የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የሕይወት ሥነ ሥርዓት 6

5- ጸልይ

ስታገኝም ጸልይ ፣ ባለህ ነገር ትረካለህ ። ስታጣም ጸልይ ተስፋን ይዘህ ትነሣለህ ። ስትስቅ ጸልይ ፣ ሳቅህን እውነተኛ ያደርግልሃል ። ስታለቅስም ጸልይ ፣ ከኀዘን ሸለቆ ያወጣሃል ። ስትወድድ ጸልይ ፣ ያረፈደው ፍቅር ያመሽልሃል ። ስትቀየምም ጸልይ ፣ ልብህን ያጥብልሃል ። በአገርህ ስትሆን ጸልይ ፣ ከወገን ጠላት ይጋርድሃል ፤ በሰው አገር ስትሆንም ጸልይ ፣ ባዕዱን ዘመድ ያደርግልሃል ። ስታሸንፍ ጸልይ ፣ ጋሻህ እግዚአብሔር ይሆናል ። ስትሸነፍም ጸልይ የእንደገና ዕድል ይሰጥሃል ። ስትደፍር ጸልይ ፣ መለኮት ድጋፍ ይሆንሃል ። ስትፈራ ጸልይ ፣ እምነትን ይሰጥሃል ። ሲሳካልህ ጸልይ ፣ የመኸር ደስታ ታገኛለህ ። ሳይሳካም ጸልይ ፣ ፈቃደ እግዚአብሔር ልብህን ያሳርፈዋል ። አስታመህ ሲድንልህ ጸልይ ፣ ፈውስ የእግዚአብሔር ገንዘብ ናትና ። አስታመህ ሲሞትብህም ጸልይ ፣ ሞት ዕረፍት ነውና ። ደግ ንጉሥ ሲነሣ ጸልይ ፣ ደግ ሰው ዘመኑ አጭር ነውና ። ክፉ ንጉሥ ሲነሣም ጸልይ ፣ ለቅጣት ይላካልና ። ስትቀደስ ጸልይ ፣ ከኃጢአት የሚያድን ኢየሱስ ነውና ። ስትቆሽሽም ጸልይ ፣ በደሙ ያጥብሃልና ። ደም በባሕርይው ያቆሽሻል ። የእግዚእ ኢየሱስ ደም ግን አምላካዊ ደም ነውና ያነጻል ። ደም ሲያዩት ያስደነግጣል ፣ የአማኑኤል ደም ግን መሢሐዊ ደም ነውና የተዘጋውን በር ይከፍታል ።

ተደርጎልህ እንደሆነ የምታመሰግነው በጸሎት ነው ። የሌሎች ጉዳት አስጨንቆህ ከሆነ የምትማልደው በጸሎት ነው ። ኃጢአትህ ከብዶህ ከሆነ ንስሐ የምትገባው በጸሎት ነው ። አጥተህ ከሆነ የምትለምነው በጸሎት ነው ። ጸሎት ለንጉሥ አቤት ማለት ነው ። ጸሎት ለዳኛ ይግባኝ ማለት ነው ። ጸሎት ለሰጪው ጌታ እጅን መዘርጋት ነው ። ጸሎት ለወዳጅ የፍቅር መልእክት መላክ ነው ። ጸሎት ለተዋጊው ጀግና መንገድ መልቀቅ ነው ። ጸሎት ለቤትህ ራስ ጉድለትህን ነግረህ መተኛት ነው ። ጸሎት ምግበ ሥጋ ፣ ምግበ ነፍስን የምንጠይቅበት ነው ። ጸሎት ወደ ሰማይ መደወያ ቍጥር ነው ። ጸሎት የሃይማኖት መሣሪያ ነው ። ጸሎት ሀልወተ እግዚአብሔርን የምንመሰክርበት ነው ።

ከሕይወት ሥነ ሥርዓት አንዱ መጸለይ ነው ። ስለዚህ አፍ ከልብ ሆነህ ፣ ስፍራና ጊዜ ለይተህ በማለዳና በምሽት ጸልይ ። ከበረታህ በሃያ አራት ሰዓት ሰባት ጊዜ ጸልይ ። ከቤትህ ስትወጣ የመንገድ ጸሎት ፣ ስትመገብ የማዕድ ጸሎት አትርሳ ። ወደ ወዳጅህ ቤት ስትሄድ ፣ ደግሞም ስልክ ስትደውል ጸልይ ። የእግርህ ኮቴ እንዲናፍቀው ያደርጋል ። ወደ ሥራ ስትገባና ሥራህን ስትጀምር ጸልይ ። ሐኪም ሆነህ እንደሆነ ሳትጸልይ በሽተኛ አትንካ ። እውቀቱን የሰጡህ ፈረንጆች ቀዶ ጥገና ከማድረጋቸው በፊት ተንበርክከው ይጸልያሉ ፣ “አንተም በእምነትህ ጸልይ” ብለው በሽተኛውን ይጠይቃሉ ። የአገሬ ሐኪም ሬሳ የምታመርተው ስለማትጸልይ ነው። ሠራተኞችህ ሊጋጩህ ሲፈልጉ ዘወር ብለህ ጸልይ ፣ ሚስትህ ለግጭት ስትፈልግህ በልብህ ጸልይ ። በማለዳ አፍህን በጸሎት ሳታሟሽ ከሚስትህም ጋር ቢሆን አትነጋገር ። ላንተ ማንጋት አልረሳምና በማለዳ ተነሥተህ አመስግን ። ታርፍ ዘንድ ላንተ ማስመሸት አልረሳምና ሲመሽ ጸልይ ። በመንገድ ስትሄድ ፣ ብቻህን ስትሆን ፣ ወደ መታጠቢያ ሄት ስትገባ ፣ ገላህን ስትታጠብ ጸልይ ። ከጸሎት ሁሉ አውራው “እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ – አቤቱ ክርስቶስ ሆይ ማረን” የሚለው ነው ። ያለማቋረጥ ይህን ጸሎት ጸልይ ። ፈተናና ትግሉ ሲበዛ መዝሙር 22ን እግዚአብሔር እረኛዬ ነው የሚለውን ደጋግመህ ጸልይ ። ደግሞም ጸሎተ ማርያምን ታዐብዮ ነፍስዬን- ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች የሚለውን ደጋግመህ ጸልይ (ሉቃ. 1፡47-55)። የመቍጠሪያ ጸሎት እጅግ ጠቃሚ ነው ። ከመዝሙረ ዳዊትም በጸሎትህ ደባልቅበት ። የልብህን ሙቀት ለጌታህ አፍስስለት ።

የግል ጸሎት ፣ የቤተሰብ ጸሎት ፣ የማኅበር ጸሎት እንዳለ አስታውስ ። የአጋንንት ፍላጻ ሲበዛ መዝሙር 90ን ደጋግመህ ጸልይ ። “በልዑል መጠጊያ የሚኖር…” የሚለውን ማለቴ ነው ። አባቶችህ ስታገኝ ጸሎት ተቀበል ። አንተም ትባረካለህ ፣ እነርሱንም ታተጋለህ ። በማለዳ ጸሎትህ ላይ ውኃ በብርጭቆ አድርገህ ጸልይ ። ራስህንና ቤተሰብህን በተባረከው ውኃ ቀድስ ። ለማግኘት ብቻ ሳይሆን ስላገኘህም ጸልይ ። የሚፈልጉትን የማያውቁና የሚፈልጉትን ያጡ በዓለም ላይ አሉ ። የሚያድናቸው ጸሎት ብቻ ነው ። ወደ ወዳጅህ ቤት ስትገባ ሳትቀመጥ ጸሎት አድርሱ ። ወደ ቤተ ክርስቲያን ስትገባ ሳትቀመጥ ጸሎት አድርስ ። ወደ ጉባዔ ስትሄድ በቃሉ እንዲናገርህ ጸሎት አድርስ ። በታላቅ መከራ ውስጥ ስትሆን ዝም ብለህ ጸልይ ። ጌታ በመስቀል ላይ ሆኖ ጸልዮአልና ። ጸሎት ለሥጋዊ ጤና ፣ ለአእምሮ መታደስ ፣ ለመንፈስ እረፍት ወሳኝ ነውና ጸልይ ። እባክህ ጸልይ ።

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መጋቢት 21 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ