የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የሕይወት ሥነ ሥርዓት (33)

18. ስፖርት

ከሕይወት ሥነ ሥርዓቶች አንዱ ስፖርት ማዘውተር ነው ። ለታላቁ ሩጫ በዓመት አንድ ጊዜ መሮጥ ፣ ለፎቶ እንጂ ለጤና ምንም ጥቅም የለውም ። የሰውነት እንቅስቃሴ ዕለታዊ ግዳጅ ነው ። እጅ ለመሥራት ፣ እግር ለመራመድ እስከ ተሠራ ድረስ መሥራትና መንቀሳቀስ አስፈላጊ ነው ። አሊያ የሞት ጎረቤት ፣ የበሽታ ዳስ ሆኖ መኖር ነው ። “መቀመጥ ቆመጥ ነው” እንዲሉ ። ዘመናዊነት ከጎዳን ነገር አንዱ የስንፍና ሠራዊት ማብዛቱ ነው ። ከምግብ እንኳ የሚታኘክ አንፈልግም ። በፋብሪካ ተቀነባብሮ ፣ ልሞ ፣ በሚሳብ መልክ መውሰድ ነው ። ይህ ጥርስ ያላወጡ ፣ ምግብ ያለመዱ ሕፃናት ይወስዱት የነበረ ነው ። ተፈጥሮአዊ ሂደቱን ጠብቆ ምግብን መመገብ ብዙ ጥቅም አለው ። መዓዛውን ፣ ጣዕሙን እንድናውቅ ያደርገናል ። ጥርሳችን ጥንካሬ ያገኛል ። ምግብን የሚፈጀው የአካል ክፍልም እየመጣ ላለው የምግብ ዓይነት ዝግጅት ያደርጋል ። ከጠዋት እስከ ማታ ከመቀመጫቸው የማይነሡ የቢሮ ሠራተኞች አሉ ። ሻይ ቡና እዚያው ጠረጴዛቸው ላይ ይመጣላቸዋል ። በየተቋማቱ ሻይ ቡና በእግር ተጉዘው ከሚጠጡበት ቦታ መዘጋጀት አለበት ። አንድ ተቋም የሠራተኞቹን ጤና መጠበቁ ለራሱም ህልውና ወሳኝ ነው ። መንግሥት በከፍተኛ ሁኔታ ሆስፒታሎችን መገንባት ሥራው ነው ። መድኃኒት በውጭ ምንዛሪ ወደ አገር ያስገባል ። ዜጎችም ከአገር ወጥተው በውድ ገንዘብ ይታከማሉ ። በዚህም ውጤቱ አነስተኛ ነው ። የስፖርት ማዘውተሪያዎች በየሰፈሩ ቢገነቡና ጤናማ ማኅበረሰብ መገንባት ቢቻል የአገር ወጪ ይተርፍ ነበር ። ችግርን ከሥሩ መከላከል ውጤታማ ያደርጋል ።

በአገራችን የአንድ ትልቅ ቤተሰብ የልጆች አስተዳደግ የሚያሟላው አራት ነገሮች ነበሩ፡- ትምህርት ፣ ግብረ ገብ ፣ ስፖርትና የዜማ መሣሪያ ማወቅ ናቸው ። ትምህርት ስለ ራሱና ስለሚኖርበት ዓለም ግንዛቤ ይሰጠዋልሰ ። ግብረ ገብ ከራሱና ከሰዎች ጋር የሚኖርበት ትልቁ የመኖሪያ ፈቃድ ነው ። “የሰው አገሩ ምግባሩ” እንዲሉ ። ስፖርት ንቃቱን ፣ ጥንካሬውን የሚጠብቅበት ነው ። የዜማ ዕቃ ፈጣሪውን የሚያመሰግንበት ፣ አምልኮተ እግዚአብሔር የሚያደርስበት ነው ። ይልቁንም ዕድሜ እየገፋ ሲመጣ ወዳጅ እያነሰ ይመጣልና የዜማ ዕቃ ጓደኛም ነው ። የሰውነት እንቅስቃሴ ከተሟላ አስተዳደግና አኗኗር የሚደመር ነው ። በዚህ ዘመን ስፖርት የሚመለከቱ ብዙ የዓለም ሕዝቦች አሉ ። እንደውም አንድ አባት እንዳሉኝ “ከእግዚአብሔር በላይ ኳስ ተከታይ አለው ።” ኳስ መመልከቱ ያን ያህል ስህተት አይደለም ። ከአምልተ እግዚአብሔር ፣ ከትዳራችን ፣ ከማኅበራዊ ግዳጃችን ከበለጠብን ግን አደገኛ ጣዖት ነው ። “የመጀመሪያውን ስብከት ለእኔ ስጡኝ ፣ የማንቸስተር ጨዋታ አለብኝ” ያለ ሰባኪ እንዳለ ሰምተናል ። እነዚህ የሚያስተምሩት በሥጋ በነፍስ ቢደነቁር አስደናቂ አይደለም ። ቤተ ክርስቲያን የሚቆጭላት አጥታ ቁማር መጫወቻ ከሆነች ቆይታለች ።

ስፖርት ማድነቅና ስፖርት መመልከት ለጤናችን ምንም የሚያደርገው አስተዋጽኦ የለም ። የሚደግፉት ቡድን በመሸነፉ ራሳቸውን ያጠፉ ወጣቶችን በቅርብ ጊዜ ሰምተናል ። የድሀን ቅብጠት የሀብታም አገር በጀት አይችለውም ። ለእውነቱ ካየነው በአገራችን መወራት ያለበት ሰው ስለ መሆን ፣ እንጀራ ስለ መብላት ፣ ስለ ንጽሕናን አጠባበቅ ነው ። የሚገርመው ስፖርት አድናቂዎች ጠጪዎች ናቸው ። የሰውነት ቅርጻቸው የተበላሸ ነው ። የሚደግፉት ቡድን ካሸነፈ በደስታ ይጠጣሉ ፣ ካላሸነፈ በንዴት ይጠጣሉ ። የስፖርት ደጋፊዎች ግብ መጠጥ መጠጣትና ለመጠጡ ምክንያት ማበጀት ነው ። የምናደንቃቸው ስፖርተኞች በብዙ ሚሊየን ዶላር የሚከፈላቸው ሲሆኑ ለእነርሱ ሥራቸው ነው ። እነርሱ ኢትዮጵያ የምትባል አገር መኖርዋን እንኳ አያውቁም ።

ስፖርት የምንሠራው ለተስተካከለ ቅርጽ ቢሆንም ፣ ቅርጻችንን ስናሳይ ለመዋል ግን አይደለም ። ይህ ራስን ማምለክ በመሆኑ በበሽታና በውድቀት ሳይቀጣ አይቀርም ። እዩኝ እዩኝ ያለ ገላ ደብቁኝ ደብቁኝ ይላል ይባላል ፤ ደግሞም እውነት ነው ። ይህ ሕግ ነው ፣ የገዛ አካላችንም ጣኦት ሆኖብን ላስመልክ ካልን በቍስል ይመታል ። ዛሬ ቅርጻቸውን አሳምረው ሀብታም ሴት የሚጠብቁ ድኩማን ወንዶች እያመረትን ነው ። ኤልያብ ተቀምጦ ዳዊት ለንግሥና የተመረጠው ቁመና መስፈርት ስለማይሆን ነው ። ቁመና እያዩ ሹመትና ማዕረግ የሚሰጡ አባቶች አሉ ። ይህ አዲስ አይደለም ነቢዩ ሳሙኤልም የተታለለበት ነው ። “እግዚአብሔር ግን ሳሙኤልን፦ ፊቱን የቁመቱንም ዘለግታ አትይ ሰው እንዲያይ እግዚአብሔር አያይምና ናቅሁት ሰው ፊትን ያያል፥ እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል አለው።” (1ሳሙ. 16 ፡ 7) ። ቁመናን እያያችሁ ባል የምታስሱ እኅቶች ከተሰናዱ ሌቦች ራሳችሁን መጠበቅ አለባችሁ ። ሰው ስፖርት የሚሠራው ለራሱ ነው ። ስለዚህ እዩልኝ እያሉ ቪዲዮ መልቀቅ ምን የሚሉት ነገር ነው ? መጽሐፍ እያነበበ ቪድዮ የሚለቅ የለም ። የመጀመሪያው መጽሐፍን እንደ እርግጠኛ ጠላታችን ነው የምናየው ። ሁለተኛው መጽሐፍ የሚያነብ ሰው እዩልኝ ስሙልኝ የሚል ኑሮ የለውም ። ራስን የመሸጥ ግርግር ውስጥ ያለው ይህ ዘመን በድሀ ሕዝብ ፊት ቍርሳቸውን እየበሉ የሚለቅቁ ፣ መኖር ባቃተው ወገን ፊት እየተገላበጡ ከየጂሙ ፎቶ የሚሰድዱ ጨካኞችን ያፈራ ነው ።

አንተ ግን የሰውነት እንቅስቃሴ አድርግ ። ግድ ጂም መግባት አያስፈልግህም ፣ የራስህ ሰውነት የስፖርት መሥሪያም ነው ። ታክሲ ለመጠበቅ አንድ ሰዓት ከመቆም አንድ ሰዓት ተራምደህ እቤትህ ግባ ። በየጂሙ ያለው ወሬና የነጋዴዎች ትውውቅ ፣ ለመቼ ቀን እንደሆነ ባይታወቅም የሰቡ ጎረምሶች የሚታዩበት ነው ። ሌላው ይሥራልኝ ብለህ የተውከው ተግባርህ በራሱ ስፖርት ነው ። ከተፈጠርንበት ሥሪት እየራቅን ስለሆነ ታላቅ የጤናና የሥነ ልቡና ጉዳት ውስጥ ገብተናል ። አንተ ግን በየቀኑ ቢያንስ ለአንድ ሰዓት ያህል የእግር ጉዞ አድርግ ። ከመኝታህ ከመነሣትህ በፊትና በተነሣህ ጊዜ መንጠራራት ፣ ሰውነትህን ማፍታታት አትርሳ ። የትንፋሽ ስፖርት ብቻ ሳይሆን የጥንካሬ ስፖርቶችንም ልመድ ።

ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሰኔ 17 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ