ጸጋህ አይጓደል ተመስገን ጌታዬ ፣
ሁሉን ያረክልኝ ባለውለታዬ ፤
አንድ አለኝ የምልህ ዘወትር ሁልጊዜ ፣
አንተ ነህ ጋሻዬ ደጋፊ ምርኵዜ ።
አቤቱ አምላክ ሆይ የሰማይ አባቴ ፣
አካሌ ሲደክም አንተ ነህ ጉልበቴ ፤
በሰላም በጤና ስኖር በዕድሜ ጸጋ ፣
ምስጋና ብቻ ነው የምሰጥህ ዋጋ ።
የኑሮዬ ባላ የሕይወቴ ቤዛ ፣
ለእኔ ያረክልኝ ውለታህ የበዛ ፤
ተመስገን ፈጣሪ ልበልህ ጠዋት ማታ ፣
ረዳቴ አንተ ነህ የቸገረኝ ለታ ።
ሲርበኝ አጉርሰህ ስታረዝ አልብሰህ ፣
ስጨነቅ አጽናንተህ ስታመም ፈውሰህ ፣
ድረስልኝ ስልህ ስምህን ጠርቼ ፣
የምፈልገውን አላውቅም አጥቼ ።
ቸኩለህ እንደ ሰው ቅጣት የማትሰጠው ፣
ሀብታምና ድሀ የማታስበልጠው ፤
ቸሩ መድኃኔ ዓለም ይድረስህ ምስጋና ፣
ረዳቴ አንተ ነህ በስምህ ልጽናና ።
ለኮንትራት ሕይወት ነገ ለሚቀረው ፣
በመንፈስ አጽናኝ ቃልህን እንዳልሽረው ፤
ኃጢአቴን ሰርዘህ አድነኝ ከዕዳ ፣
መሐሪው አንተ ነህ ለሰው ልጆች ፍዳ ።
እመካብሃለሁ በሰማዩ አባቴ ፣
የፈጠርከኝ አምላክ አውጣኝ ከኃጢአቴ ፤
ሳዝን ፈጥነህ ደራሽ ስከፋ መካሪ ፣
መከታ ጋሻዬ አንተ ነህ ፈጣሪ ፤
ዕዝራ በመሰንቆ ዳዊት በበገና ፣
እንዳቀረቡልህ ለሥራህ ምስጋና ፣
አወድስሃለሁ እኔም በዜማዬ ፣
አንተ ነህ ጠባቂ የሕይወት ጋሻዬ ።
(ምንጭ፡- ዘለሰኛ)
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሚያዝያ 10 ቀን 2016 ዓ.ም.