የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የድንግል መወለድ

እንኳን ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም ልደት በሰላም አደረሳችሁ!

ሃናና ኢያቄም ሆይ እንኳን ደስ አላችሁ ! ልጅን ለቤት ሳይሆን ለዓለም ወለዳችሁ ። ቡሩክ ማኅፀን ያለሽ ሃና ሆይ ! ያለ ዘር ያለ ሩካቤ የምትወልድ ልጅ ወለድሽ ። የልጅ ልጅ ለማየት ሳይሆን የእግዚአብሔርን ችሎታ በቤተሰብሽ ለማየት ሃና ሆይ በስእለት ድንግልን ወለድሽ ! ከእግዚአብሔር የተገኘችውን ለእግዚአብሔር ሰጠሽ ። ከእግዚአብሔር ተገኝታ ፣ በእግዚአብሔር የኖረች ልጅ ወለድሽ ! ውስጣዊ ደም ግባት ያላትን ልጅ ወለድሽ ! እግዚአብሔር የሚያየውን ውበት የተጎናጸፈች ልጅ ወለድሽ ! አዳም በገነት በተስፋ ያያትን ፣ ያችን ሴት ያለ ወንድ ዘር የምትፀንሰውን ድንግል ወለድሽ ! የፀሐዩ የክርስቶስ እናት ምሥራቅ ማርያም ካንቺ ተወለደች ። እውነተኛው ኮከብ የተወለደባት ፣ ምድራዊ ክፋት ያልቀረባት ሰማይ ዛሬ ተወለደች ። ሃና ሆይ ኢሳይያስ የተናገረውን ትንቢት ሰምተሽ ነበር ። ያ ትንቢት በእኔ ይፈጸማል ብለሽ አልጠበቅሽም ። እግዚአብሔር ግን አሳቡን በጊዜው ይፈጽማልና ድብቅ በረከት ድንግልን ዛሬ ወለድሽ !

በስደት ዓለም ላይ ድርብ ስደት የገጠመሽ ፣ በሊባኖስ ተራሮች የአርዘ ሊባኖሱን የዘንካታውን የክርስቶስን እናት ወለድሽ ! ለአምላክ አያት እሆናለሁ ብለሽ አስበሽ አታውቂም ነበር ። ቡሩክ ልጅ ስትለምኚ አምላክን የምትወልድ ልጅ ወለድሽ ! ሃና ሆይ በሕግ በሩካቤ ልጅን ወለድሽ ፣ ካንቺ የተወለደችው ድንግል ግን ከሕግ በላይ በሥልጣነ እግዚአብሔር በድንግልና ፀንሳ የምትወልድ ሆነች ። ላንቺ ጋብቻ ክብርሽ ነበር ፣ ለልጅሽ ድንግል መሆን ክብርዋና መጠሪያዋ ነው ። አንቺ እስከ ጊዜው ድንግል ነበርሽ ፣ ልጅሽ ግን ለዘላለም ድንግል ናት ። አንቺ ቤተሰቦችሽ ለወንድ አጩሽ ፣ ልጅስ ማርያም ግን አብ ለልጁ ማደሪያ እንድትሆን መረጣት ። አንቺ አምላክን በእምነት አየሽ ፣ ልጅሽ ማርያም ግን በባሕርይ ልደት ወለደችው ። አንቺ ካንቺ በኋላ ያለች ልጅን ወለድሽ ፣ ልጅሽ ማርያም ግን የሚቀድማትን ልጅ ወለደች ። ሃና ሆይ ! ደስ ይበልሽ ! የወለደም ያልወለደም በሚያዝንበት በዚህ ጎዶሎ ዓለም ሙሉ ጨረቃ ማርያም ካንቺ ተወለደች ።

ኢያቄም ሆይ ደስ ይበልህ ! የአብራክህ ክፋይ ድንግል ማርያም የባሕርያችን መመኪያ ሆነች ። ሰውና እግዚአብሔር የ5500 ዘመን ቀጠሮአቸውን በድንግል ማርያም ማኅፀን ፈጸሙ ። ምሳሌው አማናዊ የሚሆንባት ፣ ትንቢት የሚያርፍባት ፣ ንግርት የሚጠናቀቅባት ፣ ሱባዔ የሚቋጭባት ድንግል ዛሬ ተወለደች ። ክብርህ ከታላላቅ አባቶች ነው ። የዳዊት ልጅ መሆን ካኮራህ ፣ የዳዊት አምላክ ካንተ በመወለዱ እንዴት አትኮራም !! ለአምላክ አያት ለመሆን የበቃህ ኢያቄም በእውነት የተባረክህ ነህ ። እናንተ ዘረ ቅዱሳን ከአብርሃም እስከ ዳዊት ፣ ከዳዊት እስከ ኤልሳቤጥ ፣ ከሃና እስከ ድንግል ቅድስና አልነጠፈባችሁም የታደላችሁ ናችሁ ። ምነው የእናንተ ዘመድ ባደረገኝ !

የሰጪው እናት ከሁሉ ይልቅ ድሀ ነሽ ፣ ነገር ግን እንዳንቺ የበለጸገ ማንም የለም ። የቸሩ እናት አዛኝ ነሽ ፣ እንዳንቺ የሆነለት ማንም የለም ፣ ነገር ግን በበረት የወለድሽ ፣ በግብጽ የተሰደድሽ ነሽ ። ሕይወትሽ ቅኔ የሆነው ፣ ባንቺ ላይ ያለው ምሥጢር የማይፈታው የኢየሱስ እናት ማርያም እንኳን ተወለድሽ ! በመወለድሽ ብዙ ነገር እንማራለን ። እግዚአብሔር ጋብቻን እንደሚያከብር ከወላጆችሽ ተማርን ። ድንግልናን እንዳከበረ ካንቺ ተማርን ። እግዚአብሔር ለሚጠብቁት ቸር መሆኑን በስእለት በመወለድሽ አወቅን ። አንቺ ልጅሽን በበረት ብትወልጅ ፣ ያንቺ ልደትም በስደት በሊባኖስ ተራራ ላይ ሆነ ። ዓለም ለደግና ለደጎች ደግ ለክርስቶስ እንደማትሆን ተማርን ። አንቺን የመሰለች ልጅ ቢያገኙም ለእግዚአብሔር ሰጡ እንጂ የራሳቸው አላደረጉሽም ። እግዚአብሔር ጋ የተቀመጠ የት ይሄዳል ? ብለው ሰጡሽ ። መቅደስ ሆይ በመቅደስ አደግሽ ። አሮን ከገባባት ከቅድስተ ቅዱሳን የምትበልጪ የታላቁ ሊቀ ካህን የክርስቶስ መቅደስ ሆይ እሰይ ተወለድሽልን ። ድንግል ሆይ የልደትሽ በረከት ይድረሰን ። ኃጢአት ላደከመን ልጆችሽ ምልጃሽ አይለየን !

ሁሉን አዋቂ ወልድ ሆይ! ስለ ወዳጅህ ስለ አብርሃም ከማለት ስለ እናት ስለ ድንግል ማለት ይበልጣልና ። ከወዳጅ እናት ትልቃለችና ። ስለ አማኑኤል ስምህ ስለ ማርያም እናትህ ብለህ በዓይነ ምሕረት ተመልከተን ! ማዕበሉን ቀዝፈህ አሻግረን !

እንኳን ለድንግል ማርያም ልደት አደረሳችሁ!

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ግንቦት 1 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ