርስቲያን በተቃዋሚነት ይቀመጣሉ ። አገልጋዮች የሚኖሩት እኛ በምንሰጠው ገንዘብ ነው በማለት ካህናተ እግዚአብሔርን እንደ ቤት ሠራተኛቸው ማየትና ማዘዝ ይጀምራሉ ። በዚህ ምክንያት በመንጋውና በእረኛው መካከል ጠላትነት ይፈጠራል ። ተኩላው ወዳጅ ፣ እረኛው ጠላት ይደረጋል ። ተኩላው ሊያርድ እያሰባ መሆኑን የሚያውቁት ከወጡና ሜዳ ላይ ከወደቁ በኋላ ነው ።
ይቀጥላል
ጢሞቴዎስ ነኝ ክፍል 4
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
የካቲት 18 ቀን 2016 ዓ.ም.