የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የሕይወት ሥነ ሥርዓት (27)

13. ንግግርህ ብቁ ይሁን (ቸ)

22. የሰውን ምሥጢር ለማወቅ አትከጅል

ሰዎች እንዳንተ ናቸው ። አካላዊ መዋቅራቸው ከአንተ ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ ሁሉ ውስጣዊ ስሜታቸውም ተመሳሳይ ነው ። ሰውን ከሰው ልዩ የሚያደርገው ችግሮችን የሚፈታበት ጥበቡ ፣ ነገሮችን የሚቀበልበት ልቡ ነው ። ከዛሬ ሦስት ሺህ ዓመት በፊት የተጻፈ ምክር ዛሬ ላይ የሚሠራው በዚያ ዘመን ከነበሩት ሰዎች ጋር የኑሮ ዝምድና ስላለን ፣ ተመሳሳይ የሕይወት ገጽታ ስለምናስተናግድ ነው ። በሥልጣኔ ብንለያይም በመወለድ ፣ በማደግ ፣ በሞት ሕግ ተመሳሳይ ነን ። ሁላችንም ለመኖር እንበላለን ። ደስታችንም በሌሎች ጉድለት ውስጥ ተቀምጧል ። የሌሎችን ጉድለት ስንሞላ የእኛን ደስታ እንቀበላለን ። ሰዎች የራሳቸው ምሥጢር እንዲኖራቸው መፍቀድ ያስፈልግሃል ። ሚስትህም ልጆችህም ካንተ ጋር አንድ አካልና የአካል ክፋይ ቢሆኑም የራሳቸው ግላዊ ሕይወት እንዳላቸው ማመን ያስፈልግሃል ። ወደው ፈቅደው እስኪያሳውቁህ ድረስ ቀና ሰው መሆን አለብህ ።

መንፈሳዊ አገልጋይና ካህን በሆንህ ጊዜ እንደ መርማሪ ፖሊስ የሰዎችን ኃጢአት ለማወቅ አትፈልግ ። ኑዛዜ ማለት ሰዎች ፈቅደው የተናገሩት ስህተት እንጂ እኛ ለማወቅ ያደረግነው ጥረትና ውጤት አይደለም ። የሰዎችን ገመና ተገልጦ ባየህ ጊዜ ለማየት አትጓጓ ። ስለሌሎች አንተ ጋ ሲወራ ፣ ስላንተ ደግሞ ሌሎች ጋ እየተወራ ነው ። ስላልሰማነው እንጂ ሁላችንም ስም አለን ። የሰው ልጅ ሥራ ሲፈታ እንኳን መሰሉን ድንጋይንም ያማል ። ሰዎች ወደው ፈቅደው የነገሩህን በጸሎተኛ ልብ ስማ ። አንዳንድ ችግር እየጸለዩ ካልሰሙት የአሳብ ውጊያ የመንፈስ ትግል ይፈጥራልና ። ችግሩን ከሰማህ በኋላ ስሜታቸውን ተካፈለው ። ነገር ግን ያለ ምክር አትስደዳቸው ። ወዳጅህ በለመነህ ጊዜ ሳንቲም ማጣትህ ይቆጫል ። ለአንድ ቀን እንኳ አልሆንኩትም ያሰኛል ። ሰዎች ባማከሩህ ጊዜ ምክር ካጣህ በመጡበት ስሜት ይመለሳሉ ። ምክር እንዲኖርህ ተመከር ። መምህራንን ተወዳጅ ፣ መጻሕፍትን ቤተ ዘመድህ አድርግ ። ከዚህች ሰዓት በኋላ የመኖር አቅም ላይኖራቸው ይችላልና ዝም ብለህ አትሸኛቸው ።

አንዳንድ ሰዎች በራሳቸውና በቤታቸው ምን እየሆነ እንዳለ አያውቁም ። ሳያውቁት ወደ ድብርት ውስጥ እየገቡ ነው ። አካላዊና ሥነ ልቡናዊ መታወክ እየደረሰባቸው ነው ። የላኛው አካል የውስጠኛውን ሰውነት በጥቂቱም ቢሆን ይናገራል ። ይልቁንም ፊት የልብ አደባባይ ነውና ፊታቸውን አይተህ ልባቸውን ለማወቅ ይቻልሃል ። ጨዋታቸው ሲቀንስ ፣ መሄድ ሲያቅታቸው ፣ ላለመደሰት ሲሞክሩ ፣ ሁሉንም ነገር በዜሮ ሲያባዙ ፣ ከሰው ሲሸሹ ፣ ምሬት ሲያበዙ ፣ … አንድ ችግር ውስጥ እንዳሉ ምልክት ነው ። በዚህ ጊዜ በዘዴ ማማከር ይገባል ። አንዳንድ ጊዜ ምን ሆነሃል ብሎ መጠየቅ ይቻላል ። ሌላ ጊዜ ደግሞ ዙሪያ ገባውን በወሬ በማነሣሣት ሰውዬው ራሱ የውስጡን እንዲናገር መርዳት ይገባል ።

የሰዎችን ምሥጢር ለማወቅ የምሻው ለምንድነው ? ብለህ ራስህን ጠይቅ ። የሰማሁትን ምን መፍትሔ ሰጥቼዋለሁ ብለህ ራስህን ገምግም ። ምሥጢር የማወቅ ጥማት አንድ ቀን የማይሸከሙት አደጋ ላይ ይጥላል ። የደኅንነት ሠራተኞች ለመንግሥታቸው ጆሮ ሆነው ምሥጢር ቢያነፈንፉ ደመወዝተኞች ስለሆኑ ነው ። በነጻ ምሥጢርን ማነፍነፍ ግን ወሬ መውደድ ነው ። “እሺ እባክህ” ፣ “ተው እንጂ” ፣ “ይገርማል” ፣ “አያድርስ ነው” ፣ … የሚሉ ቃላት የወሬ ነዳጅ ናቸው ። ምሥጢሩ የሚያድን እግዚአብሔር ብቻ ነው ። ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያንን ማወቅና መፈጸም እርሱ የሐዲሱ ኪዳን በር ነው ።

የሰዎችን ምሥጢር ማወቅ መፈለግ ከአንተ ጋር የሚመሳሰል ሰው አግኝቶ ለመረጋጋት ነው። አንተ የምትሠራውን ኃጢአት የሚሠራ ከሆነ ብቻዬን አይደለሁም ብሎ ለመደሰት ነው ። አንድን ነገር ስትፈልግ ለምንድነው የምፈልገው ? ብለህ ራስህን ጠይቅ ። ነገር ግን መፍትሔ ፈላጊ ወንበር ላይ ስትቀመጥ ሰዎችን እየጠየቅህ ፈውስና መልስ ማዘጋጀት ሙያ ነው ።

ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ግንቦት 26 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ